Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ኢትዮጵያ በርግጥ ዴሞክራሲ ይገባታል ወይ?

$
0
0

532059_547719218612772_154310823_n በገለታው ዘለቀ

መቼም የዶክተር ብርሃኑ ነጋን ቃለ መጠይቅ ሳዳምጥ የምማርበት ኣንዳች ነገር ኣላጣም። ይህቺን ጽህፍ ስጽፍም ለመጻፍ ብየ ሳይሆን  ከሰማሁት ላይ ቀንጠብ ኣድርጌ የተማርኩትን ለራሴው ለማጎልበት ነው። ዶክተር ብርሃኑ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ኣንድ የ ፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ኢትዮጵያ ኮንስትቱየንሲ እንደሌላት ኣርጎ እንደነገራቸው ሲነግሩን ላፍታ በዚህ ኣባባል ዙሪያ ከራሴ ጋር ተወያየሁ።

 

በርግጥ በዚህ ሃሳብ ዙሪያ በተለያየ መንገድም ቢሆን የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማስተናገድ የተዘጋጀች ኣገር ናት ወይ? እውነተኛው ዴሞክራሲ ቢመጣ የምንይዝበት ኣቁማዳው ኣለን ወይ? በሚል እንደ ዜጋ ኣስቤ ኣውቃለሁ። ዛሬ ደሞ የዚያ ምሁር ኣባባል ለ ውይይት የበለጠ የሚያነሳሳ ሆነና እንደ ዜጋ ታየኝ።

 

ያ ሰው እንደ ኣንድ ኢትዮጵያዊ ምሁርነቱ ያሳሰበውን ነው የተናገረው።የዚህ ሰው ስጋት የብቻው ኣይመስልም። ባንድም በሌላም በኩል ይህን ስጋት የሚጋሩ ወገኖች መኖራቸው ኣይቀርም።

 

ይህ ሰው እና ሌሎች የዚህን ሰው ኣሳብ የሚጋሩ  ዴሞክራሲን ለማስተናገድ ኢትዮጵያ ኮንስትቱየንሲው የላትም ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ሊያብራሩ የሚገባቸው እነሱ ናቸው። ይሁን እንጂ ኮንስትቱየንሲ ሲባል መራጭ ቡድን ወይም በኣንድ የተመረጠ ወይም የተመረጡ ተወካዮች ስር የሚገኙ መራጮች እንደማለት ነው። በሌላም ኣገላለጽ የጂኦ ፖለቲካው ክፍፍል ማለትም ነው። በዚህ ጽሁፍ ኮንስትቲየንሲን በዚህ ኣጥር ክልል ውስጥ ከትተን ለመወያየት እንሞክራለን።

 

ታዲያ ይህ ቡድን ወይም ኣካል የላትም ማለት ምን ማለት ነው? መራጩ ኣካል በርግጥ ኣለ ይሁን እንጂ የላትም ሲባል ኣሁን ባለችበት ደረጃዋ ዴሞክራሲን ለማስተናገድ ኣቅም የለም ተብሎ ሊወሰድ ይችላል።

 

ርግጥ ነው ዴሞራሲ ያዢዎች (holders) ያስፈልገዋል። ግን ደሞ ዴሞክራሲን የሚይዙት ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ ግለሰቦችም ናቸው። ዴሞክራሲ ሁለት ያዢዎች ኣሉት ማለት ነው። ቡድኖች የቡድን ሃብት የሆኑትን ሁሉ የሚንከባከቡበት መርህ በዚህ በዴሞክራሲ የተቃኘ እንዲሆን ያስፈልጋል። ባንጻሩ ግለሰቦች ደሞ የራሳቸውን መብትና ግዴታ የሚይዙበት የሌሎችን መብትና ግዴታ የሚያከብሩበት መርህም በግለሰቦች ህይወትም ያድራል።

 

ወደ ላይኛው ሃሳብ እንውጣና እናውራ። የዚያን ምሁር ስጋትም ጥቂት እንመርምር። ኮንስትቲየንሲ የለም ሲሉ እነዚህ መራጭ ቡድኖች ያላቸውን ኣቅም ይመለከታል ብለናል። በዚህ ኣገባብ ዴሞክራሲን ለማስተናገድ ኣቅም ከሚገለጽባቸው ኣውዶች ኣንዱ ምንድን ነው?

 

ምርጫ

election

ኣንዱ የዴሞክራሲ ተከታይነት ችሎታ ተግባራዊ መለኪያው ምርጫ ነው:: ምርጫ በዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው የዴሞክራሲ ተግባራዊ መገለጫው ነው። ምርጫ ደሞ ውሳኔ ነው። ለ ውሳኔ ደሞ መረጃ የማግኘትና መረጃን የመገምገምን ኣቅም ይጠይቃል። የውሳኔያችን ጥራት የሚካለውም ባገኘነው የመረጃ ጥራትና በመገምገም ችሎታችን ልክ ነው።

 

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ያላትን ተክለ ሰውነት መገምገም ይገባል። የኢትዮጵያ መራጭ ቡድኖች ይህ ኣቅም የላቸውም ወይ? ብለን መጠየቅ ኣለብን።

 

እንግዲህ ኢትዮጵያ ስንል መታየት ያለበት ነገር 80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ በገጠር የሚኖረው ህብረተሰብ ቀድሞ ወደ ህሊናችን ይመጣል። ይህ ሰፊ ህዝብ ኣርሶ ኣደር እና ኣርብቶ ኣደር ነው።

 

ከሃይለስላሴ ጀምሮ ስልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ በገባ ቁጥር በገጠሩና በከተማው መካከል እያደር እየሰፋ የሄደ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ለውጥ ግዙፍ ክፍተት እጅግ ከመለያየታቸው የተነሳ ገበሬውን ከከተሜው ለውድድር ለመቅረብ እንዳይችል ያደርገዋል። በእውቀት ሃብትም ቢሆን ዘመናዊው እውቀት ከተሞች ኣካባቢ የተጠራቀመ ሲሆን ሰማኒያ በመቶ የሚሆነው ከዘመናዊነት በጅጉ ርቆ ነው ያለው። በኢትዮጵያ ውስጥ በገጠሩና በከተማው ያለው ያልተመጣጠነ እድገት የሚገለጸው በ ኑሮ ዘያቸው ሁሉ ነው ።

 

በ ኢትዮጵያ ውስጥ ኣንድን ኣርሶ ኣደርና ኣንድን ከተሜ ስናይ ባለባበስ በኑሮ ዘየ በኣነጋገር በእውቀት ያላቸው ክፍተት በርግጥ በኣንድ ኣገር የሚኖሩ የ ኣንድ ኣገር ልጆች ኣያስመስላቸውም። ይህ ማለት ከተሜው ደልቶት ወይም በጣም የተመቸው ነው ለማለት ኣይደለም። ከ ኣርሶ ኣደሩና ከኣርብቶ ኣደሩ ጋር ያለውን ህዝብ በኢትዮጵያ ካሉ ዋና ዋና ከተሞች ህዝብ ጋር ወይም 20 በመቶ ከሚሆነው ከተሜ ጋር በኣንጻራዊ መልኩ ስናይ ለማለት ነው።

 

በርግጥ ይህ ገበሬ የራሱ የሆኑ እውቀቶች ኣሉት። በልምድ ያካበታቸው የኣስተራረስ እና የከብት ኣረባብ ዘዴዎች፣ የልምድ ያየር ጸባይ እውቀት፣ ኣጠቃላይ ኣካባቢውንና ተፈጥሮን የሚያይበት የራሱ እውቀቶች ኣሉት። በተለይ በስነ -ቃሉ የሚገልጻቸው የረቀቁ ኣሳቦች ኣንዳዴ ተምሪያለሁ የሚለውም ቶሎ ወይም በቀላሉ ላይረዳው ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ሰፊ ህዝብ ታድለን ዴሞክራሲ ወደ ሃገራችን ገብቶ መድብለ ፓርቲ ተመስርቶ፣ የፓርቲዎች መወዳደሪያ ሜዳ ተደልድሎ ምርጫ ቢጀመር ኣንደኛ ምርጫ ውሳኔ ሲሆን ውሳኔ ለመስጠት ደሞ መረጃ ያስፈልጋል ብለናል ይህ ሰፊ ህዝብ ደሞ ካለው የመረጃ መረብ ውሱንነትና ኣክሰስ ኣንጻር ሰፋ ያለው ህዝብ የጠራ መረጃ የሚያገኝበት ሁኔታ ኣሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ኣልተመቻቸም። የገበሬው ኣሰፋፈር ራሱ እዚያና እዚያ ከመሆኑ የተነሳ መረጃዎችን በቀላሉ ለማፍሰስ ኣይቻልም። ሁለተኛውና ትልቁ ችግር ለምርጫ የሚሆን ኣቅም ኣለን ወይ? የሚለው ጉዳይ ነው። እንግዲህ ውይይታችን በሃቀኝነትና በቅንነት ተመስርቶ መሆን ኣለበት ብለናል።

 

የዚህን ኣርብቶ ኣደርና ኣርሶ ኣደር ተክለሰውነት ስናይ በርግጥ ፓርቲዎች ኣማርጭ ፖሊሲዎቻቸውን ሲያቀርቡ የፓርቲዎቹን ኣቋም የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ፖሊሲዎቻቸውን ይረዳል ወይ? እንደው የተሸራረፈ መረጃ እንኳንም ቢሆን ቀየው ድረስ ሄዶ ቢሰማ ስንቱን ይረዳዋል? ብለን ስናስብ በርግጥ በዚህ በምርጫ በኩል ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ኣቅም ከዚህ ከሰፊው ህዝብ ኣካባቢ በኣስተማማኝ ሁኔታ ኣናገኝም። ይህ ሃብት ወይም ኣቅም የለንም። የሌለንን የለንም ነው ማለት ያለብን። ገበሬው ይህ ኣቅም የለውም ማለት የሱ ጉድለት ኣይደለም። ኣላወቀም፣ ኣልተማረም  ምን ያድረግ።ኣሁን እየተናገርኩ ያለሁት ስለምወዳት ገበሬዋ እናቴና ስለምወደው ገበሬው ኣባቴ ነው።

 

እዚህ ላይ ስለዚህ ስለ ሰፊው ህዝብ ረገጥ ኣድርገን የምናወራው በዴሞክራሲ ጊዜ በተለይ በምርጫ ጊዜ የማጆሪቲ ጉዳይ ትልቅ ቦታ ስላለው ነው። እንግዲህ ኣገራችን ኢትዮጵያ ኣዲስ ኣበባ ብቻ ኣይደለችም። በኣራቱም ማእዘናት ያለውን ሰፊውን ህዝብ የያዘውን የገጠሩን ህዝብ ተከለ ሰውነት መገምገም ዴሞክራሲ እንዴት በኢትዮጵያ ሊስተናገድ ይችላል? ለሚለው ወሳኝ ጉዳይ ለመወያየት መነሻ ይሆናል።

 

ኣገር ሲባል የሚቆመውም በማጆሪቲ ስለሆነ ማጆሪቲ ጎናችንን ማወቅ ያስፈልጋል። እውነተኛ ዴሞክራሲ ዛሬ ተጀምሮ ወደ ምርጫ ስንገባ ይህ ሰፊ ህዝብ የሚሰጠው ውሳኔ በኣገሪቱ መጻኢ እድል ላይ ምን እንድምታስ ሊኖረው ይችላል? ተብሎም ይታሰባል። ኢትዮጵያ ዛሬ ወደ እውነተኛ ምርጫ ብትገባ  ከዚህ ከሰፊው ህዝብ እድሜው ለምርጫ የደረሰውን ብናወጣ በርግጥ ሰፊው ህዝብ እውቀት በተሞላበት በመረጃ በተደገፈ ይከውናል ማለት ከ እውነት የራቀ ነው። ይህ የህብረተሰብ ክፍል በምርጫ ጊዜ የፖለቲካ ድርጅቶችን ርእዮት ገምግሞ ሳይሆን እጩዎቹን በኣካል የሚያውቃቸው ከሆነ እከሌ ጥሩ ሰው ነው ተሰሚነት ኣለው እያለ ከመምረጥ ያለፈ ሃላፊነት ሊሸከም ኣይችልም። ይህ እንግዲህ መራራም ከሆነ እውነት ነውና መቀበል ነው። የዚያ ምሁር ስጋት ኢትዮጵያ የማጆሪቲውን ኣቅም ኣገናዝቦ ያየ በመሆኑ እውነት ነው ብለን እንድንቀበል ያደረገናል።

 

ይህን መራራ እውነት ከተቀበልን በሁዋላ ኣንዳንድ ለዴሞክራሲ መልካም ቅናት ያላቸው ወገኖች ብቻ የዴሞክራሲው መሬት ይደልደል እንጂ ስለምርጫ ችሎታችን ኣንጨነቅም፣ ህዝቡ እንዳወጣለት ይምረጥ የሚል ቸርነትና ቅንነት የተሞላበት ኣሳብ ሊሰነዝሩ ይችላሉ ። ከዚህም ኣልፎ የዴሞክራሲው ወለል ከተነጠፈ በዴሞክራሲ የሚያምኑ ፓርቲዎች ከመጡ ማንም ተመረጠ ማን ይሄን ያህል ኣገር ሊጎዳ የሚችል ነገር ስለማይፈጠር ኣያሰጋም የሚል ሃሳባዊ የሆነ ኣመለካከትም ከሌላ ኮርነር ሊመጣ ይችላል።ይህ ኣባባል መልካምነትና ቅንነት ቢታይበትም ሳይንሳዊነት ስለሚጎለው ምን ያህል ሩቅ እንደሚሄድ ኣይታወቅም።

 

በሌላ በኩል ስለኮንስትቲየንሲ ስናወራ የሚመጣልን የምርጫ ኣቅማችን ብቻ ሳይሆን እነዚህ ቡድኖች ከመረጡስ በሁዋላ በዴሞክራሲ መርህ የመተዳደር ኣቅም ኣላቸው ወይ? በርግጥ ዴሞክራሲ የሚባለው ነገር ይህ ሰፊ ህዝብ ገብቶታል ወይ? ቡድኖች ወይም ክልሎች ሊባል ይችላል ዴሞክራሲን ለመተግበር ይችላሉ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችም ኣብረው ይነሳሉ። በዚህ በኩል ኢትዮጵያ በማጆሪቲው ጎኑዋ ስትታይ በርግጥ ኣቅም ሊያንሳት እንደሚችል ኣያጠያይቅም። ካላት የተማረ ሃይል እጥረት ችግር የተነሳ በመተግበሩ ጊዜ ከፍተኛ ችግሮች መታየታቸው ኣይቀርም። ይህም መራራ እውነት ቢሆንም መቀበል ነው።

 

እንግዲህ ኢትዮጵያ ያላት ገጽታ እንዲህ የሚታይ ከሆነ የሚያስፈራ ጥያቄ ይከተላል። ታዲያ ዴሞክራሲ ይቅርብን ወይ? ለዴሞክራሲ የምንበቃው በትምህርት በልጽገን ስንገኝ ብቻ ነው ወይ? የጀመርነው የዴሞክራሲ ትግላችንስ ምን ይዋጠው? ዴሞክራሲን ለመረዳት ያልቻሉ፣ ጽንሰ ሃሳቡን ለመተንተን ያልበቁ፣ ያልተማሩ ህዝቦች ባለማወቃቸው በጭቆና ስር እንዲቆዩ ሊፈረድባቸው ይገባል ወይ? ኢትዮጵያ በዚህ ተፈጥሮዋ እንዴት ነው ዴሞክራሲን ልታስተናግድ የምትችለው? የሚሉ መራራ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያደርገናል።

 

ኢትዮጵያ ብዙው ህዝቡዋ ኣልተማረም ወይም ኣቅም ያንሰዋል ማለት ኢትዮጵያ የምትባለው ሃገር የላትም ማለት ኣይደለም። ኢትዮጵያ ከፍ ሲል እንዳልነው በከባድ ርቀት የሚሸቀዳደሙባት ኣገር ስትሆን የበራለት በቁጥሩ ኣነስተኛ ቢሆንም የተማረና ለምርጫ በሚገባ የሚበቃ ሃይል ኣላት። ይህ ሃይል በከተሞች ኣካባቢ የተከማቸ ሲሆን በገጠሩ ኣባቱና ወገኑ ዘንድ እንደ ተወካይ የሚታይ በዚህ በገጠሩ ወገኑ ላይ ከባድ ተጽእኖ ያለው ነው። ገበሬው የተማረውን ልጁን ያምናል። ሳይታደል ቀርቶ ባይማርም በትምህርት ኣጥብቆ ያምናል። በተለይ የሰሜኑ ገበሬ በስነ- ቃሉ “የተማረ ይግደለኝ” እያለ እያዜመ ለተማረ ወገኑ ያለውን እምነት ሲገልጽ ይኖራል።

 

ያልተጻፈ ስምምነት ቢሆንም ይህ ኣርሶ ኣደርና ኣርብቶ ኣደር በምርጫ ጊዜም በእጃዙር ለዚህ ለተማረው ወገኑ ውክልና የሰጠ ሁሉ ይመስላል። እዚህ ላይ ኣንድ ጊዜ የሰማሁትን ማንሳት ለሃሳቡ ማሳያ ይሆናል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኣቶ መለስ ዜናዊ ኣንድ ጊዜ በቤተ መንግስታቸው የኣዲስ ኣበባ የኒቨርሲቲ ምሁራንን ሲያነጋግሩ ኣንድ ምሁር ያሉት ኣይረሳኝም። እኚህ ምሁር ለእረፍት ጊዜ ወደ ገጠር ዘመዶቻቸው ሲሄዱ የዚያ ቀበሌ ህዝብ የሚያናግራቸው እና የሚጠይቃቸው እንደ መንግስት ተወካይ ኣድርጎ ነበር። ችግራችንን ኣሳስቡልን፣ መንገድ ስሩልን፣ ወዘተ ይጠይቁ ነበር ማለት ነው። እነዚህ ወገኖች የኣቶ እከሌ ልጅ ለትልቅ ትምህርት ኣልፎ ኣዲስ ኣበባ ነው ማለት በደመነፍሳቸው ያካባቢያቸው ተወካይ ኣይነት ነው።

 

እኒህ ሰው በሃሳብ ደረጃ የዚያ ኣካባቢ ተወካይ ናቸው ማለት ነው። እኚህ ምሁር በዚያ ኣካባቢ ህዝብ ምርጫ ላይ ከባድ ተጽእኖ ይኖራቸዋል። የሳቸው ምርጫ የዚህን ኣካባቢ ህዝብ ምርጫ በጅጉ ሊጫነው ይችላል። በምርጫ ጊዜ መተማመን የሌለው ገበሬ ከኚህ ሰው የሚያገኘው ምርጫ ለውሳኔ የማብቃት ሃይሉ ከፍተኛ ነው።

 

በቅንጅት ጊዜ ገበሬው ቅንጅትን የመረጠበት ኣንዱ ጉዳይ የልጆቹ ተጽእኖ ነበር።የኣንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ሳይቀሩ ከኣስተማሪዎቻቸው የሰሙትን ለወላጆቻቸው ሲነግሩ፣ ሲያስረዱ፣ያልተማረው ገበሬ በዚህ በኩል ልጆቹን ይሰማና ያምን ነበር። ዩኒቨርሲቲ ኣካባቢ ያሉ ወጣቶች በቅንጅት ልባቸው እንዳረፈ የተረዱና እነሱም በተወሰነ ደረጃ የገባቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ምርጫቸው የሆነው ቅንጅትን እንዲመርጡላቸው ቤተሰቦቻቸውን ዘመዶቻቸውን ተጭነው ነበር። ይህ ሁኔታም ቅንጅት በሰፊው ገበሬ ዘንድ ተመራጭ እንዲሆን ኣድርጎታል። ኣንዲት እድሜዋ ለምርጫ ያልደረሰ ልጅ ኣያቱዋን በስላሴ ኣስምላ እስከ ምርጫ ጣቢያ ድረስ መርታ ሄዳ ቅንጅትን እንዲመርጡላት ኣድርጋ እንደነበር ሰዎች ሲያወጉ ሰምቻለሁ።

 

እውነተኛ ምርጫ በኢትዮጵያ ቢመጣም መረጃው ከበራለት ትውልድ ሄዶ ሰፊውን ህዝብ በውዴታ እጁን ይዞ የሚያስመርጥበት ሁኔታ ነው እኛ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ በእጃችን ያለን ሃብት። ይህ ሂደት የዴሞክራሲን መስረታዊ ትምህርት ይጥሳል ኣይጥስም ኣንከራከርም። በመጀመሪያ ደረጃ ያ ብዙው ለምርጫ መረጃ የሌለው ወይም መረጃን ለመተንተን ኣቅም የሌለው ህዝብ በክፉ ተጽእኖ ሳይሆን በፈቃዱ የልጆቹን ምክር ሰምቶ መምረጡ ኢዴሞክራሲያዊ  ሂደት ግን ኣይደለም።ልጆቹ በሚገባ ቋንቋ ኣቅለው ኣስረድተውትም  ነው ብለን ለጠየቀንም እንመልሳለን።።

 

ዋናው ነገር መሆን ያለበት ኢትዮጵያ እንደ ሃገር የመምረጥ ኣቅም የላትም ተብላ ምርጫ ልትከለከል ከምርጫ ልትከላ ኣትችልም። የበራለት ትውልድ ሃይሉዋ ነውና። የዚያ ምሁር ፍርሃት ፋክቶችን ኣጥብቆ የያዘ ቢሆንም ያላየው የዴሞክራሲ ተፈጥሮም ኣለ። ዴሞክራሲ የሚወለድ፣ የሚያደግና የሚያደግ ነገር ነው። ኣሁን የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጥያቄ ዴሞክራሲ የትም ይሁን የት ተወልዶ ኣድጎ የጎለመሰውን ኣምጡልን ኣይደለም። ኣገራችን ይወለድ እና እናሳድገው ነው ጥያቄያችን። ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ኣጥብቃ እንድትፈልግ የሚያደርጋት ምክንያት ብዙህ ተፈጥሮዋን ለማስተናገድ ስለሚረዳት ብቻ ሳይሆን ለማህበራዊ ለውጥ ጎዳናዋ ኣዋጩ መስመር እሱ ሆኖ ስለሚታያትም ነው።

 

ቡድኖች ምርጫን ብቻ ሳይሆን ከምርጫም በሁዋላ ዴሞክራሲን ለመተግበር ልምምድ ውስጥ ስለሚገቡ የቡድኖች ኣቅም ማነስ ዴሞክራሲን ሊከለክላቸው ኣይችልም። መንግስት ሲባልም ፓርቲ ማለት ባለመሆኑ በመንግስት ሲስተም ውስጥ ያሉ የተማሩ ኣቅም ያላቸው ኣቅም የሌላቸውን የፖለቲካ ተወካዮች እየደገፉዋቸው ስለሚሄዱ በዴሞክራሲ የእድገት ጎዳና ላይ ይገባሉ።

 

እንግዲህ በዚህ በምርጫ በኩል በተለይ ኣሁን ኢትዮጵያ ባላት የመምረጥ ሃይል ዴሞክራሲን በእንዲህ ኣይነት ሁኔታ ኣስተናግዳ ማደግ የምትችል በመሆኑዋ መራጭ ቡድኖች ኣቅም ያንሳቸዋል ተብሎ ዴሞክራሲን ልትነፈግ ኣይገባትም።

 የፕሬስ ነጻነትን የ ማስተናገድ ኣቅም ኣለን ወይ?

Eskinder Negaበሁለተኛ ደረጃ የዴምክራት ሃገርነት ኣንዱ ተግባራዊ መገለጫ ፕሬስን መሸከም መቻል ነው። ዴሞክራሲ ምርጫ ብቻ ሳይሆን የፕሬስ ነጻነትን ማስተናገድም ኣንዱ ዋና መስፈርት ነው። በዚህ በኩል ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ኣማራጭ መረጃዎችን በመፈለግ በኩል ከባድ ጥማት እንዳለ ይታያል። ህዝቡ በተለይም ይህ የበራለት ትውልድ የምንለው ኣማራጭ መረጃዎችን በጥብቅ መፈለጉ ብቻ ሳይሆን ይዘታቸውንም የመመዘን ኣቅም ኣለው። በኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ ነጻነትን መሸከም ሲያቅታቸው የሚታዩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። መንግስት ትልቁን ድርሻ ይውሰድ እንጂ ራሳቸው ለዴሞክራሲ ቆመናል የሚሉቱ ፓርቲዎችም ሰፊ ልብ ኣይታይባቸውም። በሁለቱም በኩል ጥብቅ ወሰን የተሰመረ ሲሆን ኣንዳንድ በመርህ ላይ ያተኮሩ ኣስተያየቶች ለሃገር የሚጠቅሙ ትችቶች ሁለቱም ወገን ሜዳ ላይ እየጣላቸው ሊቀሩ ይችላሉ።

 

ፕሬሱ ችግር ያለበት ከመንግስትና ከ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ከራሱም በርካታ ችግሮች ኣሉበት። እውነተኛ መረጃን ማቅረብ የሃገሪቱን የዴሞክራሲ ትግል ያፋጥነዋል የሚለው እምነቱ ዝቅ ያለ ከመሆኑ የተነሳ ዘለፋዎችና በመርህ ላይ ያላተኮሩ እንካ ሰላንታዎች ኣንጀቱን የሚያርሱት ይመስላል።ኣንባቢው ወይም ኣዳማጩም ለ ዴሞክራሲና ለፍትህ መቆሙን የሚያይለት በዚህ ምት (tone) ሲቀርብ ነው ብሎም ያመነ ይመስላል።

 

ታዲያ ፕሬሱ ብዙ ችግሮች ቢኖሩበትም ከፍተኛ ኣስተዋጻኦም ኣለው። ኣንዳንድ የበሰሉ ሚዲያዎች የሚያቀርቡት መረጃ ሊበረታታ ይገባዋል ይህም ዴሞክራሲ እንዲያደግ ኣስተዋ ፆ ኣለው ።

 

ዋናው ነገር ዴሞክራሲ የሚያድግ ነገር ነው ስንል ፕሬስ የሚያደግ ነው ማለታችን ነው። ፕሬስ የሚያደግ ነው ስንል ደሞ የፕሬሱ መረጃ የማቀበል ኣቅሙ ማደግ ብቻ ሳይሆን የመንግስትና የፓርቲዎች ትእግስትና ቀናነት ማደግንም ይጠይቃል።

 

 

መንግስት እንደ ዘበኛ (watchDogs) ያሉትን ጋዜጦች ወይም ሚዲያዎች እነዚህ መንግስት ጥሩ ሲሰራ ጥሩ ሰራ የማይሉ መጥፎ ሲሰራ ብቻ መጥፎውን የሚያጩሁ ናቸው እያለ ይከሳቸዋል። እነዚህ ሚዲያዎች እኮ  ጠባቂዎች (watchDogs)  ናቸው። ተፈጥሮኣቸው ይሄ ነው። በኣንድ በኩል ኢ-ፍትሃዊነት ሲፈጸም ወይም ዝርፊያ ሲፈጸም ይጮሃሉ እንጂ መንግስት ኣንድ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ኣስፋልት ሲያነጥፍ ይህን ሰርቱዋልና ይጨብጨብለት ማለት ኣይጠበቅባቸውም።ተፈጥሮኣቸውም ኣይደለም። ይልቅ መንግስት የነሱን ጩኸት እንደ  እድል እያየው ቶሎ ጉድለቶቹን ሊሞላ ይገባው ነበር።

 

ዋች ዶግስ የማይፈሩና የማይወግኑ መሆን ኣለባቸው። ለዴሞክራሲ ትግል የቆሙትን እየታገልን ነው የሚሉትን ሁሉ ትግሉን የት ኣደረሳችሁት? ብለው ኣጥብቀው መጠየቅ ኣለባቸው። ለዴሞክራሲ ትግል የጀመሩ ቡድኖች ትግል ከጀመሩ ኣመታት ኣስቆጥረው ብዙ ፍሬ ሳይታይባቸው ሲቀር “እየተደራጀን ነው፣ ድርጅታዊ ኣቅማችንን እያጠናከርን ነው…” ሲሉ ይደመጣል። እንደው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሆነ ኣዙሪት ውስጥ ገብቶ ነው እንጂ የኢትዮጵያን የነጻነት ትግል በሚታይ መልኩ ለመጀመር ይህን ያህል እነሱ በሚያወሩት ልክ መደራጀት ኣያስፈልገውም። ይህ መንግስት የሚወድቀው በድርጅታዊ ጥንካሬ ሳይሆን በህዝባዊ ኣመጽ ነው። ይህን ህዝባዊ ኣመጽ ለመምራት ደሞ ህዝቡን ሁሉ ኣባል ኣድርገን መዝግበን መጨረስ ኣለብን እያልን በወረቀት ስራ መድከሙ ምንም ዋጋ የለውም። እውነተኛ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች መመስረታቸውን ሲያበስሩና ጥቂት ሲራመዱ ኣብዛኛው ነጻነት የናፈቀው ህዝብ በሃሳብ ደጋፊና ኣባል ነው የሚሆነው። ተመዝግቦ ኣክቲቭ ፖለቲከኛ መሆን ሳይሆን ኣድርግ የሚባላውን ለማድረግ በሚቀይሱት የትግል ስልት ዋጋለመክፈል የቆረጠ ነው።

 

መቼም ያ የቅንጅት ጊዜ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ብዙ ትምህርት ጥሎ ነው ያለፈው። በዚያን ጊዜ የነበረው የቅንጅት ጥንካሬ በቅንጅት ጽ/ቤቶች ጥንካሬ ኣልነበረም። ህዝቡ ራሱ ራሱን እንደ ቅንጅት መሪም እንደ ኣባልም እያየ ነበር ሲንቀሳቀስ የነበረው። የቅንጅት ጽ/ ቤት ሳያውቅ ቅንጅትን የሚደግፉ ስብሰባዎች ሁሉ ተዘጋጅተው ተካሂደው እንደነበር ይነገራል።

 

ትንሽ የታመኑና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ርእዩት ይዘው የተነሱ ሰዎች በትንሽ ሃይል ህዝባዊ ትግል መምራት የሚችሉበት ሁኔታ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው። ኣይ የለም ሴል እየፈጠርን ብዙ ኣባል ማፍራት ኣለብን የሚል ትምህርት ጠቅላላ እውነት ብጤ ያለው ቢመስልም ተግባራዊ ኣይደለም። ኣሁን ያለው የኢትዮጵያ ትግል የፖለቲካ ሳይሆን የነጻነት ትግል በመሆኑ ህዝቡ ተፈጥሮኣዊ በሆነ መንገድ ተዘጋጅቱዋል። ይህን የተዘጋጀ ኣካል እንዲህ ኣድርግ ወደማለት ደረጃ መራመድ ነው እንጂ ድርጅታዊ መዋቅር ላይ ጊዜ ማጥፋት የ ኣርባ ቀኑን ጉዞ ኣርባ ኣመት እንዲፈጅ ነው የሚያደርገው።

 

ኢህኣዴግን የሚጥሉት በድርጅታዊ ብቃት ሳይሆን በህዝባዊ ኣመጽ ነው ስንል መደራጀት ኣያስፈልግም ወደማለት እንዳይተረጎምብን። መደራጀት ያስፈልጋል:: ግን ኣሁን በሚባለው ደረጃ ይሄን ያህል ህዝቡን ኣንድ ላምስት እያደረግን ኣደራጅተን ሳንጨርስ ይህ መንግስት ኣይወድቅም ማለት ከዚያ ከኢህኣፓ ኣካባቢ የመጣ ትምህርት ሊሆን ይችላል። ቅድም እንዳልነው ኣሁን ያለው የኢትዮጵያ የነጻነት ትግል በእንዲህ ያለ መልኩ ሳይሆን የታመኑ ድርጅቶች በሚጠቁሙት ኣቅጣጫ መሄድ የሚችል ህዝባዊ ትግል ነው ያለው። ህዝቡን በሴል እያደራጁ ቢቆዩ ማሌሊት ኣያስጠኑት፣ወይ ደሞ ስለዴሞክራሲ ወይም ስለ ነጻነት ጥቅም ኣያስተምሩትም። የነጻነት ታጋዮች እንደመሆናቸው ፖሊሲም የላቸውም። በመሆኑም ፊገር የሆኑ መሪዎቻችን የሆነ የህዝባዊ ኣመጾችን እያሳዩ ትግል ማስጀመር ነው እንጂ በሃሳብ ኣባል የሆናቸውን ሰው ሁሉ መዝግበን ካልጨረስን እያሉ ዘክዘክ ማለት የትም ኣያደርሰንም።

 

ዎች ዶግ እነዚህን የፖለቲካ መሪዎች እንዲህ መጠየቅ ማፋጠጥ ኣለበት።  የተቃዋሚ መሪዎችን ሁሉ ኣንዴ ቢጮህባቸው እንደ ወያኔ ደጋፊ ቶሎ መታየት የለበትም። እንዲህ ከሆነ መቼም ኣናድግም።

 

በኣሁኑ ሰኣት መንግስት እሱ የሚፈልጋትን ነቀፌታ ብቻ በኣንዳንድ ጋዜጦች ላይ ብቅ እያደረገ ዴሞክራት ነኝ ለማለት ሲሞክር ይታያል። ጠንከር ያሉ ሂስ የሚያቀርቡትን፣ የሚያጋልጡትን ሁሉ ኣባሮ ጨርሶ የኣለምን ሪከርድ ሰብሩዋል።

 

የተባረሩ ጋዜጠኞች ደሞ በግፍ ስለተባረሩ ከሃገር ሲወጡ የኣክቲቪስት ስራና የኣድቮኬሲ ስራ ወዲያው ተቀብሎ ስለሚውጣቸው ለዴሞክራሲ ቆመናል የሚሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች ምንም ሳንካ እንደሌላቸው እያደረጉ እያቀረቡ መንግስትን ላለማስደሰት ይሞክራሉ። ወይ በሚስጥር የፖለቲካ ድርጅት ኣባል ይሆኑና የዚያን ፓርቲ ችግሮች ለመጠቆም ሃይል ያጣሉ።  ዞሮ ዞሮ እውነተኛ መረጃ፣ ሚዛናዊ መረጃ የሚናፍቀው ህዝብ ከመንግስትም ኣያገኝም የተገፋውም ጋዜጠኛ የነጻነት ታጋይ ስለሚሆን ሚዛናዊ ዘገባ ለማግኘት ይከብዳል።

 

በኣጠቃላይ ግን ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ፕሬስን ለመሸከም ትከሻዋን ኣስፍታ፣ ተቃዋሚዎችም በኛ ላይ ሂስ የምንፈልገውና የፕሬስን ነጻነት ሙሉ በሙሉ የምናከብረው እኛ ስልጣን ስንይዝ ነው ኣይነት ሳያስቡ ፕሬስን ማሳደግ ኣለባቸው።

 

ተወልጄ ባደኩበት ኣካባቢ ባህርና ለዋና የሚሆን ውሃ የሌለበት ኣገር በመሆኑ ዋና ሳለምድ ቀረሁ። ኣሁን እዚህ ባለሁበት ኣገር ኣንድ ቀን እስቲ ዋና ልማር ብየ በስተርጅና ወደ መዋኛ ቦታ ኣመራሁ። ትጥቄን ኣታንሱ። እነዚህ ዋና የሚችሉ ሰዎች እንደሚለብሱት ሆኜ ገባሁ። ውሃው ውስጥ ስገባ የማየው ሁሉ ይዋኛል። ውሃውን ሳያስጨንቁ መሰስ እያሉ ይዋኛሉ። እኔ ትንሽ ልጅ ነው የሆንኩት። ሳንቦጫርቅ ሳንቦጫርቅ ዋልኩ። ከጎኔ ኣንዱ  “ኣይዞህ በርታ ሳያንቦጫርቅ የለመደ የለም” ኣለኝ።

 

ፕሬስ እንደዚህ ነው። በመጀመሪያዎቹ ኣካባቢ ማንቦጫረቅ ሊኖር ቢችል ኣይገርምም። ቀስ እያለ እስኪያድግ ድረስ ትእግስት ያስፈልጋል። በኣጠቃላይ ህዝባዊ ጥማት ያለው በመሆኑ ፕሬስ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊወለድና ሊያድግ የሚችል በመሆኑ ኢትዮጵያ ኣሁን ዲሞክራሲ ይቅርብሽ  ሊያስብላት ኣያስችልም።

 

ወደሁዋላ ታሪካችንን ስናይ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንዳሉት ኣዝማሪዎች ነገስታቱን በ ስነ- ጥበባቸው ይነቅፉ ነበር። መንቀፍ ብቻ ኣይደልም ይመክሩ የህዝቡንም ብሶት ጠቆም ያደርጉበት ነበር። ይህ ዳራ ያላት ኣገር ዴሞክራሲ ነጻነት በጎለበተበት ኣለም ፈጥና በዚህ የዴሞክራሲ መስመር ልታድግ በርግጥ ትችላለች።

 

መድብለ ፓርቲን የማስተናገድ ኣቅም ኣለን ወይ?

 

ይልቅ ኢትዮጵያ ሊያሳስባት የሚገባው ይሄ ነው። የሃገራችን ብዙው ህዝብ ዴሞክራሲ የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ባይረዳም ግን መብቱ እንዲከበር፣ ከዴሞክራሲ ፍሬዎች ሊመገብ መፈለጉ ምርምር የሚሻ ኣይደለም። የሰው ልጅ ሁሉ ልማትን ዴሞክራሲን ይፈልጋል። በመሆኑም የሚያሳስበው ዴሞክራሲን የሚሸከም ህዝብ ኣለን ወይ የለንም ሳይሆን መድብለ ፓርቲ ስርኣት ስንጀምር ሃላፊነት የሚወስዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጨዋታው ሜዳ ላይ በደንብ ይጫወታሉ ወይ? ይሄ ሃብት ኣለን ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው። ።

 

የመድብለ ፓርቲ ስርኣት መቻቻልን፣ መሸነፍና ማሸነፍን የመቀበል ኣቅም ይጠይቃል።ይሄ በተግባር ታይቶ ኣስተያየት የሚሰጥበት ቢሆንም ኣሁን ያሉንን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁመና በሩቁ ስናይ መስተካከል ያለባቸው የኣቅም ማነስን የሚያሳዩ ብዙ ጉዳዮች ኣሉ።

 

ኢህኣዴግን ከዚህ እናውጣው። ምክንያቱም በባህላዊ ቡድን ፖለቲካ የሚያምን የመድብለ ፓርቲ ኣማኝ ስላልሆነ። በኣሁኑ ሰኣት በኢህኣዴግ  ጉያ  የሚፈለፈሉት የወንዝ ተቆርቋሪዎች ብዙ ስለሆኑ ይህ መንግስት የመድብለ ፓርቲ ኣራማጅ ሊያሰኘው ኣይችልም። የዚህ መንግስት እውነተኛ ተፈጥሮው ቡድኖች የየራሳቸውን የወንዝ ተቆርቋሪ ድርጅት እንዲያቋቁሙ ያበረታታል እንጂ በፖሊሲ ብልጫ ሃገር ለመምራት የሚፎካከሩ ድርጅቶችን ኣያፈራም። እውነተኛ ተፈጥሮው የኣንድ ፓርቲ ኣገዛዝን ማስፋፋት ነው። ኢትዮጵያ ኣንድ ብሄር ብቻ ብትሆን ኖሮ ኣንድ የፖለቲካ ድርጅት ብቻ ለማቋቋም የሚሻ ተፈጥሮ ያለው ነው የሚመስለው። ስለዚህ እሱ ከጨዋታው ይውጣና ሌሎቹ በርእዮት የሚያምኑቱን ብቻ ብናይ እነሱም የመግባባትና የመቻቻል ችግር ኣለባቸው።

 

ኢትዮጵያ ያለምንም የጎላ ርእዮት ልዩነት ብዙ የፖለቲ ፓርቲዎች ያሉዋት ኣሁንም በመመስረት ላይ ያሉባት ኣገር ናት። ይህ የሚያሳየው ተቻችሎ የመኖር ክህሎት ማነስ መሰረታዊ የሃገር ችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በየፊናው መሮጥን ያሳያል። ምንም ወይም ትንሽ ልዩነትን ይዞ ኣዳዲስ የፖለቲካ ድርጅት ማቆሙ ለምን ያስፈልጋል? በተለይ በኣሁኑ ሰኣት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን እንድትጀምር በሚፈለግበት ሰኣት ልዩነትን ኣቻችሎ መዋሃድ ስለምን ከባድ ስራ ሆነ?

 

ጋና ውስጥ ዴሞክራሲ በተሻለ መልኩ እየሄደ ወይም እየተስተናገደ ያለው ጋና ከኢትዮጵያ ብዙ የሚርቅ ነገር ስላላት ኣይደለም። የጋና ብዙሃን ዴሞክራሲን ለመረዳት ወይም ቅድም ያልነው ነገር ጋና የተዋጣለት ኮንስትቲየንሲ ስላላት ኣይደለም። ዴሞክራሲ መልካም ጅማሮን እያሳየ ያለው በ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ብቃት ይመስላል። ተቻችሎ መኖር፣ መሸነፍንና ማሸነፍን መቀበል፣ ህግመንግስቱን ማክበር የቻሉ ይፖለቲካ መሪዎች ስለተገኙ ነው። ኢትዮጵያ ከጋና የምትማረውም ይህንን ነው።የተሻሉ የበሰሉ ታማኝ የፖለቲካ መሪዎች በሃገራችን ዴሞክራሲን ሊያስጀምሩ ሊያራምዱ ይችላሉ።

 

ዴሞክራሲን ተቋማዊ (institutionalized) ማድረግ

timthumb

ሌላው ዴሞክራሲን የማስተናገድ ኣቅም የሚገለጸው ደሞ ዴሞክራሲን ተቋማዊ (institutionalized) በማድረግ ነው። ዴሞክራሲ ሶስት የእድገት ደረጃዎች ኣሉት ኣንበል። ኣንደኛው መወለድ ሲሆን ይህም ህዝቦች ዴሞክራሲ ያስፈልገናል ሲሉ ያምኑና ዴሞክራሲን የሚያጠነክርና ሰባዊ መብትን የሚያከብር ህገ መንግስት ያረቃሉ ያውጃሉ( claim ያረጋሉ) ። ማርቀቅ ብቻ ሳይሆን መራመድም ኣለባቸውና ሲስተም ይቀርጻሉ። የተጠያቂነት፣ ግልጽነት ወዘተ. ኣሰራሮችን ይነድፋሉ። በዚህ ጊዜ ዴሞክራሲ ተወለደ ሊባል ይችላል:: ማወጅ በራሱ ዴሞክራሲ ተወለደ ሊያስብለው ኣይችልም። ያለማችን ኣንደኛ ኣምባገነን የሰሜን ኮርያው መሪ ኣገሩን ዴሞክራሲያዊ ህዝብ ሪፐብሊክ ኮርያ (Democratic People’s Republic of Korea) ብሎ ነው የሚጠራት፣ መንግስቱ ሃይለማርያምም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ…. ብሎ ነበር የሚጠራት::

 

ሁለተኛው የዴሞክራሲ የእድገት ደረጃው ተቋማዊ የመሆን ደረጃው ነው። ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ ውስጥ ተቋማዊ ማድረግ ማለት መንግስት ከነዚህ ተቋማት ጣልቃ መግባቱን ማቆሙ ብቻ ኣይደላም። መንግስት ጣልቃ መግባቱን እንዳቆመ ዴሞክራት ኣይሆኑም። ዴሞክራት የሚያደርጋቸውን የኣሰራር ሲስተም በማዳበር ነው ወደ ዴሞክራሲ እያደጉ ዴሞክራሲ ባህላቸው እየሆነ እንዲመጡ የሚደረገው።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ ቅድም ያልነው የቡድኖች ኣቅም ማነስ በዚህ እድገት ላይ ኣሉታዊ ተጽእኖ ኣለው። ክልሎች ቀበሌዎች ካላቸው ኣቅም የተነሳ ዴሞክራሲን ሙሉ በሙሉ ላይተገብሩት በህገ መንግስቱ ላይ ያለውን በሙሉ ላይረዱት ይችላሉ። ይህ ማለት ግን መጀመር ኣይችሉም ማለት ኣይደለም። በመሆኑም በኢትዮጵያ ተቋማትን ለመገንባት ኣሁን በቂ ኣቅም የለንም እና ዴሞክራሲ ይሰንብት ማለት ኣይቻልም።መቼ ተጀምሮ እንደግ ታዲያ?

 

መንግስት ለስሙ ያልተማከለ ስልጣን (power decentralization) ዘርግቻለሁ ቢልም ግን ደሞ በውስጠ ተዋዋቂ ስልጣንን ኣምክሎ ይዞ ተቋማቱን በልጓም ጠፍሮ ይዞ ይታያል:: በተለይ እነዚህ ስድስት የዴሞክራሲ ተቋማት እንደ ፍርድ ቤት፣ ባንክ፣ ሲቪል ሰርቪስ፣ወታደር፣ፖሊስና ሚዲያ መንግስት ኣሁን ኣቅም የላቸውም በሞግዚት ኣሳድጋቸዋለሁ የሚለው ኣሳቡ  ከባድ ስህተት ነው። መንግስት ይህንን ለማለት ማን ነው እሱ? ራሱ መንግስት የህብረተሰቡ ውጤት ሆኖ እነዚህ ተቋማት ያጡትን ችሎታ እሱ ከየት ኣገኘው? ሁላችን ያንድ ሃገር ልጆች ተቀራራቢ የሆነ የማሰቢያ መንገድ ያለን ካንድ ምንጭ የጠጣን ሆኖ መንግስት ልክ የተለየ ሃላፊነትና ችሎታ በድብቅ እንዳለው ኣይነት የእነዚህን ተቋማት ሃይል ገፎ መኖር ኣግባብ ኣይደለም።

 

ዴሞክራሲ የእድገቱ መጨረሻ ተቋማዊ መሆኑ ኣይደለም። ኣገራት ዴሞክራሲን በተቋሞቻቸው እያዩ ወደ ሶስተኛው እድገት ካላለፉ ወደ ሁዋላ የመመለስ እድል ይኖራቸዋል። የዴሞክራሲ ከፍተኛው እድገት ደረጃና የማይቀለበስበት ደረጃው ዴሞክራሲ ባህል ሲሆን ነው።

 

ዴሞክራሲን ባህልማድረግ

 

ዴሞክራሲ ባህል ሆነ ስንል በ መስሪያቤቶች የኣሰራሩ ዘየ በ ዴሞክራሲ መርሆዎች ላይ ተቃኝቱዋል ብቻ ሳይሆን በዜጎች የእለት ከእለት ህይወት ውስጥ መግባቢያ “ቋንቋ” ሲሆንም ነው። ዜጎች የራሳቸውን መብትና ግዴታ ሲያውቁ፣ የሌላውን የፖለቲካ ኣመለካከት፣ሃይማኖት ባህል፣የቆዳ ቀለምና ዘር፣ ታለንትና እውቀት ማክበርና ማድነቅ ሲጀምሩ ዴሞክራሲ ለማ ወይም ኣይቀለበስም ሊባል ይችላል።ዴሞክራሲን በተቋም ደረጃው ኣሳድገው ነገር ግን ባህል ያላደረጉ ህዝቦች ከፍ ሲል ያነሳነውን የግለሰብ ልዮነት(individual difference) በሚገባ የማያከብሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ቀስ እያሉ ከነዚያ ተቋማት ከሚያገኙት ኣገልግሎት እየተማሩ ባህላቸው እያደረጉት ይመጣሉ።

 

ዴሞክራሲ ኣያስፈልገንም ከኛ ባህል ጋር ኣይሄድም የራሳችን ባህል ኣለን በሱ እንተዳደራለን የሚሉ ግለሰቦች የሚኖሩ መሆኑ ቢታመንም እንደ ህዝብ ግን ዴሞክራሲን ባህሉ ለማድረግ የማይፈልግ ህዝብ ይኖራል ብሎ ማመን ይከብዳል።

 

ምእራባውያን በድሮው ጊዜ የራሳቸው ባህላዊ ኣስተዳደር ባህላዊ ኣሰራር ነበራቸው::በባህልም የበለጸጉ ናቸው።። ወደ ዴሞክራሲ ሲያድጉ ኣንዳንዶቹ ባህላዊ ኣስተዳደራቸውን ባህላዊ ይዘት ብቻ እንዲኖረው እያደረጉ ስልጣን ከእጁ ኣውጥተው ለዴሞክራሲ እየሰጡ ተቋሞቻቸውን የዴሞክራሲ ባህል ኣስይዘዋል። ዴሞክራሲ የ የዚህኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጆች ኣድገት ጥበብ (ART) ነው። በሌላ ኣገላለጽ የዚህ ዘመን ህዝቦች ባህል ነው። የድሮ ባህሎች የተፈጠሩት በእግዚኣብሄር ሳይሆን በቀደሙት ትውልዶች ሲሆን የዚህኛው ክፍለ ዘመን  ትውልድ ደሞ ንቃተ ህሊናው ራሱ የፈጠረው ባህል ነው ዴሞክራሲ ማለት።

 

በቅርቡ ተነስቶ የነበረው የ ኣረብ ስፕሪንግ ለዚህ ኣሳብ ዋቢ ነው። የኣረብ ህዝቦች ዴሞክራሲንና ሰባዊ መብት መጠማታቸውን ለኣለም ኣሳይተዋል። ትግላቸው ፍሬ እያፈራ ነው ኣይደለም ሌላ ኣነጋጋሪ ጉዳይ ቢሆንም ግን ጥማቱ መኖሩን ህዝቡ ኣሳይቱዋል። ግብጾች ዴሞክራሲን ፍለጋ ኣስገራሚ ትግል ኣድርገው ሙባረክን ጥለው ወደ ድህረ ዴሞክራሲ ለመሄድ ሽግግር ላይ ያሉ ሲመስሉ ኣሁን ያለው ርምጃቸው ግን ኣያምርም። ግልጽ ኣይደለም። ወደ ድህረ ዴሞክራሲ መስመር ለመግባት የሚያስችላቸውን ስራ በሚገባ እየሰሩ ኣይመስሉም። ኣያርግባቸውና ባለፈው ጊዜ እንደተነሳው ኣይነት ኣመጻዎች ቢነሱ ኣቅጣጫቸው ሁሉ ግልጽ ላይሆን ይችላል። በሙባረክ ጊዜ ኣላማቸው ኣንድ ነበር ያም ሙባረክን ጥሎ የዴሞክራሲ ስርኣትን መጀመር ነው። ኣሁን ዴሞክራሲያዊ  ምርጫ ኣድርገው ከመረጡ በሁዋላ በፓርቲዎቹ ኣለመናበብ ዴሞክራሲ ሲዘገይ ህዝባዊ ቁጣ ቢነሳ ኣቅጣጫው ግልጽ ስለማይሆን የከፋ ሁኔታም ሊገጥማቸው ይችላል። ዲክቴተርን መጣል ብቻውን ለዴሞክራሲ የሚያበቃ ኣለመሆኑን ከነሱ እንማራለን። ግብጾች ኣሁን ወደ ድህረ ዴሞክራሲ መሄድ ካልቻሉ ችግራቸው የኮንስትቲየንሲ ማጣት ሳይሆን የፓርቲዎች ኣቅም ማነስ ተደርጎ ሊወሰድ ይችል ይሆናል።

 

ዋናው መነሻችን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ባህሉዋ ለማድረግ ርምጃ ለመጀመር ምንም የሚከለክላት ነገር ኣይኖርም ለማለት ነበር ። ዴሞክራሲን ባህላቸው ያደረጉ ህዝቦች መንግስቶቻቸውን በየኣጭር ጊዜው እየቀያየሩ ሲኖሩ የሚታመኑት የፖለቲካ ፓርቲዎቻቸውን ሳይሆን የዴሞክራሲ ባህላቸውን ነው። ዘመን የማይሽረው ንጉሳቸው ይህ የዴሞክራሲ ባህላቸው ሲሆን በምርጫ ህይወታቸው ኣልፎ ኣልፎ ኣስቸጋሪ መንግስት ሊገጥማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል ስላላቸው ኣስቸጋሪ መንግስት ቢመጣባቸውም ዴሞክራሲ ሊቀለበስ ኣይችልም።

 

ጉዞ ከመልካም ኣስተዳደር ወደ ዴሞክራሲ ቢሆንስ?

 

ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን እንዲሁ ብዙ ኣዳጊ ኣገሮች ዴሞክራሲን ለማስተናገድ ኣቅም ሊያንሳቸው ይችላል። በዚህ ጊዜ ኣንዳንድ ምሁራን ዴሞክራሲ በመልካም ኣስተዳደር ሞግዚት ስር ቆይቶ ቀስ እያለ ቢያድግ ይሻላል ኣይነት ሊያስቡ ይችላሉ።  እነዚህ ሰዎች የሚመክሩን ዝም ብላችሁ የኢኮኖሚ እድገታችሁ ላይ ኣተኩሩ፣ መንግስትም  መልካም ኣስተዳደርን   ያመጣል ኣይነት ነው። በዚህ ኣገባብ መልካም ኣስተዳደር ሲባል የዜጎች የመምረጥ መብት የሌለበት ነገር ግን የተሻለ ፍትህና ኣገልግሎት ማግኘት ነው።

 

መቼም እኛ ተራ የሆንን ሰዎች ዴሞክራሲን ከምርጫ ጀምሮ የምንፈልገው ምን ኣልባት ኣንድ ቀን እኔም ፕሬዚዳንት ልሆን እችላለሁ ብለን ቀቢጸ ተስፋ ይዞን ኣይደለም። ምርጫ የምንፈልገው የዚህ ዘመን ፍላጎታችን ዳይናሚክ በመሆኑ ዳይናሚክ ለውጦችን ለማየትና ለመለማመድ ስለምንፈልግም ነው። በየኣጭር ጊዜው መምረጣችን የሚጠቅመን ለመመረጥ የሚሹ ፓርቲዎችን ስለሚያነቃቃልን፣ የ ፈጠራ ሃሳብ ለማምጣት ሃይል ስለሚሆናቸው ነው።በዚህም ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን ቶሎ ቶሎ ለምፍታት፣ የተሻለ ህይወት ለመኖር ስለሚረዳን ነው። ከሁሉ በላይ ግን መልካም ኣስተዳደርን ለማስፈን ፈቃደኛ የሆነ መንግስት ምርጫን እንቢ የማለት ፍላጎቱ ዝቅተኛ ነው። በሌላ በኩል ደሞ ያለ ዴሞክራሲ መልካም ኣስተዳደር ዋስትና ኣይኖረውም። የመልካም ኣስተዳደር ዋስትናው ዴሞክራሲ ነው። በመሆኑም ማደግ ያለብን ዴሞክራሲን ጀምረን ራሱ ዴሞክራሲ እየመራን ወደ መልካም ኣስተዳደር እናድጋለን እንጂ ምርጫን ጠልቶ ወይም ስልጣን ወዶ መልካም ኣስተዳደርን ሊያመጣልን ይችላል የሚል እምነታችን በጣም ዝቅ ያለ ነው።በመሆኑም ይህ ጉዞ ዋስትና የሌለው በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ልንታለል ኣይገባንም። ዴሞክራሲን ከነሙሉ ትጥቁ ጀምረን እየተማርን እናድጋለን።

 

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ኣስተያየት ካለዎ እነሆ ኢሜይል ኣድራሻየ

geletawzeleke@gmail.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>