Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“የችግሩ መሰረታዊ ምንጭና መፍትሔው ፓለቲካዊ ነው’!! አቶ ኤርምያስ ለገሰ

$
0
0

daniel ermiasሰሞኑን በኢትዬጲያውያን ላይ የመከራ ዶፍ እየዘነበ ነው። ይህ የድቅድቅ ጨለማ ናዳ ባስከተለው አደጋ የተፈጠረው ቁጭትና መብከንከን ከቃላት በላይ ሆኗል። በኢትዬጲያውያን ዘንድ ከዚህ ውጭ የመተከዣ አጀንዳ ያለ አይመስልም። እንባ እንደ ጐርፍ እየወረደ ነው። የእናቶቻችን ደረት በእሳት የተለበለበ እስኪመስል ድረስ እየተደለቀ ነው። ወጣቶቻችን ከአረመኔዎች ጋር ግብግብ እየገጠሙ ነው። በመንገድ፣ በትራንስፓርት፣ በምግብ ቤት፣ በስራና በተለያየ አጋጣሚ የምናገኛቸው የባእድ አገር ሰዎች ሳይቀር የሀዘናችን ተካፋዬች መሆናቸውን እየነገሩን ነው። ነግረውን ብቻ አያቆሙም ። አያይዘው ፣
“ችግሩ ለምን እናንተ ኢትዬጲያውያን ላይ ባሰ?፣ ሀገራችሁን ትታችሁ ስደትን ለምን እንደ አማራጭ ወሰዳችሁ? ለምን እንደ ጨው ዘር ትበተናላችሁ?፣ ሰብሳቢ የላችሁም ወይ? ” የሚል ጥያቄ ያስከትላሉ። የሚገርመው ነገር እንደዚ አይነት ጥያቄ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን እንደተቋምም እየቀረበ ነው። ለዚህ አባባል አብነት የሚሆነኝ ባለፈው አርብ አርቲስት ታማኝ በየነ ያጫወተኝ ወግ ነው። ከእሱ ጋር በፍሎሪዳ ግዛት በነበረን ቆይታ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን / ዩኤን ኤች ሲአር / ጋር እሱና የስራ ባልደረቦቹ በነበራቸው ስብሰባ ያነሱለትን ጥያቄ አንስቶ ነበር ውይይታችን የተጀመረው። ዩኤን ኤች ሲአሮች እንዲህ በማለት ነበር የጠየቁት፣
” እናንተ ኢትዬጲያውያን ሀገራችሁን ጥላችሁ በመሰደድ ተወዳዳሪ የሌላችሁ ሆናችኃል። ሌላው ቀርቶ በኢኮኖሚ አቅሟ ከእናንተ በምንም የማትሻለዋና የተንኮታኮተች ( የደቀቀች) ሀገር ወደ ሆነችው የመን እንዴት ትሰደዳላችሁ? ”
ይህ መሰረታዊ ጥያቄ ነው።እያንዳንዱ ኢትዬጲያዊ ከጊዜያዊ ዋይ ዋይታ ተቆጥቦ ከእኛ የማትሻለውን “የመን” አማትረን የምንመለከትበት ባይነኩላር ለምን እንዳስገጠምን መነጋገር ይኖርብናል። ከፊታችን እየመጣብን ያለው አደጋ ክብደትና አስፈሪነት በግልጵ አውጥተነው ችግሩን መነጋገር ያስፈልጋል።ይህን ማድረግ ካልቻልን ከራሳችን በላይ የምናስቀድማት ” ኢትዬጲያ ሀገራችን” የመኖርና ያለመኖር የህልውና አደጋ ይጋረጥባታል። ርግጡን እንነጋገር ከተባለ አሸዋ ላይ እንደተገነባ ቤት እየፈረስን ነው። የኢትዬጲያ ህዝቦች ላይ የተጠመደ ፈንጂ ለመፈንዳት ጊዜውን እየጠበቀ መሆኑ እየታየ ነው።
ቢያድለን ኖሮ ይህን አጀንዳ መክፈት የነበረበት መንግስት ነበር። ለጵድቅ ሳይሆን ከመንግስት ዋነኛ ሀላፊነቶች አንዱ ዜጐቹን ከውጭ ጥቃት የመከላከልና የህዝቡን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ የሚጣልበት በመሆኑ ። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የመንግስትን ትርጉም እንደሚከተለው ገልፀውታል፣
“መንግስት ማለት የአንድን ህዝብ መሰረታዊ አቋሞች ፣ አንድነትና ነጳነት ከውጭ ጠላት የሚከላከል፣ የሕዝቡን ደህንነት ፣ እድገትና መሻሻል የሚመራ ፣ ሕዝቡ ከውስጥ እርስ በእርሱ ያለውን ግንኙነት ፣ መብትና ግዴታ በሕግና በስርአት እየወሰነ የስልጣን ባለአደራ ሆኖ የሚያስተዳድር ድርጅት ነው” በማለት ። ” መንግስታችን!” ፕሮፌሰሩ ባስቀመጡት ሁሉም መስፈርት በዜሮ ተባዝቷል። ይህም የውርደታችን ምንጭ ሆኗል። የባእዳን ማላገጫና አፍ መፍቻ ሆነናል።
ትላንት የውጭ ዜጐችን በስብሰባ፣ በትምህርት… ወዘተ ባገኘን ቁጥር ” ሉሲን ታውቃታለህ?፣ አስራ ሶስት ወር ሙሉ የፀሀይ ብርሀን ፀጋ እንዳለን ታውቃለህ?፣ ከአፍሪካ ሀገሮች በቀኝ ግዛት ያልተያዝነው እኛ እንደሆንን ይገባሀል? ” በማለት ደረታችንን ነፍተን እንናገር ነበር። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ይህን ማስታወሻ ስጵፍ አንድ ሁልጊዜም የማልረሳው ታሪክ አስታወሰኝ። ታሪኩ እንዲህ ነበር፣
በ1993 አ•ም• በአዲሳአባ ምክርቤት አዳራሽ በኢህአዴግ / ህውሀት የውጭ ጉዳይ ፓሊሲ ላይ ውይይት እያደረግን ነበር። የእለቱ ውይይት በፓሊሲው መግቢያ ላይ ባለው ” ብሔራዊ ውርደት” በሚለው ርእስ ላይ ነበር። በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት እጁን ያነሳው በወቅቱ የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ፕሬዝዳንት የነበረው ዶክተር ዘሪሁን ነበር። በአንድ የውጭ ኮንፍረንስ ላይ ጥናታዊ ጵሁፍ ሊያቀርብ ያጋጠመውን ነበር የነገረን። ዶክተር ዘሪሁን እንደ መንደርደሪያ ” ሉሲ፣ አስራ ሶስት ወር፣ በኮለኒ ያልተያዘች…ወዘተ” እያለ ሲደሰኩር የአንድ አፍሪካዊ እጅ ይቀሰራል። አፍሪካዊው ፍቃድ ሳይጠይቅ ” ዶክተር ለምን ጨምረህ መዝገበ ቃላት “ቸነፈር” የሚለውን ሲያብራራ ኢትዬጲያን እንደ ምሳሌ ማንሳቱን አትነግረንም?፣ …ለምን ሀገራችሁ የሟሸሸ መንግስታት በመሆኗ እንደ ሀገር መቀጠል እንዳቃታችሁ አትነግረንም?፣… ለምን በዘርና በጐሳ ተከፋፍላችሁ እንደምትኖሩ አትነግረንም?…ለምን ህዳጣን ብዙሀኑን እየገዙ መሆኑን አትነግረንም… ወዘተ ” በማለት በጥያቄ ያፋጥጠዋል። ኬሚስቱ ዶክተር ዘሪሁን በወቅቱ የሚመልሰው መልስ አልነበረውም። ጥያቄው አናሊቲካል ወይም ባዬ-ኬምስትሪ አልነበረምና!!
ዛሬም ይህ ኢትዬጲያ መሬት ላይ ያለ ሀቅ አልተቀየረም። እየባሰበት ሄደ እንጂ!…
በሀገራችን ጥቂቶች የአውሮፓና የአረብ ቅምጥል የሚኖረውን ኑሮ እየኖሩ፣ ብዙሀን በችጋር እየተገረፋ ነው።… በሀገራችን ጥቂቶች ልጆቻቸውን በአሜሪካን ሀገር በሚገኙ እጅግ ውድ ዩንቨርስቲዎች በዶላር እያስተማሩ ( የአራት ጀነራል ልጆች በጆርጅ ታወን ዩንቨርስቲ ያስተምራሉ)፣ ብዙሀን ልጁን የሚያበላው አጥቶ ከትምህርት ቤት ያስቀራል።…ጥቂቶች ባል ሜጀር ጀነራል፣ ሚስት ኮረኔል፣ ልጅ ፓይለት የመሆን እድል ይመቻችለታል፣ ብዙሀኑ “ድንጋይ ማነጠፍ ” ለመስራት አሊያም ” አፍራሽ ግብረሀይል” በቀበሌ ለመቀጠር ቦታ የለንም ይባላል።…በሀገራችን ጥቂቶች የለውጥ ውቅያኖስ ገብተው የሀብት ጋራ እንዲቆናጠጡ ይደረጋል፣ ብዙሀኑ በአፍአዊ ለውጥና ከንቱ ተስፋ እንዲሞሉ ይደረጋል። …ጥቂቶች የህሊና እምብርት ሳይበጅላቸው የሀገር ሀብት ወደ ውጭ ያወጣሉ ( በዚህ አመት ከአፍሪካ ተሰርቆ ከወጣው ቢሊዬን ዶላር ውስጥ 28•5% ከኢትዬጲያ መሆኑን ልብ ይሏል)፣ ብዙሀን በአፍሪካ ጫካ የአውሬ ራት ይሆናሉ…በሰሀራ በረሀ እንደ ሎጥ ሚስት ደርቀው ይቀራሉ… በአረብ ሀገራት እንዳበደ ውሻ ይክለፈለፋሉ ( የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል እንደወረደ!)…ጐማ ተጠቅልሎባቸው በእሳት ይጋያሉ…እንደ ዶሮ አንገታቸው ተቀንጥሶ ይጣላሉ።
ወደድንም ጠላንም የዚህ ሁሉ አቢይ መንስኤ ፓለቲካዊ ነው። የፓለቲካው መበላሸት የፈጠረው ችግር! የውስጣዊ አድልዎ ፓሊሲ የፈጠረው ችግር !…እውነት እንነጋገር ከተባለ በአድሎዋዊው ፓሊሲ ምክንያት እኩል የመማር፣ የመስራት፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች የማግኘት እድል የለም። የፓለቲካው መበላሸት የህግ ልእልና እንዳይሰፍን አድርጓል። የህግ ልእልና ባለመስፈኑ ምክንያት ደግሞ ሀሳብን በነጳነት የመግለጵ፣ የመደራጀትና በሰላም ወጥቶ የመግባት መሰረታዊ መብት ዝግ ሆኗል። የህግ የበላይነት ባለመኖሩ ሁሉም የሀይማኖት ተቋማት በጣልቃ ገብነት እየታመሱ ይገኛሉ። በዚህም ሳይወሰን የእምነት ተቋማቱ በካድሬ ተጵእኖ በመውደቃቸው ምክንያት የእምነት ነጳነት ከስም የማያልፍ ሆኗል።
ከውስጣዊው የአድሎ ፓሊሲ ባልተናነሰ የውጭ ፓሊሲያችንም “መርህ አልባ” መሆን እና ” ጠላት ሳትፈጥር አትኑር! ” የሚለው የመለስ አስተምህሮ ለችግራችን መባባስ አስተዋጵኦ አበርክቷል። በሱማሊያ የተወሰደው የጣልቃ ገብነት እርምጃ የሳጥናኤል ጭንቅላት የተገጠመላቸው የሰው ዘር ባልሆኑት አይሲሶች ጥርስ እንዳስገባን የአደባባይ ሚስጥር ነው። በህዳር 21 ቀን 1999 አ•ም• ወደ ሱማሊያ ስንገባ አቶ መለስ ፣” ወቅታዊና ተጨባጭ የሉአላዊነት አደጋ ገጥሞናል። በኢትዬጲያ ላይ የጅሀድ ጦርነት ታውጇል ። ይህን ወቅታዊና ተጨባጭ አደጋ በአጭር ጊዜ ቀልብሰን ወደ ልማታችን እንመለሳለን” የሚል ነጋሪት በፓርላማ ጐስሞ ነበር። “ቀስ ብለን እናጢነው”፣ ” በኃላ ማጠፊያው እንዳያጥረን” ” የራሷ አሮባት የሌላውን ታማስላለች እንዳይሆንብን” እያሉ ተማጵእኖ ያሰሙትን አንጋፋ ፓለቲከኞች ( ዶክተር በየነ፣ ዶክተር መራራ፣ አቶ ቡልቻ…) ” የኢትዬጲያን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፈው የሰጡ ከሀዲዎች፣ የሻእቢያ ተላላኪዎች” የሚል መልእክት ቀርፀን አብጠልጥለናል። ሰፋፊ መድረኮች ከፍተን ከፍ ዝቅ አድርገናል። እውነታው ግን የሱማሊያ ችግር እንኳን በአጭር ጊዜ ሊፈታ የኢትዬጲያ ወታደሮች ሱማሊያን ለቀው ሳይወጡ አስርተ አመት ሊደፍኑ አንድ አመት ብቻ ቀርቶአል። ውጤቱም ወንድሞቻችን በሰው በላ የዲያብሎስ መልእክተኛ በሆኑ አይሲሶች አንገታቸው መቀላት ሆኗል። የራሳችን አሮ የሌላውን እያማሰልን ነው!!

The post “የችግሩ መሰረታዊ ምንጭና መፍትሔው ፓለቲካዊ ነው’!! አቶ ኤርምያስ ለገሰ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>