Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

አዲስ አበባ በቤት ኪራይ ንረት እየተናጠች ነው

$
0
0

ዜና ትንታኔ ከብርሃኑ ፈቃደ
(ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው)

የመኪና ራዲያተር ጥገና ባለሙያ ነው፡፡ በኪራይ ምክንያት በሚሠራበት ሰባተኛ አካባቢ የተደረገበት ጭማሪ አስደንጋጭ ሆኖበት ሲበሳጭ ከርሟል፡፡ አንድ ሺሕ ብር ይከፍልበት የነበረው ቤት፣ ‹‹ብዙ ግብር መጥቶብኛል፤ ስለዚህ ሁለት ሺሕ ብር ተጨማሪ ክፍያ መደረጉንና የኪራዩ ዋጋ ሦስት ሺሕ ብር መሆኑን እንድታውቀው፤›› የሚል ቀጭን መልዕክት ደርሶት ከአከራዩ ጋር ተጨቃጭቆ መክረሙን የሚናገረው ወጣቱ ሰው፣ አልታይ ዘለቀ (ስሙ ተቀይሯል) ነው፡፡

ለጭማሪው በአከራዩ የቀረበውን ምክንያት የማይቀበለው አልታይ፣ ‹‹እንዴትም ተብሎ ግብር ቢጨምር፣ ከመንገድ ዳር ርቆ የትኛውም ደንበኛ ቤቱን አይቶ ለመምጣት በማያስችለው አካበቢ ላይ ለሚገኝ ቤት፣ ሥራው በተባራሪ እየተሠራ፣ ሥራውን ለሚያመጡ ደላሎች ኮሚሽን እየከፈልኩ ለምሠራው ሥራ በአንድ ጊዜ ይሄን ያህል ጭማሪ ማድረግ ወዴት እየወሰደን እንደሆነ ግራ ገብቶኛል፤›› ሲል ይኮንናል፡፡ የአንድ ልጅ አባት የሆነው አልታይ፣ የራሱንና የባለቤቱን ቤተሰቦች ጨምሮ ሦስት ቤተሰብ የሚያስተዳድርበት ይህ ሙያው ከዚህ ሁሉ ቤተሰብ ቀለብና ወጪ ተርፎ በአንድ ጊዜ ጭማሪ በተደረገበት ልክ የሚበቃ ገቢ ካላገኘበት፣ ወደ ክፍለ አገር አለያም ወደ ዓረብ አገር ለመሰደድ ማሰቡን ተናግሯል፡፡
appartment in addis
የአልታይ ጓደኛ የሆነው ሌላው አስተያየት ሰጪ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ትምህርት ቤት ከፍቶ መሥራት ከጀመረ ሦስት ዓመታት መቆጠራቸውን ይገልጻል፡፡ ያለቻቸውን ገንዘብ አሟጥጠው፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ገንዘብ ተቋማት ተበድረው የሚያንቀሳቅሱትን ትምህርት ቤት የከፈቱት ሕንፃ ከግለሰብ ተከራይተው ነው፡፡ ለኪራይ በዓመት ከአምስት መቶ ሺሕ ብር በላይ ይከፍላሉ፡፡ ማስፋፊያ ለማድረግ ሌላ ተጨማሪ የግለሰብ ሕንፃ መከራየት ግድ ሆኖባቸው መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ ከአንደኛ ክፍል እስከ 12ኛ ለማስተማር የሚያስችሉ ክፍሎችን ለማሟላት የግለሰብ ሕንፃ በውድ ዋጋ መከራየትና መሥራት አማራጭ የለውም ይላሉ፡፡ ሥራው እንዲህ ያለው አላስፈላጊ ጫና ባይኖርበት ኖሮ የበለጠ ጥሩ ሥራ ለመሥራት ያመቻቸው እንደነበርና ይበልጥ የሰው ኃይል ቀጥረው፣ በርካታ ተማሪዎችን ማፍራት የሚያስችላቸውን መንገድ የቤት ኪራይ ዋጋ እንዳራቀባቸው ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ለትምህርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ቢያስታውቅም፣ በደህናው ጊዜ ቦታ በርካሽ አግኝተው ሕንፃ የሠሩ ሰዎች በኪራይ ከሚያግበሰብሱት ገቢ የማያገኘውን ታክስ፣ እኒህ ተከራዮች ከሚሰጡት የትምህርት አገልግሎት ከፍተኛ ታክስ ይሰበስባል፡፡ ሆኖም ትህምርት ቤት መሥሪያ ቦታ ማግኘት የማይታሰብ እንደሆነባቸው የሚገልጹት አስተያየት ሰጪ፣ የሊዝ ግዥ ለማድረግ የሚቀርበው መነሻ ዋጋ በአስገራሚ ሁኔታ በካሬ ሜትር እስከ አሥር ሺሕና በዚያም በላይ በመድረሱ መቸገራቸውን ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት ለትምህርት ዘርፉ እንደቆዳና ሌሎች ፋብሪካዎች የሰጠውን ማበረታቻ ሲሰጥ ማየትም አልቻንም ይላሉ፡፡ በሊዝ ጨረታ መነሻ ዋጋ መሬት እንደልብ ከተማው ላይ ለእነዚህ ዘርፎች ሲሰጥ ይታያል፡፡

ከቻይናና ከሌላውም አገር ለመጡ ‹‹የውጭ ባለሀብቶች›› የሚሰጠው ድጋፍ በትምህርቱ ዘርፍ አገልግሎት ሰጥተው፣ ብዙ ሠራተኛ ቀጥረው ለሚያሠሩትና ከፍተኛ ግብር በመክፈል አስተዋጽኦ ለሚያበረክቱት ሰዎች ምንም ዓይነት ድጋፍ ከመንግሥት እያገኙ እንዳልሆነ በመግለጽ መቸገራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሕንፃ አከራይ እንዲያገኝ የተመቻቸለትን ጥቅም፣ ለብዙ ሰው የሥራ ዕድል አስገኝተውና አገልግሎት ለሕዝቡ ሰጥተው የሚሠሩ ሰዎች እንደአስቷጽኦዋቸው የሚጠቀሙበትን ዕድል አለማግኘታቸውን ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት ለአከራይ እንጂ ለሠርቶ አሠሪና በኢኮኖሚው ውስጥ እሴት ጨማሪ ለሆኑ አካላት በመሬት አቅርቦት የሚያድርገው ድጋፍ ከወለል በታች መሆኑን በመግለጽ ይተቻሉ፡፡

‹‹የመንግሥት የመደብ ጨቋኝነት ሚና››

በአዲስ አበባ ሕንፃ የገነቡ አብዛኞቹ ከመንግሥት የ70 ከመቶ ብድር አግኝተው፣ መሬት ተመርተው ወይም በርካሽ ተጫርተው በሊዝም ሆነ በይዞታ ከገዙ በኋላ ያለምንም ድካምና ውጣውረድ በመንግሥት ገንዘብ በገነቡት ሕንፃ ያለሐሳብ ሀብታሞች እንዲሆኑ በመንግሥት ዕድሉ የተሰጣቸው ናቸው፡፡ መኪና ገጣጥመው፣ ትምህርት ቤት መሥርተው፣ በፋብሪካ አምርተው ለመሥራት የሚጣጣሩ ሰዎች የማያገኙትን የገቢ ዝቆሽ፣ ሕንፃ አከራዮች በመንግሥት ተባባሪነት የሚያገኙትን ጥቅምና የዳጎሰ ገቢ በመመልከት፣ አንድ ሕንፃ በባንክ ብድር በመሥራትና ሕንፃውን ለብድር ማስያዣነት በመዋል ገርበብ ባለው የብልጽግና በር በኩል ሾልከው የተመነደጉ ጥቂት አይደሉም፡፡

በአገሪቱም ሆነ በአዲስ አበባ መዲናም መንግሥት የሚፈልገውን ያህል የማኑፋክቸሪንግ ወይም የኢንዱስትሪ መስኮች አለመስፋፋት ችግሮች መንስዔ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል እነዚህ አቋራጭና በቀላሉ የዕድሜ ልክ ባለሀብት መሆን የሚቻልባቸው መንገዶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ አንድ ባለፋብሪካ ወይም ባለትምህርት ቤቱ ባለጉዳይ እንደሚጠቅሱት ሥራቸው በበርካታ ሰዎች ትከሻ ላይ የወደቀ ነው፡፡ ብዙ ሠራተኛ ተቀጥሮና እሴት ተጨምሮ የሚሠራው ሥራ ትርፍ ማስገኘት የሚጀምረው ከፕሮጀክቱ ትግበራ አራት ወይም አምስት ዓመታት በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡ በአንፃሩ ሕንፃ ሠርተውና ሸንሽነው የሚያከራዩ ግን ቦታ አጥቶ የተቸገረ ነጋዴ ወይም ሌላው አካል በካሬ ከ500 እስከ 5,000 ብርና ከዚያም በላይ እየከፈለ ለመሥራት የሚገደድ ጭሰኛ ሆኗል ይላሉ፡፡ አከራዮች ከኪራይ በሚሰበስቡት ገንዘብ የባንክ ዕዳ ከፍለው ሀብታቸው የማይነጥፍ ቱባ ሀብታሞች ይሆናሉ፡፡

ስለዚህ ፋብሪካ ከመገንባትና ለኢኮኖሚው እሴት የሚጨምሩ ዘርፎች ላይ ከመሠማራት ይልቅ በአቋራጭና በአጭር መንገድ ሀብታም የሚያደርጉ አማራጮች በመንግሥት በኩል ስለተመቻቹ፣ ለምን ብለው ይደክማሉ፤ ለነገሩ የደከሙትስ ምን አተረፉና የሚል መከራከሪያ በከተማው በሰፊው የሚደመጥ ሙግት ሆኗል፡፡

መምህር በቀለ የተባሉ በጡረታ ላይ የሚገኙ መምህር በአንድ ወቅት በኅብረተሰብ ሳይንስ ትምህርት ወቅት ስለመንግሥት ሥርዓትና አወቃቀር ሲያስትምሩ ‹‹መንግሥት የመደብ መጨቆኛ መሳሪያ ነው፤›› በማለት ይገልጹ ነበር፡፡ ይህም ሲባል የበላይ መደብ ያላቸው፣ በካፒታልና በገንዘብ አቅማቸው የተነሳ የመንግሥትን አገልግሎት በቀላሉ ለማግኘት የሚቻላቸው መሆናቸውን ለማመልከት የሚጠቀሙበት አገላለጽም ነው፡፡

ቤት መግዛት ባትችል ትከራያለህ፣ መከራየት ባትችል ግን?

በአሜሪካ የኪራይ ቤቶችን በማስመልከት ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንድ ጥናት ይፋ ተደርጎ ነበር፡፡ በኪራይ ቤቶች ዙሪያ በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲና በአጋሮቹ የተደረገው የጋራ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ የቤት ኪራይ ዋጋ እ.ኤ.አ. ከ1980ዎቹ ጀምሮ እየጨመረ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ የዜጎች ገቢ በየጊዜው እየቀነሰና እያነሰ መምጣቱን ተመልክቷል፡፡ የሀርቫርድ የኪራይ ቤቶች ጥናት እንደሚያረጋግጠው፣ ከሆነ ከ11.3 ሚሊዮን ያላነሱ አሜሪካውያን የራሳቸው ቤት ሊኖራቸው የሚችልበት አቅም የላቸውም፡፡ የኪራይ ቤት ጥገኛ ናቸው፡፡ በዚህ ሳቢያ ከግማሽ በላይ ገቢያቸውን ለኪራይ በመክፈል ለአስከፊ ወጪ የተዳረጉና ልፋታቸውን ለኪራይ የሚገብሩ መሆናቸውን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ከእነዚህ ትንሽ ዝቅ ያለ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች ዝቅተኛ የሚባለው የኪራይ ወጪያቸው፣ የገቢያቸውን 30 ከመቶ ለኪራይ የሚከፍሉ ናቸው፡፡

ከሁለት አሜሪካውያን አንዱ በቤት ኪራይ ወጪ ናላው የሚናውዝ መሆኑን የሚጠቁመው ጥናት፣ በአሁኑ ወቅት ለከፍተኛ የኪራይ ጫና ከተዳረጉት 12 ሚሊዮን አሜሪካውያን ባሻገር 21.1 ሚሊዮን አሜሪካውያን ለቤት ኪራይ ወጪ መሸፈኛነት ገቢያቸውን በማሟጠጥ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

ጥናቱ ሰፊና አስገራሚ ዕውነታዎችን ማስነበቡን ይቀጥላል፡፡ አሜሪካውያን በፌደራል መንግሥታቸው ደረጃ በሰዓት በአማካይ የሚያገኙት ገቢ 7.5 ዶላር (በወቅቱ ምንዛሪ ቢመታ 150 ብር መሆኑ) ነው፡፡ ሆኖም ባለሁለት መኝታ ክፍል ደህና መኖሪያ ቤት መከራየት የሚፈልግ አሜሪካዊ፣ በየትኛውም የአሜሪካ ግዛቶች ይህን መሰል ቤት መከራየት የሚችለው በሰዓት ቢያንስ 20 ዶላር (በሰዓት 400 ብር ያህል) ገቢ ማግኘት የቻለ እንደሆነ ነው ሲል ጥናቱ ማረጋገጫውን አስፍሯል፡፡ ከሁለት መኝታ ቤት ያነሰ ግን ደግሞ ደህና ሊባል የሚችል ቤት መከራየት የሚፈልግ ሰው የሰዓት ገቢው 12 ዶላር መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም የአሜሪካ ግዛት በሰዓት 7.5 ዶላር ዝቅተኛውን ገቢ የሚያገኝ አንድ ዜጋ ደህና የሚባለውን ቤት ተከራይቶ መኖር አይችልም፡፡

ኪራይ የሚያንረው ባለንብረቱ ነው

የኢትዮጵያ በተለይ የአዲስ አበባ ሁኔታ ይህንን ይመስላል፡፡ ኮንዶሚኒየም ተከራይቶ ለመኖር የሚችለው ሰው ወርኃዊ ገቢው ቢያንስ ከአምስት ሺሕ ብርና ከዚያም በላይ መሆን እንዳለበት ጥናት ማድረግ ሳያስፈልገው የሚታወቅ ነው፡፡ በከተማው ትልቁን የገቢ ምንጭ የሚበዘብዘው የኪራይ ዋጋ እንደሆነ ተራ አባወራ ብቻም ሳይሆን ሕንፃ ተከራይተው ቅርንጫፎቻቸውን የሚስፋፉ ባንኮች ሳይቀር የሚገነዘቡት ነው፡፡ የባንክ አገልግሎት እምብዛም በማይፈለግባቸው የአዲስ አበባ ጠረፍ አካካቢ የተከፈቱ የባንክ ቅርንጫፎች ሲናገሩት የሚደመጥ ነው፡፡

በአንፃሩ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቢሮ ለመከራየት ሁለት ጉዳዮች ቦታ እንዳላቸው የሚገልጹት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ደምስ ጫንያለው ናቸው፡፡ አንደኛው ቤቱ የሚገኝበት ቦታ ለኪራይ ዋጋው ከፍተኛ መሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ‹‹ዓይን ቦታ›› ተብሎ በልማድ የሚጠቀሰው አገላለጽ በተለይ በንግድ ሥራ ለተሰማሩ ሰዎች የተለመደ ሲሆን፣ ገበያ እስካለውና ወጪያቸውን ሸፍኖ ትርፍ እስካስገኘ ድረስ፣ ለትራንስፖርትና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች ያለው ምቹነት እየታየ ዋጋው እንደሚለያይ ከምሁሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሌላኛው ዋጋውን ውድና ተገቢ ሊያደርገው የሚችለው ምክንያት የቤቱ ወይም የንብረቱ ባለቤትነት ነው፡፡ በግለሰቦች ይዞታና በተቋማት መካከል ባለው ልዩነት መካከል የዋጋው ከፍተኛነትና ዝቅተኛነት ሊንፀባረቅ እንደሚችልም ዶክተር ደምስ ይገልጻሉ፡፡

በኢኮኖሚ ሙያቸው የማማከርና የጥናት ሥራዎችን የሚያካሂዱት ዶክተር ደምስ፣ የኪራይ ዋጋ ከውል ውጭ ያለአግባብ ተጨምሮባቸው የተከራዩትን የግለሰብ ቤት ለመልቀቅ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከግለሰብ ተከራይተን ነበር የምንሠራው፡፡ ስድስት ወር እንኳ ሳንቆይ በአንድ ጊዜ 35 ከመቶ ያህል ጨምረውብናል፤›› ያሉት ዶክተር ደምስ፣ አብዛኞቹ ግለሰቦች ሀብቱ ስላላቸው ዋጋ እንዳሻቸው ይጨምራሉ እንጂ ገበያው ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አይተውና ጥናት አድረገው የሚጨምሩ እንዳይማስላቸውም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ለአንድ ዓመት በውል ተዋውለውና ቅድሚያ መክፈል የሚጠበቅባቸውን ከፍለው ሥራ ቢጀምሩም፣ ከውል ውጭ በተደረገው ጭማሪ ቅር ተሰኝተው ሌላ አካባቢ ፈልገው ለመግባት ተገድደዋል፡፡

የአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ለአብዛኛው ሰው የሚቀመስ አለመሆኑን ምሁሩ ብቻም ሳይሆን ነዋሪዎችና ነጋዴዎች የሚስማሙበት ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል አንዳንድ ሰዎች ‹‹ከፒያሳና ከቦሌ ዕቃ መግዛት ለነጋዴው የቤት ኪራይ እንደመክፈል ይቆጠራል፤›› ሲሉ የሚደመጡት፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚሸጡት ዕቃዎች መርካቶና ሌላው አካባቢ ከሚሸጡት የተለዩ ሆነው ሳይሆን በዋጋቸው የማይቀመሱ ሆነው ስለሚገኙ የሚነገር አገላለጽ ነው፡፡ በከተማው ለሱቅ ኪራይ በካሬ የሚከፈለው ክፍያ በአስገራሚ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በቦሌ አካባቢ ከሚገኙ ሕንፃዎች መከራየት የሚፈልግ ነጋዴ፣ በአማካይ በካሬ ከሁለት ሺሕ እስከ ሦስት ሺሕ ብር ይጠየቃል፡፡ አምስት መቶ ብርና ከዚያ ያነሰ ዋጋ በካሬ የሚከፈልባቸው ሕንፃዎች ቢኖሩም፣ አዳዲስ የተሠሩት ግን በዚህ ዋጋ የሚደፈሩ አይደሉም፡፡ አካባቢ የቤት ኪራይ ዋጋን በዚህ መልኩ ሊወስን ቢችልም፣ የግል አከራዮች የሚያደርጉት ጭማሪ ባለንብረትነታቸው ላይ ያጋድላል፡፡

በአንፃሩ አከራዮች የየራሳቸውን አካሄድ እንደሚከተሉና በርካታ ወጪዎችን በማውጣት፣ ጥሪታቸውን አሟጠው ለገነቡት ሕንፃ ተመጣጣኝና ተከራዮችንም የማይጎዳ የኪራይ ዋጋ እንደሚጠይቁ ይሟገታሉ፡፡ በተለይ ከመገናኛ እስከ ሃያ ሁለት ባለው መስመር ሕንፃዎቻቸውን የሚያከራዩ ባለንብረቶች፣ በመንገድና በባቡር መስመር ግንባታ ምክንያት ሥራ በመጥፋቱ ምክንያት ኪራይ በግማሽ የቀነሱ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንም በመንገድ ሥራው ምክንያት ሥራ ቀንሶባቸዋል ባላቸው ድርጅቶችና አነስተኛ ነጋዴዎች ላይ የሚጥለው ታክስ ላይ አስተያየት ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡

በአዲስ አበባ ኬሻ በጠረባ ከሚተኛባቸው የጎጃም በረንዳ፣ የአሜሪካ ግቢ፣ የሰባተኛ ሰፈሮች አንስቶ እስከ ቦሌ፣ ገርጂ፣ ቤቴል የመሳሰሉት አካባቢዎች ቤት የሚከራይባቸው ናቸው፡፡ ኬሻ በጠረባዎቹ ቤት ለአዳር ያከራያሉ፡፡ ኬሻ በጠረባ እየተባሉ የሚታወቁት ቤቶች፣ ድሮ ድሮ ኬሻ፣ አሁን አሁን ካርቶን ተነጥፎ ለአንድ አዳር ሰው እንደጣውላ ተደርድሮ የሚታደርባቸው ቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ቤቶች ድሮ ከነበራቸው ማደሪያ የለሽ ደንበኛ ባሻገር፣ ከየክፍለ አገሩ ይጎርፉ የነበሩ የዓረብ አገር መንገደኞች የሚያገኙት ገቢ አስተማማኝ ሆኖላቸው ቆይቷል፡፡ ዓረብ አገር የሚሄዱ ሴቶች እንደከተማው ማደሪያ ቢስ ሰካራም ሳይሆን እጥፍ ከፍለው ያድሩ እንደነበር ሪፖርተር ያነጋገራት የጎጃም በረንዳ ኬሻ በጠረባ አከራይ ሺመታ አሕመድ ታስታውሳለች፡፡ አሁን ግን በጎጃም በረንዳ ኬሻ በጠረባ እያበቃለት መምጣቱን የሚጠቁም አካሄድ በባቡሩ መስመር ግንባታ እየታየ ነው ትላለች፡፡ ከፊት ለፊት የነበሩት ሱቆች አብዛኞቹ በመፍረሳቸው፣ አልጋ ያከራዩ ከነበሩት ቤቶች አንዳንዶቹ ለሱቆች ዕቃ ማከማቻነት እየዋሉ መምጣታቸውን ትገልጻለች፡፡ አብዛኞቹ ግን ለአዳር ከሚያከራዩዋቸው ቤቶች ውስጥ አብረው የሚኖሩ በመሆናቸው፣ ቤቶቹ ሲፈርሱባቸው ዕድል ከቀናቸው ኮንዶሚኒየም ቤት የሚቀየርላቸው በመሆኑ የገቢ ምንጫቸው ላይ አደጋ እንደተጋረጠበት ሥጋት የገባቸው ናቸው፡፡

ከእነዚህ ባሻገር ያሉት የገርጂና የቦሌ ቤቶች ቅንጡ ናቸው፡፡ የሚከራዩት በድረ ገጽ በሚለቀቁ ማስታወቂያዎች ሲሆን፣ ከ800 (16,000 ብር) እስከ 4,000 ዶላር (80,000 ብር) ድረስ የኪራይ ዋጋ የሚጠየቅባቸው ቤቶችም በአዲስ አበባ ጥቂት አይደሉም፡፡ አብዛኞቹ ቦሌ፣ ኦሎምፒያ፣ ገርጂ (በይበልጥ ሰንሻይን አፓርታማዎች)፣ ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኙ ቤቶች ባለአንድ፣ ባለሁለትና ባለሦስት መኝታ መሆናቸው እየተገለጸና ዘመናዊ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ እንደተሟላላቸው የሚገልጹ ማስታወቂዎች የሚያጅቧቸው ናቸው፡፡

ኪራይ የሚቆልሉት ደላሎች ናቸው

ከፍና ዝቅ ያለውን የአዲስ አበባ የኑሮ ቅኝት እንዲህ የሚመሰክሩት የአዲስ አበባ የኪራይ ቤቶች፣ በመካከሉ ላለው ነዋሪ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና የሚፈጥሩ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ሌላው ጥልቅ ችግር ለመሆኑ በመንግሥትም በሕዝቡም ስምምነት የሚደረግበት ትልቅ ችግር የደላሎች ሚና ነው፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር በተለያዩ አጋጣሚዎች የደላሎችን ተግባር በማስመልከት ከፍተኛ ቅሬታ ሲያሰማ ማድመጥ የተለመደ ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ስለብርቱካን ዋጋ መወደድ ለማሳሰብ በተጠራው የንግድ ሚኒስቴር ስብሰባ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ደላሎች ከሚችለው በላይ ሆነውበት መቸገሩን አስታውቋል፡፡

ጥቂት ቢቆይም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ‹‹ጉዳይ እናስፈጽማለን›› በሚሉ ደላሎች መቸገሩን አስታውቆ ነበር፡፡ ዋናው መሥሪያ ቤት ድረስ ሰተት ብሎ የረዘመው የደላሎች እጅ፣ በተለይ ከሦስት ዓመት በፊት ጡዘት ላይ ደርሶ የነበረውን የአነስተኛ ግብር ከፋዮች ጉዳይ መነሻ በማድረግ በባለሥልጣኑ ጉዳያቸውን ሊያይ የሚችል አካል እንደሚያውቁና እንደሚያስጨርሱላቸውና ውክልና ሳይቀር እንዳላቸው በመግለጽ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሳይቀር ማስቸገራቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡

ይህ መሆኑ ደግሞ በየትኛውም የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ላይ ደላሎች አይነኬና የማይፈነቀል ሚና ይዘው ለመቆየታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ከቤት ሠራተኛ ቅጥር ጀምሮ በቤት ሽያጭና ግዥ፣ አሁን በግልጽ አይሁን እንጂ በድብቅ የመሬት ሽያጭና ግዥ በማካሄድ፣ ከውጭ ዕቃ በማስመጣትና ደንበኛ በማፈላለግ ላይና በየትኛውም የኢኮኖሚ አውታር ላይ የደላሎች ሚና ከደም ሥር በላይ ሆኖ ይታያል፡፡

በቤት ኪራይ ላይ የሚታየው የደላሎች ጣልቃ ገብነት ደግሞ አብዛኛውን የከተማ ነዋሪ ከማንገሽገሽ አልፎ አንዳንዶችን ለጠብ ሲጋብዝ ማየት እየተለመደ ነው፡፡ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ለሚከናወኑ የኪራይ ድርድሮች ደላሎች ማዕከላዊውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ ያለደላሎች ጣልቃ ገብነት የትኛውም ቤት አይከራይም፣ አይሸጥም ሲባል መስማት የተለመደ ነው፡፡ በመካኒሳ ባቱ አራት ባለሁለት መኝታ ቤት ለመከራየት ፈልጋ ዘበኞችን የጠየቀችው እመቤት ጌታቸው የተባለች ወጣት፣ አከራዩን በስልክም በአካልም ማግኘት እንደማትችል ይልቁንም የቤቱን ቁልፍ ከያዘው ደላላ ጋር ተነጋግራ ከተስማማች መከራየት እንደምትችል እንደተነገራት ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡

በገዥና ሻጭ መካከል በቀጥታ የሚደረጉ ስምምነቶችን በዚህ ምክንያት ማድረግ አደጋች ሆኖ ይታያል፡፡ አንዳንድ የኮንዶሚኒየም ኮሚቴዎች ግን ይህንን አጥር በመስበር፣ በአከራይና ተከራይ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ ሲጣጣሩ ይታያሉ፡፡ ደላሎች ለአከራዩ የቅድሚያ ክፍያ ለአንድ ዓመት፣ ለስድስት ወር አለያም ለሦስት ወር የሚደረጉ የኪራይ ክፍያዎች ላይ ከሦስት እስከ አምስት በመቶ የአገልግሎት በማስከፈል እንደሚያከራዩ ሲገለጽ፣ ደላሎች በባለቤት ስም ሆነው ለሚያከራዩት ቤት እስከ አሥር በመቶ እንደሚያስከፍሉም ይታወቃል፡፡

የቤት ኪራይ ዋጋን በሚመለከት በአሜሪካ እንደሚሠራው ዓይነት ጥናት በኢትዮጵያ ይፋ ሲደረጉ ባይታም፣ ለአገሪቱ የዋጋ ንረትና ግሽበት አስተዋጽኦ እንዳለው የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ በየወሩ ይፋ የሚያደርገው የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ አሃዝ ያመለክታል፡፡ የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ (ሸማቾች ለተወሰኑ ዕቃዎችና አገልግሎቶች የከፈሉትን አማካይ የዋጋ ለውጥ ለመለካት የሚያገልገግል ጠቋሚ አሃዝ ነው ሲል ኤጀንሲው ይገልጸዋል) ሲተነትን፣ ምግብ ነክ የሆኑና ምግብ ነክ ያልሆኑ የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ብሎ ባስቀመጣቸው መለኪያዎች መሠረት፣ ምግብ ነክ ካልሆኑት መመዘኛ አሃዞች መካከል፣ የሸማቾች የችርቻሮ መመዘኛ ዋጋን በዘንድሮውና በዓምናው መካከል ያለውን ልዩነት በማነፃፀር ያቀርባል፡፡ በዚህ መሠረት ከቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ ከውኃና ኢነርጂ ወጪዎች ጋር የተደለደለው የቤት ኪራይ አንድ ላይ 7.8 ከመቶ ጭማሪ በማሳየት፣ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ከነበረው አገር አቀፍ ጠቅላላ የችርቻሮ ኢንዴክስ ጋር ሲነፃፀር የ7.9 ከመቶ ጭምሪ እንዲሳይ ምክንያት ለመሆን መቻሉን የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል፡፡ እስካሁን ባለው አካሄድም የቤት ኪራይ ወጪ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ ሆኖም ይህ ጠቋሚ አሃዝ የቤት ኪራይ ዋጋን በተናጠል ካለማመልከቱም በላይ፣ ምን ያህል የቤት ተከራዮች እንዳሉ (የመኖሪያና የሥራ ቦታ) አያሳይም፡፡ ምን ያህል ተጨማሪ ተከራይ ሊኖር እንደሚችል፣ የኪራይ ዋጋ በቀጣዩ ወር ወይም ዓመት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ወዘተ. ያለውን ትንታኔም የሸማቾች ዋጋ መመዘኛው አይጠቁምም፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>