Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ዶ/ር መረራ ጉዲና እና አቶ ገብሩ አስራት ለአንድነት ፓርቲን ጥያቄ ምላሽ ሰጡ

$
0
0

በአንድነት የግምገማ ሪፖርት ላይ የመድረክ

 አባል ፓርቲዎች ምላሽ

-   አንድነት በመድረክ ውስጥ ስላለው ሚና በተመለከተ ለአንድ ወር ተካሂዶአል የተባለው ጥናት የመንገድ ላይ ሥራ ነው

      ዶ/ር መረራ ጉዲና

-   የአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት መድረክ እንዲገመገም ማዘዝም ሆነ በዚህ ላይ ተመስርቶ የሚሰጠው ውሳኔ ተቀባይነት የለውም

    አቶ ጥላሁን እንደሻው

-   “በመድረክ ሕገ-ደንብና ፕሮግራም ላይ ለመነጋገር በመድረክ ጉባኤም ላይ ተወስኗል”

አቶ ገብሩ አስራት

 

በዘሪሁን ሙሉጌታ
Dr Merera gudinaየአንድነት ፓርቲ መድረክን የሚገመግም ሪፖርት በብሐራዊ ምክርቤቱ ቀርቦ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ሌሎች የመድረክ አባል ፓርቲ አመራሮች አስተያየት ሰጥተዋል። ምንም እንኳ የግምገማው የውሳኔ ኀሳብ በትክክል ባይረዱትም ከዚህ ቀደም በወጡ መረጃዎች በአንድነት በኩል እየተሰጠ ባለው ኀሳብ ላይ ምላሽ ሰጥተዋል። አመራሮቹ የሰጡት ምላሽ እንደሚከተለው ቀርቧል።
የመድረክ አባል ድርጅቶች የሆኑት የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረንስ (ኦህኮ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው አንድነት በመድረክ ውስጥ ስላለው ሚና በተመለከተ ለአንድ ወር ተካሂዷል የተባለው ጥናት ‘‘የመንገድ ላይ ስራ ነው’’ ሲሉ አጣጥለውታል። እስካሁንም በአንድነት በኩል በፅሁፍ የቀረበ ነገር እንደሌለ ገልፀዋል።
በአንድነት ፓርቲ ውስጥ መድረክን በተመለከተ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች እንዳሉ አይካድም ያሉት ዶ/ር መረራ መገንዘብ ያለባቸው ግን ‘‘ከመድረክ ውጪ መንቀሳቀስ አይጠቅማቸውም። ሁላችንንም አይጠቅምም ተነጣጥሎ መሄድ ማንንም አይጠቅምም። ለአለፉት ሃያ አመታት ያየነው ነገር ነው። ስለዚህ ፖለቲካ ያልገባቸው ሰዎች በዛም በዚህም በሁሉም አካባቢ እንዲህ ቢሆን… እንደዚያ ቢሆን የሚሉት ነገር አይጠቅምም’’ ብለዋል።
‘‘አንዳንዶቹ በሚያውቁትም በማያውቁት ዝም ብለው እኚ… እኚ ይላሉ እንጂ ችግሩ ከብሔርና ህብረብሔር በላይ የሰፋ ነው። ህብረብሔር ነን የሚሉትም የሚባሉትን አልሆኑም። የብሔር ንቅናቄ እንፈጥራለን የሚሉትም የሚባሉትን አልሆኑም። ስለዚህ የፖለቲካ ግራ መጋባት ነው’’ ሲሉ ገልፀውታል።
ይሁን እንጂ ባለፉት አራት አመታት መድረክ በሚፈለገው ደረጃ እየተንቀሳቀሰ አለመሆኑ ግን ‘‘ሁላችንንም ያስማማናል’’ ያሉት ዶ/ር መረራ ‘‘መንግስት በፈጠረው የተበላሸ የፖለቲካ ሁኔታም ሆነ በራሳችን ችግር በምንፈልገው ደረጃ ላይ አይደለንም። ይሄ ችግር የእኛ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሀገሪቱ ፖለቲካ ታስሮ ነው ያለው’’ ብለዋል።
መድረክ ወደ ‘‘ግንባር’’ ሲያድግ መታየት የነበረባቸው የፕሮግራም ልዩነቶች በተመለከተም ዶ/ር መረራ ሲናገሩ፤ ‘‘የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር የፕሮግራም ችግር አይደለም። ከኢህአፓ እና መኢሶን ጀምሮ ያለው ችግር የፖለቲካ ፕሮግራም ችግር አይደለም። አንዳንዶች ዝም ብለው ነው የሚቃዡት፤ ለምሳሌ ኢህአፓና መኢሶን መሰረታዊ የፖለቲካ ልዩነት አልነበራቸውም። ልዩነቱ የአካሄድ ወይም የአሰራርና የስትራቴጂ ሊሆን ይችላል። አሁንም የኢህአዴግ ከሚቀልባቸው ሰዎች የሚነሳ ጥያቄ እንጂ ችግሩ የፖለቲካ ፕሮግራም አይደለም’’ ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከአንድነት ፓርቲ እየተነሳ ያለው ጥያቄ ለወደፊቱ መድረክን ምን ያህል ሊጎዳው እንደሚችልም የተጠየቁት ዶ/ር መረራ ‘‘ማንኛውም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት ብቻውን ኢህአዴግን መግፋት አይችልም። አሁንም አስረግጬ የምናገረው ማንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቡድን ብቻውን ይሄንን መንግስት ወደ ድርድር አምጥቼ አሸንፋለሁ ቢል ህልም ነው የሚሆነው። የሰፋ ህብረት የሰፋ ትብብር፣ የሰፋ መተማመን ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ የሚንቀሳቀሱ ህልመኞችና ፖለቲካም ጨርሶ ያልገባቸው ናቸው። ብዙ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ኃይሎች በዓለም አብረው ሲሰሩ ይታያል። ለምሳሌ በጀርመን የቀኝ ኃይል ከሶሻል ዲሞክራሲ ከሚባለው የግራ ዘመም ኃይል ጋር እየሰራ ነበር። በእስራኤልም ቀኝም ግራም ሆነው መሀል ላይ ሆነው ሲሰሩ ነበር። በእኛ በኩል ዋናው ችግር አብሮ የመስራት ነው። በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ መደራደርም ይቻላል።’’ ሲሉ መልሰዋል።
Arenaየአረና ትግራይ ለሉአላዊነት (አረና) ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ምን እንደሆነ እንደ አረናም ሆነ እንደ መድረክ የታወቀ ነገር እንደሌለ ከገለፁ በኋላ በመድረክ ህገ-ደንብና ፕሮግራም ላይ እራሱ መድረክ እንዲነጋገርበት ባለፈው የመድረክ ጉባኤ ላይ መወሰኑን አስታውሰዋል።
አንድነት እንደ አንድ የመድረክ አባል ድርጅት ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ ማንሳት እንደሚችል የገለፁት አቶ ገብሩ ሁሉም ፓርቲዎች በመድረክ ውስጥ እንዲሟሉላቸው የሚፈልጉትን ጥያቄ ማንሳት ይችላሉ ብለዋል። ይሁን እንጂ ፓርቲዎቹ የሚያሳስባቸውን ጉዳይ አነሱ ማለት በቀጥታ መድረክን ያፈርሰዋል በሚል መነሻ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል። ነገር ግን ጥያቄዎች ካሉ ተነስተው በዛ ላይ ውይይት ማድረጉ አግባብ ነው ብለዋል።
 የመድረክ የወቅቱ ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንደሻው አንድነት ፓርቲ መድረክን የመገምገም ስልጣን የለውም ብለዋል። ‘‘መድረክ እራሱን የሚገመግምበት የራሱ አሰራር አለው። የራሱ የፓርቲ አካላት አሉት። ጉባኤና ስራ አስፈፃሚ አለው። ስራ አስፈፃሚውም የራሱ የተግባር ኮሚቴዎች አሉት። ስለዚህ መድረክ በራሱ አካላት ነው መገምገም ያለበት። አባል ድርጅቶችም ቢሆኑ እዛው መድረክ ውስጥ ባላቸው ተወካዮች አማካኝነት የራሳቸውን ድርሻ ያበረክታሉ እንጂ አንድ አባል ድርጅት መድረክን የሚገመግምበት አሰራር የለም።’’ ሲሉ መልሰዋል።
አንድነት መድረክን ከመሰረቱ ፓርቲዎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን የመድረክን አጠቃላይ የፖለቲካ አካሄድ የመገምገም መብት የለውም ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ ጥላሁን፤ ‘‘መድረክ እራሱ ባቋቋማቸው አካላት አሰራሩን በሚገመግምበት ወቅት እራሳችንን እንገምግም ብሎ ኀሳብ ማቅረብ ይችላል። አንድነት ባቀረበው ኀሳብ ለይ ተመስርቶ የመድረክ አካላት ግምገማውን ማካሄድ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ አንድ አባል ፓርቲ በራሱ መድረክን መገምገም አይችልም’’ ሲሉ መልሰዋል።
አቶ ጥላሁን ኀሳባቸውን ሲያጠናክሩ ‘‘የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት መድረክ እንዲገመገም ማዘዝም ሆነ በዚህ ላይ ተመስርቶ የሚሰጠው ውሳኔ ተቀባይነት የለውም። ብሔራዊ ምክር ቤቱ በመጀመሪያ ደረጃ እራሱን ይገምግም። እኛ በመድረክ ጉባኤ ውስጥ ያሉትን የአንድነት ተወካዮችን ነው የምናውቀው። እነዚህ የምናውቃቸው የአንድነት ፓርቲ ተወካዮች እስካሁን መድረክን እንገምግም ብለው ጥያቄ አላቀረቡም። ከዚህ ውጪ የአንድነት ብሔራዊ ምክርቤት ግምገማ ሙሉ በሙሉ ህገ-ወጥ ነው’’ ብለዋል።
የአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት የመገምገም ስልጣን ያለው በመድረክ የሚሳተፉ የራሱን የአንድነት ተወካዮችን ‘‘ምንሰራችሁ?’’ ብሎ መገምገም እንጂ መድረክን እንደ አንድ አካል መገምገም አይችልም ያሉት አቶ ጥላሁን የአንድነት ግምገማ የድርጅቱ (የአንድነት) የውስጥ ትግል ነፀብራቅ ነው ብለዋል።
Medrek 2‘‘መድረክ ከተመሰረተ ጀምሮ የአንድነት አባላት መድረክ ውስጥ አብረን እንሂድ ወይስ እንተው በሚሉ ወገኖች ክርክር ነበር። የመድረክን ፕሮግራም አንቀበልም ያሉ የፓርቲው አባላት ከፓርቲው መውጣታቸውን እናውቃለን። እንቀበላለን ያሉት ደግሞ በድምፅ ብልጫ አሸንፈው አንድነት ወደ መድረክ እንዲገባ አድርገዋል። በነገራችን ላይ አንድነት ወደ መድረክ የገባው ሌሎቻችን አንድ ፎርም አቋቁመን በዛ ላይ ውይይት ካደረግን በኋላ ዘግይቶ ነው። በመድረክ ምስረታ መነሻ ላይ አንድነት አልነበረም። እንዲገባ ስንጋብዘው ‘‘እንግባ አንግባ’’ በሚል ተከራክረዋል። በድምፅ ብልጫ የተሸነፉት ወጥተው ሰማያዊ የሚባል ፓርቲ እንደመሰረቱ እናውቃለን። አሁንም እንደገና ተመልሰው መድረክ አልጠቀመንም የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ይጠቅመናል መድረክ ውስጥ መቆየት ይሻለናል የሚሉም አሉ። እና በእነዚህ ሰዎች መካከል የሚደረገው ክርክር የራሱ የአንድነት የውስጥ ክርክር እንጂ እኛን የሚመለከት አይደለም። እኛ አንድነት መድረክ ውስጥ መሳተፍ ይጠቅመናል ብሎ ወስኖ ካቀረበው አካል ጋር እየሰራን ነው ያለነው። ያ አካል ደግሞ በመድረክ የተግባር ኮሚቴ ውስጥ ተመድቦ እየሰራ ሲሆን መድረክ ይገምገም የሚል ኀሳብ እስካሁን አላቀረበም’’ ሲሉ ገልፀዋል።
በመድረክ ውስጥ እንቀጥል ወይስ አንቀጥል የሚለው የአንድነት የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ እኛን አይመለከተንም የሚሉት አቶ ጥላሁን ይልቁኑ መድረክ የትግል ጉዞውን በመቀጠል በቅርቡ ይፋ ያደረገውን ማኒፌስቶ በመያዝ ሕዝብ ለማወያየት ጥረት እያደረገ መሆኑን አያይዘው ገልፀዋል።n
(ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 399 ሚያዚያ 23/2005)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>