ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ
የሺዋስ አሰፋ ከተቀመጠበት አልነሳም አለ!
‹‹ምስክሬ ላይ ዛቻ እና ድብደባ ስለተፈጸመ ምስክርነቱ በዝግ ችሎት ይሁን›› አቃቤ ሕግ
‹‹በማስረጃ ባልተረጋገጠ አቤቱታ ችሎት በዝግ ሊታይ አይገባም›› የተከሳሽ ጠበቆች
‹‹ሞት የሚያስቀጣ ክስ ቀርቦብን ጉዳያችን በአደባባይ መታየት አለበት፤ እናንተ ብቻ አይደላችሁም ፈራጆች…››ዳንኤል ሺበሺ
‹‹ምስክርነቱ በዝግ ችሎት የሚታይ ከሆነ ዛሬውኑ የምትፈርዱብንን ተቀብለን ለመመለስ ዝግጁ ነን›› ሀብታሙ አያሌው
‹‹የአቃቤ ህግን አቤቱታ በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ አልተቀበልነውም፤ የምስክሮች ስምና ቃል ግን በሚዲያ እንዳይዘገብ ወስነናል›› ችሎቱ
ዛሬ ሰኔ 01 ቀን 2007 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በእነዘላለም ወርቅአፈራሁ የክስ መዝገብ የተከከሱ 10 ሰዎች ጉዳይ ታይቶ ነበር፡፡ መዝገቡ የተቀጠረው አቃቤ ህግን ምስክሮች ለማድመጥ እና የአቃቤ ህግን ባቀረባቸው ተጨማሪ አቤቱታዎች ላይ ውሳኔ ለመስጠት መሆኑን ከችሎቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ተከሰሾች በቀደም ተከተል ስማቸው እየተጠራ ሲቆሙ የሺዋስ አሰፋ ከመቀመጫው አልነሳም ብሎ ነበር፡፡ የቀኝ ዳኛው ተነስ ቢለውም የሺዋስ በሀሳቡ ጸንቶ አልተነሳም፡፡
አቃቤ ህግ ካስመዘገባቸው 15 ምስክሮች መካከል 12ቱን ዛሬ ማቅረብ የቻለ ቢሆንም ‹‹በአንደኛ ምስክር ላይ ዛቻ እና ድብደባ ስለተፈጸመ፣ እንዲሁም የሁሉንም ምስርክሮች ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ምስክርነቱ በዝግ ችሎት ይደረግልን›› ሲሉ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ አቤቱታቸውን አሰምተው ነበር፡፡
ተከሰሾች 3 ጠበቆች የነበሯቸው በመሆኑ ከ1ኛ-5ኛ ተራ ቁጥር ድረስ የተከሳሾች ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጉ የአቃቤ ሕግን አቤቱታ እንዲህ በማለት ተቃውመዋል፡- ‹‹ችሎት አስተማሪ በመሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ መርህ ነው፡፡ ችሎት ዝግ የሚሆነው በተለየ መንገድ ነው፡፡ በሕገ-መንግሥቱ ይህንን በተመለከተ ተደንግጓል፡፡ የችሎት ዝግ መሆን ሊፈቀድ ቢችል እንኳን በማስረጃ ተረጋግጦ መሆን ይኖርበታል፡፡ አቃቤ ሕግ ያቀረበው አቤቱታ በማስረጃ ዘርዝሮ የት፣ መቼ፣ እንዴት የሚለውን አላቀረበም፡፡ ችሎት በአቤቱታ ብቻ አይዘጋም፡፡ በማስረጃ ባልተረጋጋጠበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ሊፈቅድ አይገባምና የአቃቤ ህግ አቤቱታ ውድቅ ይደረግልን፡፡›› የተቀሩት ሁለት ጠበቆችም በተመሳሳይ መልኩ የአቃቤ ህግን አቤቱታ ተቃውመዋል፡፡
የቀድሞ አንድነት አመራር የነበረው አቶ ዳንኤል ሺበሺም እጁን በማውጣት እንደምንም ካስፈቀደ በኋላ፤ ‹‹ሞት የሚያስቀጣ ክስ ቀርቦብን ጉዳያችን በዝግ መታየት የለበትም፡፡ በአደባባይ ሊታይ ይገባል፤ እናንተ ብቻ አይደላችሁም ፈራጆች፤ ሁሉም ይፍረድ፡፡ ሁሉም ይፈርዳል›› ብሏል፡፡
አቶ ሀብታሙ አያሌውም እንዲናገር ጠበቃ ተማም ለዳኞቹ ተናግረው ሀብታሙ ‹‹አቃቤ ህግ ክስ ሲመሰርትብን በዝርዝር የምስክርችን ስም አልገለጸም፡፡ እኛ ዋስትና ተከልልለን በእስር ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ምስክሮችን ልናውቅ የምንችልበት ዕድል ዝግ ነበር፡፡ ዛሬ ገና ነው በከፊል ምስክሮችን እዚህ ያየናቸው፡፡ አቃቤ ህግ ‹ምስክሮቼ ዛቻ ደረሰባቸው፣ ተደበደቡ› ካለ ሊጠየቅ የሚገባው እሱ ነው፡፡ ማነው በጀርባ ያለው? እኛ ከእስር ቤት ሆነን እንዴት ብለን ልናስፈራራ እንችላለን? ይሄ ከአየር ላይ የመጣ ፍረጃ ሲሆን የተፈጸመ ነገር ካለ በግልጽ ይታይ፡፡ የተባለው ነገር በማስረጃ ቀርቦ እንጂ በግምት ሊሆን አይገባም፡፡ ፍርድ ቤቱ ‹በዝግ ችሎት ሂደቱ ይታይ› ብሎ የሚወስን ከሆነ ዛሬውኑ የምትፈርዱብንን ተቀብለን ለመመለስ ዝግጁ ነን፡፡ አቃቤ ህግም ሆነ እናንተ የግፍ እስረኞች መሆናችንን ታውቃላችሁ ብለን እናስባለን፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡
ሶስቱም ዳኞች ‹‹የአቃቤ ህግን አቤቱታና በተከሳሾች በኩል የቀረበውን አስተያየት በጽ/ቤት ተመካክረን ተመልሰን እንወስናል›› ብለው ከችሎት ወጥተው ከ30 ደቂቃ በኋላ በመመለስ ጉዳዩን መመርመራቸውን የቀኝ ዳኛው ገልጸው፤ ችሎት በዝግ የሚታይበትን ሁኔታ በህገ-መንግሥቱና በሌሎች ህጎች ላይ የተደነገጉትን ፍሬ ነገሮች በመዘርዘር ‹‹የአቃቤ ህግን አቤቱታ በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ አልተቀበልነውም፤ የምስክሮች ስምና ቃል ግን በህተመት እና በኤሌክትሮኒኪስ ሚዲያ እንዳይዘገብ ወስነናል›› የሚል መልስ ከሰጡ በኋላ ምስክሮችን ወደማድመጥ ሂደት ገብተዋል፡፡ የቃቤ ህግን ምስክሮች የማድመጥ ሂደት እስከፊታችን ሐሙስ ሰኔ 04 ቀን 2007 ዓ.ም ዕለት ድረስ እንደሚዘልቅ ዳኞች ተናግረዋል፡፡
The post በዝግ ችሎት ይሁን/ አይሁን በሚል ከርክር ያስነሳው እና በሚዲያ የምስክሮች ቃል እንዳይዘብ የተከለከለው የእነሀብታሙ፣ አብርሃ …የፍርድ ቤት ዘገባ appeared first on Zehabesha Amharic.