ከሰሜን ተራሮች በራስ ደጀን ተራራ ላይ የሚገኘውን የቅዱስ ያሬድን ገዳም ለእኔና ለበረሃው ጓዴ አብርሃም ዳልሽሃ ደርሶ መልስ 17 ሰዓት ያህል የወሰደብንን የእግር ጉዞ ካደረግን በኋላ ጎንደር በሰላም መግባታችንን ነግሬያችሁ ነበር ።
ጎንደር መዋል ማደሬም ካልቀረ ደግም ለምን ትክልድንጋይ ሄጄ ምንም ቢደክመኝ ለምን በሊብያ የተሰዋው ልጅ ቤት አልሄድም ብዬ ለራሴ ወስኜ ነበር ። ይሁን እንጂ በስዊዘርላንድ የሚኖረውና የቀድሞው ወደገዳማት በምናደርገው ጉዞ ጓደኛዬ የነበረው ጴጥሮስ አሸናፊም ጎንደር ከደረስክ አይቀር እባክህ ተጎጂው ቤት ደርሰህ አሳውቀን የሚለው ውትወታውም አበርትቶኛል ።
ወደዚህ ተጎጂ ቤተሰቦች ዘንድ ለመሄድም ስነሳ ከእኔ ቀድሞ እዚህ ልጅ ወላጅ ቤት ሄዶ የነበረውን አርቲስት ዮሴፍ ገብሬን/ጆሲን/አድራሻ ጠይቄ የስራ ባልደረቦቹ አቶ አባተ እና አቶ ዮሴፍ የሰጡኝን ስልክ ይዤ የሟችን ወንድም በማናገር ቤተሰቦቹ ጋር እንዲወስደኝ ጠየቅሁት።
ወንድምየውም በስልክ እናቴ ወደ ከተማ መምጣት አትችልም እንጂ አባቴን እዚሁ ትክልድንጋይ ድረስ እንደጆሲ ላስመጣልህ ። አንተም ቤተሰቦቼ ያሉት ገጠር ነውና እጅግ አድካሚ ተራራዎችን መውጣትም ይጠበቅብሃልና ግድየለም ከምትደክም አባቴ ትክል ድንጋይ ድረስ ላስመጣው ቢለኝም አይሆንም እዚያው ያሉበት ድረስ ትወስደኛለህ አልኩትና ስልኩን ዘግተን ተለያየን ።
ብዙ በግል ለመሄድ መዘጋጀቴን የነገርኳቸው በጎንደር የሚገኙ ወዳጆቼም አከባቢው አርማጨሆ ስለሆነ እንደው የጸጥታ ችግር ይኖርበት ይሆናልና ገጠር መግባቱን ትተህ ትክል ድንጋይ ድረስ ሂድ ቢሉኝም አለሰማኋቸውም ። ከዚህ ይልቅ እግሬ በስትራፖ ነው የሚባል ተሳስሮ ከአልጋና ደረጃ መውረድ አቅቶኝ ስለነበር እንዴት እራመድ ይሆን ብዬ ነበር ስጋት የያዘኝ ። የሆነው ሆኖ እንድቀር ሺ ምክንያቶች ቢኖሩኝም እና ከፊቴ ቢደረደሩም በጊዜው ለመሄድ ወስኜ ነበርና ወደስፍራው ለመሄድ ተነሳሁ ።
ውድ ጓደኞቼ እንደሰሞኑ ሁሉ ከእኔ ጋር አዋሬ የብርሃኑ ቤተሰብ ጋር ፣ ገርጂ የአያልቅበት እናት እማማ አለሚቱ ጋር ፣ ቂርቆስ የኢያሱ ባለቤት ሮዚና ጋር እንደሄድን ሁሉ ዛሬ ደግሞ ሰሜን ጎንደር በላይ አርማጨሆ ወርቅምድር ቀበሌ ወደሚገኘው የሟች ዲያቆን እንዳልከው ሐጎስ ቤተሰቦች ጋር ልንሄድ ነውና በዓይነ ህሊናችሁ ተከተሉኝ ።
ወደ ሰማዕቱ ቤት ለመሄድ መጀመሪያ ከጎንደር አውቶብስ ተራ ወደ ትክልድንጋይ እንሄዳለን። በመቀጠል ከትክል ድንጋይ ሌላ መኪና እንይዝና ሙሴባምብን አልፈን ኩርቢ የምትባል ከተማ እንደርሳለን ። መኪና ከጎንደር ኩርቢ ድረስ በቀጥታ ይገኛል ይህ የሚሆነው ግን ትክልድንጋይ የሚገኘው የሟች ወንድም ቀደሞ ወርዶ ከጠበቃችሁ ብቻ ነው። ከዚህ በኋላ ግን ከኩርቢ ጀምሮ የተጎጂው ቤተሰቦች ቤት ለመድረስ ወገብን ጠበቅ ማድረግ ነው ከፊት ለፊት የሚገኙትን ተራሮች ለመጋፈጥ ።
ትክልድንጋይ ስደርስ እንዲነግረኝ የጠየኩት አንድ በተሳፈርኩባት ሚኒባስ መኪና ውስጥ አጠገቤ ተቀምጦ የነበረ ወጣት ወዴት እንደምሄድ ምርመራ ቢያበዛብኝ ጊዜ የምሄድበትን ስነግረው ምሳውን ሳይበላ አብሬህ ነው የምሄድ ብሎኝ ተከተለኝ ። የሟችን ወንድም ማቲያስን ከትክልድንጋይ ይዘን ኩርቢ ደርሰን የእግር ጉዞ ጀመርን ። በኩርቢ ከተማ ወጣቱ በሙሉ ይህን ክላሽ እንደ ከዘራ በእጁ ይዞ መታየቱን ባልወደውም ደግነቱ የሟች ወንድምም የሀገሬው ሰው ሰላምታ ሲያበዙለት ማየቴ እንድረጋጋ አድርጎኛል ።
ማትያስ እኔን እና አብሮኝ ድንገት መንገድ የጀመረውን አማኑኤልን ከመንገድ በማቆም ወደ አንዲት ሱቅ በመሄድ አንድ ክላሽንኮቭ እና አንድ ሽጉጥ ይዞ በመምጣት ክላሹን ለራሱ ሽጉጡን አብሮኝ ለመጣው ልጅ ሰጥቶ ጉዞ ጀመርን ።
እኔ እያነከስኩ ማትያስ ስለወንድሙ እያጫወተኝ የበረሃውን መንገድ ተያያዝነው ። በመሳሪያ ታጅቤ መሄዱን ባልወደውም ግን የሀገሩ ባህል ከሆነ ምን ይደረግ ።
መሃል መንገድ ላይ ስንደርስ ሰማዩ ጠቆረ ። ድንገትም ጨላለመ ። ከየት መጣ ያላልነው ዝናብም አንዴ ተዘረገፈብን ። መጠለያ የለ ፣ ወይ ጥላ አልያዝን አማራጩ ከመቆም ወደፊት በዝናቡ እየተወገርን መሄድ ብቻ ነበር ። አሁን እንደምንም በእኔ አካሄድ ወደ 2 ሰዓት የፈጀውን ጉዞ ጨርሰን የሰማዕቱ እንዳልከው ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት ጋር ደረስን ።
የሟች ወንድም አስቀድሞ እንግዳ እንደሚመጣ ስለነገራቸው በመጠኑም ቢሆን ጎረቤቶቻቸው ተሰብስበዋል ። ወላጅ አባት የግብርና ሥራቸውን ጀምረዋል የመጡትም ከሥራ ላይ ነው ። እናት ግን ሀዘኑ እስካሁን የለቀቃቸውም አይመስልም ። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ። ድሮስ እናት እናት አይደለች ። የወለደ አንጀት አይደል የሚባለው ።
ትንሽ አረፍ እንዳልን የመጣሁበትን ምክንያት ተናግሬ ፣ ልቅሶ ለመድረስ ሳይሆን ከሰማዕቱ በረከት ለመቀበል የዚህንም ለማዕተቡ ሲል ዋጋ ይከፈለኝ ወላጆች ለማየት እና ከእናንተም በረከት ለመቀበል የመጣሁ መሆኑን ጭምር በመጥቀስ ጥቂት የማጽናኛ ቃል ከተናገርኩ በኋላ ስለ ልጃቸው እንዲያጫውቱኝ ጠየቅኋቸው ።
እጅግ አድርጎ የግብርናው ስራ እንደጎዳቸው የሚያስታውቁት አቶ ሐጎስ ስለ ልጃቸው እንዲህ ሲሉ በትካዜና አንዳንዴም በቁጭት አጫወቱኝ ። እኔም የሟች ወላጅ አባት ያጫወቱኝን ለእናንተ ለጓደኞቼ በአጭሩ ከብዙ በጥቂቱ እንዲሁ አቀረብኩላችሁ ።
1983 ዓም ጥር 12 ቀን የቃና ዘገሊላ ዕለት የደርግ መንግሥት ይህን ሥፍራ ለቅቆ በምትኩ የኢህአዴግ ሠራዊት አካባቢውን የተቆጣጠረ ዕለት ነበር ህጻን እንዳልክ ሐጎስ ከአባቱ ከአቶ ሐጎስ አየለ እና ከእናቱ ከወይዘሮ የሺእመቤት አስማረ የተወለደው ።
“የበኩር ልጅ የእግዚአብሔር ነው ስለተባልኩ ነፍስ እንዳወቀ በቀጥታ ወስጄ ለየኔታ ኃይለሚካኤል አስረከብኳቸው ። የኔታም በአግባቡ ከፊደል ገበታ ጀምሮ አስፈላጊውን የአብነት ትምህርት አስተምረውት ለክብረ ዲቁና አብቅተውታል ። ልጄም ጎንደር በመሄድ ድቁናውን በመቀበል ከዚህች የገጠር መንደር እስኪወጣ ድረስ በአጥቢያችን በሚገኘው የወርቅ ምድር ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አገልግሏል ። አቤት ድምጽ አቤት ቅዳሴ ድፍን ሐገር ነበር የሚያፈዝ ። እህህህ ። ኋላ ላይ ወርቅ ምድርን ለቅቆ ትክልድንጋይ ገባ ።
ለምን ? የእኔ ጥያቄ ነበር ።
ይኸውልዎ ከቤተክርስቲያን አገልግሎቱ ጎን ለጎን ዘመናዊ ትምህርቱን እንዲከታተል ስላደረግሁት ዘመናዊ ትምህርቱን ይከታተል ነበር ። በውጤቱም ከክፍሉ ሳይሆን ከአጠቃላይ 1ኛ ነበር የሚወጣ ። በኋላ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በወርቅ ምድር እስከ 8ተኛ ክፍል ከተማረ በኋላ ወደ 9ነኛ ክፍል ሲያልፍ በላይ አርማጨሆ ወረዳ በትክልድንጋይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ሄደ ። እዚያም ይኸው 10ኛ ክፍል ገብቶ እየተማረ ነበር ። የግማሽ አመቱንም ፈተና ወስዷል እኮ ። ምን ሆኖ ተነስቶ ሄዶ እንዲህ እንደሆነ አላውቅም ። ዝምታ …… ትካዜ ….. ልቅሶ ።
አቶ ሐጎስ ይቀጥላሉ ። ይገርምዎታል ፣ ልጁ ጎበዝ ነው ። እኔ ከአፈር ጋር ስታገል የምኖር አርሶ አደርገበሬ ነኝ ከእጅ ወደ አፍ በሆነችው ኑሮአችን ላይ 6 ልጆችን ወልደናል ። 3 ወንዶችና 3 ሴቶች ። እንግዲህ እሱ አንጋፋ ስለሆነ ተምሮ ከቁምነገር ደርሶ ለተናናሾቹ ብርሃን ይሆናል ብየ ነበር የምጠብቀው ። እኔ ምንም የመርዳት አቅም ስለሌለኝ ራሱን እየረዳ ነበር የሚኖረው ። ከራሱ አልፎ ታናሹን ማትያስን መስመር ለማስያዝ ይጥር ነበር ። ወይ ልጄን ። በአጭር ቀረብኝ እንጂ ።
በመሃል አቶ ሐጎስ ጠየቁኝ ። እኔምሎት ልጄ የሞተው ተርስዎ ልወቅ ብዬ ነው በጥይት ነው ወይስ ከታረዱት ነው ። እሱን ብቻ ይንገሩኝ ።
አይ የእርስዎ ልጅ ከታረዱት ሳይሆን በጥይት ከተገደሉት መሀል ነው አልኳቸው ።
እንዲያስ ከሆነ ደግ ። በጥይትማ እዚህ ታገራችንም ስንቱ ነው ሁል ጊዜ የሚሞት ። አዩ ሀዘኔን ይህ ያቀልልኛል ። መሞቱ ታልቀረ እንደወንዶቹ እንኳንም በጥይት ሆነ ።
ታዲያ ለምን ትምህርቱን አቋርጦ ተሰደደ ? የኔ ጥያቄ ነበር ። ይህን በተመለከተ አባት ምንም አይነት ነገር እንደማያውቁ ፣ ይኽን የሚያውቀው ተሰበሰቡ እንደሆነ እነሱ የልጁን ሞት እንጂ ስደቱን ኋላላይ እንደሰሙ ስለነገሩኝ ቀሪውን ታናሽ ወንድሙ ማትያስ ይነግረናል ።
ማትያስ እንዲህ ይላል ። “ስደትን ከእሱ ከሟች ወንድሜ ቀድሜ የማውቅ እኔ ነኝ በ1995 ወደ ሱዳን ሄጄ ከጥቅምት እስከ ሚያዝያ ድረስ ካርቱም ቆይቻለሁ ። ጨቅጭቆ ጨቅጭቆ አይሆንም ብሎ እየደወለ አባብሎ የመለሰኝ እሱ ነው ። እሱ በመሥራት እና በመማር ነው የሚያምነው ። በትክልድንጋይ በመጀመሪያ ጸጉር ቤት ኋላ ላይ ደግሞ ሞተር ሳይክል ገዝቶ በማከራየት ይኖር ይኖር ነበር።
ድንገት እኮ ነው ተነስቶ ሞተሩን ሽጦ ባህርዳር ሄጄ እስቲ ደግሞ ልሞክር ከፍ ካላሉ ከፍ ማለት የለም ብሎኝ እኔን ብቻ በማማከር ወደ ባህር ዳር የሄደው ። ጥቂት ቆይቶ ደግሞ መተማ ነኝ እዚህ የሚሠራ ሥራ እያጠናሁ ነኝ አለኝ ። ቀጠለና ወደ ሱዳን ልገባ ነው የሆኑ ልጆች አግኝተውኝ ሊቢያ ለምን አትሄድም ብለውኝ ስላሉኝ ልሄድ ነው ። ገንዘቤን በአንተ አካውንት አስገብቻለሁ ። እነሱ ደላሎቹ ገንዘብ ሲጠይቁህ ስጣቸው ብሎ አንዱን ደላላ በስልክ አስተዋወቀኝ ።
እኔም ይሁን ብዬ ሊቢያ የሚገባበትን ቀን መቁጠር ጀመርኩ ። የትንሳዔ ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ሲሆን ከካርቱም ተነስተናል ልክ የዛሬ ሳምንት ሊቢያ እንገባለን ። ቀሪውን ብርም ያንጊዜ ለደላላው ስጥልኝ ብሎኝ የመጨረሻ ድምጹን ሰምቼ ተለያየን ።
ታዲያ ማረፉን እንዴት ሰማህ ?
ማረፉንማ እንዴት ሰማሁ መሰለህ ። ደላላው ደውሎ ሊቢያ ገብተዋልና ተዘጋጅ ይለኛል ። እኔም መልካም እንግዲያውስ የወንድሜን ድምጽ አሰማኝ አልኩት ። እሱም እሺ ብሎኝ ። ስልኩን ዘጋ ። በከፈተው ጊዜም ስደውል አላነሳ አለኝ ። በኋላ እንዴት ነው ነገሩ ብዬ መተማ ሄጄ የሱዳን ስልክ ገዝቼ ስደውል አነሳልኝ ። እህሳ የወንድሜ ጉዳይስ ስለው ከብዙ ማመንታት በኋላ እንዴት እንደሞተ አትጠይቀኝ እንጂ በሕይወት የለም ሂድና ለቤተሰብህ እርማቸውን እንዲየወጡ አድርግ ። ከአሁን በኋላ ስልኬን ዘግቻለሁ አታገኘኝም ብሎ ስልኩን ዘጋው ። እኔም ያው መጥቼ ቤተሰቡን አረዳሁ ። በቃ ይኸው ነው አለኝ ማትያስ አንገቱን ድፍት አድርጎ በትካዜ ።
አሁን እየመሸ ነው ። የወጣሁትን ዳገት እንዴት እንደምወርድ እያሰብኩ ለመሄድ ተነሳሁ ። እንዳድር ግድ ቢሉኝም መሄድ እንዳለብኝ ነግሬ ተነሳሁ ። አባት አቶ ሐጎስ የእግር ውኃ አምጥተው ደንብ ነው ደግሞም መመለስህ ካልቀረ ይሄን የጓጎለ እግርህን ልሽልህ ብለው ከመሬት ተነጠፉ ። አይደረግም ብዬ እምቢ ብልም የኔ ማጠብ ይቀራል እንጂ ሳትታጠብማ አትሄድም ብለው እግሬን ማትያስ እሽት በማድረግ እንዲያጥበኝ አድርገው የተሳሰረውን እግሬን ፈታ አድርጎልኛል ።
በመቀጠል ለካ ማትያስ እንግዳ እንደሚመጣ ነግሯቸው ነበርና ተዘጋጅተው በፍጥነት የሰሯትን ምግብ አቅርበው ስስት በሌለበት መልኩ መሶብ ሙሉ እንጀራ ድስት ሙሉ ክሽን ያለች የዶሮ ወጥ አቅርበውልን በጉርሻ እያጣደፉ ደስ የሚል ግብዣ አድርገውልን ተመልሰናል ።
እኔም የገበሬ ልጅ ነኝ ። የከተማ ሰዎች አምሮብን ደምቀን የምንኖረው በገበሬ ድካም ነው ። ገበሬ ባይኖርም ምን ይውጠን ነበር ። ገበሬ ደግ ነው ፣ ገበሬ እንግዳ ተቀባይ ነው ። እሱ ከመደቡ ወርዶ መሬት የሚተኛ ። ገበሬ አማኝ ነው ተስፋውን ሁሉ በአምላኩ ላይ አሳርፎ የሚኖር ። አቤት መስተንግዶ ፣ በእውነት ሃዘናቸውን ነው የሚረሱት እንግዳሰው ሲያስተናግዱ ።
የሟች እናትም በዚያ እሾህና ድንጋይ በበዛበት በረሃ ከእንግዲህ እስክሞት ጫማ አላደርግም ብለው የነበረ ቢሆንም ከብዙ ማግባባት በኋላ ጫማቸውን አድርገዋል ።
እነዚህን ሰዎች እንደነገሩኝ ከሆነ ከጆሲ በቀር አንድም የጠየቃቸው እና ያጽናናቸው የለም ። የሀገሬው ሰው ግን ለእንዳልከው እንዳለቀሰ ለማንም እንዳላለቀሰ በአድናቆት ይናገራሉ ።
ከማን ምን እንጠብቅ ?
ይህ የግል ሃሳቤ ነው ። እንደቀደመ ጽሁፌ ሁሉ ባለ ድርሻ አካላት ብዬ ለማስባቸው አካላት መልእክቴን አስተላልፋለሁ ።
በቅድሚያ የክልሉ መንግሥትም ፦ መቼም ይህን ብሔራዊ ሐዘን ምነው አልሰማንም አትሉም ። እንዲህ እንዳትሉ ሀዘኑ የድፍን ሐገር ነው ። እናስ ምነው ምነው ሌላው ቢቀር እኒህን አርሶ አደር ገበሬ ማጽናናት እንዴት አቃታችሁ ። ምኑስ ከበዳችሁ ። እንደክልል መንግሥትነታችሁ ኃላፊነታችሁን ብትወጡ እላለሁ ።
፪ኛው ፦የክልሉ የሚድያ ሰዎች ገጠር ድረስ ሄዶ ዘገባ መስራት ቢያቅታችሁ እንኳን እስከ ኩርቢ ድረስ በመሄድ እኒያን ደካማ ቤተሰቦች ብታጽናኑ ምን ክፋት ይኖረዋል ። በዚያውም የስደትን አስከፊነት ለሌሎች ለማስተማር ይጠቅማችዃል ። እናም እንደእኔ እንደእኔ አንዲት የማጽናኛ ፕሮግራም ብትሰሩ እላለሁ ።
፫ኛ፦ የሰሜን ጎንደር ሀገረስብከት ፦ ይህ የሞተው ልጅ የቤተመቅደሱ አገልጋይ ዲያቆን ነው ። ሲሆን ሲሆን ሊቀጳጳሱ ጭምር ሄደው ቢያጽናኑ ካልተቻለም ደግሞ ቢያንስ ምን አለበት የሀገረ ስብከቱ ሰባክያን ወይም ደግሞ የወረዳው ሰባክያን ሄደው ቢያጽናኑ ። አሁንም አልረፈደም የ40ኛ ቀን መታሰቢያው እየደረሰ ስለሆነ አስቡበት ።
፬ኛ ፦ የጎንደርና የአካባቢው መንፈሳውያን ማኅበራት ፦ መቼም እናንተን በኅብረታችሁ ፣ በመንፈሳዊ ህይወታችሁ የማይቀና ኢትዮጵያዊ የለም ። በአክሱም ፣ በላሊበላና በግሸን እንዲሁም በጣና ክርስቶስ ሠምራ ገዳም የምታደርጉት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ይታወቃል ። ከሁሉ በላይ የጥምቀትን በዓል ልዩ የሆነ መንፈሳዊ ድባብ እንዲኖረው ማድረጋችሁ ይታወቃል እናም እዚህ ከአፍንጫችሁ ሥር ባለ ታሪክ ላይም እንድትረባረቡ እጠቁማችሀለሁ ። በተለይ ሰማዕቱ ቀድሶ ያደገባትን የወርቅ ምድር ቅዱስ ሚካኤልን ቤተክርስቲያን ሄዳችሁ በረከትን ተቀበሉ ።
፬ኛ ፦ እኛ ደግሞ በተቻለን አቅም በሐገር ውስጥም ሆነ ከሐገር ውጭ ያለን ኢትዮጵያውያን የተቻለንን ከቁርሳችንም ቢሆን ቀንሰን ብንረዳቸው በህይወት ያሉትን በትምህርት ራሳቸውን የሚችሉበትን ዘዴ በ ንፈልግላቸው መልካም ነው ።
እኔ ወደ ጎንደር መኪና በመጥፋቱ ከኩርቢ ለ3 በአንድ ሞተር ላይ ሦስታችን ከትክልድንጋይ ጎንደር ድረስ ደግሞ እኔና ባለሞተርሳይክሉ ብቻችንን በዚያ ጨለማ በየቦታው ፍተሻ እያደረግነ አሁን ከማረፊያዬ ገብቻለሁ ። በፕሮግራሜ መሰረትም ዛሬ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ወደቤተሰቤ እመለሳለሁ ። አብርሃምም የጎን አጥንት መሰንጠቅ እንደገጠመው ተነግሮት በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል ።
“የረዳኸኝ ብርታትና ጥንካሬንም የሰጠኸኝ አምላኬ ሆይ ! ተመስገንልኝ “።
“ድንግል ሆይ እናቴ ! ዛሬም እንደትናንቱ ቅደሚ ከፊት ከኋላዬ ” አሜን
በተረፈ እኔ ከስንቄ የተረፈኝን ሳንቲም እና ወደዚያ እየሄድኩ መሆኔን በአጋጣሚ ሰምታ የነበረች እህቴ በዚያው ከአንተ ስጥልኝ ባለችኝ መሠረት ሰጥቻለሁ ። ቤተሰብ ለሚላኩ ብሮች ከተማ ድረስ መምጣት ስለማይችሉ ጆሲ የሰጠው ብር ጭምር በታናሽ ልጃቸው ስም በባንክ የተቀመጠ በመሆኑ በዚያው ባንክ ቁጥር አስገቡላቸው ።
ማትያስ ሐጎስ አየለ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ትክልድንጋይ ቅርንጫፍ
የባንክ ሒሳብ ቁጥር
833501000418 ነው ።
ስልክ ቁጥር + 251934527249 ማትያስ ብላችሁ ደውሉለት ።
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ግንቦት 13/9/2007 ዓም
ጎንደር— ኢትዮጵያ
The post ቆይታ ከዲያቆኑ ሰማዕት ቤተሰቦች ጋር ※ (አዲስ ዜና ነው! በጥሞና ያንብቡት) – ዘመድኩን በቀለ appeared first on Zehabesha Amharic.