በአሸናፊ ደምሴ
ሰንደቅ ጋዜጣ እንደዘገበው በሬጌ የሙዚቃ ስልት አጨዋወቱ በበርካቶች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈው ድምጻዊ እዮብ መኮንን ባሳለፍነው ቅዳሜ ለህክምና በሄደበት ኬኒያ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ አጋ-ካሃን የተሰኘ ሆስፒታል ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ ትናንት ማምሻውን ወደሀገሩ የተመለሰው አስክሬኑ፤ ዛሬ ከቀኑ በ9ሰዓት በቅዱስ ስላሴ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩ እንደሚፈፀም ምንጮች አስታወቁ።
“እንደቃል” በተሰኘው ብቸኛና የመጀመሪያ አልበሙ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፎ የነበረው ድምፃዊ እዮብ፤ ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት የእህቱን ልጅ ትምህርት ቤት አስመዝግቦ ከተመለሰ በኋላ የግቢውን በር በማንኳኳት ላይ ሳለ ራሱን ስቶ መውደቁ የታወቀ ሲሆን፤ ህመሙም የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ (stroke) መሆኑ ታውቋል።
ከድንገተኛ አደጋው በኋላ ራሱን ስቷል። በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል የህክምና እርዳታውን ሲያገኝ የቆየው ድምፃዊው፤ ለተሻለ የህክምና እርዳታ ወደኬኒያ፤ ናይሮቢ አምቡላንስ ባለው የግል አውሮፕላን ቅዳሜ ምሽት ከሀገሩ የወጣው እዮብ ጤናውን ይዞ መመለስ ሳይችል ቀርቷል።
በኬኒያ የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች የወጣቱን ድምጻዊ ህይወት ለመታደግ የተቻላቸውን የጣሩ ቢሆንም፤ ድምጻዊ እዮብ መኮንን ግን በተወለደ በ38 ዓመቱ እሁድ ነሐሴ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ምሽት 3፡45 አካባቢ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
ድምጻዊው ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ሲሆን፤”እንደቃል” በተሰኘው ተወዳጅ አልበሙ በተጨማሪም በቅርቡ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቅ የሙዚቃ ስራውን ከ70 በመቶ በላይ አጠናቆ እንደነበር ምንጮች ይጠቁማሉ።
↧
የድምፃዊ ኢዮብ መኮንን የቀብር ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ይፈፀማል
↧