Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የ21 ዓመቱ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰማዕት ተስፎም ታረቀኝ / ተስፋ ማርያም (የISIS ሰለባ) –ከዘመድኩን በቀለ

$
0
0

” እርስዎ ለማንበብ ትዕግስት ቢያጡ እንኳን ሼር በማድረግ በትዕግስት ለሚያነብ ሰው ያካፍሉ ”
ይህን ታሪክ በከባድ ሐዘን ውስጥ ሆኜ በእንባ ጭምር ጻፍኩላችሁ ። እነሆ በእርጋታ ያንብቡት ።

የኢንቲጮው ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ሰሎሞን በሰማዕቱ ዳንኤል ሐዱሽ የነበረንን ቆይታ እንዳጠናቀቅን “ከፊታችሁ የሚጠብቃችሁ በረሃ ነው ። ፀሐይ ሳትበረታ ሙቀቱ ሳያይልባችሁ በቶሎ ወደ ገርሁ ስርናይ ሂዱ ባሉን መሠረት መጀመሪያ ከኢንቲጮ ከተማ ወደ መቐለ በሚወስደው መንገድ ጥቂት ከተጓዝን በኋላ ወደ ታላቁ ገዳም ደብረ ዳሞ ከመድረሳችን በፊት ወደ ግራ በመታጠፍ የሰሜኑን አቅጣጫ በመያዝ በኤርትራ ድንበር ፆረና አካባቢ ወደምትገኘው ገርሁ ስርናይ ከተማ አቀናን ።
tesfom

Tesfom 12

የከንቲባው ሾፌር ወጣት ክብሮም ፣ የዳንኤል ሐዱሽ ታላቅ ወንድምና የሹፌሩም ጓደኛ በጉዞው አብረውኝ ነበሩ ። በመንገድ ላይ አስቸጋሪውን ስደት ከሃገራቸው ኤርትራ በመነሳት ዕድል ቀንቷቸው የኤርትራ ድንበር ተሻግረው በሰላም ኢትዮጵያ የገቡትን ኤርትራውያንን የጫኑ የUNHCR መኪኖችን እያሳለፍን ፣ በቅርብ ርቀት የሚታየውን የኤርትራን መንደሮች እና ከተሞች ከአድማሱ ባሻገር እየተመለከትን ፣ 38 ኪሜትሮችን እንደሄድን የሰማዕቱ ተስፎም ቤት ደረስን ።

ከተማዋ ገርሁ ስርናይ ትባላለች ። በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በማዕከላዊው ዞን በአህፈሮም ወረዳ ውስጥ ነው የምትገኘው ። ከተማዋ በ957 ዓም የተመሰረተች ሲሆን በውስጧም ወደ አንድ ሚሊዮን ሊጠጋ የተቃረበ ህዝብ ይገኝባታል ። እዚህች ከተማ ሆነው የኤርትራን ከተሞች በቅርብ ርቀት የማየት ዕድል ይኖርዎታል ።
ውድ ጓደኞቼ አሁን የሰማዕቱ ቤተሰቦች ቤት ደርሰናል ። በኔትወርክ ያለመስራት ምክንያት ቀደም ብለው ተሰብስበው ባይጠብቁንም ፣ የመምጣታችን ዜና እንደተሰማ በፍጥነት ሁሉም በአካባቢው ያሉ ቤተሰቦች ተገኝተዋል ። አባት አቦይ ታረቀኝ ዘግይተው ከመምጣታቸው በቀር ሌሎቹን አግኝተናቸዋል ።
እንግዲህ በእዚህ አከባቢ የእኔን መልእክት ለቤተሰቡ የእነሱን ደግሞ ለእኔ ንግግራችንን የሚተረጉምልን ያስፈልግ ነበርና በዚህ በኩል አብሮኝ ከኢንቲጮ የመጣው የሰማዕቱ ዳንኤል ሐዱሽ ወንድም አቶ ጌታቸው ሐላፊነቱን በሚገባ ተወጥቷል ።

ወሮ ፅጌ ገብረ መድህን የሰማዕቱ እናት ናቸው ። ጥቂት ስለልጃቸው ተስፎም እንዲያጫውቱኝ በጠየኩዋቸው መሠረት ከብዙ እንባ ጋር እንዲህ ሲሉ ያጫወቱኝን አንጀት የሚበላና እጅግ የሚያሳዝነውን የቤተሰቡን ታሪክ ጭምር እነሆ ተከታተሉት ።
Tesfom family

ዮሴፍ ታረቀኝ ፣ ትርሓስ ታረቀኝ ፣ ተስፎም ታረቀኝ ፣ ሸዊት ታረቀኝ ፣ ብርሃነ ታረቀኝ ፣ የማነ ታረቀኝ እኒህ ስድስት ልጆች ወሮ ፅጌ አምጠው የወለዷቸው ፣ በከፋ ድህነት ውስጥም ሆነው እነሱ ጦማቸውን እያደሩም ቢሆን ልጆቻቸው ጠግበው እንዲያድሩ የተቻላቸውን በማድረግ ልጆቻቸውን እያሳደጉ ያሉ ናቸው ።
በገጠር ይኖሩ የነበሩት እኒህ ቤተሰቦች ፣ የግብርናው ኑሮ መሬት በቂ ምርት አልሰጣቸው ብትል ጊዜ ይሻል እንደሁ ብለው አሁን ወዳሉበት ገርሁ ስርናይ ከተማ ጎጆ ቀልሰው ይገባሉ ። ይህን ማድረጋቸው ደግሞ ሌላ ችግር አመጣባቸው ። እነሱ ከተማ መግባታቸው እንደተጨማሪ ሥራ ፍለጋ ቆጥረውት የነበረ ቢሆንም መንግሥት ደግሞ መሬትን በመሬቱ ላይ ሆኖ የማይንከባከብ መሬቱን ተነጥቆ ሌላ ለሚንከባከብ ይሰጣል በሚለው መመሪያ መሰረት ለሌላ ሰው ይሰጥባቸዋል ።
ይህ ደሃ ቤተሰብ የማያውቀውን የከተማ ኑሮ ጥርሱን ነክሶ መግፋት ይጀምራል ። ግን ብዙ መዝለቅ አልተቻለም ። ኑሮ እየከበደ ፣ እጅም እያጠረ ፣ ለለልጆችም የሚያስፈልግ ነገር እየሳሳ መሄዱን ያዩት ነፍስ ማወቅ የጀመሩት ልጆች ቤተሰቡን ከችግር ለማውጣት ብለው ስደትን እንደ አማራጭ ይዘው በመመካከር ለተግባራዊነቱ ዝግጁ ይሆናሉ ። በዚህም መሠረት በመጀመሪያ እርምጃ ወስዶ ስደት የጀመረው ታላቅ ወንድማቸው ዮሴፍ ታረቀኝ ሆነ ።
ዮሴፍ ታረቀኝ ፦ በመጀመሪያ ሱዳን ከዚያም ግብፅ በመቀጠል በአስቸጋሪው የሲና በረሃ አድርጎ እስራኤል ይገባል ። ከዚያም የሚያገኛትን ቢልክም የሚልካት ብር ቀሪውን ቤተሰብ የሚያኖር አለመሆኑን የተመለከቱት ልጆች ምንም እንኳን እድሜያቸው 18 ዓመት በማይሞላም እነሱም የታላቅ ወንድማቸውን ፈለግ ይከተላሉ ። ነገር ግን ወንድምየው በሲና በረሃ ያየውን አበሳ ስለሚያውቅ በዚያ በኩል እንዳይሞክሩ መማፀኑ አልቀረም ።
ትርሓስ ታረቀኝ ፦ ሳዑዲ አረቢያ ለመሄድ መንገድ ጀምራ በኢትዮጵያ ፀጥታ ሐይሎች ጅጅጋ ላይ ተይዛ በመመለስ አሁን አዲስ አበባ በሰው ቤት ተቀጥራ ምቹ ጊዜ ስታገኝ የጀመረችውን የስደት መንገድ ለማሳካት በመጠባበቅ ላይ ያለች ።
ሸዊት ታረቀኝ ፦ የሰማዕቱ ተስፎም ታናሽ ወንድም ነው ። ዘንድሮ 18ኛ ዓመቱን ይዟል ። የመስቀል ዕለት ስደትን በሶማልያ በኩል በባህር የመን በመግባት አሁን ሳዑዲ የሚገኝ ።

ብርሃን ታረቀኝ 14 ዓመት የማነ ታረቀኝ 13 ዓመት እነዚህ ሁለቱ አሁን ለእነ አቶ ታረቀኝ በእጃቸው ላይ የቀሩ ሕፃናት ናቸው ።

ሰማዕቱ ተስፎም ታረቀኝ መጋቢት 24 የጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ዕለት ንጋት ላይ ተወለደ ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ከ1— 10 በዚያው ገርሁ ስርናይ ከተማ ተከታትሏል ። በ2003 ዓም ትምህርቱን ጨርሶ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያሸጋግረውን ውጤት ባለማምጣቱ ከቤት መዋል ጀመረ ። ይህ መቀመጥና አማራጭ ማጣት ደግሞ የታላቅ ወንድሙን ፈለግ እንዲከተል አስገደደው ። የጉዞ መስመሩን ግን በጅጅጋ ፣ ቦሳሶ ፣ ሶማሊያ የቀይ ባህርን በመሻገር በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አደረገው ።
tesfom ISIS

የሚገርመው ተስፎም በሳዑዲዓረቢያ ብዙም አልቀናውም ። በ2004 ዓም ወደ ሳዑዲ ቢያቀናም 8 ወር እንደቆየ የሳውዲ ፖሊሶች እጅ ወድቆ ታስሮ ወደ ሀገሩ ተመልሷል ። በዚያው አስቸጋሪ መንገድ ለ2ተኛ ጊዜ በመሄድ ሳዑዲ ቢገባም 3 ወር እንደቆየ ተይዞ እስር ቤት ገብቶ ይመለሳል ። እዚህ ሲመጣ ደግሞ አያስችለውም እንደገና ተመልሶ በዚያው አስቸጋሪ የባህር ጉዞ በየመኖች የጦርነት አውድማ ውስጥ በማለፍ ሳዑዲ ይገባል ።

አሁን እንኳን ብቻውን ሳይሆን ፊሊሞን አሰፋና ዜናው ገብረሚካኤል የተባሉ አብሮ አደግ ጓደኞቹን አስከትሎ ነው ጉዞ የጀመረው ። ምን ያደርጋል ዳሩ ግን 1 ዓመት ከስድስት ወር ያህል ብቻ ነው የመቆየት እድልም ተሯሩጦም ተደብቆም የተገኘውን ሥራ በመሥራት ቤተሰቡን መርዳት የቻለው ። ደግሞ ተያዘ ፣ ከዚያም ታሰረ በመጨረሻም ዘንድሮ ጥር 4 2007 ዓም ከሳዑዲ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ ።

አመጣጡ በኢትዮጵያ ለመኖር የነበረ ቢሆንም አራት አብሮአደግ ጓደኞቹ መንገድ ልንጀምር ነው ምን አሰብክ ይሉታል ። በየት በኩል አሰባችሁ ይላቸዋል ። በየመን በኩል እና በሲና በረሃ አልሞክረውም ይላቸዋል ። አይ በሁለቱም አይደለም በሊቢያ አውሮፓ ነው ይሉታል ። ከእነርሱ ጋር በመስማማት ወደ እናቱ ጋር በመምጣት እናቱን እንዲህ ይላቸዋል ።
” እማ !! በልጅነቴ ውለታሽን ለመመለስ በበረሃና በባህር በመጓዝ ብዙ ጣርኩ ነገር ግን አልተሳካልኝም እናም አሁን ለመጨረሻ ጊዜ ከጓደኞቼ ጋር በሌላ መንገድ ልሞክር ነውና እባክሽን እናት ዓለም መርቂኝ ብሎ እግራቸው ላይ ተደፍቶ ጉልበታቸውን በመያዝ ካለመረቅሽኝ አልነሳም ይላቸዋል ።

እናት ደግሞ አይሆንም ይላሉ ። ምክንያትም ነበራቸው የበኩር ልጃቸውን በስደት ፣ ሴቷንም በስደት አጥተዋል ። ይባስ ብሎ የተስፎም ታናሽ 18 ዓመት ሳይሞላው አሁን ያለው ሳውዲ ነው ። ከተስፎም ጋር አልተገናኙም ። ሸዊት ሳዑዲ የገባ ዕለት እግሩ ጅዳን እንደረገጠ ተስፎም ታስሮ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል ። ስድሰት ልጆች የወለዱት ወሮ ጽጌ ቢያንስ ሦስቱ ከርሳቸው ጋር እንዲኖሩ በመለጋቸው አይሆንም የትም አትሄድም እዚሁ የሆነውን ሆነን አብረን እንኖራለን በማለት በአቋማቸው ለመጽናት ይሞክራሉ ። ልጅ ተስፎም ግን ” ካልመረቅሽኝ አልነሳም ” በሚለው አቋሙ በመጽናቱ እናት ተሸነፉ ። መረቁትም እያለቀሱ መረቁት ። ክፉ አያግኝህ ።

ጥር 28 ሆነ ። ተስፎምና አራቱ የሰፈር አብሮ አደግ ጓደኞቹ ሁመራ መግባታቸውን ተናገሩ ከዚያም ሱዳን መግባታቸውንም አሳወቁ ወደ ሊቢያ ጉዞ እንደጀመሩ ከመናገራቸው በቀር ከዚያ ወዲህ ተስፎምን ጨምሮ የ5ቱም ድምጽ ጠፋ ። ከ ሁለት ወር በኋላ ግን ተስፎም ከትውልድ ሀገሩ ዳንኤል ሐዱሽ አጠገብ ከኢትዮጵያውያኑ እና ከኤርትራውያን ወንድሞቹ ጎን ብርቱካናማ ቱታ ለብሶ ከአራጆቹ ፊት በክብር አንገቱን ደፍቶ ታየ ። ተፈልጎ በስዕለት እንኳ የማይገኝውን የከበረውን የሰማዕትነት ማዕረግ ተቀበለ ።
ተስፎም ሐይማኖቱን የሚወድ ፣ ቤተሰቡን የሚያፈቅር ፣ ድህነትን ለማሸነፍ በህፃንነት ዕድሜው አስከፊውን የስደት ህይወት የተጋፈጠ በመጨረሻም በስደት ላይ 21ኛ ዓመቱን ባከበረ ማግስት ህልሙን እውን ሳያደርግ በበረሃ የቀረ የሚያሳዝን ልጅ ነው ።

ወሮ ጽጌ እንዲህ አሉኝ ። እባክዎን አንቱ ይህቺ አዲስ አበባ የምትገኘዋን ልጄን ትርሓስን ይማጸኑልኝ ። የትም እንዳትሄድብኝ ይኸው ስልክ ቁጥሯ እነሆ ። እባክዎን በማርያም ። ይለምኑልኝ ።

አባት አቶ ታረቀኝ ኋላ ላይ ዘግይተው ቢመጡም መጨረሻ ላይ እነ ህይወት ከአሜሪካ ፣ ኢትዮ ዙሪክ የእግርኳስ ቡድን አባላት እነ ቴዲ ከስዊዝ አቶ አማረ ከአሜሪካ የላኩትን 21,077,95 ሳንቲም ሳስረክባቸው ከመመረቃቸውና ምስጋና ከማቅረብ በቀር ትክዝ ብለው በመቀመጥ አንዳች ያሉት ነገር የለም ።
እዚህም ትንሽ ወቀሳዬን ላቅርብ ። የክልሉ ቴሌቭዥን ቦታው ርቆት ይሆን ወደ እነዚህ ምስኪን ቤተሰቦች ቤት ያልሄደው? ምን አለ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በዚያውም የስደትን አስከፊነት ለማስተማርም ይረዳዋል ሄደው ቢያፅናኑዋቸው ።

መንግሥትም በተለይ በዚህ ወረዳ ላይ ሥራ በቶሎ ካልሰራ አንድም ወጣት ከስደት የሚቀር አይመስልም ። በትግራይ ክልል በስደት ይህን ወረዳ የሚያክለው እንደሌለ ነው ነዋሪዎች የሚናገሩት ። እንደውም የተስፎም ታወቀና ቤተሰብ ዕርሙን አውጥቶ ተገላገለ እንጂ ከተስፎም ጋር አብረው ወጥተው እስካሁን ድረስ ይኑሩ ይሙቱ ሳያውቁ አምላካቸውን በቀን በማታ የሚማጸኑ እናቶች በርካቶች ናቸው ።

በመላው ዓለም የምንገኝ ኢትዮጵያውያንም ዘር ፣ ጎሣ ፣ የፖለቲካ አቋም ሳይለየን ይህን ድህነትና ስደት የበታተነውን ቤተሰብ እንታደገው ። ለእህታችን ትርሓስም እንድረስላት ።
አርቲስት ዮሴፍ ገብሬን ይመሰገናል ። ከመቐለ እና በቅርብ ከተማዋ አድዋ የሚገኙ ጋዜጠኞች ፣ አርቲስቶች ፣ የቤተክህነት ሰዎችና ፖለቲከኞች አንዳቸውም ሳያይዋቸው እሱ ግን ቦታው ድረስ በመገኘት የ40 ሺህ ብር ድጋፍ ከመስጠቱም ባሻገር አፅናንቷቸው ተመልሷል ። የምንወደውና የምትወደን ሕዝባችን ብሎ መናገር ኢንተርቪው ላይ ብቻ እኮ አይደለም ። የምትወዱት ህዝባችሁ እንዲህ በሐዘን በደቂቃ ጊዜ ከጎኑ ካልሆናችሁ ለመቼ ልትሆኑለት ነው ። በተለይ ሐገረ ስብከቱን ያስወቅሳል ፣ ያስተዛዝባልም ። አሥራት በኩራት መሰብሰብ ብቻ አይደለም ሄዶ ማጽናናትንም ይጠይቃል ።
zemedkun and Tesfom family

የመቀሌ ምእመናን ሰማዕቱ ዳንኤል ሐዱሽ ቤት እንደሄዳችሁት ሁሉ አሁንም ፆረና ግንባር ሰማዕቱ ተስፎም ቤተሰቦችም ቤት ሂዱ ። አፅናኑዋቸው ። የትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችም አልረፈደባችሁም ።

አሁን ሁሉን ጨርሼ ወደ አዲስ አበባ ተመልሻለሁ ። ነገ ሐሙስ ወይም አርብ ወደ ወለጋ እሄዳለሁ ። በዚያም ለጊዜው ለእኔ የመጨረሻዬ የሆነውን ባለፈው ጆሲን ልኬው ሄዶ የጎበኘውን የሰማዕቱ የትውልድ መንደር ወደሆነችው ነቀምት ዙሪያ ወደምትገኘው ምስራቅ ወለጋ ዞን ዋዮጡቃ ወረዳ እሄዳለሁ ።
ለዚህ ጉዞም ከሚኒሶታ በአቶ ሰሎሞን በኩል የተሰበሰበ ብር ፣ ከዚያው ከአሜሪካ በባልንጀሮቼ በቀሲስ ዘማሪ ወንደሰን በቀለና በቀሲስ ሱራፌል ወንድሙ ፣ እንዲሁም ሕይወትና ጓደኞቿ እህቴ ሔለን ነጋሽና ቤተሰቦቿ አቶ አማረም ከአሜሪካ ያደረሱኝን ብር የባንክ ቡክ በመክፈት ለመንግሥቱ ጋሼ ቤተሰቦች አስረክባቸዋለው ።
እስከዚያው በእኔ በኩል ሰላም ሁኑልኝ ። የሰማዕቱ ተስፎምን ቤተሰብ ለመርዳት የምትፈልጉ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል
ፀጋ ገብረመድህን
የባንክ ሂሳብ ቁጥር
1000103650066 ብላችሁ ላኩላቸው ።
ትግርኛ የምትናገሩ ሰዎች ወሮ ፀጋን በስልክ ቁጥር +251 92 044 8338 የምታገኟቸው ሲሆን አማርኛ ተናጋሪዎች ደግሞ በጎረቤታቸው በአቶ አበበ በኩል
+251 91 291 8879 ላይ ደውላችሁ መልእክቱን ማድረስ ትችላላችሁ ።በእኔ በኩል ለዛሬ አበቃሁ ።
ማንኛውንም አስተያየት ተግሳፅም ጭምር ለመቀበል በእኔ በኩል እንደሁልጌዜው ሁሉ ዝግጁ ነኝ ። +251911608054 የእጅ ስልኬ ነው ። ማወቅና መረዳት የምትፈልጉት ነገር ካለ ያወቅሁትን ልነግራችሁ ዝግጁ ነኝ ።
Share በማድረግ ላልሰማ አሰሙ ላላወቀ አሳውቁ ። ይህን በማድረግዎ ከሰማዕቱም በረከት ያገኛሉ ። ቤተሰቡንም ይረዳሉ ።
ከሁላችሁ የማንስ አክባሪ ወንድማችሁ ።
ያጆሌ ኦሮሞ ወለጋረቲ ነኤጋ ። ረቢ ኑወጂን ሀተኡ ገለቶማ ።
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ሰኔ 3/10/ 2007 ዓም
አዲስአበባ — ኢትዮጵያ

The post የ21 ዓመቱ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰማዕት ተስፎም ታረቀኝ / ተስፋ ማርያም (የISIS ሰለባ) – ከዘመድኩን በቀለ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>