በግሩም ተ/ሀይማኖት
የመን ምጥ በቁና መሆኑን ትታ ምድራዊ ሲዖል እየሆነች ነው፡፡ ባስነጠሳት ቁጥር ግዙፍ ግዙፍ ሚሳኢሎቿን የሚያወድም ሚሳኤል ከአየር እየተወረወረላት ነው፡፡ ያኔ ማስነጠሱ ቀርቶ ይነስራታል፡፡ በዜጎቿ ደም ነስሯን ታንቦለቡላልች፡፡ ሰሞኑን ሰነዓ ከተማ ውስጥ ፈጂ አጣን የሚባለው ቦታ ላይ ያለ የመሳሪያ ክምችት በተከታታይ ተመታ፡፡ ፓለስቲክ ሚሳይሉ ያለው እዛ ውስጥ እንደሆነ ነው የሳዑዲ ባለስልጣኖች የሚናገሩት፡፡ በእርግጥ ትክክልም ይመስላል፡፡ በፍንዳታው አካባቢው በመጥፎ ኬሚካል ተበከለ፡፡ ከ1 ኪሎ ሜትር ራዲየስ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ሳል፣ ቋቅታ፣ ወደላይ ወደታች አናወጣቸው፡፡ በሳዑዲ የሚመራው ህብረ ሀይል አንድ መላ ቀየሱ….
ቦታውን ታርጌት አድርገው ከባህር ያስወነጨፉት ሚሳይል እየተመዘገዘገ ከተማውን አቋርጦ ሲያልፍ ጀት መስሏቸው ሲተኩሱበት እንደነበር የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ሚሳይሉ ግን ታርጌት የተደረገበትን ቦታ በሀይለኛው ድባቅ በታና ወደታች ይዞጥ ጦለመ፡፡ ከፍ ብሎ በቀጥታ ወደታች ቁልቁል ይዞት ሲወርድ ከላዩ አፈር አለበሰው የሚበነው ኬሚካል ተቀበረ፡፡ ለአካባቢው ሰላም ሰጠ፡፡
የመን ሰሞኑን ጫን በርታ ያለ ድብደባ እየደረሰባት ቤቶቻችንም አረገደች ምድር እያሉ እንቅጥቅጥ ድንከራቸውን ተያይዘውታል፡፡ በተመታ ቁጥር ቤቶቹ ያረግዳሉ፤ መስኮት ይከፈታል፣ ህጻናት በድንጋጤ ከተኙበት ተሳቀው ይነሳሉ፡፡ የልብ ምታችን በመቶ እጥፍ ይጨምራል፡፡ የሰነዓ ከተማና መብራት ከተገናኙ ዛሬ ስድስተኛ ቀናቸው ነው፡፡ ውሃ ዋጋው የወርቅ ሆኗል፡፡ ቆሻሻ በየቦታው ተከምሮ ይታያል፡፡ ነዳጅ ከወትሮው ዋጋ በ5 እጥፍ ጨምሯል፡፡ 3000 ሪያል የነበረው በአንዴ 15.000 እና 20.000 ሪያል ገብቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ቆሻሻ የሚያነሱት ሰራተኞች መስራት አልቻሉም፡፡ የግማቱ ነገር የፈነዳ ሽንት ቤት ውስጥ የተቆረቆረች ከተማ ሊያስመስላት ነው፡፡
ርሃብም ብዙዎችን ለማጨድ አቆብቁቦ የሸመቀ ይመስላል፡፡ መንገዱ ላይ ውርውር የሚሉት መኪናዎች በጣት የሚቆር ነው፡፡ ሰዉም ቢሆን ከረመዳን ጊዜው የባሰ ጥፍት ብሎ ከተማዋ በጭርታ የተኩስ ድምጽዋን እያዳመጠች ነው፡፡ የሁቲይ ሚኒሻዎች ጄቶቹን ለመከላከል ተኩሱን ከየአቅጣጫው ያዳምቁታል፡፡ ግን ጀቶቹ ጋር የመድረስ አቅም የለውም፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ በዚህች አይነቷ የመን ውስጥ ነው በጭንቅ እያነቡ ያሉት፡፡ በእስር የነበሩት 680 ኢትዮጵያዊያን ከሚግሬሽን እስር ቤት ከተፈቱ በተኩል ሰዓት ውስጥ አካባቢው በተኩስ ተናውጦ በአየር ተደበደበ ምንም እንኳን የእስር ቤቱ ባይመታም ዙሪያውን ያሉት ተቋሞች ተደበደቡ፡፡ የሚያሳዝነው ግን ከእስር የተፈቱትን 680 ኢትዮጵያዊያን 30 የሞላውን እንኳን ማግኘቱ ከባድ ሆነ በእውነት ልባችን እንደፈራው ሆኖም መሰለኝ፡፡
በድሮው ፕሬዘዳንት አብደላ ሳላህ ጊዜ ደቡብ የመን እና ሰሜን የመን ሲዋጉ ኢትዮጵያዊያኑን በጦርነት አሰልፎ የነበረው የሰሜን የመን ከጦርነት በኋላ ዜግነት የሰጣቸው ዘሬም ስንት ኢትዮጵያዊያን አሉ፡፡ ታሪክ ራሱን ይደግማል ይባላል፡፡ እኛ ላይ ግን መድገም ብቻ ሳይሆን መደጋገም ሆኖ ጢቢጢቢ እየተጫወተብን ነው፡
The post ኢትዮጵያዊያኑ የመን ውስጥ በጭንቅ እያነቡ ነው ያሉት appeared first on Zehabesha Amharic.