ይታረድ ፍሪዳዉ ግባልኝ ከቤቴ
እነሆ የላም ልጅ ከርጎ ከወተቴ
የእግዚአብሔር እንግዳ እረፍ ከመደቡ
እግርህም ይታጠብ በወጉ በደንቡ
ያዳም ልጅ እኮ ነን የእጆቹ ሥራ
ተጫወት ወንድሜ እንግዲህ አትፍራ!
እንዲህ እንዳልነበር ባህል ልማዳችን
ዉጣልን አማራ ጥፋ ከፊታችን
ጫንልኝ ደራርበህ ዳርግልኝ ላደጋ
ጎጃምና ጎንደር ወሎም ሆነ ቡልጋ
እየገፈተርከዉ በሰደፍ ባለንጋ!
እንዳልተሰዋለት እንዳልተዋደቀ
ላገር ስልጣኔ እንዳልተጨነቀ
ለሰንደቅ ዓላማዉ ሌት ተቀን የተጋ
ኢትዮጵያን ያለ ሰዉ የለዉም ወይ ዋጋ?
ዘዉዱን ከክህነት ያስተባበራችሁ
የቅዱሳን አገር ከቶ ምን አላችሁ
በግሸኗ ማርያም በክቡር መስቀሉ
አገር እያጠፉ ወገን ሲበድሉ
ባንዳ ሲዘባነን አርበኛዉ ሲጉላላ
አይታጠንም ወይ ቅዱስ ላሊበላ?
ዓይኑ እስኪታክተዉ ጋምቤላን ሲመራ
ህንዱ ካራቱሬ ሊተክል ሊዘራ
ቻይና ኮሚኒስቱ ስንት ግፍ ሲሰራ
በገዛ አገራችን ሲኮራ ሲዳራ
ምን ዓይነት ልማት ነዉ አማራን ላሞራ
ይናገር መቅደላ ይፋረደኝ ቋራ!!
ከፋኑኤል አበበ
ኒዮርክ