ናይጄሪያ የዓለም ዋንጫ ህልሟን እውን ለማድረግ ኢትዮጵያን ማሸነፍ ነበረባት፡፡ አዲስ አበባ ላይ 2-1 ድል ካደረገች በኋላ በካላባር ከተማም በሌላ ድል ቲኬቷን ቆረጠች፡፡ ኬኔት ኦሜሮ ከፈንጠዚያው በኋላ ወደ ቼልሲ ሲመለስ ዴቪድ ሉዊዝ ጨብጦት ‹‹ወደ ብራዚል እንኳን ደህና መጣችሁ›› ብሎታል፡፡ ሉዊስ በሀገሩ የሚስተናገደውን ውድድር አስመልክቶ ያበረታታው ወጣት በቼልሲ ተሰላፊነትን አያግኝ እንጂ የስታምፎርድ ብሪጁ ክለብ ንብረት ነው፡፡ በሰማያዊዎቹ ክለብ ውስጥ የሚገኙት የሉዊዝ ሀገር ልጆች ኦስካር፣ ራሚሬዝና ዊልያንም የ20 ዓመቱን የመሀል ተከላካይ ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› ብለውታል፡፡ ከዚያም ሌሎቹም ተጨዋቾች እየተፈራረቁ ቀጥለዋል፡፡
ኦሜሮ በቼልሲ ገና የመጀመሪያ ጨዋታውን እንኳን አላደረገም፡፡ ሆኖም በተጨዋቾች ዘንድ ይወደዳል፡፡ 59 ቁጥር ማሊያ ያደርጋል፡፡ በጆዜ ሞውሪንሆም የዋናውን ቡድን ማሊያ እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡ ተስፋም ጥለውበታል፡፡ ስለዚህ ከሙሉ ቡድኑ ጋር አብሮ ልምምድ ይሰራል፡፡
በ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ ከወጣት ከዋክብት መካከል ኦሜሮ እንደሚካተትበት ከወዲሁ ግምት ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ዓመትም በጥሩ ሁኔታ አልፎለታል፡፡ ናይጄሪያ ከኬፕቬርዴ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፏል፡፡ በብራዚል የኮንፌዴረሽን ዋንጫ ላይ ተሳትፏል፡፡ ለ15ኛ ጊዜ ለንስሮቹ ባደረገው የካላባር ጨዋታም ሃገሩን ለዓለም ዋንጫ ለማሳለፍ በቅቷል፡፡
‹‹በዓለም ዋንጫ ላይ ለመጫወት ስመኝ ኖሬያለሁ›› ኦሜሮ ይናገራል፡፡ ‹‹በኮንፌዴሬሽንስ ካፕ ላይ መሳተፋችን ዓለም ዋንጫ ላይ የመቅረብ ፍላጎታችንን ጨምሮልናል፡፡ አሁንም የምድብ ድልድሉን በጉጉት እጠባበቃለሁ፡፡
‹‹በቼልሲ ብቻ ትኩረታችንን በክለባችን ላይ አድርገን እንሰራለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጆዜ ያስቀናል፡፡ ባለፈው ሳምንት አንድ የልምምድ ፕሮራም ላይ አንድ ኳስ ላቀብል ብዬ ተበላሸብኝ፡፡ ጆዜም እንዲህ አለኝ፡፡ ‹‹በዓለም ዋንጫ ላይ እንዲህ ካደረግክ ናይጄሪያ ከውድድሩ ትወጣለች›› ሁላችንም ሳቅን፡፡ አሁን ስለ ዓለም ዋንጫ በተጨዋቾች መካከል ምንም ነገር የለም፡፡ ያለው ዝምታ ብቻ ነው፡፡ ከዕጣው ድልድል በኋላ ግን ጫጫታ ይኖራል፡፡
‹‹ስለዓለም ዋንጫው ከሉዊዝ ጋር አውርተናል፡፡ ጥሩ እንግሊዝኛ ያወራል፡፡ በእውነቱ መልካም ሰው ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ልንጫወት ስንሄድ ሉዊዝ ‹‹እውን አሁን ለዓም ዋንጫ ልታልፉ ነው›› እያለ ሲያሾፍብን ነበር፡፡ አሸንፈን ስንመለስ ግን ሁሉ ደስታቸውን ገልፀውልናል፡፡ ሉዊዝም ‹‹ጥሩ ሰርታችኋል፣ እንኳን ወደ ብራዚል ደህና መጣችሁ›› ብሎ ተቀብሎናል፡፡
‹‹ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሁሉም በጣም ደስተኛ ሆኗል፡፡ ልክ የአፍሪካ ዋንጫን እንዳነሳንበት ጊዜ አይነት ነው፡፡ ህዝብ ወደ ጎዳናዎች ወጥቷል፡፡ ደጋፊዎቻችንን ቅር አላሰኘንም፡፡ ለእነርሱ ሲባል ማለፍ ነበረብን፡፡ (በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ከስፔን ጋር ስንጫወት የትከሻ) ጉዳት በደረሰብኝ ጊዜ ከደጋፊዎች መልዕክቶችና ትዊቶች ይደርሱኝ ነበረ፡፡ እኔን ለማየት ምን ያህል እንደናፈቁ ይገልፁልኛል፡፡ አሰልጣኝ ስቴፋን ኬሺም በምን አይነት ጤንነት ላይ እንዳለሁ እየደወለ ይጠይቀኝ ነበር፡፡ አሁንም የቡድኑ አባል መሆኔን ይነግረኛል፡፡ ስለዚህ በድጋሚ ለመጫወት ጓጉቼ ነበር››
ለንስሮቹ የዘንድሮ አምስተኛው የዓለም ዋንጫ ነው፡፡ 160 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሀገር ቡድኗን በታላቅ ስሜት ትደግፋለች፡፡ ‹‹ልጅ ሳለሁ ናይጄሪያ ስታሸንፍ ባደግኩባት ዋና ከተማ አቡጃ ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ደስታውን ሲገልፅ እኔም ተቀላቅያቸው ነበር፡፡ አባቴ የቧንቧ ሰራተኛ ነው፡፡ እናቴ ደግሞ ትንሽ ሬስቶራንት አላት፡፡ የናይጄሪያ ጨዋታዎች ሁልጊዜ እንከታተል ነበር፡፡
‹‹ገና ልጅ ሳለሁ አንድ ቀን የናይጄሪያን ብሔራዊ ቡድን ማሊያ መልበሴ እንደማይቀር እናቴ ትነግረኝ ነበር፡፡ እንዳለችውም ሆነ፡፡ በ2009 የዓለም ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ በአቡጃ ተዘጋጅቶ ነበረ፡፡ ያም እናቴን በጣም አስደስቷታል፡፡ ምንም ያመለጣት ነገር የለም፡፡ ሬስቶራንቷን ሳይቀር ዘግታ ወደ ስታዲየም መጥታለች፡፡ ሁልጊዜም መልካም ዕድል እንዲገጥመኝ ትመኛለች››
በ1994 ናይጄሪያ በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ 16 ቡድኖች አንዷ ስትሆንና በፈረንሳይ የዓለም ዋንጫ (ኢትዮጵያን… ወደ ገጽ 23 የዞረ)
ስትሳተፍ ኦማር ጨቅላ ህፃን ስለነበር አያስታውስም፡፡ ‹‹ሰዎች ሁልጊዜ ስለ 1994ቱ ቡድን ያወራሉ፡፡ ማይክል አሜናሎ (የአሁኑ የቼልሲ የቴክኒክ ዳይሬክተር) የቡድኑ አባል ነበር፡፡ የአሁኑ የንስሮቹ አሰልጣኝ ኬሺ ደግሞ የቡድኑ አምበል ነበር፡፡ ‹‹ሲመክረን በአሁኑ ቡድን ውስጥ ከ1994ቱ ቡድኑ ጋር የሚመሳሰል መንፈስ እንደሚመለከት ይነግረናል፡፡ ይህ ደግሞ ለእኛ ብዙ ትርጉም አለው›› አሚሮ ለ1994ቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን ያለውን ክብር ይገልፃል፡፡
‹‹በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ አንድነት የሌለባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ በ2010 በውጤቱ ሃገሪቷ አዝና ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ ጉድላክ ጆናታን ቡድኑ በደቡብ አፍሪካ ባሳየው ብቃት በጣም ከመቆጣታቸው የተነሳ ለተወሰነ ጊዜ አግደውት ነበር፡፡ አሁን ግን በቡድኑ ዙሪያ ያለው ነገር ሁሉ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በህብረት እንሰራለን፡፡ ብትመለከተን ሁሉም እርስ በርሱ ቀልድ ሲለዋወጥ ታያለህ፡፡ በቡድናችን ውስጥ አዙቢኬ ኤግዌክዌ የተባለ ቀልድ ወዳጅ ተጨዋች አለ፡፡ በናይጄሪያ ለዋሪ ዋልቭስ ክለብ የሚጫወተው የመሀል ተከላካይ ነው፡፡ ካልጮኸ አያወራም፣ በጣም ቀልደኛ ነው፡፡ አሰልጣኛችንን እንኳን ሳይቀር ያስቃቸዋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫን አሸንፈናል፡፡ በኖቬምበር የዓለም ከ17 ዓመት በታች ዋንቻ አንስተናል፡፡ እንደገናም ለብራዚሉ የዓለም ዋንጫ አልፈናል፡፡ በዓለም ዋንጫ ላይ ደግሞ ተደናቂ ነገር ማሳየት አለብን›› ይላል፡፡
ኦሜሮ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው በቀላሉ አይደለም፡፡ ከአቡጃ ጎዳናዎች ተነስቶ ብዙ ለፍቷል፡፡ ‹‹የአቡጃ ልጅ ነኝ፡፡ ያደግኩት እግርኳስን በሚያፈቅር ቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡ አባቴ ግብ ጠባቂ ነበር፡፡ በከፍተኛ ደረጃ አልተጫወተም እንጂ ታላቅ ወንድሜም እንዲሁ ይጫወታል፡፡ ታናሼ ለሙከራ ስታንዳርድ ሉዬዥ ይሄዳል፡፡ የአንድ ክለብ አሰልጣኝ ወደ ቤታችን መጥቶ ከወላጆቼ ጋር ተነጋገረ፡፡ ልጃችሁ ከእኔ ጋር ይጫወታል አላቸው፡፡ ዕድሜዬ 10 ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ በባዶ እግሬ ተጫውቻለሁ፡፡ በ2009 ለሁለት ወራት ሙከራ ወደ አንደርሌክት ሄጄ ተመለስኩ፡፡ ከዚያም ስታንዳርድ ሊዬዥ ላከልኝ፡፡ ለሊዬዥ ተጠባባቂ ቡድን ውስጥ መጫወት ጀመርኩ፡፡ ከዚያም ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ላይ ቀረብኩ፡፡ ቼልሲም ሊያስፈርመኝ ፍላጎት አሳየኝ፡፡ የጠራኝ ኤሚላኖ ነበር፡፡ ላምን አልቻልኩም፡፡ ያደግኩት ቼልሲን እያየሁ ነው፡፡ ሚኬልን እወደዋለሁ፡፡ ስለሴሌስቲን ባባደሮም እሰማ ነበር፡፡ ቼልሲ ሲያሸንፍ በናይጄሪያ ልክ የሀገራቸው ቡድን ያሸነፈ ያህል ይጨፍራሉ፡፡ በናይጄሪያ ከማንቸስተር ዩናይትድ የበለጠ ቼልሲ ብዙ ደጋፊ አለው፡፡ ዩናይትድ በሁለተኛ ደረጃ ይጠቀሳል፡፡
‹‹ቼልሲን ማንቸስተር ዩናይትድ ሲጫወቱ በአንዳንድ ቦታዎች ሁከትና ጥል ይነሳል፡፡ በከተማ ውስጥ ወዲያ ወዲህ የሚሉ ብስክሌተኞች የቼልሲን ወይም የማንቸስተር ዩናይትድን አርማ የውለበልባሉ፡፡ በናይጄሪያ እግርኳስ ይህን ያህል ይወደዳል፡፡
‹‹ቼልሲ እንዳስፈረመኝ ሳይውል ሳያድር ለዴን ሃግ ክለብ በውሰት ሰጠኝ፡፡ ብቃቴን እንዳሻሽል ተብሎ ነው፡፡ ደጋፊዎቻቸው በጣም ስሜታዊ ናቸው፡፡ ለእያንዳንዱ ተጨዋች ብቃቱን እንዲያሳድግ በደጋፊዎች በግል መዝሙር ይወጣለታል፡፡ የዴንሃግ ክለብ ደጋፊዎች ስሜት እየጠሩ ዘምረዋል፡፡
‹‹እዚህ ነው፣ እዚያ ነው፡፡ ሁሉ ቦታ ነው እያ ይዘምሩልኝ ነበር››
አሜሮ የተጎዱ ተጨዋቾችን ለመተካት ሲባል በቀኝ መስመር ተከላካይነት ተጫውቷል፡፡ ሆኖም ‹‹ምርጡ ቦታዬ የመሀል ተከላካይ ቦታ ነው›› ይላል፡፡ አሰልጣኝ ሞውሪንሆም በትክክል መዝነውታል፡፡ ‹‹(ሞውሪንሆን) ጓደኛዬ ኬኔት›› እያለ ይጠራኛል፡፡ ስለ እኔ የሚያወራበት መንገድ ሁሉ ደስ ይላል፡፡ ከአፍሪካ ዋንጫ በኋላ እንደፈለገኝ ሚኬል ነግሮኛል፡፡ ስላወቀኝ በጣም ተደሰትኩኝ፡፡
‹‹በናይጄሪያ ሁሉም ሰው ልጅ ሰው ይለዋል፡፡ ስትቀርበው ደግሞ ልዩ ሰው መሆኑን ትረዳለህ፡፡ ተጫዋቾች ያከብሩታል፡፡ ተጨዋቾችን እንዴት መያዝ እንዳለበት ያውቅበታል፡፡ ከእኛ ጋር እንዴት መነጋገር እንደሚገባውም ይረዳል፡፡ ልምምዱ ምርጥ ነው፡፡ በመጀመሪያ ለመልመድ ተቸግሬ ነበር፡፡ ከዌስትሃም ጨዋታ በፊት ተጋጣሚያችን በምን አይነት ዘዴ እንደሚጫወት ያውቃል፡፡ ጆዜ በልምምድ ሜዳ ላይ የሚናገረው ሁሉ በጨዋታ ላይ ሲሆን ታየዋለህ፡፡ በዚህ ምክንያት የበለጠ አክብሬዋለሁ፡፡
‹‹ተጨዋቾች ጥሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ማይክል ኤሲዬን ለእኔ መልካም ነው፡፡ አሽሊኮል ሁልጊዜም ያበረታታኛል፡፡ ትክክለኛ ሸርተቴ በወረድኩ ቁጥር የእርሱን የማበረታቻ ድምፅ ትሰማለህ፡፡ አይዞህ ኬኔት ይለኛል፡፡ ጊዜህ ይመጣል፡፡ ሩቅ አይደለም፡፡ ዕድል ስታገኝ ተጠቀምበት እያለ ይመክረኛል፡፡ ጆን ቴሪም እንዲሁ ጥሩ ሰው ነው፡፡ ያወያየናል፡፡ ግዙፍና ጠንካራ ነው፡፡ እንደ ወጣት ተጨዋችነቴ አንጋፎቹ በልምምድ ላይ ብዙ ሲሰሩ ስመለከት ለራሴ ብዙ መስራት እንዳለብኝ እነግረዋለሁ፡፡
‹‹በልምምድ ላይ በትኩረት ተግቼ መስራት አለብኝ፡፡ እያንዳንዱ አጥቂ የየራሱ ተሰጥኦ አለው፡፡ ለአምስት ደቂቃዎች ጎል ካልተቆጠረብህ በየትም ቦታ ብጫወት እችላለሁ ብለህ ታምናለህ፡፡ ከፈርናንዶ ቶሬዝ ጋር በተቃራኒ ሆነህ መጫወት ይከብዳል፡፡ ጠንካራ መሆን አለብህም፡፡ እንዳያልፍህ መጠንቀቅ ይገባሃል፡፡ እነዚህ በቤልጂየም ሳለሁ ስከታተላቸው የነበሩ ታላቅ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ከእነርሱ ጋር መጫወት ያስደስታል፡፡ ሳሙኤል ኤቶ በአፍሪካ ትልቅ ተጨዋቾች ነው፡፡ ኤቶንና ኤሲዬንን ማግኘት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ሆኛለሁ›› እያለ ኦሜሮ በቼልሲ ህልሙን እየኖረ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ህልሙ ግን በዚህ አያበቃም፡፡ ከፕሪሚየር ሊጉ ታላላቅ ክለቦች በአንዱ ውስጥ በቋሚነት መጫወት ደግሞ ቀጣይ ምኞቱ እንደሚሆን ጥርጥር አይኖርም፡፡