Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: ሰውየው!! –የጆዜ ሞውሪንሆ ልዩ ገፅታ

$
0
0

jose-mourinho
‹‹አንድ ችግር አለብኝ›› ይላሉ ጆዜ ሞውሪንሆ፡፡ ‹‹እሱም በሥራዬ ሁሉ መሻሻሌን መቀጠሌ ነው፡፡ በሁሉም ነገሬ ለውጥ አለኝ፡፡ ጨዋታን የማነብበት መንገድ፣ ለጨዋታ የምዘጋጅበት ሁኔታ እንዲሁም ቡድኔን የማዘጋጅበት ዘዴ ሁሉ በብዙ ተሻሽያለሁ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመልካም ሁኔታ ላይ እገኛለሁ፡፡ ያልተለወጥኩበት አንድ ነገር ግን አለ፡፡ ሚዲያውን የምጋፈጥበት መንገድ ያው ነው፡፡ አስመሳይ አይደለሁምና››

ቁጥሮችን መሰረት ባደረገ መመዘኛ ሰውየው በዓለም እግር ኳስ እጅግ ስኬታማው የክለብ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ በአሰልጣኝነት በሰሩባቸው አራት ሀገሮ (ፖርቹጋል፣ ጣልያን፣ ስፔን እና እንግሊዝ) ሁሉ የሊግ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ሁለት ጊዜ አንስተዋል፡፡ የጆዜ መገለጫ ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በእግርኳሱ ዓለም እንደ እርሳቸው ብቻውን ሰዎችን በጉራ ለይቶ በክርክር የሚጠምድ አወዛጋቢ አሰልጣኝ አይገኝም፡፡ እንደ ሞውሪንሆ በተደጋጋሚ የባላጋራ ደጋፊዎችን በቁጣ እንዲነዱ በማድረግ የተካነ አሰልጣኝ አልታየም፡፡ ከዳኞች ጋር ይጨቃጨቃሉ፡፡ የእግርኳስ ማህበሩን በነገር ይወጋሉ፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫዎቻቸውን ባልተጠበቀ መልኩ ይዘጋሉ፡፡ በሜዳ ጠርዝ ላይ ቆመው ግርግር ይፈጥራሉ፡፡ ከእግርኳሱ ሌላ የሞውሪንሆ ሁኔታዎች በራሳቸው ብዙ ትኩረት ይስባሉ፡፡

ባለፈው ሳምንት የቼልሲው አሰልጣኝ ለንደን ውስጥ በሚገኝ አንድ ስቱዲዮ ለሁለት ሰዓታት ፎቶግራፎችን መነሳት ነበረባቸው፡፡ ቀለል ያሉ ልብሶችን እየለዋወጡ በተደጋጋሚ ጃጓር የስፖርት መኪናቸው ውስጥ ገባ ወጣ እንዲሉ ሲጠየቁ ታዛዥ ነበሩ፡፡ ጆዜ በአለባበሳቸው ዘናጭ የሚባሉ አይነት ቢሆኑም ለልብሶች ብዙ ግድ እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ ትኩረታቸው ከፋሽን ይልቅ ምኞታቸው ላይ ያመዝናል፡፡ በፎቶግራፎቻቸው ላይ የሚያሳዩት ገፅታ ምንም አይናገርም፡፡ እንደ ሁልጊዜው ሞውሪንሆአዊ ፊታቸው አይለወጥም፡፡ ሌላው ቀርቶ በአቅራቢያቸው በነበረ አንድ ስቱዲዮ ለራሱ የማስታወቂያ ፎቶግራፎችን ሲነሳ የቆየው ዲዲዬ ድሮግባ ድንገት ዘልሎ ገብቶ የእርሳቸውን ቀረፃ ያስተጓጎለ ሲመስል እንኳን ገፅታቸው ብዙ አልተቀየረም፡፡

የፎቶግራፍ ስነ ስርዓቱ አልቆ ሁሉም ሰው ለመመልከት በኮምፒዩተሩ ዙሪያ ተሰበሰበ፡፡ የሁሉም አይኖች ግን ከፎቶግራፎቹ ይልቅ ወደ ጆዜ እየተመለከቱ ሰውዬው የሚሉትን ለመስማት ይጠብቁ ነበር፡፡ ‹‹መጥፎ ነው?›› ምናልባት በእርግጥም እንደተጠቀሟቸው ቃላት ‹‹መጥፎ አይደለም›› ማለት ይሆን? ይህንን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ያስቸግራል፡፡
የሞውሪንሆ ጠዋት የሚጀምረው በቼልሲ የልምምድ ማዕከል ኮብሃም ነው፡፡ ይህ ጊዜ አጠባበቃቸው አይዛባም፡፡ ሁልጊዜም ጠዋት 1፡30 ሰዓት ማዕከሉ ከደረሱ በኋላ በቀጥታ ወደ ቢሯቸው ገብተው ከውስጥ ይቆልፉታል፡፡ በዚያው ለሁለት ሰዓታት ያህል ይቆያሉ፡፡ ‹‹ብቻዬን የምሆንበት ጊዜ ያስፈልገኛል›› ይላሉ ሞውሪንሆ፡፡ ‹‹እንደምታውቁት በእግር ኳስ እኔ አዛውንት የሚያስብል ዕድሌ የለኝም፡፡ አሁን በ52 ዓመቴ ገና ለማሰልጠን ከፊቴ 20 ዓመታት ሊኖሩኝ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ራሴን ከወዲሁ ‹‹ነባር›› አድርጌ እመለከታለሁ፡፡ ምንም አያስፈራኝም፡፡ ብዙ የሚያስጨንቀኝ ነገርም የለም፡፡ ምንም አዲስ ነገር የሚፈጠርብኝ አይመስልም፡፡ አሁን በእጅጉ ሰክኛለሁ፡፡ ስሜቶቼን መቆጣጠር እችላለሁ፡፡ በድንገት በውድቅት ሌሊት እየባነንኩ ስለ አንደኛው ተጫዋቼ ጉዳት ወይም ስለ አንደኛው ጨዋታ ታክቲክ አልጨነቅም፡፡ ይልቅ የራሴ የሆነ የማሰቢያ ጊዜ ያስፈልገኛል፡፡ ሁኔታዎችን ከተለያየ አቅጣጫ መመዘን እና ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሜ መገመት ይኖርብኛል፡፡ ስለዚህ የግል ጊዜ ያሻኛል››

የሞውሪንሆ ወላጅ አባት ጆዜ ግብ ጠባቂ ነበሩ፡፡ እንዲያውም ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን በአንድ ጨዋታ የመሰለፍ ዕድል አግኝተዋል፡፡ የኋላ ኋላ እርሳቸው አሰልጣኝ ሲሆኑ ልጃቸው አልፎ አልፎም ቢሆን ያጅባቸው ነበር፡፡ አባት የሚያሰለጥኑት ቡድን ጨዋታ ሲኖረው እና ሰውየው በግጥሚያ መካከል ለተጨዋቾቻቸው መልዕክት ሲኖራቸው ወጣቱ ሞወሪንሆ በሜዳው ጠርዝ እየሮጠ መመሪያቸውን ያደርስላቸው ነበር፡፡ ልጁ በፖርቹጋል ሁለተኛ ዲቪዚዮን በሚሳተፍ ክለብ በተከላካይነት ሚና የመጫወት ዕድል ቢያገኝም እዚህ ግባ የሚባል የተጨዋችነት ዘመን ሳያሳልፍ ወደ አሰልጣኝነቱ ሙያ ለመቀላቀል ወሰነ፡፡ ሊዝበን ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርቱን ተከታትሎ መምህር ሆነ፡፡
የሞውሪንሆ የመጀመሪያ ሥራ ከውልደታቸው አንስቶ አካላዊ እና አዕምሯዊ እክል ያለባቸውን ልጆች ማስተማር ነበር፡፡ ‹‹በጣም ፈታኝ ነበር›› ይላሉ ጆዜ፡፡ ‹‹እነዚያን ልጆች ለማገዝ በቴክኒክ ረገድ ዝግጁ አልነበርኩም፡፡ ነገር ግን ስኬታማ የመሆኔ ምክንያቱ አንድ ነበር፡፡ ከእነርሱ ጋር የፈጠርኩት ከውስጥ የሆነ ትስስር፡፡ ፍቅር፣ ቅርበት እና ስሜትን መጋራት ያገኘኋትን የተአምር ያህል የምትቆጠር፣ አነስተኛ ስኬት አምጥቶልኛል፡፡ አንድ ዕድሜ ልኩን ወደ ህንፃ አናት ለመውጣት ፈቃደኛ ያልነበረ ልጅ አስታውሳለሁ፡፡ ሌላው ደግሞ እጅግ ቀላል የሚባሉ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን በአንድነት ማከናወን የተሳነው ነበር፡፡ ልጆቹ የተለያየ ችግር የሳባቸው ነበሩ፡፡ ከሁሉም ጋር የነበረኝ የውስጥ ትስስር ግን በብዙዎቹ ላይ መልካም ለውጥ እንድናመጣ አግዞኛል፡፡

‹‹ከዚያ በኋላ ከ16 ዓመት በታች ታዳጊዎችን ማሰልጠን ጀመርኩ፡፡ አሁን ደግሞ የዓለም ምርጥ ተጨዋቾችን አሰለጥናለሁ፡፡ በሥራዬ ትልቁ ነገር በቴክኒክ ራሴን ማዘጋጀቱ ሳይሆን ከተጨዋቾቼ ጋር የምፈጥረው ከውስጥ የሆነ ቁርኝት ነው፡፡ በእርግጥ እውነት እና ነገሮችን በጥልቀት የምትመለከትበት አቅም ያስፈልግሃል፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ሁሉ ቁልፉ የምትፈጥረው ጠንካራ ግንኙነት ነው፡፡ ቁርኝትህ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከቡድኑ ጋርም ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም የሚያሸንፍልህ ቡድን ነው››
‹‹ቡድን›› የሚለው ቃል በጆዜ ቃለ ምልልሶች ውስጥ በብዛት ይደመጣል፡፡ አሰልጣኙ ባለተሰጥኦ ተጨዋቾችን ወደ ቡድን ተጨዋችነት የሚለውጡት እንዴት ነው? ዕድሜያቸው 21 ዓመት እንኳን ሳይሞላ ለከፍተኛ ደመወዝ ባለቤት የሚበቁትንስ ከዋክብት የሚያስተዳድሩት በምን መልኩ ይሆን? ‹‹ትክክል ነው›› ይላሉ ጆዜ ድምጻቸው ከፍ እያደረጉ፡፡ ‹‹ቀደም ባለው ጊዜ ተጨዋቾች ወደ እግርኳስ ዓለም ሲመጡ ሃሳባቸው ጫማቸውን ሲሰቅሉ ሀብታም መሆን ነበር፡፡ የአሁኖቹ ደግሞ ባለሁበት መሆን የሚፈልጉት ገና የመጀመሪያ ጨዋታቸውን እንኳን ሳያደርጉ ነው››

እግርኳስ እንደ ሌሎቹ የጥበብ ዘርፎ ሁሉ የራሱን ዝነኞች ይፈጥራል፡፡ ለፊልም ተዋናዮች ከሚሰጠው ትልቅ የእውቅና ሽልማት አካዳሚ አዋርድ ጋር የሚነፃፀረው ባሎንዶር በእግርኳስ ግለሰቦች የሚገዝፉበት ነው፡፡

ሞውሪንሆ ራሳቸው እንደሚመሰክሩት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ከአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ጋር የሚያስማማቸው ብዙ ነጥብ የላቸውም፡፡ ‹‹ነገር ግን ቬንገር ንድ ጥሩ ነገር ተናግሯል፡፡ በባሎንዶር አስፈላጊነት አይስማማም፡፡ ትክክል ነው፡፡ አሁን በእግር ኳስ የሰዎች ትኩረት ከቡድን ይልቅ ግለሰቦች ላይ እየሆነ ነው፡፡ ሁልጊዜም ትኩረታችን የአንድ ተጨዋች ብቃት እና ስታስቲስቲክ ላይ ሆኗል፡፡ የትኛው ተጫዋች ብዙ እንደሚሮጥ መነጋገር እናበዛለን፡፡ በአንድ ጨዋታ አንተ 11 ኪሎ ሜትር እኔ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ከሮጥን አንተ ከእኔ የተሻልክ ነህ ማለት ነው? ላይሆን ይችላል፡፡ ምናልባት ከ11ዱ ኪሎ ሜትር ይልቅ ዘጠኙ ይበልጥ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል›› ብለው ይስቃሉ አሰልጣኙ፡፡
‹‹ለእኔ እግርኳስ በጋራ የምትወዳደርበት ነው፡፡ ለግለሰብ ቦታ አለን በተለይ ቡድናችንን የሚያበረታ ከሆነ፡፡ ነገር ግን ግለሰቡ ለቡድኑ መስራት አለበት እንጂ ቡድኑ ለእርሱ ሊለፋለት አይገባም፡፡ ትልቅ ተጨዋች ሲመጣ ቡድኑ ቀደም ብሎም አለ፡፡ ኮሎምቦስ አሜሪካንን እንዳገኘው አንድ ተጨዋች ቡድኑን ሊያገኝ አይችልም፡፡ እንደ አሰልጣኝ ለተጨዋቾችህ ይህንን ሁልጊዜ ማስታወስ ይኖርብናል፡፡ በንግግር እና በቃላት ሳይሆን ተጨዋቹ ሃሳብህን እንዲገነዘብ ጥሩ ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለተጨዋች መስጠት የማትችለው ተፈጥሯዊ ተሰጥኦን ነው፡፡ ቡድኑ ከተጨዋቹ ምን ይፈልጋል? ተጫዋቹ ብልህ እና እንዲሻሻል ከአንተ የሚደረግለትን እገዛ የሚፈልግ አይነት ነው? ቡድኑ ከእርሱ እንደሚተልቅ ሲነገረው የማይሰማ ራስ ወዳድ እና ረባሽ ነው? እነዚህ ሁሉ አይነት ባህሪያት ያላቸው ተጨዋቾች ገጥመውኛል፡፡ የትም ቦታ እንከን የለሽ የሚባል ስብስብ አይገኝም፡፡ ከተጫዋች እጅግ ወሳኙ ነገሩ ምንድነው? ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ ተሰጥኦ ነው፡፡

‹‹ለምሳሌ አንድ ተጨዋች ነበረኝ፡፡ ስሙን አልነግራችሁም፡፡ ለዋናው ቡድኔ እንዲጫወት ዕድል ሰጠሁት፡፡ ለሁለት ሳምንታት እንደተጫወተ አባቱ ምስሪያ ቤታቸውን ለቀቁ፡፡ እናቱም ሥራቸውን ተዉ፡፡ አብረውት መኖር ብቻ ሳይሆን የእርሱን ህይወት መኖር ጀመሩ፡፡ በተጫዋቹ ዙሪያ ትልልቅ ውሳኔዎችን የሚያሳልፉት እነርሱ ሆኑ፡፡ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡››

ተጫዋቹ ለመጨረሻ ምን ሆነ? ጆዜ ምላሽ ለመስጠት ቃላት አልተጠቀሙም፡፡ ትከሻቸውን ሰበቁ፡፡ የልጁ የእግርኳስ ህይወት የኋሊት ተጓዙ፡፡
‹‹ይህ ልሰጣችሁ ከምችላቸው 1 ሺ ምሳሌዎች አንድ ብቻ ነው፡፡ ተጫዋቾች ጥሩ ወላጆች ካሏቸው ዕድለኞች ናቸው፡፡ መልካም ወኪል ካገኙም እንዲሁ ዕድለኞች ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ትምህርትም ያስፈልጋቸዋል፡፡ አንድ ሌላ ተጫዋቼ ትዝ ይለኛል፡፡ አንድ ቀን አዲስ መኪና እያሽከረከረ መጣ፡፡ ደግሞ ሌላ? ለምን? ለመሆኑ መኖሪያ ቤት አለህ? ብዬ ጠየቅኩት፡፡ አልነበረውም፡፡ ይልቁን እንዲህ ሲል መለሰልኝ፡፡ ይህንን መኪና እኔ አልገዛሁትም፡፡ አባቴ በነፃ የሊዝ ዕድል ወሰደልኝ፡፡ እኔም ሰነዱ ላይ ፈረምኩ፡፡ ይሄን ጊዜ ሊሊ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ብዬ ደግሜ ጠየቅኩት፡፡ እርሱም በነፃ መውሰድ ማለት ነው አለኝ፡፡ አይደለም፡፡ እስኪ ተቀመጥ፡፡ ብዬ ስለ ሊዝ አስረዳሁት፡፡ ምንም አላወቀም ነበር፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው አላብራራለትም ነበር››

‹‹እኔ ብዙ ሊባል የሚችል ገንዘብ በእጄ የገባው በ2003 በፖርቶ ለሁለተኛ ጊዜ ኮንትራት ስፈርም ነው፡፡ በወቅቱ ዕድሜዬ 30ዎቹ ውስጥ የነበረ ሲሆን ባለትዳርም ነበርኩ፡፡ ወጣቶቹ ተጫዋቾች ይህንን ሁሉ ገንዘብ ሊያገኙ ዕድሜያቸው 16፣ 17፣ 19 ወይም 20 ዓመት ቢሆን ነው፡፡ በገንዘቡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም፡፡››
‹‹በቼልሲ ተጨዋቾችን በተለያዩ ሁኔታዎች የሚያግዝ ዲፓርትመንት አለን፡፡ ስለገንዘብ ሁኔታ የሚያስረዷቸው ሰዎች በባንክ አሉ፡፡ ቤት መግዛት ብትፈልግ ውል የምትፈፅመው ከትክክለኛው ሰው ጋር መሆኑን የሚያረጋግጡልህ ይኖራሉ፡፡ ወደ ክለባችን የሚመጡ ወጣቶች መኪና መግዛት አይኖርባቸውም፡፡ ስፖንሰራችን መኪና አምራቹ ኦዲ መኪና ይሰጣቸዋል፡፡ ተጫዋቾች እንዲህ አይነት እንክብካቤ ያሻቸዋል፡፡ ምክንያቱም ያለንበት ዓለም ውስብስብ ነው፡፡

ስለዚህ ጆዜ ራሳቸውን እንደ አባት ኃላፊነት ሲወስዱ እያገኙት ይሆን? ‹‹ይህ ኃላፊነት ነው›› ሲሉ ይመልሳሉ፡፡
ሞውሪንሆ እና የትዳር አጋራቸው ማቲልደ በፍቅር የተቆራኙት ገና ለጋ ወጣቶች ሆነው ሲሆን በፖርቹጋሏ ሴቱባል መኖሪያ ቤታቸውን የሚለየው አንድ ጎዳና ብቻ ነበር፡፡ ለትዳር ለ26 ዓመታት የቆዩት ጥንዶች ሁለቱን የአብራካቸው ክፋዮ ማቱልደ እና ጆዜ ሲሉ ሰይመዋቸዋል፡፡
FOOTBALL/ITALIAN CHAMP/ATALANTA BERGAMASCA v INTER MILANO
ስኬታማው ጆዜ የአሰልጣኝነት ህይወታቸው የጀመረው በ2000 የፖርቹጋሉን ቤንፊካ ሲረከቡ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ከቦቢ ሮብሰን ጋር መጀመሪያ በተርጓሚነት በኋላም በአሰልጣኝ ረዳትነት በስፖርቲንግ ሊዝበን፣ ፖርቶ እና ባርሴሎና ሰርተዋል፡፡ በቤንፊካ ከተሾሙ በኋላ ከሶስት ወራት በላይ አልቆዩም፡፡ ከክለቡ ፕሬዝዳት ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ስራቸውን ለቀቁ፡፡ ቀጣዩ ስራቸው በኡናዮ ደ ሌይሪያ ነበር፡፡ ከዚያ ወደ ፖርቶ ሲመጡ የሀገሪቱን ሊግ ሁለት ጊዜ፣ የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ዋንጫን እና የቻምፒዮንስ ሊግን አሸነፉ፡፡ ይሄ ስኬታቸው ወደ እንግሊዝ መራቸው፡፡ በቼልሲ በ2004/05 እና 2005/06 በተከታታይ ፕሪሚየር ሊጉን ድል ነሱ፡፡ የኤፍኤ ካፕ እና የሊግ ካፕን ሁለት ጊዜ አሸነፉ፡፡ የኢንተር ሚላን አሰልጣኝ ሆነውም ሴሪአውን ሁለት ጊዜ በተከታታይ ድል አድርገዋል፡፡ በ2010 ወደ ሪያል ማድሪድ አምርተው ኮፓዴል ሬይ እና ላሊጋ በተከታታይ ዓመታት አሸንፈዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ በ2013 በድጋሚ ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ ተመልሰዋል፡፡

ሞውሪንሆ የቅርብ ጓደኛዬ ብለው የሚጠቅሱት ሩይ ፋሪያን ነው፡፡ እኚህ ሰው ከጆዜ ጋር ከቤንፊካ የመጀመሪያ ሥራቸው አንስተው በየክለቡ አብረዋቸው ሲዟዟሩ የቆዩ ናቸው፡፡ ‹‹ሩይ አንድ የሚናገሩት ነገር አለች›› ይላሉ ሞውሪንሆ እየሳቁ፡፡ ‹‹በዚህች ዓለም ምርጥ ህይወት ማለት አሸናፊ አሰልጣኝ የሚኖረው ነው ይላል፡፡ ትክክል ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ሀገር ተከታታይ ጨዋታዎች እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ በአንዱ ጨዋታ ውጤት ስሜት ውስጥ መቆየትን አትችልም፡፡ 5-3 ተሸንፈን በቀጣዩ ቀን የልምምድ ፕሮግራም አለ፡፡ ከሁለት ወይም ሶስት ቀናት በፆፄላ ደግሞ ሌላ ጨዋታ ይኖረናል፡፡ ከዚህ ስሜቴን ውጬ ሽንፈት እና ድልን መቀበል አለብኝ፡፡

‹‹አሰልጣኝ እጅግ ወሳኙ ሰው አይደለም፡፡ በክለብ ውስጥ እጅግ አስፈላጊው አካል ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ባለቤቶቹ ቀጥለው ይቀመጣሉ፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ተጨዋቾች አሉ፡፡ እኔ የምመጣው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም ሰው ትኩረቱን ያደረገው አሰልጣኝ ላይ ነው፡፡ ተጨዋቾችም አንተን ይመለከታሉ፣ ይታዘቡሃል፡፡ ለነገሮች ምላሽ የምትሰጥበትን መንገድ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ እርጋታህንም እንደዚሁ ይመዝናሉ፡፡ በክለብ የሚሰሩ ሰዎችም እንደዚህ በጥንቃቄ ይከታተሉሃል፡፡ ምላሻቸውም አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ይሆናል፡፡ ደጋፊዎችም አሰልጣኞችን ይከታተላሉ፡፡ ከሽንፈት ማግስት ለቀጣዩ ጨዋታ ዝግጁ መሆንህን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡ እንዲህ አይነቱ ሁኔታ የሚቆጣጠር አቅም አለኝ፡፡ ሰዎች በአሉታዊ እና አዎንታዊ አስተያየታቸውን በሚዛናዊ መልኩ ማስኬድ እችላለሁ፡፡ በቤቴ ጥሩ አይደለሁም፡፡ እነርሱ በሚገባ ያውቁኛል፡፡ ስሜቴን ልደብቅ አልችልም፡፡ ጠንቅቀው ያውቁኛል፡፡››

ጆዜ ከእግርኳስ ወጣ ብሎ በቅርቡ የገጠማቸው ለየት ያለ ነገር ካለ ተብለው ሲጠየቁ በworld food progeramm Ambasador Agminst Hunger ተልዕኮ የጎበኟትን አይቮሪኮስት ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ከባለቤቴ እና ልጆቼ ጋር ሆኜ የተመለከትኩት ሁሉ ልዩ ተሞክሮ ሆኖልኛል፡፡ ድህነትን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ከእውነታው ጋር ቀጥተኛ ፍጥጫ ውስጥ መግባት ለየት ይላል፡፡ በአዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጎኑ ይህንን ከመሰለው እውነታ ጋር መጋፈጥ እና ሚና መውሰድ ልዩ የኩራት ስሜት ይፈጥራል፡፡››
አሰልጣኙ እና ባለቤታቸው በሀገራቸው ፖርቹጋልም የካቶሊክን የምግብ ፕሮግራ በሴቱባል ያግዛሉ፡፡ ‹‹ሆኖም ከቤተሰባችን መርህ አለን፡፡ የምናደርገውን ሁሉ የምናደርገው ሰዎች ስለ እኛ ብዙ እንዲያውቁ አይደለም፡፡ ይህንን የምንሰራው ማድረግ ስለምንችል ነው፡፡ ወንድ እና ሴት ልጆቻችን እኛ ወላጆቻቸው ምን አይነት መልካም አጋጣሚዎች የተፈጠሩልን ሰዎች እንደሆንን እንዲያውቁ እንሻለን ሌሎች ብዙ እገዛ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዳሉ እንዲገነዘቡም እንፈልጋለን››

ሞውሪንሆ ሃይማኖተኛ እንደሆኑ ያስባሉ፡፡ ‹‹እምነት አለኝ፡፡ ሁልጊዜም እፀልያለሁ፡፡ ሁልጊዜም ከፈጣሪ ጋር እነጋገራለሁ፡፡ በየዕለቱ ወደ ቤተክርስቲያን አንሄድም፡፡ በየሳምንቱም ቢሆን አይሳካልኝም፡፡ ሆኖም መሄድ እንዳለብኝ ሲሰማኝ እሄዳለሁ፡፡ ፖርቹጋል ውስጥ ከሆነ ግን በየዕለቱ እሄዳለሁ፡፡››
ጆዜ የሚፀልዩት ለማን ይሆን? ‹‹ለቤተሰቤ፣ ለልጆቼ፣ ለባለቤቴ፣ ለወላጆቼ፣ ስለደስተኛነቴ እና መልካም የቤተሰብ ህይወት እፀልያለሁ፡፡ እውነቴን ብነግራችሁ ግን ከፈጣሪዬ ጋር ለመነጋገር ወደ ቤተክርስቲያን ስሄድ ርዕሴ እግርኳስ አይሆንም፡፡ በፍፁም!››

አሰልጣኙ ራሳቸውን መልካም ሰው አድርገው ያስባሉ? ‹‹ይመስለኛል፡፡ እንደዚያ ለመሆን እሞክራለሁ፡፡ ከቤተሰቦቼም ጋርም ሆነ ከጓደኞቼ ጋር ችግር የለብኝም፡፡ ለቤተሰቡ መልካም ሰው ነኝ፡፡ ጥሩ ጓደኛም ነኝ፡፡ የማላውቃቸውን ሰዎች እንኳን ለማገዝ እነሳለሁ፡፡ ስህተቶች እሰራለሁ? አዎን፡፡ የሥራ ባህሪዬ የፉክክር ብቻ አይደለም፡፡ ስሜታዊነትንም ይቸምራል፡፡ በዚህ ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ልትደርስባቸው ትችላለህ፡፡ ሆኖም ፕሮፌሽናል ህይወትህ ከአንተነትህ የሚገለፀው ከፊሉን ነው፡፡ የግለሰብ ስብዕና ከዚያም የላቀ ነው፡፡››

ሰውዬው የፕሮፌሽናል ህይወታቸውን ከቤተሰባቸው አኗኗር ሊለዩት ብዙ ይጥራሉ፡፡ ከባለቤታቸው ጋር ስለ እግርኳስ አያወሩም፡፡ ‹‹የእርሷ ዓለም ሌላ ነው፡፡ በምወደው ክለብ እና በምወደው ቦታ እንድቆይ እንዲሁም ከሚመቹኝ ሰዎች ጋር እንድሰራ ትመክረኛለች፡፡ምክንያቱም በዚህ መልኩ የቤተሰባችን ህይወት መልካም ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ ቀላል አይሆንም፡፡ የቤተሰቤን ህይወት ከእግር ኳስ ለመነጠል ብሞክርም የማይሳካበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ በወሳኝ ጨዋታ ሽንፈት ከገጠመኝ የፊቴን ገፅታ ቀላል አድርጌ ወደ ቤቴ ለመሄድ እሞክራለሁ፡፡ ነገ ሌላ ቀን ነው፡፡ በቃ ይህ አንድ የእግርኳስ ጨዋታ ብቻ ነው እያልኩ ለራሴ እናገራለሁ፡፡ ነገ ሌላ ቀን ነው፡፡ በቃ ይህ አንድ የእግርኳስ ጨዋታ ብቻ ነው እያልኩ ለራሴ እናገራለሁ፡፡ ሆኖም ቤቴ ስገባ እነርሱ ብሰው አኩርፈው አገኛቸዋለሁ›› ብለው ጆዜ ይስቃሉ፡፡ ‹‹ስለ እኔ እነርሱ ያዝናሉ››

በእንግሊዝ የእግርኳስ ትልልቅ ክለቦች ባሉበት ከተማ የሀብታሞች መኖሪያ ብዙዎቹ የክለቡ ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች መኖሪያ ቤቶች አይጠፉም፡፡ በቼሻየር ዳርቻ በምትገኘው አልደርሌይ ኤጅ መረቡን የጣለ አሰልጣኙን ጨምሮ ማንቸስተር ዩናይትድ የቡድን አባላት ብዙዎቹን ይይዛል፡፡ በኮብሀም አካባቢም ያንዣበበ ሁሉ በርከት ያሉ የቼልሲ ተጨዋቾችን ያገኛል፡፡ ሞውሪንሆ ግን እዚህ አታገኟቸውም፡፡ ከቤተሰባቸው ጋር በቤልራቪያ አካባቢ ይኖራሉ፡፡ ቤተሰባቸው ቦታውን እንደሚወደው ይናገራሉ፡፡ ‹‹እኔም እወደዋለሁ›› ከማድሪድ ወይም ሚላን በተለየ ለንደን ትመቻቸዋለች፡፡ ‹‹ጤናማ ህይወት›› መኖር የሚችሉባት ከተማ ነች፡፡

ሞውሪንሆ በመኖሪያቸው አካባቢ ባለ ጎዳና የእግር ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ‹‹በአምስት ደቂቃዎች ውስጥ›› የቼልሲ ደጋፊ፣ የቶተንሃም ደጋፊ፣ የአርሰናል ደጋፊ ያገኛሉ፡፡ ‹‹ሌላው ቀርቶ የሊቨርፑል ወይም የዩናይትድ ደጋፊዎችም አገኛለሁ፡፡ ይህ ያስደስተኛል፡፡ በሰራሁባቸው ሌሎች ከተሞች በእግርህ የምትጓዘው በክለብህ ደጋፊዎች ታጅበህ ነው፡፡ በሚላን 50 በመቶ የኢንተር 50 በመቶ የኤሲ ሚላን ደጋፊዎች ይኖራሉ፡፡ ምናልባት ማድሪድ 70 በመቶ ሪያል 30 በመቶ አትሌቲኮ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በፖርቶ 100 በመቶ ናቸው፡፡ ማንም ሰው ወደ እኔ ቢመጣ ላደምጠው ዝግጁ ነኝ፡፡ ስለ እግር ኳስ ሊያስተምረኝ ቢፈልግ ግን አልሰማውም፡፡››

‹‹የለንደን ነዋሪዎች ሰውን በመረበሽ እና ባለመረበሽ መካከል ያለውን ልዩነት ይገነዘባሉ፡፡ ሰዎች ነፃነት እና ክብር እንደሚፈልጉ ያውቃሉ፡፡ እዚህ እኔ ከተረበሽኩ በእርግጠኝነት ሲያገኙኝ እንድፈርምላቸው እና አብረውኝ ፎቶግራፍ መነሳት ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ተመግቤ እስክጨርስ ይጠብቁኛል፡፡ መደብሮች ውስጥ ሊያገኙኝም ይጠብቁኛል እንጂ አይረብሹኝም፡፡ በመንገድ ስራመድም እንደዚያው ነው፡፡ በእንግሊዝ በቡድንህ ውጤት የተበሳጨ ደጋፊ ከቤተሰብህ ጋር እየተራመድክ መጥቶ አይጨቃጨቅህም፡፡ ይህ አይታሰብም፡፡ በማድሪድ እና ሚላን ግን ሁልጊዜም እንዲህ አይነት ነገሮች ይገጥሙሃል፡፡››

‹‹ሁሉም ደጋፊ አሰልጣኝም ነው›› ይላሉ ጆዜ በሁኔታው ደስተኛ አለመሆናቸውን በሚያሳጣ የፊት ገፅታ፡፡ ሰዎች እግር ኳስን በተጋነነ መልኩ ይወስዱታል፡፡ ያለጥርጥር እኔ እግር ኳስን እወድዳለሁ፡፡ ሆኖም እኛ ፕሮፌሽናሎቹ እግርኳሱን ሁሉ ነገራችን ካረግነው ችግር ውስጥ ነን ማለት ነው፡፡ ለደጋፊውም ተመሳሳይ ነው፡፡ በፖርቹጋል አንድ ሰው በህይወቱ እናቱን እና የሚደግፈውን ክለብ ሊቀይር እንደማይችል ሲናገር ታደምጣላችሁ፡፡ የእግርኳስን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባህላዊ ጉልበት እገነዘባለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ የእግር ኳስ ተጨዋች ከዓለም 100 ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ተመዝግ በፎርብስ መፅሔት እንዴት እውቅና እንደሚሰጠው አይገባኝም፡፡ ለዚያውም አንድ ሳይሆን ሁለት ተጨዋቾች ተመሳሳይ ዕድል አግኝተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ክርስቲያኖ ሮናልዶ በዝርዝሩ 360ኛ ደረጃ ላይ ተገኝቷል፡፡ ሊዮኔል ሜሲም 45ኛ ሆኗል፡፡

‹‹ይህ ቀልድ ነው፡፡ እኛ የማንንም ህይወት ከአደጋ አናድንም፡፡ ሰዎች ቡድናቸው ሲሸነፍ ከአምስተኛ ፎቅ ራሳቸው ሊወረውሩ እንደሚችሉ አውቃለሁ፡፡ እንግዲህ የሚያደርገው ሰውዬ ችግር አለበት፡፡ የእግርኳስ ተጨዋች ወይም አሰልጣኝን ከሳይንቲስት ወይም ዶክተር ጋር እንዴት ልታነፃፅር ትችላለህ? አይነፃፀሩም፡፡››

ሞውሪንሆ በእንግሊዝ እግርኳስ የቅርብ ወዳጅ እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹አንዳንዶቻችን እንወደዳለን እንግባባለንም፡፡ ሆኖም ጥብቅ ወዳጆ አይደለንም፡፡ ሆኖም ሞውሪንሆ ያለ ገደብ የሚያደንቋቸው አንድ ሰው አሉ- ሰርአ ሌክስ ፈርጉሰን፡፡ ሁለቱ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት በ2007 ፖርቶ ማንቸስተር ዩናይትድን ከቻምፒዮንስ ሊግ ሲያሰናብተው ነበር፡፡ ‹‹የዚያን ታላቅ ሰው ሁለት ገጽታ ያስተዋልኩት ያን ጊዜ ነበር›› ይላሉ ሞውሪንሆ፡፡ ‹‹አንደኛው መልካቸው ተፋላሚ ነው፡፡ ሰውዬው ለማሸነፍ ሁሉንም አይነት መንገዶች የሞከሩ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሁልጊዜም በመርህ የሚጓዙ ነበሩ፡፡ ተጋጣሚን ያከብራሉ፡፡ እነዚህ ሁለት መልኮች ለእኔ እጅግ አስፈላጊዎች ነበሩ፡፡
‹‹በእኛ ባህል፣ በፖርቹጋል እና ላቲን ባህል ሁለት መልክ የለንም፡፡ በእግርኳስ አላማችን ማሸነፍ ብቻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ሌላ መልክ አይኖረንም፡፡ በቻምፒዮንስ ሊግ ዩናይትድን ስናሸንፍ በሰር አሌክስ ፊት ላይ የተመለከትኩት ማራኪ ገፅታ ለእኔ ቢሆን ብዬ የተመኘሁት ነበር፡፡ ይህንን ለማድረግ እሞክራሁ፡፡››

የሞውሪንሆ ጥረት እና ፈተና ሁልጊዜም በሌሎች ዘንድ ቦታ የሚያገኝ አይመስልም፡፡ ብዙዎች ጆዜን ‹‹ቀጣፊው›› ይሏቸዋል፡፡ ‹‹እኔ ራሴን እንዲዚያ ነኝ ብዬ አላምንም›› ይላሉ አሰልጣኙ፡፡ ጆዜ እርሳቸውን በዚህ መልኩ የሚጠቅሱ ፅሑፎችን አንብበው ያውቃሉ? ‹‹አዎን! እንደዚያ እንደሚሉኝ አውቃለሁ፡፡ በእርግ አልፎ አልፎ የምሰጣቸው አስተያየቶች እንደዚያ ሊያስመስሉኝ እንደሚችሉ እረዳለሁ፡፡ ከዚህ ያለፈ ነገር የለም፡፡››

ሁሉም አሰልጣኝ የዳኝነት ውሳኔዎች ላይ ቅሬታውን ያሰማል፡፡ ፍፁም ቅጣት ምት ነበር፤ በፍም አልነበረም፤ ዕድለኞች አልነበርንም የመሳሰሉ ንግግሮች በተደጋጋሚ ይደመጣሉ፡፡ ሞውሪንሆ ግን የቅሬታ አቀራረብን በጥበራ የማድረግን ደረጃ አሳድገዋል፡፡ ዳኞች ብቻ ሳይሆኑ የቀረው ዓለም ሁሉ የሞውሪንሆ ተቃራ መሆኑን ማሳየት ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም የቡድናቸውን ስነ ልቦና ከፍ ሲያደርጉ እግረ መንገዳቸውንም ስኬታማ ሳይሆኑ ሊረዷቸው የሚችሉ ሰበቦችንም ያስቀምጣሉ፡፡

ሞውሪንሆ ሁልጊዜም ይበልጥ ሃያል ሆነው በሚቀርቡባቸው የጋዜጣዊ መግለጫ መድረኮች ብንነግራቸው ለተለያዩ ወገኖች ያላቸውን ዝቅ ያለ ግምት ለማንፀባረቅ ይሞክራሉ፡፡ ተጋጣሚዎቻቸውን፣ የእግርኳስ ባለስልጣናትን፣ ሪፖርተሮችን ሁሉ ያጣጥላሉ፡፡ አድናቆታቸው እንኳን በራሳቸው የተሟሉ አይደሉም፡፡
ይህ የፈርጉሰን ባህርይ ነው፡፡ ብዙ የፃፈ ጋዜጠኛ አለ፡፡ ‹‹ጆዜ ለሰዎች መልካም ከሆነ ሰዎቹ ስጋቶቹ አይደሉም ማለት ነው››

ሞውሪንሆን ቃለ ምልልስ ሲያደርግ የነበረው ሰው የዚህን ጋዜጠኛ አስተያየት ሲያስታውሳቸው ጆዜ ክፉኛ መከፋታቸው ያስታውቅባቸው ነበር፡፡ ‹‹በፍፁም! ሰዎች አድናቆት የተገባቸው ሆነው ሲገኙ አደንቃቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌ ከሽንፈት በኋላ ድንቅ ዳኛ እያልኩ መናገር እወዳለሁ፡፡››

ጆዜን ሰዎች ሁልጊዜም በተሳሳተ መንገድ ይረዷቸው ይሆን? በቃለ ምልልስ አብሯቸው የቆየው ጋዜጠኛ አሰልጣኙን በዓለም ላይ እውነተኛ ስሜታቸውን ከሚያስነብቡ ኮሜዲያኖች አንዱ ያደርጋቸዋል፡፡ ለዚህም ሃሳቡን እንዲህ ይገልፃል፡፡ ‹‹ሞውሪንሆ በዝምታ ያስተውለኛል፡፡ ከዚያም በፊቱ ገፅታ በዝግታ የደመቀ ፈገግታ ያስነብባል፡፡››

The post Sport: ሰውየው!! – የጆዜ ሞውሪንሆ ልዩ ገፅታ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles