• ኢብኮና የአዲስ አበባ አስተዳደር መገናኛ ኤጀንሲ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት መልሰዋል
• ‹‹አማራጫችን እንዳናቀርብ እየተከለከልን ነው›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የአዲስ አበባ አስተዳደር መገናኛ ኤጀንሲ የሰማያዊ ፓርቲን የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አናስተላልፍም›› ብለው መመለሳቸውን ድርጅቶቹ ለፓርቲው በላኳቸው ደብዳቤዎች ገልጸዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ መጋቢት 16/2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የብሔራዊ ራዲዮ በአማርኛ ስርጭት የሚተላለፍ ‹‹መንግስታዊ አወቃቀር›› የሚል የቅስቀሳ መልዕክት ልኮ የነበር ሲሆን ባለፉት 24 አመታት ተግባራዊ የሆነው የጎሳ ፌደራሊዝም ለግጭት መንስኤ መሆኑን በመረጃ ዘርዝሮ ማቅረቡን የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
ይሁንና ኢብኮ ይህን የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹በተለያዩ ጊዜያት በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ተከሰቱ ያሉትን ግጭቶች በመዘርዘር በህዝቦች መካከል ሌላ ግጭት እንዲቀሰቀስና እንዲባባስ የሚያደርጉና ግጭት የሚያራግቡ፣ አንዱን ብሔር ከሌላ ብሔር የሚያገጩ ናቸው፡፡›› በሚል እንደማያስተላልፍ ገልጾአል፡፡ ከዚህም ባሻገር በመልዕክቶቹ ውስጥ ‹የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት›፣ እንዲሁም ‹የህወሓት/ኢህአዴግ ስርዓት› የሚለው አገላለጽ የፓርቲውን ህጋዊ መጠሪያ የማይወክል በመሆኑ›› በሚል እንደማያስተላልፍ ገልጾአል፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ግጭቶች በአሁኑ ወቅትም የቀጠሉና የጎሳ ፌደራሊዝሙ እስካለ ድረስ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍሉ መሆናቸውን የገለጸው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ መልዕክቶቹ ከፓርቲው ማንፌስቶ የወጡ፣ ኢብኮ እንዳለው ለግጭት ሳይሆን ከግጭቶቹ መማር እንዲቻልና አሁን ያለው የጎሳ ፌደራሊዝም ከተስተካከለ ችግሮቹ እልባት እንደሚያገኙ በሚያሳይ መልኩ የተላለፈ መልዕክት ነው ብሎአል፡፡ ‹‹እኛ ያቀረብነው አማራጫችን ነው፡፡ አማራጫችን ስናቀርብ ደግሞ የጎሳ ፌደራሊዝም የፈጠረውም ቀውስም በማሳያነት ማቅረብ አለብን፡፡ ይህን እውነታ የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ዘግበውታል፡፡ አብዛኛዎቹ መንግስትም ያመነባቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ስርዓቱ የሰራቸው ጥፋቶች ይፋ አውጥተን እንዳናቀርብ ስለተፈለገ መልዕክቱን መልሰውታል፡፡ በግልጽ አማራጫችን እንዳናቀርብ ተከልክለናል›› ሲል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ አስተዳደር መገናኛ ኤጀንሲ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹ከሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ጋር የሚጻረር፣ ብሔር ብሄረሰቦችን ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዲያመሩ የሚገፋፋ፣ የሌላ ፖለቲካ ፓርቲን ስም የሚያጎድፍ ይዘት የተካተተባቸው›› ናቸው በሚል መልሷል፡፡ ይህ የሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ሲመለስ ለ8ኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
The post የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ለ8ኛ ጊዜ ተመለሰ appeared first on Zehabesha Amharic.