Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

አነጋጋሪው የጥላሁን ገሰሰ መጽሐፍና የባለቤቱ ሮማን በዙ ምላሽ

$
0
0

Tilahun and Roman Bezu
በጋዜጠኛ ዘከርያ መሀመድ የተጻፈውና ‹‹ጥላሁን ገሠሠ የሕይወት ታሪክና ምስጢር›› በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃውን መጽሐፍ አስመልክቶ የተለያዩ ሀሳቦች እየተነሱ ነው፡፡ ዘከርያ በቁም ነገር መጽሔት 202ኛ እትም ላይ በሰጠው ቃለምልልስ መጽሐፉን ለማዘጋጀት ዋና ምክንያት የሆነው በጥላሁን ገሠሠ ዙሪያ የሚነሱ የተዛቡ ታሪኮችን ማጥራት መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና የጥላሁን ባለቤት ወ/ሮ ሮማን በዙ ‹ከመጽሐፉ መታተም ጀርባ ሌላ ታሪክ አለ› ትላለች፡

ቁም ነገር፡- ጋዜጠኛ ዘከርያ የጻፈው መጽሐፍ ለንባብ ከመብቃቱ በፊት እየተጻፈ እንደሆነ ታውቂ ነበር?
ወ/ሮ ሮማን፡- አንድ ጊዜ በጥላሁን ዙሪያ ኮሚቴውን ለማመስገን አንድ ዝግጅት ቤታችን ውስጥ ተዘጋጅቶ በነበረበት ወቅት ንጉሤ የሃረሩ መጥቶ ነበር፡፡ እሱ ነው መጀመሪያ የነገረኝ፡፡ ‹ዘከርያ የሚባል ሠው እኔን አነጋግሮኛል፤ በጥላሁን ዙሪያ መጽሐፍ እያዘጋጀ ነው ለምን ባለቤቱን አታነጋግራትም ብየው ነበር› አለኝ፡፡ ከዚያ ወዲያው ደወለለትና ከኔ ጋር አገናኘን፡፡ እኔም ‹‹ከበፊቱ መጽሐፍ የተለየ ነገር አለኝ የምትል ከሆነ በአካል እንገናኝና እናውራ፤ ጥላሁን ሠፊ ነው፤ ብዙ የምንልለት ነገር ይኖራል፡፡ የጥላሁን ነገር በአንድ
መጽሐፍ የሚያልቅ አይደለም፤ ስለዚህ አዲስ ነገር ካለህ እንገናኝና አብረን እንሰራለን›› አልኩት፡፡ እሽ ተባብለን ስልኩን ዘጋሁት፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ጠፋ፡፡

የሚሆነው ይመስለኛል፡፡ ንጉሤ በትክክል ጊዜውን ያስታውሰው ይሆናል፡፡ በንጉሴ ስልክ ነው ያወራነው፡፡ ከዚያ በኋላ አንድ ቀን ንጉሤን ‹ያልከኝ ሰውዬ የታለ› አልኩት፡፡ እሱም እኔም ጋ መረጃ ከወሰደ በኋላ ጠፍቷል፡ ከአንች ጋር በስልክካወራችሁ በኋላ ደውሎልኝ አያውቅም አለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ መጽሐፍ እየተጻፈ ነው.. ሊያልቅ ነው የሚለውን ወሬ መስማት ጀመርኩ፡፡

ቁም ነገር፡- መጽሐፉን መቼ ነው ያየሽው?
ወ/ሮ ሮማን፡- መጽሐፉ ውስጥ ያነጋገራቸው አንዳንድ የጥላሁን ወዳጆች እየደወሉ ይጠይቁኛል፡፡ አንች ጋር አልመጣም እንዴ? እኛን እኮ መጥቶ አነጋግሮናል፤ እሷ ጋ መሄድ አለብህ ብለነዋል ብለው ሲነግሩኝ እኔ ጋ አልመጣም ብዬ እመልስላቸዋለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ መጽሐፉ ታትሞ ወጣ፡፡
መፅሐፉ ከወጣ በኋላ የእሱ ጓደኞች አንጋፋዎቹ ተናደው ምንድነው አሁን የሞተን ሠው አንስቶ ዋሽቷል እንዲህ ብሏል ማለት፣ እንዴት ዝም ትያለሽ ብለው ይደውሉልኛል፡፡ እኔ ደግሞ መጽሐፉን ገና አላነበብኩትም ነበር፡፡ መጽሐፉን ላንብበውና የምንለውን እንላለን አልኳቸው፡፡

ቁም ነገር፡- እነ ማናቸው ?
ወ/ሮ ሮማን፡- የጥላሁን ወዳጆች ናቸው፤ ጥላሁንን ከስር ከመሠረቱ የሚያውቁ ወዳጆቹ ናቸው፡ ፡ ነይ ብለው ብሔራዊ ቴአትር ቤት ጠርተው ቁም ነገር መጽሔት ላይም ወጥቷል፤ መጽሐፉንም ነይ አንብቢ ብለውኝ እዚያ ሄጄ ነው መጀመርያ ያየሁት፡፡ ከዚያ ወዲያው ነው መጽሐፉን ይዤ ቤቴ ሄጄ ማንበብ
የጀመርኩት፡፡
ቁም ነገር፡- መጽሐፉን ካነበብሽ በኋላ ልክ አይደሉም ያልሻቸው ሃሳቦች የትኞቹ ናቸው?
ወ/ሮ ሮማን፡- ከሀሉም በፊት መነሳት ያለበት ይሄ መጽሐፍ ለምን ተጻፈ የሚለው ነው፡፡ ስለ መጽሐፉ ይዘት ከማውራታችን በፊት ሌላ ማወቅ ያለብን ነገር አለ፡፡ መጽሐፉን ካነበብኩ በኋላ ስደርስበት ከደራሲው በስተጀርባ ያለው ሠው ነው ዋና ምክንያቱ፡፡ መነሻው የአቶ ፈይሣ ልጅ የሆነው ሳምሶን ነው፡፡ በመጽሐፉ ላይ የሳምሶን እጅ እንዳለ ሳውቅ መጽሐፉ በምን ደረጃ እንደሚጻፍ ይገባኛል፡፡ እያንዳንዱን ገጽ እንኳ ማንበብ አይጠበቅብኝም፡፡

አቶ ፈይሳን አውቃቸዋለሁ፡፡ ደብረብርሃን ወስዶ ጥላሁን አስተዋውቆኛል፡፡ የእሳቸው ልጅ ሳምሶን ደግሞ እኛ ቤት ይኖር የነበረ ሠው ነው፡፡ እኔና ጥላሁን በትዳራችን መሃል ለተፈጠረው ግጭት ዋናው መሳሪያ ሳምሶን ነበር፡፡ ለጥላሁን የሆነ ያልሆነ ነገር ይነግረው ነበር፡፡ እንዲህ እያደረገች… እንዲህ ልታስደርግህ…ብዙ ነገር…በቃ እኔ ልናገረው የሚዘገንነኝን ነገር ሁሉ እያለ ጥላሁንን ከቤት እንዲወጣ አደረገው፡፡ ከዚያ ጥላሁን ወጣ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ እቃዎቼን ስመለከት ብዙ ነገር ጠፍቷል፡፡ በሻንጣ የነበሩ ልብሶቼና ወርቅ ሁሉ ሳይቀር ይጠፋል፡፡ ላንቻ ፓሊስ ጣቢያ አመልክቼ ሰራተኞቹ ሁሉ ሲመረመሩ ሳምሶን ነው የወሰደው ብለው ተናገሩ፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰደ፡፡ እሱ ግን ሊያምን አልቻለም፡፡ ታሪኩ በጣም ረዥም ነው፡፡ በኋላ ፖሊሶቹን ደብረብርሃን እንሂድ አልኳቸውና እዚያ ስንሄድ በሙሉ ከአሜሪካ ሀገር ያመጣኋቸው 7 ሻንጣ ልብስና ወርቆቼ ሳይቀር ተገኙ፡፡

ጥላሁን ይህን ሲያውቅ ፖሊሶቹ ሲነግሩት መሬት ላይ ነው የተደፋው፡፡ ‹‹የልጄ እናት ይቅርታ አድርጊልኝ፣ ለዚህ ያበቃኝ እሱ ነው፤ ብዙ ነገር እየነገረ››
ብሎ አለቀሰ፡፡
በአጭሩ ሳምሶን ማለት ይሄንን ያደረገ ሰው ነው፡፡ ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ብትጠይቁ መረጃውን ታገኛላችሁ፡፡ ፖሊሶች ከሳምሶን ኪስ ውስጥ ብዙ የጥንቆላ ነገሮችን ሁሉ ነው ያገኙት፡፡ ‹‹ጥላሁንን እንዲህ አርግልኝ…ምናምን›› የሚል እንዲሁም ደግሞ ጥላሁን ከተለያየ ሠው እንደተበደረ አስመስሎ ያዘጋጀው ወረቀት ሁሉ ተገኝቶበታል፡፡ ጥላሁንን ትብትብ አድርጎ የተጫወተበት ሰው ነው ሳምሶን ማለት፡፡

ቁም ነገር፡- ከጥላሁን ጋር ምንድነው ዝምድናቸው?
ወ/ሮ ሮማን፡- አቶ ፈይሳ ለጥላሁን እናት አጎት ናቸው፡፡ ሳምሶን ደግሞ የእሳቸው ልጅ ነው፡፡ አቶ ፈይሳ ስለጥላሁን ሊያውቁ የሚችሉት ብቸኛው ነገር ምናልባት የተወለደበትን ቦታ ነው፡ ፡ እሱንም ቢሆን የጻፉትን መረጃ ማየት አለብን፡፡ አቶ ፈይሳ በዚያ ዘመን የረቀቁ ሰው ሆነው ጥላሁን ወደፊት እዚህ ደረጃ እንደሚደርስ ታይቷቸው ነው የጻፉት? ጠንቋይ ናቸው? የወደፊቱ ይታያቸዋል? የጥላሁንን ብቻ ነው ወይስ የልጆቻቸውን ታሪክ ጽፈዋል? ምንድነው? በማስረጃ መረጋገጥ አለበት፡፡

ቁም ነገር፡- መጽሐፉ ለሆነ የተለየ አላማ የወጣ ነው ብለሽ ታምኛለሽ?
ወ/ሮ ሮማን፡- አንደኛ ሳምሶን ምን ያህል ገንዘብ እንደሚወድ አውቃለሁ፡፡ ጥላሁን ገና በህይወት እያለ እንኳ ሊሸጠው ሊለውጠው የፈለገ ሠው ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ መጽሐፍ ጀርባ ከደራሲው ጋር በምን እንደተደራደረ ባላውቅም የተወሰነ ሳንቲም ሊገኝበት ይችላል፡፡ ትልቁ አላማው ሳንቲም ነው፡፡ ሳምሶንን ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ ከዚህ በተረፈ መጽሐፉ ምንድነው ያመጣው አዲስ ነገር? ትንሽ የተለየ አገኘሁ ብል የት ተወለደ የሚለውን ነው፡፡ ሌላው ግን የቃላት ጨዋታ ነው እንጂ ምንም የተለየ ነገር የለውም፡፡ ‹‹አንድን መጽሐፍ ሽፋኑን አይተህ ግምት አትስጥ›› የሚባለው እውነት ነው፡፡ ‹‹ምስጢር›› ይላል ግን ምንም አዲስ ምስጢር የለም፡፡ በእርግጥ ስለሙያው ጥሩ አድርጎ ጽፏል፡፡ እሱም ቢሆን ግን ከዚህ በፊት ያልተባለ ነገር አይደለም፡፡ የትዳሩን ጉዳይ በተመለከተ ግን ዝም ብለህ ቁጭ ብለህ የምትጽፈው አይደለም፡፡ የስሚ ስሚ ልትጽፍ አትችልም፡፡ በትዳር ውስጥ ስላለው ጉዳይ የሚያውቁት ባለቤቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ እኔ እንኳን ልናገር ብል እኔን በተመለከተ ያለውን እንጅ ከዚያ በፊት ስለነበረው የትዳር ህይወት ግን ማንም ገብቶ ከሁለቱ ባልና ሚስት ውጭ እውነቱን ሊናገር አይችልም፡፡ ልትጽፍ የምትችለው ባለቤቱ ራሱ የተናገረውን ነው፡፡

ስለእኔ ተጽፏል፡፡ ግን ፀሐፊው እኔ ጋ አልመጣም፡፡ አውቃለሁ፡፡ ሳምሶን ዘከርያ ወደእኔ እንዲመጣ አይፈልግም፡፡ ምክንቱም እኔ ምን እንደምል ያውቃል፡፡ ግን ፀሐፊው መጽሐፉ ውስጥ ስለኔ የሚያወራ ከሆነ መጥቶ ሊያነጋግረኝ ይገባ ነበር፡፡ ስለ አንድ ሰው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ
ነገር ስትጽፍ ባለቤቱን ማናገር ያስፈልጋል፡፡

ቁም ነገር፡- ያ ችግር ከተፈጠረ በኋላ ሳምሶን ከጥላሁን ወይም ከአንቺ ጋር ተገናኝቶ ያውቃል?
ወ/ሮ ሮማን፡- በፍፁም፡፡ ከጥላሁን ጋር ራሱ አስራ ምናምን አመት ይሆናቸዋል፡፡ ሕይወቱ ካለፈ በኋላም ለቅሶ እንኳ እኔ ጋ መጥቶ
አልደረሰም፡፡
roman bezu

ቁም ነገር፡- የደራሲያን ማህበር በጻፈው መጽሐፍ ላይ ጥላሁን የተወለደው አዲስ አበባ መሆኑን ይገልፃል፤ በአዲሱ መጽሐፍ ደግሞ የጥላሁን የትውልድ ቦታ ወሊሶ መሆኑ ተጽፏል፤ ያሄን እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው?

ወ/ሮ ሮማን፡- እኔ አሁን በሁለቱም ጎን ሆኜ ጥላሁን አዲስ አበባ ነው የተወለደው ወይም ወሊሶ ነው የተወለደው ማለት አልችልም፡ ፡ ለምሳሌ አቶ ፈይሳ ለጥላሁን በእናቱ በኩል ባላቸው ዝምድና ስለጥላሁን ማስታወሻ ጽፈው እዚያ ላይ የገለጹት ወሊሶ እንደተወለደ ነው ተብሏል፡፡ ማስረጃ ካለ ላምን እችላለሁ፡፡ ግን ይቅርታ አድርግልኝና እሳቸው ጽፈዋል በሚል ሳምሶን ያን ሊያደርገው አይችልም የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሳምሶን ጥላሁንን በቁም እያለ ሊሸጠው የነበረ ሠው ነው፡፡

ዞሮ ዞሮ ወሊሶ ነው የተወለደው ወይም አዲስ አበባ ያንን የሚያውቀው ራሱ ባለቤቱ ነው፡ ፡ በነገራችን ላይ ጥላሁን የውልደት ቦታ ወይም የብሔር ነገር የሚያሳስበው ሰው አልነበረም፡ ፡ በተለያዩ ቦታዎች የሆነ ፎርም ሲሞላ እንኳ ብሔር ሲባል ኢትዮጵያዊ ብሎ ነበር የሚሞላው፡፡ ጥላሁን ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በዚያ ላይ አዲስ አበባ መወለድም ሆነ ወሊሶ መወለድ የሚያሰፍርም ሆነ የሚያኮራ ነገር የለውም፡፡ ስለዚህ ሊደብቅ የሚችልበት ምክንያት የለም፡፡ የደራሲያን ማህበሩ መጽሐፍ ላይ ጥላሁን አዲስ አበባ ጠመንጃ ያዥ ሠፈር እንደተወለደ ነው የገለጸው፡፡ የተቀረጸና ከሰውዬው አንደበት የተሰማ ነው፡፡ ነገር ግን በማስረጃ እስከተጻፈ ድረስ በዚህኛው መጽሐፍ ላይ የሠፈረውንም ቢሆን አምነዋለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- ስለዚህ በአጠቃላይ መጽሐፉ የተጻፈው በሳምሶን ግፊትና ለጥቅም ሲባል ነው ብለሽ ነው የምታምኚው?

ወ/ሮ ሮማን፡- ለጥቅምና ስም ለማጥፋት ተብሎ የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ እኔ እንዳጋጣሚ በጥላሁን የትዳር ህይወት ውስጥ መጨረሻ ላይ ሆንኩኝ፡፡ ማንም ሠው የህይወቱን አጋጣሚ አያውቅም፡፡ የእኔ ከሱ ጋር የመጨረሻ መሆን የሰሞኑ አጀንዳ ሳምሶንና የሳምሶን አጃቢዎችን ስላናደዳቸው ‹‹ጥላሁን እሷ ጋር በነበረበት ወቅት ተጎድቷል በጥሩ አታስታምመውም ነበር›› ብለዋል፡፡ ይሄ እኮ ስም ማጥፋት ነው፡፡ ይሄ ባይሆን እኔ ጋ መጥቶ ይጠይቀኝ ነበር፡፡ አንድ ሶስቱን የቀድሞ የትዳር ጓደኞቹን መርጦ አነጋግሮ እነሱ ጋ እንክብካቤው ከፍ ያለ እንደነበር አድርጎ፤ እኔ ግን እንደበደልኩት አድርጎ ነው የጻፈው፡፡ እኔን ግን አላናገረኝም፡፡ በተጨማሪ የሞተን ሰው አሁን አንስተህ ዋሽቶ ነበር፤ በህይወቱ ደስተኛ አልነበረም፤ እያሉ መጻፍስ ምን ይጠቅማል፡፡ እሱ ታዋቂ ስለሆነ ማንም ተነስቶ እየዘለፈ መጻፍ ያለበት አይመስለኝም፡፡

ቁም ነገር፡- ጥላሁን ራሱን ለማጥፋት እንደሞከረ በመጽሐፉ ተገልጾዋል፤ በዚህ ጉዳይ ምን ትያለሽ?
እየተባለ ነው የተፃፈው፡፡ የሠው ስምም ተጠቅሶ እከሌም ይጠረጠራል ተብሎ ተጽፏል፡፡ አሁንም በ‹ሆድ ይፍጀው› ዙሪያ ነው እንጅ የተቀመጠው መፍትሔ አልሰጠውም፡፡ መፍትሔ የሚሰጠው ማስረጃ ሲኖረው ነው፡፡ ለጥርጣሬ ለጥርጣሬማ ሠው እቤቱ ቁጭ ብሎ እኮ ‹‹ራሱን ሊያጠፋ ሞክሮ ይሆን እንዴ? ለምንድነው ሆድ ይፍጀው ያለው?›› እያለ ሊነጋገር ይችላል፡፡

ቁም ነገር፡- አቶ ፈይሳ የቤተሰብ ማስታወሻ እንደሚጽፉ ታውቂ ነበር፤ ከጥላሁን ጋር ሲያወሩ ሰምተሸ ይሆን ?
ወ/ሮ ሮማን፡- አንድ ሁለት ጊዜ ነው ደብረብርሃን ሄጄ ያገኘኋቸው፡፡ ምንም የማውቀው ጉዳይ የለም፡፡ በጣም በቅርብ የማውቀው ልጃቸው ሳምሶንን ነው፡፡ እሱ እኛ ቤት ነው ይኖር የነበረው፡፡

ቁምነገር፡- ደራሲያን ማህበር የፃፈው መጽሐፍ ጥላሁንን በበቂ ሁኔታ ገልጾታል ብለሽ ታምኛለሽ?
ወ/ሮ፡- ጥላሁን በህይወት እያለ ነው መጽሐፉ የተጀመረው፡፡ ከትውልዱ አንስቶ ትዳሩ ደረጃ እስኪገባ ድረስ ራሱ የተረከው ነገር ነው፡፡ እርግጥ ህይወቱ ካለፈ በኋላ ያለው ሲጻፍ በጥልቀት ሊኼድበት ይገባ ነበር የሚለውን አስባለሁ፡፡ እንጅ በህይወቱ እያለ ለተጠየቀው ሁሉ ጥላሁን እሱ ያመነበትን መልስ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ እኔ ሁሌ እንደምለው ጥላሁን በእያንዳንዱ ሠው ህይወት ውስጥ የገባ ሠው ነው፡፡ ሁሌም ብትጽፈው አያልቅም፡፡ ይኼኛው መጽሐፍ ግን ሆነ ተብሎ ለተለየ አላማ የተጻፈ ነው፡፡ እንደዚያ ባይሆን ኖሮ የደራሲያን ማህበር በጥላሁን ዙሪያ መረጃ ያላችሁ ስጡን ሲል ነበር፡፡ ለምን ያኔ ሳምሶን የአባቴ ማስታወሻ አለ ብሎ አልመጣም፡፡ ‹‹በህይወት እያለሁ እንዳይወጣብኝ›› ብሏል አይደል የሚሉት፡ ፡ ያ ከሆነ ታዲያ ለምን ከሞተ በኋላ ለደራሲያን ማህበር መረጃውን አልሠጡም፡፡

ቁምነገር፡- በመጨረሻ ከጥላሁን ገሠሠ አደባባይ ጋር በተያያዘ ምን አዲስ ነገር አለ?
ወ/ሮ፡- የአደባባዩ ጉዳይ ሁሉም የሚያነሳውም ነገር ነው፡፡ በመንገዱ ስራ ምክንያት ነው እንደዚያ የሆነው፡፡ ባለፈው ጊዜ ከኢንጅነር ፈቃደ ሃይሌ ጋር ተገናኝተን ተነጋግረናል፡፡ ሌላ ቦታ፣ የማይነካ ቦታ ላይ አደባባይ ለመሰየም ታስቧል፡ ፡ ሐውልቱን ለማቆም ከቀራጺያን ጋር መነጋገር ጀምረን ሁሉ ነበር፡፡ አሁን ተለዋጭ አደባባይ ለማግኘት በሂደት ላይ እንገኛለን፡፡
ቁምነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡

The post አነጋጋሪው የጥላሁን ገሰሰ መጽሐፍና የባለቤቱ ሮማን በዙ ምላሽ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>