“አሜሪካ ይዞን ከሄደ በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ አንድ የገበያ አዳራሽ (ሞል) ውስጥ ጥሎን ጠፋ…ፖሊስ ሁለት ግዜ ይዞን ነበር… በርሃብ ተቀጣን፣ ርሃብ ጸንቶበት ሆስፒታል የገባም ልጅ አለ። … በየሬስቶራንቱ እየዞርን ለምነናል።” ይላል አንድ የ 11 አመት ሕጻን ሳይንቲስት። ሂውስተን ቴክሳስ ያሚገኘውን ናሳ የጠፈር ምርምር ተቋም ለመጎብኘት ከአዲስ አበባ ሄደው ነው አስሩ ሕጻናት ዲሲ ላይ የሚሰቃዩት።
አስሩን ህጻናት በአንድ መኪና(ትራክ) ውጽጥ አጭቆ ነበር ወደ ሞሉ የወሰዳቸው። የያዘው መኪና ከአራት ሰው በላይ መጫን አይችልም። እመንገድ ላይ ፖሊስ እንዳያያቸው “ሁላችሁም ጎንበስ በሉ።” ይላቸው እንደነበርም ህጻናቱ አጫውተውኛል።
እነዚህ ሕጻናት ሀገሪቱ የምትመካባቸው የነገ ሳይንቲስቶችዋ ናቸው። ከአጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ተወዳድረው ከፍተኛ፤ እጅግ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ታዳጊዎች። በነዚህ ታዳጊዎች እና በወላጆቻቸው ላይ የደረሰው በደል እጅግ ብዙ ነው። ታሪኩ አንድ አሳዛኝ ፊልም ይወጣዋል። ወላጆቹ አሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ደውለው ይህ በደል ለህዝብ ይፋ እንዲሆንላቸው ቢጠይቁም የራዲዮ ጣብያው ጉዳዩን ባልታወቀ ምክንያት አፍኖታል። ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለጻፉት የአቤቱታ ደብዳቤም ምላሽ ተነፍገዋል። ጉዳዩ ለሚመለከተው ክፍል ሁሉ አቤት ብለዋል። ሰሚ ግን አላገኙም።
ይህንን በደል የፈጸመው ግለሰብ ከአዲስ አበባ እንዲሸሽ ተደርጎ በዚያው በዋሽንግተን ዲሲ በአንድ የፕሮቴስታንት ፓስተር ቤት መሽጓል። በአሜሪካ የመኖርያ ፈቃድ የለውም። የባንክ ሂሳብ ግን አውጥቶ ገንዘቡን እዚያው አከማችቷል።
የትንግርታዊው “ዶክተር” ሳሙኤል ዘሚካኤልን የሽወዳ ስልት ገና ከአእምሯችን ሳናወጣ፤ ሌሎች የእሱ ደቀ መዝሙሮች ብቅ እያሉ ነው። ስልታቸውን ይቀይሩ እንጂ የሁሉም ቁጭ በሉዎች አላማ አንድ ነው – ህዝብን ማታለል። አንዳንዶቹ ለሽወዳቸው ረቀቅ ያለ ዘዴ ሲጠቀሙ ሌሎች ደግሞ ዘርካካ በመሆን የዋሁን ህዝብ በዘረፋ ተያይዘውታል።
ዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት አጭበርባሪ የረቀቀ ስልት ባይጠቀምም ለሌብነቱ የተለየ መንገድ ይዞ ነው ብቅ ያለው። ሰናክሪም መኮንን ይባላል። ይህ ሰው የገዥው ፓርቲ አባል በመሆኑ ለዝርፊያው ምቹ መንገድ እንደፈጠረለት ይነገራል።
የሰናክሬም መኮንን አንድ አዲስ ፕሮጀክት ነደፈ። ከመላው ትምህርት ቤቶች በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያመጡትን አወዳድሮ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ታዳጊዎችን አሜሪካ በመውሰድ ሂውስተን ቴክሳስ የሚገኘውን ናሳ የጠፈር ምርምር ተቋም ማስጎብኘት። ከዚህም ሌላ የላቀ ውጤት ላመጡ ህጻናት የላፕቶፕ እና የአይፓድ ልዩ ሽልማት እሰጣለሁ ብሎ ቃል ይገባል። በየትምህርት ቤቱ እየዞረ የትምህርት ቤቶቹን እና ልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም አላማውን አስፈጸመ። ወጪውን ሁሉ የሚሸፍኑ ስፖንሰሮች አገኘ። አዲካ ትራቭል፣ ኦሮሚያ ባንክ እና ኢትዮጵያ አየር መንገድ የህጻናቱን ወጪ በሙሉ የሚሸፍን በቂ የሆነ ስፖንሰር ተገኘ።
ሰናክሬም የስፖንሰሩን ድጋፍ እና የአስሩን ህጻናት ፓስፖርት ይዞ አሜሪካ ኤምባሲ ለቪዛ ሄደ። በቂ የስፖንሰር ድጋፍ ስለነበረው ያለምንም ችግር የልጆቹን ቪዛ አገኘ።
ጫወታው እዚህ ላይ ነው የሚጀምረው። ስፖንሰሩን እና ቪዛውን በእጁ ካስገባ በኋላ የህጻናቱን ቤተሰቦች በተናጥል እየጠራ እያንዳንዳቸው የህጻናቱን የትራንስፖርት እና የመስተንግዶ ወጪ እንዲሸፍኑ ጠየቃቸው። ሰውየው በቂ በጀት ከስፖንሰሮች እንዳገኘ በወላጆቹ ይታወቃል። በመጀመርያ የገባውን ቃል አጥፎ ወላጆቹ የልጆቻቸውን ወጪ እንዲሸፍኑ መጠየቁ ለሁሉም እንግዳ ሆነባቸው። ሁሉም አንከፍልም ሲሉ መለሱለት።
ሰናክሬም ግን አጭር መልስ ሰጣቸው። “ወጪውን የማትሸፍኑ ከሆነ እድሉል ሌሎች ልጆች እሰጠዋለሁ።” ሲል የባሰ መርዶ አመጣባቸው።
ወላጆች አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ። በአንድ በኩል ልጆቻቸው ወደ ሂውስተን ለመሄድ ተነሳስተዋል። የልጆቻቸውን ስሜት መጠበቅ ግድ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሰው እያጭበረበራቸው መሆኑን አውቀውታል። ከብዙ ማንገራገር በኋላ ግን ገሚሱ ወላጅ የአውሮፕላን ትኬት፣ የአምስት ኮከብ ሆቴል፣ የመስተንግዶ እና የኮቴ ከፍሎ ልጆቹን ወደ አሜሪካ ላከ። ሰናክሬም ከውጭ ሃገር ከተቀበለው ዶላር ውጭ ወላጆቹ የከፈሉት ገንዘብ በድምሩ አንድ ሚሊዮን ብር ይጠጋል።
ይህንን ወጪ መክፈል ያየልቻሉ ህጻናትን ተሰረዙ። የነሱ እድል ሌሎች ጥሩ ውጤት የሌላቸው ግን ገንዘብ ላላቸው ወላጆች ተሸጠ። ዘረፋው በዚህ መልኩ ተፈጸመ። አስሩ ህጻናትም ወደ አሜሪካ ተጓዙ።
ወደ ዋና ድራማው ደግሞ ልውሰዳችሁ። አሜሪካ ዋሽንግተን እንደገቡ ለአንድ ቀን ብቻ በማሪዮት ሆቴል ቆይታ ያደርጋሉ። በነጋታው ሁሉም በአንድ ትራክ ተጭነው እዚህ ግባ የማይባል ማረፍያ ውስጥ በቡድን በቡድን ታጎሩ።
የጉዞው ዋና አላማ በሂውስተን የሚገኘውን የናሳ ጠፈር ምርምር ተቋም መጎብኘት ነበር። እሱን እርሱት ብሏቸዋል ሰናክሬም። ለግዜው ወላጆችን ማታለያ አስሩንም በቡድን ፎቶ አነሳቸው። የናሳን ማስክ በፎቶሾፕ እያስገባ አለበሳቸው። ናሳ የሄዱም አስመሰላቸው። ፎቶውንም በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ለጠፈው።
አሁን ልጆቹም ስለናሳው ጉዳይ አያስቡም። ከወላጆቻቸው ተነጥለው ወጥተው በአንድ ሃላፊነት በጎደለው ሰው እጅ ላይ ወድቀዋል። በአንድ ክፍል ወስጥ ተቆልፎባቸው ይውሉና ለተወሰነ ሰዓት በገበያ አዳራሽ ውስጥ ይለቀቃሉ። በአሜሪካን ሃገር በርሃብና ጥማት እየተሰቃዩ ነው። ረሃብ ጸንቶባቸው ሆስፒታልም የገቡ አሉ።
ወላጆቹ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ*፣ “ሰናክሬም ከእያንዳንዱ ወላጅ የአምስት ኮከብ ሆቴል ሂሳብ ተቀብሎ ሳለ ህጻናቱ ግን ተገቢውን የሆቴል አገልግሎት አላገኙም። ሴቶቹ የማይታወቁ ሰዎች ቤት እንዲያርፉ መደረጉ እና ወንዶቹ ደግሞ በቡድን በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲያድሩ አድርጓል።” ብለዋል።
ምግብን በተመለከተ ተገቢውን ምግብ ሳይመገቡ ለረሃብና ለህመም መዳረጋቸውና ከዚህም የተነሳ በምግብ ማጣት ጉዳት ሆስፒታል መግባታቸው፤ የተወሰኑት ከአቶ ሰናክሬም ተወስደው ወደ ዘመድ ቤት እንዳረፉ በደብዳቤው ላይ ተገልጿል። በመጀመርያዎቹ ቀናት ማክዶናልድ እየወሰደ ይመግባቸው እንደነበር ልጆቹ ተናግረዋል። ከዚያ በኋላ ነው የረሳቸው።
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ ደግሞ እነዚህን በአደራ የተቀበላቸውን ህጻናት በዋሽንግተን ዲሲ ለልመና መጠቀሙ ነው። “ከሄዱበት አላማ ውጪ በአደራ የተቀበላቸውን ህጻናት በየቤተክርስትያኑ እያዞረ ‘ለችግረኛ የሚሆን’ በማለት ኩፖን በማሸጥ አሰማርቷቸውም ነበር።” ይላል ደብዳቤው። ልጆቹን በዚህ መልኩ በልመና በማሰማራት በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሰበሰበ ህጻናቱ ይናገራሉ። በተለይ ዋሽንግተን ዲሲ ያለው ወንጌላዊ ቤተ-ክርስትያን ህጻናቱ በጉባኤው ፊት ቆመው የልመናውን ኩፖን እንዲያሳዩና እንዲሸጡ አድርጓቸዋል። ይህ የሆነው የቤተ-ክርስቲያኗን ፓስተር ሃንፍሬይን በማታለል ነው።
ሕጻናቱ በዚህ መልኩ ተንገላትተው ግን ለመጡበት አላማ ምንም ነገር ሳያደርጉ ሊመለሱ ነው። በአካባቢው ያሉ የቤተሰብ አባላት አንድ ሃሳብ አመጡ። ኢትዮጵያዊው ጠረፍ ሳይንቲስት የሆኑትን ዶ/ር ብሩክ ላቀውን በጉዳዩ አማከሩዋቸው። ዶ/ር ብሩክም ፈቃደኛ ሆኑ። በወላጆች ትውውቅ የመጡት እኚህ ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት ህጻናቱ ካረፉበት ስፍራ ድረስ በምሄድ ስለ ናሳ አስረዷቸው።
ህጻናቱም ይህችን እውቀት ይዘው፤ ናሳን በቴለቭዥን እንኳን ሳይመለከቱ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። የሰናክሬም የናሳ ጉዞ ፕሮጀክትም በዚህ ላይ ተጠናቀቀ። ገቢው አጓጊ ነውና ሰናክሬም አሁንም ሌላ ዙር ሊሰራ ማሰቡ አልቀረም።
የህጻናቱ ቤተሰቦች ግን በመሰባሰብ የጋራ አቋም ላይ ደርሰዋል። ያላግባብ የተወሰደባቸው ገንዘብም እንዲመለስ ጠይቀዋል። ሰናክሬም ግን ሸሽቶ አሜሪካ መሽጓል።
ይህ መረጃ እንደደረሰኝ ሰናክሬም መኮንን በኢሜል አግኝቼው ነበር። ጉዳዩን እልባት እንዲሰጥ፤ የሰዎቹንም ገንዘብ እንዲመልስ በተደጋጋሚ ጠየቅኩት። ይህ ከልሆነ ታሪኩን ለህዝብ ይፋ እንደማደርገውም ነግሬው ነበር። ይህ ጉዳይ ሜድያ ላይ ከወጣ ታዋቂ እንደሚያደርገው ተናግሮ አሾፈብኝ።
ይህንን የማደርገው ለሌሎች ወላጆች ትምህርት እንዲሆን ነው። ጉዳዩን ለበርካታ የሜዲያ አካላት ማሳወቄም ግድ ነው። ለጥንቱ ወዳጄ ሰይፉ ፋንታሁንም የህጻናቱን በደል ነግሬው ነበር። ህጻናቱን አነጋግሯቸዋል። ጉዳዩን በቅርቡ እንደሚያቀርበው ነግሮኛል።
ወላጆች በጋራ በመሆን ለሚመለከተው አካል የጻፉትን አቤቱታ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ።*
*
The post በአሜሪካ የመሸገው የሳሙኤል ዘሚካኤል ደቀ-መዝሙር appeared first on Zehabesha Amharic.