(ዘ-ሐበሻ) ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ዝምታን ሰብሮ አደባባይ በመውጣት ስም ያተረፈው ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙት የመብራት ኃይል አዳራሽና በምኒልክ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አዳራሾች ውስጥ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ባቅድም በቢሮክራሲያዊ መንገድ ተከለከልኩ አለ።
ሰማያዊ ፓርቲ በፌስቡክ ገጹ “በቃል እንጂ በተግባር የማይታየው ህገ-መንግስታዊ መብት” በሚል በበተነው መረጃ ነሀሴ 19 ቀን 2ዐዐ5 ዓ/ም. በመብራት ሀይል አዳራሽ በሰማያዊ ፓርቲ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ሕዝባዊ ስብሰባ በተለመደው የመንግሥት ቢሮክራሲና አፈና ተደናቀፈ ብሏል፡፡ ይኸውም የአዳራሹ ባለቤት የሆነው የኢ.መ.ኃ.ባ. ስብሰባው በአስተዳደሩ እውቅና ያለው መሆኑን የሚገልፅ ደብዳቤ ሲጠይቅ የአ.አ. መስተዳድር ደግሞ አዳራሹን እንድትከራዩ ባለስልጣን መ/ቤቱ የፈቀደላችሁ መሆኑን የሚገልፅ ደብዳቤ አምጡ በሚል ውስጣዊ መነጋገር ባለበት ግልፅ ቢሮክራሲ ስብሰባው እንዳይደረግ መሰናክል ፈጥሯል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰማያዊ ፓርቲ ነሀሴ 26 ቀን እንዲካሄድ ኘሮግራም የያዘለትን ሁለተኛ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ዝግጅት በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ በዛሬው እለትም ለአ.አ. መስተዳድር የሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ ማሣወቂያ ክፍል የማሣወቂያ ደብዳቤውን ያስገባ ሲሆን ይህ ክፍል ግን የእውቅና ደብዳቤውን ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆንም እንደተለመደው ደብዳቤውን በብዙ ምስክሮች ፊት በማሳወቂያ ክፍል ኦፊሠሩ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠው መጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል የፓርቲው የህግ ጉዳይ ኃላፊ ወጣት ይድነቃቸው ከበደ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፀው ፓርቲው በመጪው እሁድ በመብራት ኃይል አዳራሽና በምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አዳራሽ ጥያቄ አቅርቦ የአዳራሾቹ ባለቤቶች ፓርቲው ስብሰባ ለማካሄድ ከአዲስ አበባ አስተዳደር የፈቃድ ደብዳቤ እንዲያመጣ ሲጠይቁ የአዲስ አበባ አስተዳደር በበኩሉ ለአዳራሽ የከፈላችሁበትን ደረሰኝ አምጡ በማለቱ ቢሮክራሲያዊ በሆነ መንገድ አዳራሾቹን መከልከሉን ተናግረዋል።
“ወደ አዳራሾቹ ባለቤት ሄደን ክፍያ ልንፈፅም ስንል ፈቃድ አምጡ ይሉናል። ከአዲስ አበባ አስተዳደር ደግሞ ፈቃድ ስንጠይቅ የተዋዋላችሁበትን ደረሰኝ አምጡ በማለት አጉላልተውናል” ያለው ወጣት ይድነቃቸው በግል የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የሆኑትን አቶ አባተ ስጦታውን ቢያናግሩም ፈቃዱ ሊሳካ አልቻለም ብሏል።
በተያያዘ ፓርቲው ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የእውቅና ደብዳቤ ማስገባቱንና ሰልፉን ሊያደምቁ የሚችሉ ልዩ ልዩ ቅድመ ዝግጅቶች እያካሄዱ መሆኑን ከወጣት ይድነቃቸው ገለፃ መረዳት ተችሏል።
በሌላ በኩል ፓርቲው ቀበና በሚገኘው ጽ/ቤቱ በየሳምንቱ እሁድ ምሁራንን እየጋበዘ የሚያደርገውን ውይይት በመቀጠል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መምህር የሆኑትን ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬን በመጋበዝ “የግጭት አፈታት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በቀጣይ እሁድ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ፓርቲው ለተለያዩ ሚድያዎች በላከው መግለጫ ላይ አስታውቋል። ጋዜጣው በዘገባው ማጠናቀቂያ ላይ እንዳለው ዶ/ር በቃሉ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ሲሆኑ በሳይኮሎጂና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሁለት ማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በትምህርት (Education) የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በቋንቋና ስነልቦና የፒኤች ዲግሪ አላቸው። ከአስር ዓመት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማስተማር ላይ ይገኛሉ።
↧
ሰማያዊ ፓርቲ በመብራት ኃይል አዳራሽና በምኒልክ ት/ቤት ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳላደርግ በቢሮክራሲያዊ መንገድ ተከለከልኩ አለ
↧