በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የተለያዩ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ሲካሄዱ ቆይተው የመጨረሻዎቹ አስራ ስድስት ክለቦች የመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ተፋላሚዎች መሆናቸው ታውቋል።
ወደ መጨረሻው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ካለፉት አስራ ስድስት ክለቦች መካከል አምስቱ ቀደም ሲል የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያነሱ ናቸው።
ከአምስቱ ክለቦች መካከል የሞሮኮዎቹ ፋር ራባትና ዋይዳድ ካሳብላንካ ግንባር ቀደሞቹ ሲሆኑ፤ የኮትዲቯሩ ኤ ኤስ ኢ ሲ ሚሞሳህ አስራ ስድስት ውስጥ የገባ ሌላኛው ክለብ ሆኗል።የቱኒዚያው ኢቶይል ሳሌህና የግብፁ ኢስማኤሊ ከአምስቱ የቀድሞ የአፍሪካ ሻምፒዮኖችና የአሁኑ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ተፋላሚዎች ሆነዋል።
ከአስራ ስድስቱ ክለቦች መካከል የቱኒዚያው ኤስ ሲ ፋዚየን መካተት ችሏል።ይህ ክለብ አህጉራዊ ዋንጫ ከማንሳቱም ባሻገር በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች አፍሪካን ወክሎ መሳተፍ የቻለ ውጤታማ ክለብ እንደነበር ይታወሳል።
ወደ መጨረሻው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከገቡ ክለቦች መካከል የሞዛምቢኩ ክለብ ሊጋ ሙከልማና መካተቱ የስፖርት ቤተሰቡን ያስገረመ ጉዳይ ሆኗል።ይህ ክለብ የመጨረሻውን ጥሎ ማለፍ ውድድር የተቀላቀለው የናይጄሪያውን ሎቢ ስታርስ ክለብን ማፑቶ ላይ ሰባት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፎ ነው። ሊጋ ሙከልማና ክለቡ ይህ ነው የሚባል ስም የሌለው እንደመሆኑ መጠን በሰፊ ውጤት ማሸነፉ ያልተጠበቀ ነበር።
የጋቦኑ ዩ ኤስ ቢታም ክለብ አስራ ስድስት ውስጥ መግባት ከቻሉት ክለቦች አንዱ ሆኗል።ይህ ክለብ በቀደሙት ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አስራ ሰባት ግቦችን በማስቆጠር ባለ ክብረወሰን ነው። በመጪዎቹ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችም ውጤታማ ይሆናል ተብሎ ግምት ተሰጥቶታል።
ዩ ኤስ ቢታም ክለብ ካስቆጠራቸው ግቦች መካከል አራቱ ግቦች ሶኒቶ የተባለው ተጫዋች ኳስን ከመረብ ያዋሃዳቸው ናቸው። በእዚህም የዋነጫው ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን ይመራል።
የሞሮኮው ፋር ክለብ የአፍሪካ ሻምፒዮን በመሆን በሞሮኮ ክለቦች ታሪክ የመጀመሪያው ነው።ይህ ክለብ የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነውም እ.ኤ.አ በ1985 እንደ ነበር ይታወሳል። ክለቡ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫን ከስምንት ዓመት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ ማንሳቱም አይዘነጋም።
በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የተሻለ ታሪክ ያለው የታንዛኒያው አዛም ክለብ በሜዳው ግብ ባልተቆጠረበት ሕግ የሊቢያውን አል ናስር ክለብን ጥሎ አስራ ስድስት ውስጥ ገብቷል። አዛም ከእዚህ በፊት በነበረው ጥሎ ማለፍ የላይቤሪያውን ባራክ ያንግ ኮንትሮለርስ ክለብን በጥሎ ማለፍ ማሸነፉ ይታወሳል።
«ዘ ነርሰሪ» በመባል የሚታወቁት ኤ ኤስ ኢ ሲ የኮትዲቯርን በርካታ ከዋክብት ያፈራ ክለብ ነው።ይሁን እንጂ በኮንፌደሬሽን ዋንጫ ተጠቃሽ ታሪክ የለውም።ይህ ክለብ የአፍሪካ ሻምፒዮን የነበረበት ጊዜም እ.ኤ.አ በ1998 ነው።
የአገራችንን ክለብ ደደቢትን በሜዳው አንደ ለባዶ በማሸነፍ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ባዶ ለባዶ በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቶ ወደ ቀጣይ ዙር ያለፈው የሱዳኑ አል አህሊ ሸንዲ ክለብ አስራ ስድስት ውስጥ መግባት ከቻሉ ክለቦች አንዱ ነው።አል አህሊ ሸንዲ በቀጣይ ጥሎ ማለፍ ጨዋታም የግብፁን ኢስማይሊ ክለብን እንደሚገጥም ታውቋል።