ፍቅረኛዬ ቤተሰቦቼ አግቢ ስላሉኝ አግባኝ ወይም እንለያይ የሚል ምርጫ ሰጠችኝ፤ ምን ይሻለኛል?
ቢ ነኝ
ውድ ጠያቂያችን ቢ የሁኔታህን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት ከሌሎች ደብዳቤዎች ያንተን በማስቀደም ይኸው ፈጣን ምላሻችንን ሰጠንህ፡፡ ከጽሑፍህ እንደተረዳነው በማግባትና በመለየት መካከል አንዱን ለመምረጥ ተቸግረሃል፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሄው ውሳኔ የመስጠት ክህሎትን (Decision Making Skill) ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ክህሎት ስር ያሉ የተለያዩ ስልቶችን/techniques/ በማንሳት ላንተ ሁኔታ አቅጣጫ በሚጠቁም መልኩ እናሳይሃለን፡፡
እንደዚህ አይነት ውሳኔ ለመስጠት የሚያስቸግሩ ነገሮች በሚያጋጥሙ ጊዜ መጨነቁና መወጣጠሩ የግድ ነው፡፡ ነገር ግን ቁምነገሩ መጨናነቁ ሳይሆን፣ ጊዜ ወስዶ ስለጉዳዩ በጥሞና በማሰብ የመፍትሄ እርምጃ መውሰዱ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ የመጀመሪያው ተግባር ችግሩን በሚገባ መለየት (Identify the problem) ነው፡፡ ፍቅረኛህ ለምንስ ሁለት አማራጮችን ብቻ ሰጠችህ? በጽሁፍህ እንደገለፅከው ቤተሰቦቿ እንድታገባ ስለፈለጉ ፍቅረኛህን ወጥረው ያዟት እሷም ላንተ ይህንን ምርጫ ሰጠችህ፡፡ ስለሆነም አሁን ያንተ ዋነኛ ችግር እሷን ከማግባትና ከእርሷ ጋር ተለያይቶ በመኖር መካከል መወጠርህ ነው፡፡ ያ ማለት የመጀመሪያው ተግባርህ ችግሩን መለየት ሲሆን ይህንንም ከውነሃል፡፡
ቀጣዩ ተግባርህ፣ ያሉህን አማራጮች በሙሉ ማየት (brain strom all possible option) ነው፡፡ በዚህም መሰረት ያሉህ አማራጮች አንደኛ ቤተሰቧ በሚሰጧችሁ ገንዘብ መሰረግና ከፍቅረኛህ ጋር አብሮ መኖር፣ ሁለተኛ ፍቅረኛህን አለማግባትና ከእሷ ተለይቶ መኖር ሲሆን ሶስተኛ አማራጭም አለህ፡፡ ይህም ፍቅረኛህን በማሳመን የተወሰነ ጊዜ ቆይቶ ራስን አጠንክሮ መጋባት ነው፡፡
ዋናው ጉዳይ ደግሞ ያለው፣ ከእነዚህ አማራጮች ውስጥ አንዱን መምረጡ ላይ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ቀጣዩን ተግባር መወሰኑ ወሳኝ ነው፡፡ ይህም እያንዳንዱ አማራጭ በአጭር ጊዜና በረጅም ጊዜ የሚያስከትለውን ጥሩና መጥፎ ነገሮችን መለየት ነው፡፡ ውድ ቢ ሶስቱንም አማራጮች በወረቀት አስፍራቸውና በእያንዳንዱ ስር ያን አማራጭ ብትመርጥ ምን ጥሩ፣ ምንስ መጥፎ ነገሮችን ሊያስከትል ይችላል ብለህ በሚገባ በማሰብ በዝርዝር ጻፋቸው፡፡
ምሳሌ ልስጥህ፤ የመጀመሪያው አማራጭ ፍቅረኛህን ማግባት ነው፡፡ ይህንን አማራጭ ብትተገብረው ተከትሎ ከሚመጡ ጥሩ ነገሮች አንዱ፣ የምትወዳት ፍቅረኛህ ጋር አብሮ መኖር ትችላለህ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ተከትለው ከሚመጡ መጥፎ ነገሮች ውስጥ አንዱ በሌሎች ገንዘብ ሠርግህን ታከናውናለህ፡፡ እንዲህ እያደረክ ይህንን አማራጭ ብትመርጥ የሚከተሉትን ጥሩና መጥፎ ነገሮችን በዝርዝር ፃፋቸው፡፡ ለሌሎች አማራጮችም በተመሳሳይ ምርጫውን ተከትለው የሚመጡ ጥሩና መጥፎ ነገሮችን ዘርዝረህ ፃፍ፡፡
እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን መናገር ይኖርብኛል፡፡ አንደኛው ይህ ጥሩ ወይም መጥፎ ነገር ይከሰታል ብለህ ብታሰፍር በቂ መረጃዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ ይገባሃል፡፡ በሌላ ቋንቋ ለእያንዳንዱ ይከሰታል የምትለው ጉዳይ አላማና የሆነና ምክንያታዊ መረጃ ሊኖርህ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ሶስተኛውን አማራጭ ብትመርጥ ፍቅረኛዬን ማሳመን አልችልም የሚል ነገር ብታስቀምጥ፣ ይህ እምነትህ ትክክል ለመሆኑ በቂ የሆነ ማስረጃ ሊኖርህ ይገባል፡፡
ሌላው ጉዳይ ደግሞ ዲካታስትፎፊንግ /Decatastrophing/ የሚባል ስልት አለና ይከሰታሉ የምትላቸውን መጥፎ ነገሮን ስታስቀምጥ ይህን ስልት ተጠቀምበት፡፡ ይህ ስልት ማለት ደግሞ አንድ መጥፎ ነገር ይከሰታል ስትል፣ ነገሩ የመከሰት ዕድሉ ምን ያህል ነው የሚለውን ማጤን፣ የችግሩ መጠን ምን ያህል ክብደት /Magnitude/ ይኖረዋል የሚለውን መገመት ብሎም ችግሩን ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል የምትችልባቸውን መንገዶችን ወይም ችግሩ ሊከሰት መቋቋም የምትችልበትን መንገዶች ቀደም ብሎ ማሰብ ማለት ነው፡፡ በምሳሌዎች ላስረዳህ፡፡ አንደኛውን አማራጭ ብትመርጥ ከሚከተሉት መጥፎ ነገሮች አንዱ ራሳችሁን ሳትችሉ ልጅ መውለድ ይመጣል የሚል ነገር አሰፈርክ እንበል፡፡ በዚህ ጊዜም ልጅ የመውለድ እድላችሁ ምን ያህል ነው፡፡ ልጅ ቢወለድ የሚከሰትባችሁ ችግር ምን ያህል ነው እና ልጅ እንዳትወልዱ ማድረግ የምትችሉባቸው መንገዶች ወይም ልጅ ቢወለድና ችግር ውስጥ ብትገቡ እንዴት አድርጋችሁ ችግሩን መቋቋም እንደምትችሉ ማሰብ ማለት ነው፡፡ በተቃራኒው አማራጭ ሁለትን ብትመርጥ ከፍቅረኛህ ጋር መለያየት ተከትሎ የሚመጣ መጥፎ ነገር ነው ብለህ አሰብክ እንበል፡፡ ስልቱንም በተግባር ለማዋል አንጋባም ብትላት፣ ፍቅረኛህ ጥላህ የመሄድ ዕድሏን ማጤን፣ ጥላህ ብትሄድ ምን ያህል እንደምትጎዳ መገመትና ጥላህ እንዳትሄድ ማድረግ የምትችልበትን መንገዶች ወይም ጥላህ ስትሄድ የሚደርስብህን ጉዳት ለመቋቋም የምትችልበትን መንገዶች ማሰብ ይኖርብሃል፡፡
በአጠቃላይም፣ እያንዳንዱ አማራጭ ብትመርጠው ተከትለው የሚመጡ ጥሩና መጥፎ ነገሮን በዝርዝር ማብሰልሰልና በጽሑፍ ማስቀመጥ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ በመቀጠል ደግሞ ከሶስቱ አማራጮች ብዙ ጥሩ ነገሮችን የሚያስከትለውን ወይም ብዙ መጥፎ ነገሮች የማያስከትለውን አንዱን አማራጭ መምረጥ፣ ብሎም በዛ ምርጫህ ምክንያት ሊመጡ የሚችሉ ጉዳቶችን አምኖ ለመቀበል ራስን ማዘጋጀት ነው፡፡
እዚህ ላይ አንድ ነገር ልጠቁምህ፡፡ አሁን አንተ እየመረጥክ ያለኸው ምርጫ እንደ ሌሎች አይነት ምርጫዎች /ለምሳሌ ሁለት ቦታ ስራ አልፈህ አንዱን መምረጥ/ ቀላል አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ አይነተኛ ምክንያቱ አንተ እየመረጥካቸው ያሉ አማራጮች ስሜታዊ የሆኑ ጉዳዮች (emotional component) አሉት፡፡ የብዙ ዘመን ፍቅረኛን ማጣት የሐዘን ስሜት፣ እሷን ከቤተሰቦቿ በሚገኝ ገንዘብ ማግባት የተረጅነት ስሜት፣ እሷን አሳምኖ ሰርጉን ማዘግየት በእሷ በኩል የመናደድ ስሜት፣ ባንተ በኩል እሷን ለማሳመን የትዕግስት መፈተን ስሜት፣ ወዘተ በውሳኔህ ውስጥ አብሮ ይኖራል፡፡ እንደነዚህ አይነት ስሜታዊ ጉዳዮችን ለመወሰን የስነ ልቦና ባለሙያዎች ጥሩ ስልት የሚሉት፣ ከእያንዳንዱ ምርጫ ጋር የሚመጡ ሁኔታዎችን ማጤን ብሎም ራስን ውሳኔው በሚነካው ሰው ቦታ የማስቀመጥ ስልትን (reattribution) መጠቀም ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም ፍቅረኛህን አላገባሽም የሚለውን ውሳኔ ለማሳወቅ ከመነሳትህ በፊት፣ ራስህን በፍቅረኛህ ቦታ አድርገህ፣ ላገባ ነው የሚለውን ውሳኔ ለቤተሰቦችህ ከማሳወቅህ በፊት፣ ራስህን በቤተሰቦች ቦታ አድርገህ፣ የተወሰነ ጊዜ ጠብቂኝ ብለህ ለፍቅረኛህ ከመናገርህ በፊት እራስህን በፍቅረኛህ ቦታ አስቀምጠህ ወዘተ ማሰቡ ጠቃሚ ነው፡፡
አንዱን አማራጭ ከመረጥክና በምርጫህ የተነሳ የሚመጣውን ነገር ለመቀበል ከተዘጋጀህ በኋላ፣ የመጨረሻ ተግባርህ የወሰንከውን ለፍቅረኛህ ማሳወቅ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ ሁለት ዘዴዎችን መጠቀሙ ጠቃሚ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ አንደኛው ፍቅረኛህ ራሷን በአንተ ቦታ እንድታስቀምጥና ውሳኔ እንድትሰጥ መጠየቅ (Reattribution) ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ካንተ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ታሪኮችን በመንገር (story telling) ወደ ራስህ ውሳኔ የማሳወቅ ተግባር መሄድ ነው፡፡ ብሌን ኪኖር የተባለ ምሁር በ2005 እ.ኤ.አ በሰራው ጥናት ለሰዎች የሌሎችን ታሪክ መናገር፣ ሰዎቹ ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ወይም ቢያንስ የእኛን ሁኔታ እንዲረዱና እንደሚያደርጋቸው አሳይቷል፡፡ ስለሆነም አንተ ተመሳሳይ ታሪኮችን በመንገርና ፍቅረኛህ ባንተ ቦታ ሆና እንድትወስን በማድረግና ውሳኔህን በማሳወቅ በውሳኔህ መሰረት በመንቀሳቀስ ውጥረትህን ማርገብ ትችላለህ፡፡ በስተመጨረሻም እላይ የጠቀስኳቸውን ተግባራት በቅደም ተከተል በመተግበር፣ ከችግርህ እንድትወጣ እያሳሰብኩ መልካሙን በመመኘት የዛሬ ምላሼን በዚሁ አጠናቀቅሁ፡፡
The post Health: ፍቅረኛዬ ቤተሰቦቼ አግቢ ስላሉኝ አግባኝ ወይም እንለያይ የሚል ምርጫ ሰጠችኝ፤ ምን ይሻለኛል? appeared first on Zehabesha Amharic.