በመንቃት ላይ ባሉ ፍጡራን መሀከል ያረረው ይበስላል ጥሬው እስኪበስል (ጎሞራው)
የምልከታ መነሻ
” አምላክ ከፈጠራቸው ፍጡራኖቹ በተለየ ለሰው ልጅ የሰጠው የማሰብ ፀጋ (ማሰብ እና ማሰላሰል መቻሉ) በራሱ የሰውን ልጅ ክቡርነት አመላካች ነው’’:: ይህን የተናገሩት ይችን አለም በተፈጦሮአዊው ሞት የተለዩት የግብፅ ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ አቡነ ሺኖዳ ናቸው፡፡ እውቁ ህንዳዊው ኢኮኖሚስት አማርታሲያን ሴን በበኩሉ የሰው ልጅ የማሰብ እና የማሰላሰል ፀጋውን ተጠቅሞ የራሱንም ሆነ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት እንዲችል ከምንም በላይ ነፃነት ያስፈልገዋል ይላል፡፡ እንደ ሴን ሁሉ እውቁ ፊሎሰፈር በርናንድ ሾው ማሰብ የጀመረ ሰው ያለ ነፃነት መኖር ሞቱ ነው ይላል፡፡ ከላይ የጠቀስኩአቸውን የሴን እና የበርናንድን ዘመን ተሸጋሪ እይታዎች መነሻ ስናደርግ ማሰብ ማለት ነፃነት ስለመሆኑ የሚያመላክተን ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩልም ለዚህ ፅሁፍ መግቢያ ያደረኩትን የአቡነ ሺኖዳን መንፈሳዊ ትንታኔ ከሴን እና ከበርናንድ እይታዎች ጋር ስንገምደው የማሰብን ፀጋ አምላክ ለሰው ልጅ ከሌሎች ፍጡራን በተለየ የሰጠው እንደመሆኑ የማሰብ ፀጋም ሆነ ነፃነት የሰው ልጅ ሰው መሆኑ ብቻ የሚያገኘው ነው እንደማለት ስለመሆኑ የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡ከላይ እንደጠከስኩአቸው ሴን፣በርናንድ እና አቡነ ሺኖዳ ሁሉ በሙያቸው እስከ አሁን ምትክ አናገኝላቸው ይሆን እያልን የምንጨነቅላቸው የአደባባይ ሙሁሩን የፕ/ሮ መስፍን ወልደማርያምን አንባገነኖች አእምሮአቸውን ስተው በጡንቻቸው ማሰብ ሲጀምሩ የሰውን ልጅ ክቡርነት ረስቶ ፍትህን ማጉአደል የሚጀምሩበትን ሁነት የተነተኑባቸውን ዘመን ተሸጋሪ ፅሁፎቻቸውን ማእከል ስናደርግ የአንባገነኖች ክፋት ከፈጣሪ የተሰጠውን የማሰብ ነፃነት ለመገደብ መሞከራቸው ስለመሆኑ የሚያመላክተነት ይመስለኛል፡፡
ዘመን ተሸጋሪ ስራዎቻቸውን አስቀምጠውልን በህገ ሞት ይቺን አለም ለተሰናበቱት ለበርናንድ እና ለአቡነ ሺኖዳ ለነብሳቸው እረፍትን እየተመኘው እንዲሁም ዘመን ተሸጋሪ ስራዎቻቸውን ላበረከቱልን እና ገና ለሚያበረክቱልን ለፕ/ር መስፍን ወልደማርያም እና ለአማርታ ሲያን ሴን ረዥም እድሜን ከመልካም ጤንነት ጋር እየተመኘው የዚህ ፅሁፍ ትኩረት ወደሆነው በእስር ቤት በጀርባ ህመም በመሰቃየት ላይ የሚገኘው ሰው በጠፋበት ሀገር ሰው ስለሆነው የትውልድ ተጋሪዬ ወጣት ስመለስ ወጣቱ ልጅ ሰው በጠፋበት ሀገር ሰው እንዲሆን ያስቻለውን ምክንያቶች ከሀገራዊ ፋይዳዎቻቸው (ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ) አኩአያ ለማሳየት እሞክራለው፡፡
ግለሰብ Vs አንባገነናዊ ስርአተ መንግስት
በአንድ ሉአላዊ ሀገር የሚኖሩ ህዝቦች ውስጥ እንደ ግለሰብ ለማህበረሰቡ የሚያበረክተውን ፋይዳም ሆነ ሚና እንዲሁም ማህበረሰቡ ደግሞ ለግለሰቦች የሚያበረክተውን ፋይዳ ከሀገራዊ ሀብት ክፍፍል እና ከፍትሀዊ ስርአተ መንግስት አኩአያ ለማየት መንግስታዊውን ባህሪ መነሻ በማድግ መንግስታዊው ባህሪ በግለሰብ እና በማህበረሰብ ላይ ያለውን ተፅእኖ መነሻ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ መንግስት ማለት እንደ እኔ እምነት ህዝቦች በሰጡት የሚታደስ እና የሚነጠቅ ውክልና ህዝቦችን የሚያስተዳድር የግለሰቦች ስብስብ ሲሆን፣ በግለሰቦችም ሆነ በአንድ ግለሰብ የሚዘወረው እና የመንግስታዊው ባህሪ መገለጫ አንባገነናዊነት በሆነበት ስርአተ መንግስት የስርአቱ አንባገነንነት ስፋት ግለሰብንም ሆነ ህብረተሰብን ሳይለይ ሁሉንም ህዝቦች በአንባገነናዊ ስርአት መግዛት እንደመሆኑ አንባገነናዊ ስርአት የግለሰብንም ሆነ የህብረተሰቡን መብት የመደፍጠጡ ሁነት አይቀሬ ነው፡፡ ትልቁ ጥያቄ ግን አፍጦ አግጦ ለመጣ አንባገነናዊው ስርአት የግለሰቦች እና የማህበረሰቡ ምላሽ እስኬት ነው የሚለው ይመስለኛል፡፡
አፍጦ አግጦ ለመጣ አንባገነናዊ ስርአተ መንግስት እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ የሚኖርን (መፍራትም ሆነ መተቸት ሊሆን ይችላል) ምላሽ ለማየት የእውቁን ራሺያዊው ፀሀፊ ቶልስቶይ አንድ ዘመን ተሸጋሪ ፅሁፍ እና የስሎቫኩን ፊሎሰፈር ዙዜክ እይታዎች በአስረጂነት ማቅረቡ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
አንድ ግለሰብ ፊልም ለማየት ወደ ሞስኮ ቲያትር ቤት ገብቶ ወደ ሲኒማ ቤቶቹ ውስጥ ከሚገኙት ወንበሮች ውስጥ መጨረሻ ላይ ወደሚገኘው ወንበር ገብቶ ተቀመጠ፣ ከጥቂት ደቂቃዎች በሁአላ አንድ ጄነራል እንደ ግለሰቡ ሁላ ፊልም ለማየት ወደ ሲኒማ ቤቱ በመግባት መጀሪያው ረድፍ ላይ ከሚገኙት ወንበሮች ውስጥ አንዱ ላይ ይቀመጣል፣ ፊልሙ እንደተጀመረ ጂነራሉ ወደ ሁአላ ዞር ሲሉ ጥግ ላይ የተቀመጠው ግለሰብ ጄነራሉ አብዮቱን እንደምደግፍ አወቁብኝ እንዴ በማለት ግራ ይጋባል፣ ጄነራሉ በድጋሚ ወደሁአላ ዞር ሲሉ ጥግ ላይ የተቀመጠው ግለሰብ በቃ አለቀልኝ ጄነራሉ አብዮቱን እንደምደግፍ አውቀውብኛል በማለት ይደመድማል፣ ጄነራሉ ለሶስተኛ ጊዜ ዞር ሲሉ ጥግ ላይ የተቀመጠው ፈጠን ብሎ ወደ ፊልም ሲከታተሉ በየ ሁነቱ ወደ ሁአላ ዞር ማለት አመላቸው ወደ ሆነው ጄነራል በመሄድ እግራቸው ስር በመውደቅ ለዛሬ ይማሩኝ ተሳስቼ ነው የአብዮቱ ደጋፊ የሆንኩት በማለት ተናዘዘ፡፡ ከላይ የገለፅኩት ረሺያዊው ጠሀፊ ቶልስቶይ አንባገነናዊ ስርአተ መንግስት ከሻፊ ግለሰቦች ላይ ስለሚፈጥረው መርበድበድ የገለፀበት ስነፅሁፉ አንባገነናዊ ስርአተ መንግስት ግለሰቦች ላይ ስለሚፈጥረው ሽብር ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ስሎቫካዊው ፈላስፋ ዚዜክ የግለሰቦች ንቃተ ህሊና ሚዛናዊ ሲሆን በንቃተ ህሊናው ልክ የሆነ ስርአተ መንግስት የመፈለጉን አይቀሬነት ይገልፃል፡፡ እንደ ዙዜክ እምነት በግለሰቦች ሚዛናዊ ንቃተ የተነሳ የሚፈጠረው ግለሰባዊ ፍላጎት ከግለሰባዊ ንቃተ ህሊና በታች ለሆነው ግለሰቡ ለሚኖርበት ማህበረሰብ ያለው ፋይዳ አንባገነናዊ ስርተ መንግስትን በመጋፈጥ ህብረተሰቡን ለሚዛናዊ ንቃተ ህሊና ማድረስ እንደመሆኑ ለግለሰቡ ከሚኖረው ፋይዳ በላይ ነው፡፡
ተመስገን !
አምላክ ለሌሎች ፍጡራኑ ያልሰጠውን ነገር ግን ለሰው ልጆች ብቻ የሰጠውን የማሰብ ፀጋ ተግባራዊ በማድረጉ የተነሳ ነፃነቱን ለድርድር የማያቀርበው በፋክት መፅሄት ላይ የአምድ ባልደረባዬ የነበረው ተመስገን ደሳለኝ ለኔ ማሰብ የጀመረ ሰው ከምንም በላይ ለነፃነቱ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ማሳያ የሆነ ግለሰብ ነው፡፡ በእኔ እምነት የአባት እዳ ለልጅ እንዲሉ መጠላለፍ እና አሸናፊነትን እና ተሸናፊነትን ብቻ ፖለቲካዊ ባህሉ ላደረገው እና አሁንም የሀገሪቷን ፖለቲካ ከሚዘውረው የያ ትውልድ ፖለቲካ ባህል ውስጥ ከመጠላለፍ ውስጥ ህብረትን፣ ከአሸናፊነት እና ተሸናፊነት ውስጥ አሸናፊነትን እና አሸናፊነትን ብቻ ያሳየ የአዲሱ ትውልድ አፍ ነው ፡፡ ከጳጳስ እስከ ሼካ፣ ከሼካ እስከ ምሁር፣ከምሁር እስከ ኪነጥበብ ባለሞያ ወዘተ ሀገርን እና ህብረተሰብን ወደ ጎን በመተው ለጓዳው ብቻ በማሰብ ምናገባኝ ባይ በሆነበት ሀገር ውስጥ ከአንባገነናዊው ስርአተ መንግስት በላይ የሚያስጨንቀው እንደ እኔ እምነት አርአያ የሚሆን ግለሰብ ያጣችው እና የሞራልን ዋጋ የናዱ ግለሰቦች የሚፈነጩባት ሀገር እጣ ፈንታ ነው፡፡ እንደ እኔ እምነት ተመስገን ደሳለኝ አርአያ የሚሆን ግለሰብ ላጣቸው እና የሞራልን ዋጋ የናዱ ግለሰቦች መፈንጫ ለሆነቸው ሀገሩ ሀገሬ በግለሰቦች የግል ፍላጎት የተነሳ ህልውናዋ አደጋ ላይ ሊወድቅ አይገባም በሚል ብእሩን የግለሰቦች ስብስብ በሆነው ስርአት እና የስርአቱ አንቋላጮች ላይ ያነሳ የሀገሩ እጣ ፈንታ ያስጨነቀው ግለሰብ ነው፡፡
ከህዝብ በሚሰበሰብ ቀረጥ የሚከናወነው የልማት እንቅስቃሴ ወደ ግለሰቦች ጓዳ በሚገባበት፣ ከኢህአዴግ አባልነት ውጪ ስራ ማግኘት ከባድ በሆነበት፣ የወጣት ጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራት የፋይናንስ ዋስትና አደጋ ላይ በወደቀበት፣ ባለሀብቱ ዛሬ ደግሞ ምን ሊሉን ይሆን በሚል በነጋ በጠባ በሚጨነቅበት፣ ባህል እና እሴቶቻችን ጠፍተው የህዝብን እና የሀገርን ሀብት የዘረፈ ደሩትን ነፍቶበአደባባይ በሚሄድበት እና በሚከበርበት፣ ፍትህን ለገንዘብ ብሎ ያዛባ ያሻውን በሚያደርግበት፣ ከዲግሪ እስከ ፒኢች ዲ በዘረፈው ገንዘብ ገዝቶ በማን አለብኝነት በአስተዳዳሪነት በተቀመጠበት በዘመነ ኢህአዴግ ላይ ለአቅመ አዳም የደረሰው ተሜ የአዲሱ ትውልድ አካል እንደ መሆኑ ለአዲሱም ሆነ ለነባሩ ትውልድ በመረጃ የተደገፈ ሚዛናዊ ሂስ እና ትችት ከፍ ሲልም ማስጠንቀቂያና መፍትሄን ከድፍረት ጋር ማቅረብ እንደሚቻል ያሳየ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጲያዊነትን ማንም መስጠትም ሆነ መንፈግ እንደማይችል በተግባር ያሳየ ሰላማዊ ባለሞያ ነው ለኔ፡፡
ተመስገን ደሳለኝ ከፍትሀዊ ሀብት ክፍፍል እስከ አንባገነናዊ የግለሰቦች ጭቆና በብእሩ መግለፁ በአንድ በኩል እንደ ህዝብ የደረሰበትንም ሆነ ወደፊት ስለሚጠብቀው አደጋ ለባለቤቱ በማሳወቅ ረገድ በሌላ በኩል ለጭቆናወቅም ሆነ ለሌብነቱ መንስኤ ለሆኑት ግለሰቦች በነሱ የተነሳ በህዝቡ እና በሀገሪቷ ላይ ስለደረሰው እና ስለሚደርሰው ሁነት በማሳየት ረገድ ከፍተኛ ሚና ያበረከተ ብቻ ሳይሆን ገና የሚያበረክት ስለመሆኑ ሳስብ ፊቴ ላይ ድቅን የሚለው እና የሚያሳስበኝ ተሜ ሰው በጠፋበት ሀገር ሰው በመሆኑ የተነሳ በዝዋይ እስር ቤት ታስሮ በጀርባ ህመም የመሰቃየቱ ነገር ነው፡፡ በመንቃት ላይ ባሉ ፍጡራን መሀከል ያረረው ይበስላል ጥሬው እስኪበስል ብሎ የገጠመው ጎሞራው በህይወት ኖሮ የተሜን ህመም ቢሰማ ምን ይል ነበር ?
The post ሰው ማለት ሰው የሆነ ነው ሰው የጠፋለት! – ኤድመን ተስፋዬ appeared first on Zehabesha Amharic.