የፊታችን እሑድ በሚደረገው ጠቅላላ ምርጫ ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በዘንድሮ የምርጫ ተሳትፎው ላይ በርካታ ችግሮች እየገጠሙት ቢሆንም፣ በምርጫው እስከ መጨረሻው ድረስ ተሳትፎው እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
‹‹ለመርሆዋችን ተገዥ በመሆን የምርጫ ተሳትፎአችን እስከ መጨረሻው ይቀጥላል፤›› በሚል ርዕስ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ በምርጫ ተሳትፎው ላይ እየደረሱ ነው ያላቸውን ችግሮች ኢዴፓ ገልጿል፡፡
ፓርቲው ያገኛቸውን ነፃ የአየር ሰዓቶች በመጠቀም አማራጮቹን ለሕዝብ እንዳያደርስ በሚዲያ ተቋማት የደረሰበትን ሳንሱር፣ በየክልሉ በሚወዳደሩ ዕጩዎቹ ላይ የማዋከብ፣ የማስፈራራት፣ ስም የማጥፋትና የመደብደብ ዕርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው፣ ዕጩዎቹና ደጋፊዎቹ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ መከልከላቸው፣ የፖስተር መቀደድ እንደ ገጠመው፣ ባነሮችን ከቦታቸው ላይ መሰወርና ዕጩዎቹን ከሥራ ማባረር፣ ደመወዝ መከልከል፣ ከአገልግሎት ማግለልና የመሳሰሉት እየደረሱበት ካሉ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ አስታውቋል፡፡
ኢዴፓ በዚህ መጠኑ ያለፈ ተፅዕኖ ምክንያት በክልል የሚገኙ ጥቂት ዕጩዎቹ ራሳቸውን ከምርጫ እንቅስቃሴ ለማግለል የሚያስገድዳቸው ሁኔታ እንደተፈጠረ በመግለጫው የጠቆመ ቢሆንም፣ የፓርቲው የጥናትና ምርምር ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ግን ችግሩ በድርድር ተፈቶ አሁን ዕጩዎቹ ሥራዎቻቸውን በአግባቡ እያናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
አቶ ዋሲሁን፣ ‹‹ቁጫና ወላይታ ላይ አባሎቻችን ከሌሎች ፓርቲ አባላት ጋር በመሆን ከምርጫው ራሳቸውን እንደሚያገሉ ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ችግሩ በመፈታቱ ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ የምርጫ ቅስቀሳውንም ሲያከናውኑ ነበር፤›› በማለትም አክለዋል፡፡
‹‹ፓርቲያችን እነዚህ ከመጠን ያለፉ ጫናዎች ቢኖሩም፣ አባሎቻችንና መዋቅሮቻችን ችግሩን ተቋቁመው በምርጫው ውስጥ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እስከ መጨረሻው እንዲዘልቁበት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፤›› በማለት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም በምርጫው ተሳታፊነቱን እንደሚያረጋግጥ ኢዴፓ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በዚህ አገር የምርጫ ሥርዓቱ ጠንካራ መሠረት ላይ ሊቆም የሚችለው በማኩረፍና ራስን ከምርጫ ሒደት በማግለል ሳይሆን፣ በሒደቱ ውስጥ በመቆየት ችግሮችንና ጫናዎችን በመቋቋም፣ በማጋለጥና ችግሮች እንዲፈቱ ጥረት በማድረግ ነው ብሎ እንደሚያምንም ኢዴፓ አትቷል፡፡
በዘንድሮ ምርጫ ከሚሳተፉ 58 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ኢዴፓ፣ 165 ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ 501 ዕጩዎችን ካቀረበው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እና 270 ዕጩዎችን ካስመዘገበው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በመቀጠል፣ በርካታ ዕጩዎችን በማስመዝገብ ሦስተኛ ፓርቲ መሆኑን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ ያመለክታል፡፡ በቦርዱ መረጃ መሠረት 139 ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡
The post ኢዴፓ በዕጩዎቹ ላይ እንግልት እየደረሰባቸው ቢሆንም በምርጫው እንደሚገፋ አስታወቀ appeared first on Zehabesha Amharic.