የሰማያዊ ፓርቲ የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተባባሪ የሆነው አቶ አዲሱ ጌታነህ በትናንትናው ዕለት በደህንነቶች ድብደባ እንደተፈፀመበት ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡ መንግስት አይ ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ የወሰደውን እርምጃ ለመቃወም በጠራው ሰልፍ የባህርዳር ከተማ አስተዳደርና ጸጥታ ኃላፊ አቶ አጃናው ‹‹በሰልፉ ጉዳይ መነጋገር አለብን›› ብለውት እንደነበር የገለጸው አቶ አዲሱ ‹‹ሰልፉ ላይ በግለሰብ ደረጃ እንጅ እንደ ፓርቲ ስለማንገኝ የምንነጋገረው ነገር የለም›› የሚል መልስ እንደሰጠ ገልጾአል፡፡
ከሰልፉ ቀደም ብሎ በጠዋት ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ሲያቀና ቢሮው በፖሊስ ተከቦ እንዳገኘው የገለጸው አቶ አዲሱ እሱና ሌሎች የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ሰልፉ ላይ በተሳተፉበት ወቅትም ደህንነቶች እየተከታተሉ ፎቶ ሲያነሷቸው እንደዋሉ ገልጾአል፡፡ ከሰልፉ መልስ ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ያመራው አቶ አዲሱ ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ ከቢሮ ወጥቶ ወደ ቤት በሚሄድበት ወቅት በደህንነት ድብደባ እንደደረሰበት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
በደህንነቶች ድብደባ የተፈፀመበት አቶ አዲሱ ‹‹ኢህአዴግ በሀሰብ መብለጥ ሲያቅተው የነፃነት ትግሉን በኃይል ለማስቆም እየጣረ ነው፡፡ ይህ እርምጃ ትግሉን ይበልጡን የሚያጠናክረው ይሆናል እንጅ ወደኋላ የምንልበት አጋጣሚ አይኖርም›› ብሏል፡፡
The post የምዕራብ ጎጃም ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪ ድብደባ ተፈፀመበት appeared first on Zehabesha Amharic.