የፎቶ ስቱዲዮው የሚገኝበት ስፍራ ከቴምስ ወንዝ ብዙም አይርቅም፡፡ ሱሬይ በመባል በሚታወቀው የከተማዋ ክፍል አንድ ጥግ ላይ ይገኛል፡፡ ዲዬጎ ኮስታ በስራ ተጠምዶ የሚታየው በዚያ ነው፡፡ ዳግም ለቅጣት ላለመዳረግም ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ ጊዜውን በሚገባ ለመጠቀም በእነዚህ ቀናት ከስፖንሰሮቹ ጋር የሚሰራውን ስራ እያስኬደ ነው፡፡ ያለፉት ጥቂት ሳምንታት ለእርሱ አስደሳች አልነበሩም፡፡ ባለፈው ወር መጨረሻ ማንቸስተር ሲቲ ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ መጥቶ ሰማያዊዎቹን ሲገጥም በጉዳት ከሜዳ ከራቀው ሴስክ ፋብሪጋዝ ጋር በመሆን በደጋፊዎች መካከል ተቀምጠው ጨዋታውን ተከታተሉ፡፡ በቪላ ፓርክ ቡድናቸው ያደረገውን ጨዋታ ከነጭራሹ በስታዲየም ተገኝተው አልተከታተሉም፡፡ ቼልሲ ኤቨርተንን በጠባብ ውጤት ያሸነፈበትን ጨዋታ ግን ታድመዋል፡፡ ‹‹መጫወት አለመቻል ያበሳጫል፡፡ ሜዳ ላይ ተገኝቼ የቡድን ጓደኞቼን መርዳት አለመቻሌ ያናድደኛል፡፡ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ እንደተመለከትነው ጨዋታው ፈታኝ ከሆነ አደብ ገዝቼ መመልከት አይሆንልኝም፡፡ ኳስ በተመታ ቁጥር እቁነጠነጣለሁ፡፡ ተረጋግቼ የምመቀጠው የጨዋታው ውጤት አስተማማኝ ከሆነ አልያም ቡድኔ የበላይነት ከወሰደ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በቀላሉ ስሜታዊ እሆናለሁ››
ያንን ከ15 ቀናት በፊት ከአጥቂው ፊት ለፊት የተቀመጡ ተቀያሪ ተጨዋቾች ሊመሰክሩ ይችላሉ፡፡ በተመልካች እና ተቀያሪዎች መካከል የነበረውን መለያ አጥር በተደጋጋሚ በቡጢ ሲነርት ተመልክተዋል፡፡ ገለልተኞች ይህ ሁሉ ነገር እንዲሆን ያደረገው ኮስታ እራሱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በካፒታል ዋን ካፕ ሊቨር ፑልን ሲገጥሙ ኤምር ቻንን ባይረግጥ ኖሮ ለቅጣት ባልተዳረገ ነበር ይላሉ፡፡ አሰልጣኙ በተደጋጋሚ ውሳኔውን ተቃውመው ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ ሲነሳባቸው እንደ አዲስ ንድድ ይላሉ፡፡ አጥቂው በጉዳዩ ዙሪያ ብዙ እንደተናገረ ያስባል፡፡ ከአሁን በኋላ በተመሳሳይ ርዕስ ላይ ላለመነጋገርም ወስኗል፡፡ ነገር ግን ጥፋተኛ አይደለሁም በሚለው አቋሙ እንደፀና ነው፡፡
ግጭት አስደሳች አልነበረም፡፡ ነገር ግን ተንኮል አይታይበትም፡፡ ‹‹ሆን ብዬ አላደረግኩትም፡፡ ቪዲዮውን መመልከት ይቻላል›› ያንን ስለሚያምን ፀፀት በውስጡ የለም፡፡ አቋሙም ግልፅ ነው፡፡ አጨዋወቱን የሚቀይርበት ምንም አይነት ምክንያት የለም፡፡ በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ አካባቢ በማንቸስተር ሲቲዎቹን ቨንሶ ካምፓኒ እና ፓብሎ ዛባሌታ እንዲሁም በሊቨርፑሎቹ ማርቲን ስክርትል እና ማማዶ ሳኮ ላይ የበላይነት እንደወሰደው ሁሉ በሌሎቹም ላይም ማድረጉ አይቀርም፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የአትሌቲኮ ተጨዋች ሳለ በቻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ቼልሲን ሲረቱ ጆን ቴሪን ማስጨነቁም አይዘነጋም፡፡
ሁልጊዜ የተወዳዳሪነት መንፈስ በውስጤ አለ፡፡ ያንን ያምናል፡፡ ‹‹ወደ ሜዳ ስገባ እለወጣለሁ›› በማለት ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ በ19 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 17 ጊዜ ኳስ እና መረብ ማገናኘት ባልቻ ነበር፡፡ ኤምር ቻን ላይ የፈፀመው ጥፋት ብዙ ነገሮችን ያስታውሳል፡፡ ዳኞች እና የእግርኳስ ተንታኞች አጋጣሚውን ጨከን ባለ እይታ ሊገልፁት ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንድ የማይካድ ሐቅ አለ፡፡ የተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች ትንሿን ንክኪ አጋንነው የማቅረብ ባህል አላቸው፡፡ ያንን የሚያደርጉት የተጋጣሚን ተጨዋች ለመተንኮስ ነው፡፡ ‹‹ለረዥም ጊዜ የከላካዮች ኢላማ ሆኜ ቆይቻለሁ፡፡ በእነርሱ መጎሸምን ተለማምጄዋለሁ፡፡ ሲጥሉኝም በቶሎ እነሳለሁ›› ሲል ተሞክሮውን ያካፍላል፡፡
‹‹ያንን አውቃለሁ፡፡ አንዳንድ ተከላካዮች ለትንሽ ንክኪ ተቃውሞ ሲያቀርቡ ብሰማም መታገሌን እና ሸርተቴ መውረዴን አላቆምኩም፡፡ ለእኔ ሁሉም ነገር የሚጠናቀቀው ጨዋታው እንደተፈፀመ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ሜዳ ውስጥ ትተን እጅ ለእጅ ተጨባብጠን እንወጣለን፡፡ አልቢትሩ የተበሳጨሁት እና አላስፈላጊ ድርጊት የፈፀምኩት ስንት ጊዜ ከተረገጥኩ እና ከተመታሁ በኋላ እንደሆነ ከግምት ሊያስገባ እንደሚገባ አስባለሁ፡፡ በእንግሊዝ የሚገኙ አልቢትሮች ብቃት ያላቸው ናቸው፡፡ በሜዳ ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ነገር ይገነዘባሉ፡፡ ያንን ከግምት ያስገባሉ፡፡
‹‹ወደ ሜዳ የምገባው የተለየ አላማ ይዤ አይደለም፡፡ ድክመቱን እጠቀማለሁ ብዬ አንድ የተወሰነ ተጨዋችን መርጬ ወደ ሜዳ አልገባም፡፡ ከጨዋታ በፊት ያንን ካደረግክ ከዋነኛ አላማህ ትስተጓጎልና ወደ አላስፈላጊ ግጭት ታመራለህ፡፡ በዚህ ምክንያት በጥሩ ሁኔታ መጫወት ይሳንሃል፡፡ ሜዳ ውስጥ ልንነታሪክ እንችል ይሆናል፡፡ ንክኪዎችም ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን የታቀደበት ነገር አይደለም፡፡ ስሜት ነው፡፡ ፍልሚያ ነው፡፡ የተለየ ዕቅድ የሚባለውን ነገር እርሱት፡፡ ብቸኛ አላማዬ ጎል ማስቆጠር እና ለቡድኔ ጠቃሚ በሆነ መንገድ መጫወት ነው፡፡ ከእኔ የሚጠበቀው በጥሩ አቋም ላይ ለመገኘት መሞከር እና ያንን ማሳካት ነው›› በማለት የቀድሞው የአትሌቲኮ አጥቂ ስሜቱን ያካፍላል፡፡
ባለፈው የውድድር ዘመን በላሊጋው ከየትኛውም ተጨዋች በላይ ፋውል ተሰርቶበታል፡፡ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ እንኳን የእርሱን ያህልጥፋት አልተፈፀመባቸውም፡፡ ጥፋት ሲሰራበት ላለመውደቅ የሚያደርገው ከፍተኛ ጥረት የቡድን ጓደኞቹ ያደንቁለታል፡፡ ያንን ሲመለከቱ ይበረታሉ፡፡ እርግጠኝነትም ይሰማቸዋል፡፡ በቪሴንቴ ካልዴሮንም ሆነ በቤርናቢዮ ሰርጂዮ ራሞስ የፈፀመበትን ተደጋጋሚ አስቀያሚ ጥፋቶች ታግሶ አልፏል፡፡ ነገር ግን ብራዚላዊው የስፔን ዜግነት እንዲቀበልያግባባው ይኸው ተከላካይ ነው፡፡ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ጨዋታ በርንሌን ለመግጠም ከማምራታችሁ በፊት ከቴሪ ጋር ተገናኝቶ የአጨዋወት ዘይቤው እንዲደግፍለት አግባብቶታል የሚል ወሬ ሲናፈስ ነበር፡፡ ተቀባይነት ያገኘም ይመስላል፡፡ ያንን በሚያደርግበት ወቅት ይህንን የመሰለ ቅጣት ሊያጋጥመው እንደሚችል ግን ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ነገር ግን የ26 ዓመቱ ተጨዋች ትልቅ ሃብት መሆኑን የቡድን ጓደኞቼ ያውቃሉ፡፡
ተጋፊነቱ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በእግር ኳስ እዚህ ለመድረስ ያለፈበት አስቸጋሪ ጉዞ ነፀብራቅ ነው፡፡ በላጋርቶ ጎዳናዎች ላይ ልቡ የደነደነ ተጨዋች ባህሪይ ነው፡፡ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ተጋሪዎቹ በሀብታም ክለቦች ስር በሚገኙ አካዳሚዎች አላደገም፡፡ ቤተሰቦቹን ትቶ በ2 ሺ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሳኦፖሎ ያመራው ገና በ14 ዓመቱ ነው፡፡ በዚያ ኤድሰን በተባለ አጎቱ ሱቅ ስራ መስራት ጀመረ፡፡ ባርሴሎና ኢስፓርቲቮ ካፔላ በሚባል በከተማዋ ደቡባዊ ክፍል በሚገኝ ክለብ አቅሙን ማሳየት ጀመረ፡፡ 100 ፓውንድ ወርሃዊ ደመወዝ ይከፈለው ጀመር፡፡
ኮስታ የመጀመሪያውን ‹‹ፕሮፌሽናል›› ጨዋታ ያደረገው በባርሴሎና ኡሲ ነው፡፡በዚያ በወጣት ቡድኑ ጥሩ አቋም አላየ፡፡ ወደ ፖርቱጉኤዛ፣ ሳኦ ፓውሎ እና ፓልማይራስ ይዘዋወራል የሚሉ ጭምጭምታዎች ተናፈሱ፡፡ ነገር ግን እውን አልሆኑም፡፡ በ18 ዓመት ለዝነኛው ወኪል ሆርጌ ማንዴዝ የሚሰራ ወኪል ተመለከተው፡፡ ከዚያም በአውሮፓ ከክለብ ክለብ መዟዟር ጀመረ፡፡ ሜንዴዝ ተጨዋቹን በመጀመሪያ ያስቆጠረው በብራጋ ነው፡፡ በስፔን እና ፖርቹጋል በሚገኙ አምስት ክለቦች በውሰት ተጫውቷል፡፡ በእነዚህ ዓመት አራት ቋሚ ዝውውሮች አድርጓል፡፡ ያ ወቅት አለመረጋጋት የሞላበት ነበር፡፡ እራሱን እስከ መጠራጠር ደርሷል፡፡ ነገር ግን ያደገው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አትሌቲኮ እርሱን ሁለት ጊዜ እንዲያስፈርመው አድርጓል፡፡ በ2007 ከብራጋ አስፈረመው፡፡ ከሶስት ዓመት በኋላ ደግሞ ከቫያዶሊና፡፡ ተጫዋቹ ስኬታማ ለመሆን ያለው ተነሳሽነት ወደር የለውም፡፡
‹‹እግር ኳስ ህይወቴ ነው፡፡ እራሴን በሌላ ሥራ ውስጥ ላስብ አልችልም፡፡ የማስበው ሜዳ ውስጥ ገብቼ ስለመጫወት ብቻ ነው›› ሲል ዲያጎ ኮስታ ማብራራቱን ይጀምራል፡፡ ‹‹እዚህ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፌያለሁ፡፡ በዚህ ደረጃ እራስህን ከምርጥ ተጨዋቾች ተርታ አሰልፈህ ለመቀጠል የተሻለ ተጨዋች እና የተሻለ ግለሰብ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ በመሆኑም ምንም ነገር ለነገ ሳልተው ጠንክሬ መስራት ይጠበቅብኛል፡፡ ባለኝ ነገር ደስተኛ ነኝ፡፡ ሰዎች ይመኩብሃል፡፡ እዚህ ለመድረስ የተጓዝኩበት መንገድ በተለየ እይታ ልመለከተው ይገባል፡፡ የተመኘሁላቸውን አይነት ህይወት ለቤተሰቦቼ በመስጠቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ የእኔ ኃላፊነት ያ ነው፡፡››
እርስዎ ከዚህም በላይ አድርጓል፡፡ በሰሜን ምስራቅ ብራዚል በምትገኘው እና ወደ 100 ሺ የሚጠጉ ነዋሪዎች ባሏት የትውልድ ከተማው ላጋርቶ የሚገኘውን ቦላ ዴ ኡሮ የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ የእግርኳስ ‹‹አካዳሚ›› በገንዘቡ ይደግፋል፡፡ አካዳሚው ከወዲሁ የአካባቢውን ኩራት ሆኗል፡፡ እርሱ ታዳጊ በነበረበት ወቅት በዚያ የነበረው ሰፋፊ ጎዳናዎች አቋርጠውት የሚያልፉት ሜዳ ነበር ትልልቅ የእርሻ መኪኖች ሲመጡ የልምምድ መርሃ ግብሮችን ለተወሰነ ጊዜ ማቋረጥ የግድ ነበር፡፡
አሁን ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ አካዳሚው በመሻሻል ላይ ነው፡፡ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የትምባሆ እርሻ አጠገብ ተዘዋውሯል፡፡ አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎች ተሟልተውለታል፡፡ አደረጃጀቱ እና መዋቅሩም ተስተካክሏል፡፡ የህክምና ማዕከል፣ የመማሪያ ክፍሎች እና ሶስት የቤት ውጪ የመጫወቺያ ሜዳዎች አሉት፡፡ በእነዚህ ላይ የማስፋፊያ ስራ ለመስራትም ተዘጋጅተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአካዳሚው ዕድሜያቸው እስከ 17 ዓመት የሚደርስ 230 የአካባቢው ተወላጆች ይገኛሉ፡፡ አካዳሚው ከወዲሁ በአካባቢው በጎ ተፅዕኖ እያሳረፈ ነው፡፡
ባለፈው ክረምት በተከናወነው የዓለም ዋንጫ የስፔንን ማልያ ለብሶ ወደ ሜዳ ሲገባ አብዛኞቹ ብራዚላውያን ተበሳጭተውበታል፡፡ ንዴታቸውን በዘለፋ እና ስድብ ገልፀዋል፡፡ በላጋርቶ ዋነኛ አደባባይ ግን ስሜቱ የተለየ ነበር፡፡ በዕለቱ ስፔን ሆላንድን ስትገጥም አብዛኞቹ ቀዩን የስፔን ማሊያ ለብሰው ነበር፡፡ በዚህም ደስተኛ ነው፡፡
‹‹ወደ ኋላ መለስ ብዬ አሰብኩ፡፡ ህልሜን እውን ለማድረግ ላጋርቶን ለቅቆ ስሄድ በዚያ የነበረውን ነገር አውቃለሁ፡፡ ፕሮጀክቱን የጀመርኩት በወኪሌ ድጋፍ ነው፡፡ እርሱ ከዓለም ምርጥ ተጨዋቾች የተወሰኑት ደንበኛ ነው፡፡ በመሆኑም በዚያ የሚገኙ ልጆች መንገዱ እንዲመቻችላቸው ተስፋ አደረግኩ፡፡ በዚያ ያሉ ልጆች እኔ ያላገኘሁት ዕድል ይመቻችላቸዋል፡፡ በቤተሰቦቸው አቅራቢያ ይኖራሉ፡፡ ከጎዳና ህይወት እና ከአደንዛዥ ዕፅ ይርቃሉ፡፡ በጥሩ ከባቢ ውስጥ ያድጋሉ፡፡ የተሻለ አቅጣጫ የሚያመላክታቸው ያገኛሉ፡፡
‹‹ላጋርቶ ትንሽ ከተማ ናት፡፡ እግር ኳስ ተጫዋች መሆን የሚፈልጉ ህፃናት በቂ ምቹ አጋጣሚ አያገኙም፡፡ በመሆኑም ይህ ፕሮጀክት ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ በማዕከሉ የሚሰሩ ትልልቅ ፕሮፌሽናሎች አሉን፡፡ ወሳኙ ነገር ያ ነው፡፡ መዋቅሮቹ ገና በመሻሻል ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን እዚህ በነበርኩበት ወቅት ከነበሩት የተሻሉ ሜዳዎች በአካዳሚው ይገኛሉ፡፡ ምግብ፣ ጥሩ ህክምና እና ድጋፍም ይሰጣቸዋል፡፡ የጎደለ ነገር የለም፡፡ ልጆች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሚሆኑበት ወቅት መምህራን እና አሰልጣኞች በሙሉ ተነሳሽነት ይረዷቸዋል፡፡ የአካዳሚው ዋነኛ አላማ ፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጨዋቾችን ማፍራት ሳይሆን ታዳጊዎቹን በዕውቀት ማነፅ ነው፡፡ የቀለም ትምህርትን መከታተል ግዴታ ነው፡፡በትምህርቱ ደካማ የሆነ ልጅ በልምምድ መረሃ ግብሮ ተሳታፊ እንዲሆን አይፈቀድለትም፡፡ አንዳንዶቹ ልጆች እግርኳስ ተጫዋች አይሆኑ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በአካዳሚው ውስጥ በማለፋቸው የተሻሉ ሰዎች ይሆናሉ፡፡ ከሚያጡት ይልቅ የሚያገኙት ይበልጣል›› በማለት ዲያጎ የፕሮጀክቱን አላማ እና ግብ ይገልፃል፡፡
የራሱን ትሩፋት ትቶ ለማለፍ መፈለጉ ክፋት የለውም የሚያስመሰግነው ነው፡፡ ይህ ድርጊቱ ኮታን በተለየ መንገድ ይገልፀዋል፡፡ ሰዎች እንደሚያስቡት ከፊቱ የቆሙትን ሁሉ ረጋግጦ የሚያልፍ አለመሆኑንም ያሳያል፡፡ የአትሌቲኮ ተጨዋች በነበረበት ወቅት ከሄታፌ ጋር ሲጫወቱ ኳስ እና መረብ ለማገናኘት ሲጥር ለከፍተኛ ጉዳት ተጋልጧል፡፡ በእርግጥ እንዳሰበው ኳስ መረብ ላይ አረፈች፡፡ እርሱ ግን ከቋሚው ጋር ተላትም ተሰበረ፡፡ በወቅቱ አሰልጣኝ ዲያጎ ሲሞን ያዘነው ለቋሚው ነበር፡፡ ‹‹ጭረት ነብርን አይጎዳም፡፡ የማዝነው ለቋሚው ነው›› ብሏል የአትሌቲኮው አሰልጣኝ፡፡
ኮስታ አጋጣሚውን ሲያገኝ በአግባቡ ተጠቀመበት፡፡ ሰርጂዮ አጉዌሮ፣ ራዳሜል ፋልካኦ እና ዲያጎ ፎርላን ለቅቀው ሲሄዱ ክፍተቱን እርሱ ደፈነ፡፡ በሁለት የውድድር ዘመናት 56 ጎሎን አስቆጠረ፡፡ ቼልሲ 32 ሚሊዮን ፓውንድ የከፈለው ብቃቱን ላረጋገጠ ተጨዋች ነው፡፡
‹‹በአትሌቲኮ በነበርኩበት ወቅት በለውጥ ሂደት ውስጥ ነበርኩ፡፡ በየዓመቱ ለመሻሻል ጥረት አደርጋለሁ፡፡ የሚቀርፅህ ሰው ማግኘት ወሳኝ ነው›› ይላል ኮስታ፡፡ ‹‹ጆዜ ሞውሪንሆ ከእኔ ምን እንደሚፈልግ ያውቃል፡፡ ጎል ከማስቆጥር በተጨማሪ ታትሬ እንድሰራ ይፈልጋል፡፡ ለታታሪነት ቅድሚያ ይሰጣል የእስካሁኑ የቼልሲ ቆይታዬ መልካም ነው፡፡
‹‹በስኳዱ ውስጥ የአንድነት መንፈስ አለ፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን በአትሌቲኮ ከነበረው መንፈስ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁላችንም የምንፈልገው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ የስራ ባህላችንም የምንፈልገው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ የስራ ባህላችንም አንድ አይነት ነው፡፡ እንደ ቡድን ውጤታማ ለመሆን ያንን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሴስክ ፋብሪጋዝን የመሰለ ተጨዋች በቡድን ውስጥ ማግኘቴ አግዞኛል፡፡ በስፔን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የጎል አጋጣሚዎችን የሚፈጥርልኝ መሆኑ ጠቅሞኛል፡፡ ኳስ የማቀበል ብቃቱ ያስገርማል፡፡
ሁለቱ ተጨዋቾች ከወዲሁ ደመነፍሳዊ ግንኙነት መስርተዋል፡፡ ኮስታ የእንግሊዝን እግርኳስ የለመደበት ፍጥነት ደግሞ ያስገርማል፡፡ ኮስታ ወደ ሜዳ የሚመለሰው ከየትኛውም ጊዜ በላይ ልዩነት ለመፍጠር ተነሳስቶ ነው፡፡ ምንም እንኳን ፊቱ ላይ የፌዝ ፈገግታ የነበረ ቢሆንም ከቼልሲ የአሰልጣኞች ስታፍ አባላት አንዱ ‹‹ቅዱስ›› ብሎ ጠርቶታል፡፡ እርሱስ እራሱን የሚገልፀው እንዴት ነው? ‹‹አዎን ይስማማኛል፡፡ ቅዱስ ብላችሁ ጥሩኝ›› ሲል በፈገግታ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
The post Sport: ‹‹እግርኳስ ህይወቴ ነው›› – ዲያጎ ኮስታ appeared first on Zehabesha Amharic.