SaveYourCoins # EthioMuslimsPeacefulStruggle #Boycott #CivilDisobedience
2ኛው አነስተኛ የትብብር መንፈግ ተቃውሞ መርሃ ግብር
ሳንቲም በመሰብሰብና በማጠራቀም ራስ ላይ የመቆጠብ እቀባ በማድረግ ለመንግስት የተቃውሞ መልእክት ማስተላለፍ
ረቡዕ መጋቢት 16/2007
በሰላማዊ ህዝባዊ ትግል ውስጥ ትብብር የመንፈግ እና የቦይኮት ተቃውሞ ከመንግስት ኃይሎች ጋር ሳይፋጠጡ እና አካላዊ ግጭት ውስጥ ሳይገቡ ትብብርን በመንፈግና የቦይኮት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ በደል እያደረሰ ለሚገኘው አካል የተቃውሞ መልእክት የማተላለፍ ስልት ነው፡፡ የትብብር መንፈግ ተቃውሞዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓይነቶች ያሏቸው ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ የሚገባንን የዜግነት መብት እስክናገኝ ድረስ ለመታገል ቆርጠን በገባንበት ታላቅ ህዝባዊ ትግል ውስጥ ካሁን ቀደም እምብዛም ሳይሞከር ቆይቷል፡፡
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቃውሟችን ወደቦይኮት እና ትብብር የመንፈግ ስልቶች እንደሚሸጋገር፣ ይህም አደባባይ ተኮር በሆኑ ተቃውሞዎች የገዛ ህዝቡ ላይ ጥይት ለመተኮስ የማያመነታው መንግስት ጡጫ እንዳያሳርፍብን ለመከላከል እንደሚያስችል መገለጹ ይታወሳል፡፡ እስካሁንም በጥቂት አጋጣሚዎች በቀኑ ክፍለ ጊዜ ስልክን በማጥፋት እና በአስገዳጅ ሁኔታዎች ውስጥ ካልሆነ ባለመጠቀም ውስንና አነስተኛ የቦይኮት ተቃውሞን በኢትዮ ቴሌኮም ተቋም ላይ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ አሁን ደግሞ ትንሽ ከፍ ያሉ የትብብር መንፈግ ስልቶችን ቀስ በቀስ ወደመላመዱ እና ወደመተግበሩ፣ ቀስ በቀስም ወደማሳደጉ መግባት ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ ባለፈው ጁሙዓ እየገባንበት ያለውን የትግል ስልት ስኬታማ እንዲያደርግልን እና መሪዎቻችንንም ከእስር ነጃ እንዲልልን በአገሪቱ በሚገኙ መስጂዶች ተሰባስበን ዱዓ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ከፊታችን ጁሙዓ መጋቢት 18/2007 ጀምሮ ሳንቲም በመሰብሰብና በማጠራቀም ራስ ላይ የመቆጠብ እቀባ በማድረግ ለመንግስት የተቃውሞ መልእክት ወደማስተላለፍ እንቅስቃሴ የምንገባ ይሆናል፡፡
መንግስት በገዛ ህዝቦቹ ላይ በሃይማኖታችን ምክንያት እያደረሰብን የሚገኘው ከፍተኛ በደል የሚሳለጠው ከእኛው በሚሰበሰብ ግብር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ህዝቡን እየደበደቡ እና እየገደሉ ያሉት የመንግስት ኃይሎች ደሞዛቸው የሚከፈለውም ከህዝቡ ኪስ በሚወጣ ገንዘብ ነው፡፡ በመሆኑም እንደዜጋ ገንዘባችንን በራሳችን ላይ ኢንቨስት ያለማድረግ የዜግነት መብታችንን በመጠቀም የሳንቲም ዝውውሩ ላይ እጥረት ስንፈጥር በእርግጥም ከእኛ ኪስ የሚገኘው ገንዘብ ላይ እኛም እንደህዝብ የተወሰነ ስልጣን እንዳለን ለመንግስት ግልጽ እናደርጋለን። ጥያቄዎቻችንን ባለመመለሱም የተቃውሞ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
እንደሚታወቀው መንግስት አንዲትን ሳንቲም ከዓለምአቀፍ የገንዘብ አምራች ተቋማት ሲያሰራ ከዋጋዋ በላይ አውጥቶባት ነው፡፡ ለሳንቲም ማሰሪያ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑም ሳንቲም ዝውውሩ ላይ ችግር ሲፈጠር ከፍተኛ ጫና ይደርስበታል፡፡ ምናልባት መንግስት ክፍተቱን ተጨማሪ ሳንቲም በማተም ለመሙላት ቢሞክር እንኳን የሰበሰብነውን ሳንቲም መልሰን ወደ ገበያው በማስገባት የዋጋ ዝቅጠት መፍጠር የምንችልበት አጋጣሚ የሚኖር መሆኑም ከግንዛቤ የሚገባ ነው፡፡ በዚህ የተቃውሞ ዘዴ ልናሳካው የምንሻው ጊዜያዊ ዓላማ ለሶስት ዓመታት ‹‹የፍትህ ያለህ!›› ስንል ቆይተን ከተጨማሪ በደል ውጭ መልስ ላልሰጠን መንግስት እንደህዝብነታችን አቅም እንዳለን እና ተጽእኖ ማሳደርም እንደምንችል ማሳየት ነው – ያለህዝብ ይሁንታ የመንግስት ህልውና ቢዘግኑት የማይዘገን ጉም መሆኑን ማስመስከር!!
ሳንቲም ሰብስቦ የመቆጠቡ ተቃውሞ አተገባበር
1/ የምንሰበስበው እና ቆጥበን የምናስቀምጠው እጃችን ላይ የገባውን ሳንቲም በሙሉ አይደለም! ይልቁንም ለኑሯችን አስገዳጅ የሆነውን ያክል ብቻ በመጠቀም ቀሪውን ማስቀመጥን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ በመሆኑም እጃችን ላይ ከሚገቡት ሳንቲሞች የግድ አስፈላጊ የሆነውን ያክል ብቻ በመጠቀም ቀሪውን በማስቀመጥ ብቻ እንወሰናለን፡፡
2/ ሳንቲም ቆጥቦ የመሰብሰብ ተቃውሞው የሚካሄደው በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች እና ከተሞች ነው፡፡
3/ ሳንቲም ቆጥቦ የመሰብሰብ ተቃውሞው የሚጀምረው የፊታችን አርብ መጋቢት 18/2007 ጀምሮ ሲሆን በዚሁ ገጻችን ማብቃቱ እስኪገለጽ ድረስም ላልተወሰነ ጊዜ ይቀጥላል፤ በአላህ ፈቃድ!
አዎን! እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሃይማኖታችን ምክንያት በመንግስት ከፍተኛ በደል እየደረሰብን ያለን ሰላማዊ ዜጎች ብንሆንም መንግስት ከበደሉ ሊቆጠብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለዓመታት ሰላማዊ ትግል ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ሰላማዊነታችንን ለመግለጽ ነጭ ጨርቅ እያውለበለብን በአደባባይ በተገኘን ቁጥር መንግስት አስፈራርቶናል፤ ዘልፎናል፤ ደብድቦናል፤ ዘርፎናል፤ አስሮናል፤ ገድሎናል፡፡ እኛ ነጭ ሶፍት ይዘን ሰላማዊነታችንን በአደባባይ ስንዘምር መንግስት ደግሞ ዝናሩን ታጥቆ በጥይት እሩምታ ተቀብሎናል፡፡ የማይጠፋ ጠባሳ የጣለ ጥቁር ሽብር ፈጽሞብናል፤ ፈርመን የላክናቸውን ወኪሎቻችንን በግፍ እስር እና በከፍተኛ ቶርቸር አሰቃይቶብናል፡፡ እስካሁንም ነጻነታቸውን ነፍጎ የምርጫ ቅስቀሳ መጠቀሚያ እያደረጋቸው ነው። እንግዲህ አሁን ላይ መንግስት ጥይት ሊተኩስበት በማይችለው ሜዳ ሰላማዊ ተቃውሟችንን ከመቀጠል ውጭ ሌላ ምርጫ ያለን አይመስልም፡፡ ዛሬ ይፋ ያደረግነው የትብብር መንፈግ ተቃውሞ ዋነኛ ዓላማም መንግስት ጥይት የሚተኩስበት ዒላማ የማያገኝበትን የትግል ድባብ በመፍጠር መብታችንን የማጎናጸፍ ግዴታውን እንዲወጣ የተቃውሞ መልእክት ማስተላለፍ ነው፡፡ ወደፊትም አንድ ብርና ከዛም በላይ ያሉ የብር ኖቶችንም ከመሰብሰብ ጀምሮ ሌሎች በአተገባበራቸውም ሆነ በእንድምታቸው ጠንክረው እያደጉ የሚሄዱ የትብብር መንፈግ እና የቦይኮት ስልቶችን ቀስ በቀስ በመለማመድ ሰላማዊ ትግላችንን እስከድል ደጃፎች እንቀጥላለን፡፡ ከአላህ ፈቃድ ጋር ይሳካልናል፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
The post ድምፃችን ይሰማ 2ኛውን የሰላማዊ ተቃውሞ ይፋ አደረገ * “ሳንቲም በመሰብሰብ በራስ ላይ እቀባን በማድረግ ለመንግስት ተቃውሞን መግለጽ” appeared first on Zehabesha Amharic.