Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ኢትዮጵያዊ ማንነታችን የሚፈተንበት ቁጥር ፫ –የሰማዕቱ ኢያሱ ባለቤት ሮዛ ገ/ፃዲቅ

$
0
0

ከዘመድኩን በቀለ

” እህት ያላችሁ ፣ ሴት ልጅም የወለዳችሁ ፣ እናታችሁን የምትወዱ ሚስታችሁን የምታፈቅሩ በአግባቡ ከልብ ሆናችሁ በደንብ አንብቡት ። ”
[ይህን ጽሑፍ አንብቦ የማይጨረስ አይጀመረው]

roza gebrestadik
ሰሞኑን አዋሬና ገርጂ ድረስ በመሄድ የ ” ሰማዕት ብርሃኑን ” የሚያሳዝኑ ልጆችና ገርጂ ጊዮርጊስ ባጃጅ ማዞሪያ ድረስ በመሄድ ” የአያልቅበትን እናት እማማ አለሚቱን ስናፅናና መቆየታችን ይታወሳል ። እጅግ በጣም ደስስ ይላል ። የሃይማኖት ልዩነት ሳናደርግ ሁላችን ከመላው ዓለም ተረባርበን በሰብአዊነት ሁለቱንም የተጎጂ ቤተሰቦች ለመርዳት ያሳየነው መነሳሳት እጅግ የሚያስደስት ነው ። የብርሃኑም ባለቤት ከነልጆቿ የአያልቅበትም እናት በሚገርም ሁኔታ አሁን በህዝብ እየተጎበኙም እየተረዱም ነው ።
ዛሬ ደግሞ እንደሰሞኑ ሁሉ አንድ ስርቻ ውስጥ ብቻዋን ኩርምት ብላ በጭንቀት ከምትሰቃይ በሊብያ በረሃ የተሰዋ ” ሰማዕት ” ህጋዊ ሚስት ከሆነች ታዳጊ ወጣት ቤት እወስዳችዃለሁ ።

ውድ ጓደኞቹ እስካሁን የነገርኳችሁን በማመን እና በወሰድኩዋችሁ ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር በዓይነ ሕሊናቸሁ እየተከተላችሁኝ በመሄድ ባስለቀሰኝ ጉዳይ ላይ እያለቀሳችሁ ባሳዘነኝ ጉዳይ ላይም እንዲሁ እያዘናችሁ እንደቆያችሁ ይታወቃል ። ዛሬ ደግሞ በጀመርኩት ርእስ ላይ የመጨረሻዬ የሆነውን አሳዛኝ ታሪክ ወደ ዓየሁበት ቤት ልወስዳችሁ ነውና እባካችሁ ተከተሉኝ ።

እኔን ወደዚህ አሳዛኝ ታሪክ ወደአላት ሴት ቤት እባክህ ዘመዴ እንሂድ ብሎ በመጎትጎት የወሰደኝ የማኅበረ ወይንዬው ደረጀ ነጋሽ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜም የሄድነው እኔ ፣ ዘማሪ ዲያቆን ልዑልሰገድ ጌታቸው ፣ ዶክተር ህንፃዊት እና ዘማሪት ትእግስት ነበርን ።

ቤቱን ቀደም ብሎ ደረጀ ነጋሽ ያውቀው ስለነበር ለማግኘት አልተቸገርንም ። በአንድ የጥንት ግቢ ውስጥ በእኔ ዕይታ ያየሁትን ቤት ብዬ አፌን ሞልቼ የማልናገርላት 2×3 በምትሆን ቤት ውስጥ ፣ አንዲት ለግላጋ ልጅ እግር ወጣት ፣ ነገር ግን ሐዘን ያደቀቃት ሴት ከላይ እስከታች ጥቁር በጥቁር ልብሷን እንደለበሰች በቤት መሳይዋና ከሦስት ሰዎች በላይ በማትይዘው ቤቷ ውስጥ ተቀምጣ አገኘናት ።

በዚያች ቤት ውስጥ ከተዘረጋው ትንሽዬ አልጋ ፣ አንድ ወንበርና የልብስ ሻንጣ በቀር ሌላ ምንም አይነት ንብረትና ቁሳቁስ አይታይም ። ቤቷ ከመጥበቧም በተጨማሪ ለደቂቃዎች የማያስቀምጥ መጥፎ ጠረን ይገጥሞታል ።ይህ መጥፎ ጠረን ደግሞ መምጫው በአልጋው በኩል ከመጋረጃ መሳይ ነገር በተሸፈነ ከኮምፐርሳቶ ከተሠራ ግድግዳ በኩል ነው ። ለካ ይሄ ቤት መሳይ ቤት የተሠራው በሽንት ቤት ላይ ነው ። እኔ ለደቂቃ መቀመጥ ባቃተኝ ቤት ውስጥ ግን አልጋ ዘርግታ የምትኖር ሴት አለች ። ዛሬ ከዚህች ምስኪን የሰማዕት ሚስት ጋር ነው ቆይታ የምናደርገው ። ተከተሉኝ ።

ይህች ሴት ደረጀ እንደነገረኝ የዚህ ሰማዕት ሕጋዊ ሚስት ከሆነች ለምን አንድም እንኳን አስተዛዛኝ ይጠፋል በሚል ጥያቄ አዕምሮዬን ወጥሬ የቤቱንም መጥፎ የሽንት ቤት ጠረን ተቋቁሜ በትእግስት ተቀመጥኩኝ ። በገርጂ በእማማ አለሚቱ ቤት 2 ሰው በአዋሬ በብርሃኑ ቤት ጥቂት ሰዎችም እንኳን ቢሆኑም አስተዛዛኝ አይቻለሁ ። በዚህ ቤት ግን አንድም ሰው የለም ።
Rosa Gebretsadik
ቢያንስ የሚያፅናና ጎረቤት እንኳን ለምን አይኖርም የሚለው ጥያቄዬን በአዕምሮዬ እንደያዝኩ እንደምንም ታሪኳን እንድታጫውተኝ በጠየኳት መሠረት ያጫወተችን፣ በብዙ ዝምታዎችና ልቅሶ የታጀበው ታሪኳን እነሆ በአጭሩ እንዲህ አድርጌ አቅርቤላችዃለሁ እና ተከታተሉት።

ይህች ሴት ሮዚና ገብረ ጻድቅ ትባላለች ። አሁን 24ተኛ አመቷን ጨርሳ 25ተኛ ዓመቷን በመጀመር ላይም ትገኛለች ። ሮዚና ሁለት ወንድሞች ያሏት ሲሆን አሷ ለቤተሰቦቿ ሁለተኛ ልጅ ናት ። እነ ሮዛ ወላጅ እናትና እና አባታቸውን ገና ፍቅራቸውን በቅጡ ሳይጠግቡ ነው በልጅነታቸው በሞት የተነጠቁት ። ወገን ዘመድና የሚረዳቸው ባለመኖሩም የግድ ሕይወታቸውን ለማቆየት ሲሉ ታዳጊዎቹ በየፊናቸው ሥራ ፍለጋ በለጋ ዕድሜያቸው ተበታተኑ ። አያድርስ ነው ። እንዲህ አይነት ታሪክ ያለቻው በሚልየን የሚቆጠሩ ሰዎች ይኖራሉ ። ማን ያውቃል ምናልባትም ይህን ጽሑፍ ከምታነቡ ሰዎች መሃልም ትኖሩ ይሆናል ።

እሷ ለቤተሰቡ ሴትና ሁለተኛ ልጅ ስትሆን በትምህርት በኩልም 10ኛ ክፍል ላይ ነው ያቆመችው ። ይህ ሆኖም ዕድሜዋም አስራዎቹ መጨረሻ ላይ ቢገኝም ህይወትን ለማቆየት ሲባል በሰዎች እርዳታ ጭምር ወደ ኳታር ዶሃ ከተማ ትጓዛለች ። በዚያም ሳለች በልጅ አቅሟ የምትሰራውን እየሠራች ለወንድሞቿም እየላከች መኖር እንደጀመረች ነው የእህል ውሃ ነገር ሆኖ በቅርቡ በሊብያ በረሃ ውስጥ ” ሰማዕት ” ከሆነው የህግ ባለቤቷ ኢያሱ ይኩኖ አምላክ ጋር የተገናኘችው ።

ኢያሱ በሾፌርነት እሷም የልብስ መሸጫ ሱቅ ውስጥ እየሠራች ብዙም ሳይቆዩ እሱም እሷም በዚያ በረሃ የቋጠሯትን እና የያዟትን ጥሪት ቋጥረው በመመለስ በሃገራቸው ለመኖር በመወሰን አዲስ አበባ ይገባሉ ። አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት ግን ኢያሱ በኳታር እንደታሰና ንብረቱንም እንደተቀማ ሮዛ በቁጭት ታስታውሰዋለች ።

የሆነው ሁሉ ሆኖ ያለፈውም ሁሉ አልፎ የሁለቱ የፍቅር ግኑኝነታቸው በማደጉ እነሱም ሁኔታውን መልክ በማስያዝ ህጋዊ ጋብቻን ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው በተገኙበት የሠርግ ስርዓታቸውን በመፈጸም አሁን ሮዛ ተቀምጣ ያለችበትን ቤት ማድቤት እና ሽንት ቤት ሆና ተገለግል የነበረችውን የቀበሌ ቤት አልጋ ዘርግተውባት መኖር ይጀምራሉ ።
ኋላ ላይ የአዲስ አበባው ኑሮ እየከበዳቸው የመጣው የሟች ባለቤት በዚህ አይነት ሁኔታ መቀጠል ስለሌብን እኔ ዳግመኛ ወደ ስደት መሄድ አለብኝ ብሎ ይወስናል ። ኳታር ከመሄዱ በፊት ተመዝግቦ ከጋብቻ በፊት የደረሰውን የኮንዶሚኒየም ቤት ሸጦ እሷ ጋር የነበረውንም ጥቂት ሳንቲም ጨምሮ አይሆንም እባክህን ብትለውም እንደምንም አሳምኗት ከጓደኛው ጋር በመሆን ጎዞአቸውን በሱዳን በኩል ወደ ሊቢያ እንዳደረጉ ሮዛ ትናገራለች ።

ኢያሱ ድምጹን እስካጠፋበት ጊዜ ድረስ የሟች ታላቅ ወንድም ባለቤቷ ገንዘብ ላኩልኝ ባለ ጊዜ ሁሉ ብር እየላከለት መቆየቱን ትናገራለች ። ኢያሱም ለእሷም በየደረሰበት ቦታ ሁሉ ስልክ እየደወለ አይዞሽ ሮዚ በቅርቡ ያልፍልናል እያለ ያጽናናት እንደነበር ሮዛ በእንባ እየታጠበች ስትናገር አንጀት ትበላለች ።

በኋላ ላይ የቀን ክፉ የቀን ጎዶሎ ብላ በምትጠራው እለት ኢንተርኔት በመጠቀም ላይ የነበሩ ጓደኞቿ ባለቤቷን በሊብያ በረሃ በሜዲትራንያን ባሕር አጠገብ ጥቁር ቱታ ለብሶ እጁን የዃሊት የፊጥኝ ታሥሮ በእንብርክክ ለእርድ ከተዘጋጁት መሃል የአራጆቹ መሪ ከጀርባው ቆሞ ዲስኩሩን ሲያሰማ ባሏ በዝምታ አንገቱን ደፍቶ በማቀርቀር ሲያደምጠው ከዚያም አረመኔያዊ ድርጊት ሲፈፀምበት የሚያሳየውን ዘግናኝና አሰቃቂ ፊልም ተመልክተው ለእሷም በመንገር እንድታረጋግጥ ይነግሯታል ። ሮዛም እውነት መሆኑን ቪድዮውን በማየት አረጋገጠች ።

ሮዛ ከዚያ በኋላ የሆነውን ማስታወስና ማውራት አትፈልግም ። ዕድለቢስነት ይሰማታል ። ሞት እየተከታተለ በመጀመሪያ በ13 ዓመቷ ወላጅ እናቷን ፣ በመቀጠል በ19 ዓመቷ የምትመካበት አባቷን አሁን ደግሞ ተስፋዋን የጣለችበትና የወላጆቿን መርሻ ያደረገችውን ውድ ባሏን ነጥቋታል ። ኢያሱ የሄደበት መንገድ አደጋ እንዳለው ባውቅም እንዲህ አይነት አደጋ ይደርስበታል ብዬ በፍጹም አላሰብኩም ትላለች ሮዛ ። እኔ ብዙ ሰው የሚያልቅበትን የባህሩን የጀልባ ላይ ጉዞና በየበረሃው መንገላታት ይገጥመው ይሆናል ብዬ ነበር የፈራሁት እንጂ እንዲህ አይነት ዘግናኝ አረመኔያዊ ድርጊት ይፈጸምበታል ብዬ በህልሜም በውኔም መች አስቤው ።
እሱም ያለኝ ይሄንኑ ነው ። በኳታር ቆይታው አረብኛ መናገር በደንብ ስለሚችል መንገድ ላይ ክፉ እንደማይገጥመው ነበር የነገረኝ ። ግን መናገሩም ቋንቋን መቻሉም አላዳነውም ። ልቅሶ ……

አሁን በምን አይነት ሁኔታ ላይ ነው ያለሽው ?
ምንም ይኸው የማደርገው ግራ ገብቶኝ መረጋጋት አቅቶኝ ቁጭ ብያለሁ ። ” አንድ ኮንዲሚንየም ቤት ነበረን እሱንም ሽጦ ለመንገዱ ከፍሎ ነው የሄደው ። አብረን እያለን ከመሄዱ በፊት እዚህች ቤት ውስጥ የነበረንን ንብረት በሙሉ ቴሌቪዥንና ሻንጣዎቻችንን ሳይቀር በሌባ ተዘርፈናል ። ሌቦቹ ትተውልን የሄዱት ይህን አልጋ ብቻ ነው ። እኔ ጋርም የነበረችውን ሳንቲም ለስንቁ ሰጥቼዋለሁ ። ቶሎ አውሮፓ ገብቶ ያወጣውን ወጪ ሁሉ እንደሚመልስ እና ኑሮአችንን እንደሚለውጥ ነበር ተስፋ አድርገን የተቀመጥነው ።
ግን ሁሉም እንዳሰብነው ሳይሆን በስደት በበረሃ ያገኘሁትን ፍቅሬንና ባሌን በበረሃ በግፍ ብቻውን አስቀሩብኝ ።

እያሱ ለእናቱ ልዩ ፍቅር አለው ። እናቱን ስለሚያማቸው አብዛኛውን ጊዜ እሳቸውም ጋር እየሄደ በማደር ይንከባከባቸውም ነበር ። አብዛኛውን ገንዘቡን በእሳቸው ህክምና ላይ ያውለው ነበር ። እናቱን ያከብራል ፣ ይወዳል ፣ ዝምተኛ ነው ፣ ያሰበውን ካላሳካ ብቻ ነው ሲናደድ የማውቀው ። በተለይ ከእኔ ውጪ አብሮት የተሰዋው ለአብሮአደግ ጓደኛው ለባልቻም ከአክብሮት ጋር ልዩ የሆነ መዋደድ አላቸው ። ባልቻ ለኢያሱ ስንጋባም ሚዜው ነበር ።

እኔ አሁን ምን እንደምሆን ምንም እንደማደርግም ግራ ገብቶኛል ። አደጋውን በአይኔ ካየሁበት ዕለት ጀምሮ እንቅልፍ የሚባል የለኝም ። ጨለማ ማየት እፈራለሁ ። ኦሬንጅ ልብስ የለበሰ ሳይ እደነግጣለሁ ። ሌላም የሚቆጨኝ ነገር እግዚአብሔር አልፈቀደውም እንጂ የአራት ወር ፅንስ ይዤም ነበር ። ይኸው ተመልክተው ህክምና የተከታተልኩበትን ። በድንገት ደም ሲፈሰኝ አብሮ አደጉና ሚዜው ከነበረው ባልቻ ጋር ዘውዲቱ ሆስፒታል ወስደውኝ ነው ጽንሱ ተበላሽቶ እኔ ከሞት የተረፍኩት ።
አሁን ምን አማራጭ አለኝ ። እዚህ የሚረዳኝ ዘመድ ወገን የለኝም ። እየበላሁት ያለውን ቆሎና አስቤዛ ለጊዜው አምጥቶ ያረጋጋኝ ደረጄ ዘወይንዬ ነው ። ቤተሰቦቻችን በህይወት ስለሌሉ ሁሉም ሕይወቱን ለማቆየት ከእኔ ጋር የሉም ። ተበታትነናል ። እኔ እድለቦስ ነኝ ። የወንድሞቼን ፍቅር ፣ የወላጆቼን ፍቅር ፣ የባለቤቴን ፍቅር ሳላጣጥም እንድኖር የተፈረደብኝ ሰው ነኝ ። ልቅሶ ልቅሶ ልቅሶ ።

ዶር ሕንፃዊት ልቅሶ ዘማሪዋ ልቅሶ ሉሌም ደረጄ ልቅሶ ማንም ማንንም ሊያጽናና አልወደደም ። እኔ እሷ ይህን እየነገረችኝ ስለራሴ ልጆች ማሰብ ጀመርኩኝ ። ለ3 ወር እነበጋሻው ከሰውኝ ቃሊቲ ብከርም ለልጆቼ ያለሁበትን እናታቸውና ቤተሰብ ባይነግሯቸውም በትምህርት ቤት ይሰሙት ስለነበር እንዴት መማር እንዳቃታቸው ፣ መብላት ፣ መጠጣት ፣ እንቅልፍ መተኛት እንዳቃታቸው አሰብኩ ። ተፈትቼ እቤት የመጣሁ ቀን እንዴት ተጠምጥመውብኝ እንዳለቀሱ አስታወስኩት ። ቆይ እንዲህ ለጥቂት ጊዜ የተለየኋቸው ሞቼስ ቢሆን ኖሮ ብዬ ሳስበው ያሳዝኑኛል ።

እኔም እንዲህ አልኳት ። ሮዛ አይዞሽ አንቺም እኮ እድለኛ ነሽ ። የባልሽ የሰማዕቱ ኢያሱ ስም በተነሳ ቁጥር የአንቺም ስም አብሮ ይነሳል ። ገድሉም ቢጻፍ ፣ ስንክሳርም ቢጻፍ አንቺም በዚያ አለሽ ። የታሪኩም አንድ አካል ነሽ ። ደግሞም ባልሽ ታማኝነቱን እስከሞት ያስመሰከረ ግሩም ሰው መሆኑን አይተናል ። ስለትና ጥይት ከአምላኩ ፍቅር አልለየውም ። እስከ ሞት ድረስ የታመነ የሰማዕቱ የቅዱስ ቂርቆስ ፍሬ ነው ። እናም ልትረጋጊ ያስፈልጋል ።
እኔ አንቺ የምትረጂበትን መንገድ አመቻቻለሁ ። ደግሞ ለልመና ማን ብሎኝ ። አንቺም ቃል ግቢልኝ እንድትረጋጊ ። እግዚአብሔር ከረዳኝ ለመንግሥትም ለህዝብም በመላው ዓለም ላሉ ኢትዮጵያውያንም ችግርሽን አሰማለሁ ። እመኚኝ ችግርሽ ይፈታል ብቻ ጥቂት ቀን ታገሺኝ ብዬ ሌሎቹም እንዲሁ የሚያፅናና ቃል አካፍለዋት እያለቀስን ተለይተናት ሄድን ።
Rosa Gebretsadik  2
የብርሃኑን ልጆችና የአያልቅበትን እናት ጉዳይ ከዳር አድርሼ ለህዝብ ይፋ ሳደርግ ቆየሁና በዚያም ከመላው ዓለም የተገኘው ነገር ደስስስስ ስላሰኘኝ የመጨረሻዬ የሆነውን የሮዛን ጉዳይ ለመጀመር ስደውልላት ሌሊት ሌሊት የባሏ አሟሟት እየመጣባት እየተቸገረች እንደሆነች ስለነገረችኝ እኔም ዛሬ ከወንድሜ አብርሃም እንዳሻውና ከአባ ወልደ ኢየሱስ ጋር በመሄድ አባ ጸሎት አድርገው ቤቷንም ጸበል ረጭተው አረጋግተው ፣ መክረው አጽናንተዋታል ።
ሮዛ እንደነገረችኝ የሚበላ የላትም የታክሲ ቤሳቤስቲን የላትም ። አሁን ወደምታውቀው ስደት ለመሄድ እንደተዘጋጀችም ነገረችኝ ። በሁኔታው ሁላችንም ደነገጥን ። እኔም አይሆንም አይደረግም አልኳትና ። ተነሽ ልብስሽን ልበሽ ብዬ ምንም እንኳን ሰዓቱ ቢመሽም ፒያሳ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመምጣት በመሐል አራዳ ቅርንጫፍ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በባንኩ ሥራ አስኪያጅ በአቶ ወንድራድ ይሁኔ ቀና ትብብር የባንክ ሂሳብ ደብተር አውጥተንላታል ።
መክፈቻውንም አልማዝ እርገጤ የተባለች እህት በአቶ ወንደሰን ውቤ በኩል በላከችው 100 የአሜሪካን ዶላር ዘርዝረን በሁለት ሺህ አርባ ብር ጀምረናል ። ይቀጥላል ። እማምላክ ምስክሬ ናት እውነት እውነት እላችኋለሁ የዚህችን ወጣት ሕይወት እንደሚለወጥ ቅንጣት ታህል ጥርጥር የለኝም ።
ከማን ምን ይጠበቃል ?

መንግሥት ፦ ብትስማማም ባትሰማም መናገሬን እቀጥላለሁ ። ለሮዛ አንዲት የቀበሌ ቤት እንኳን የምታጣ አይመስለኝምና የመኖሪያዋን ጉዳይ እንዲያው ከተቻለ ብትይዝልኝ ።
ቤተክህነት ፦ እስካሁን የዚህችንም ልጅ ፣ የብርሃኑንም ልጆች ጉዳይ እንዳልሰማችሁ ልቁጠረውና እኒህን የእምነቱን ተከታይ ልጆች ባዶ ቤት አይጠፋምና እንደው ብትጸድቁባቸው ። ካልተቻለ ደግሞ ጥቂት የገንዘብ ድጋፍ ብታደርጉላቸው ።

የሴቶች ጉዳይ ፦ አለ ወይስ የለም ? ካለ ስለነዚህ የግፍ ሰለባ የሆኑ ሴቶች ምን ትላላችሁ ? ምነው ዝምታ አበዛችሁ ።
ባለሐብቶች ፦ ይቅርታ የእናንተን ስም በስህተት ነው የጠቀስኩት ። ስም ያለው አትሌት ፣ ዘፋኝ ፣ እግርኳስ ተጫዋች ካልሆነ እንደማትረዱ ያልተጻፈ ህግ አውጥታችኋል ለካ ። ይቅር በሉኝ ተሳስቼ ነው ።
እኛ ኢትዮጵያውያን ፦ በቃ ከኛ በቀር ለእኛ የሚደርስ ማንም የለም ። እናም በያላችሁበት ሐገር ያላችሁ ሁላችሁ አነሰ በዛ ሳትሉ የእርዳታ እጃችሁን ዘርጉ ።
ዮሴፍ ገብሬ /ጄሲ/ ያው እንደተለመደው ለምነህም ሆነ አስለምነህ ለሰማዕቱ ኢያሱ ባለቤትም ስለ እግዚአብሔር ብለህ ድረስላት ። ከተቻለ እግረመንገድህን ውላ የምትገባበት ሥራ የሚያሰሯት ድርጅቶችም ካሉ ፈልግላት ።
እኔም የምስራች አለኝ ፦
★ ለሮዛ አንዲት የገዳማውያን አባቶች መከታ የሆነች መንፈሳዊት እህቴ በሕይወት ዘመኗ ሁሉ ገና ልጅም ስለሆነች ትምህርቷን የፈለገችውን አይነት ዘርፍ መርጣ መማር ብትፈልግ እስከመጨረሻው አስተምራታለሁ ብላለች ።
★ ወሮ ገነት ከጀርመን 50 ዩሮ
★ አብሮ አደግ እህቴ የልጅ አዋቂዋ Helen Negash Mekonnen /ሚጢጢ / 150 ዶላር። እልካለሁ ያለች ሲሆን ። እህቴ ሚሚ ነጋሽም ሰምተሻልና ቶሎ ቃልሽን ስጪ ።
★አበባ ለገሰ ከአሜሪካ 500 ዶላር እልካለሁ ብላለች ። እንጠብቃለን ። ሌሎቻችሁም ፍጠኑ እና ድረሱላት ። የሰማዕት ሚስት ናትና እንንከባከባት ።
ሮዛ ገብረ ጻድቅ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
መሃል ከተማ ቅርንጫፍ
ሂሳብ ቁጥር 1000127035184
የእጅ ስልኳ +251946399795 ነው ። ደውሉና አጽኗኗት ። አይዞሽ ፣ በርቺም በሏት ።
እኔም እስከ ቅዳሜ ድረስ አዲስ አበባ ነኝ ። እስከዚያው የሮዛ ባንክም ምን እንደደረሰ እነግራችኋለሁ ።
ማንኛውንም አስተያየት በእጅ ስልኬ +251911608054 ላይ አስተናግዳለሁ ። እንደተለመደው ይህም ጽሑፍ ሼር ይፈልጋል ። ይቆየን ።
በነገራችን ላይ ሰማዕት እያሱን የገደለው ነፍሰ በላ ዛሬ የመገደሉ ዜና ተሰምቷል ። ” በቀል የእግዚአብሔር ነው ” አይደል የሚባለው ።
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ግንቦት 6/9/2007 ዓም
አዲስ አበባ — ኢትዮጵያ

The post ኢትዮጵያዊ ማንነታችን የሚፈተንበት ቁጥር ፫ – የሰማዕቱ ኢያሱ ባለቤት ሮዛ ገ/ፃዲቅ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>