የሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴን አርባኛ የልደት በዓል አስመልክቶ ስፓይክስ የተባለው ድረ ገጽ የአትሌቱን አስር አይረሴ ውድድሮች ዝርዝር ለትውስታ ማቅረቡ ይታወሳል።እኛም ከእነዚህ ውድድሮች መካከል አምስቱን ባለፈው ቅዳሜ እትማችን ማቅረባችን ይታወሳል።ዛሬ ደግሞ ቀሪዎቹን አምስቱን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።
1999 የማዕባሺ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በእዚህ ውድድር « ሁለ ገብ » መሆኑን ያሳየበት ነበርና አውሮፓውያኑ « Multi-eventer » የሚል ቅጽል ከስሙ በፊት እንዲጨምሩ አስገድዷቸዋል።
በውድድሩ ብዙ ጊዜ በማይስተዋል መልኩ ሻለቃ ኃይሌ በአንድ ሺ አምስት መቶና በሦስት ሺ ሜትር ውድድሮች ምርጥ ችሎታውንና ለረጅም ርቀት ሩጫ የተፈጠረ አትሌት መሆኑን አሳይቷል።
የሦስት ሺ ሜትር ርቀት ውድድር የሚታወቅበትና በበርካታ ውድድሮች ላይ ችሎታውን ያሳየበት በመሆኑ ማሸነፉ ብዙም አስደናቂ ባይሆንም በውድድሩ የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ውድድርን በተደጋጋሚ በመርታቱ የተነሳ « ስፔሻሊስት » ለመባል የበቃውን ላባን ሮቲችን መርታቱ በወቅቱ እንደተአምር ተቆጥሮ ነበር ።
1999 የዓለም ሻምፒዮና ሲቪያ
ይህ የዓለም ሻምፒዮና አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በአስር ሺ ሜትር ተፎካካሪዎቹን በሙሉ ተስፋ ያስቆረጠበት ነበር።
በውድድሩ የመጨረሻውን ዙር ከአንድ ደቂቃ በታች ማለትም በ54 ነጥብ 5 ሰከንድ በመሮጥ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ በአስር ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን መሆን የቻለበት ነው። በእዚህ ውድድር ሁለተኛ የወጣው ማን እንደሆነ አንባቢ ግምቱን ይስጥ ቢባል ኬንያዊው ፖል ቴርጋት ከተባለ መልሱ ትክክል ይሆናል ።
ተአምረኛዋ ሰኞ 2000ሲድኒ ኦሊምፒክ
የአውስትራሊያዋ ሲድኒ ያስተናገደችው ይህ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በተሳትፎዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ሜዳሊያዎችን ያገኘችበት በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ነበር።በመሆኑም ነው ከልጅ እስከ አዋቂ ባለድል አትሌቶቹ ወደ አገራቸው ሲመለሱ አደባባይ ወጥቶ የጀግና አቀባበል ያደረገላቸው።
ይህ ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ቢሆንም ሻለቃ ኃይሌ ደግሞ ተስፋ አለመቁረጥን ፣ ኢትዮጵያዊ ወኔን ለዓለም ያሳየበት ነው ማለት ይቻላል።
ልክ የሪያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ችሎታ በአርጄንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ችሎታ እንደተሸፈነው ሁሉ በኃይሌ ገብረሥላሴ ተአምራዊ ብቃት ሁል ጊዜ ሁለተኛ መውጣትን የተለማመደ የሚመስለው ኬንያዊው ፖል ቴርጋት የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ለመውሰድ አስራ አምስት ሜትሮች ብቻ ሲቀሩት ድሉን ለማስጠበቅ በመወዳደር ላይ የነበረው ኃይሌ ከኋላ መጥቶ የወርቅ ሜዳሊያውን የነጠቀበት ሁኔታ የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪዎች ሁሌም የሚያስታውሱት ክስተት ሆኗል።
የስድኒ ኦሊምፒክ በአስር ሺ ሜትር ያስመዘገበው አስደናቂና ልብ አንጠልጣይ ድል አትሌት ኃይሌ የአትላንታ ክብሩን ያስጠበቀበት ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ በተከታታይ ሁለት ኦሊምፒኮች በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ እንድታገኝ ያስቻለ ነበር ።
ለንደን ግራንድ ፕሪ 2004
በእዚህ ጊዜ ኃይሌ ሜዳ ላይ ምርጥ ብቃቱን የሚያሳይበት ጊዜው ያለፈበት ቢመስልም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ግን የቀድሞ ብቃቱን ማሳየት አልተሳነውም።
በእዚህ ውድድር ላይ ባለምርጥ ብቃቱ ወጣት አውስትራሊያዊ ክሬግ ሞትራም ተሳታፊ ነበር። ወጣቱ እንደተጠበቀውም ኃይሌን ቀድሞ በመግባት ለማሸነፍ ከጫፍ ደርሷል።ይሁንና ኢትዮጵያዊው ተለይቶ የሚታወቅበትን ፈጣን የአጨራረስ ብቃት ተጠቅሞ አንደኛ ወጣ።
ኃይሌ ውድድሩን በ12 ደቂቃ ከ55 ነጥብ 51 ሰከንድ ቢያሸንፍም ከወጣቱ አውስትራሊያዊ የነበረው የሰዓት ልዩነት የዜሮ ነጥብ 25 ሰከንድ ብቻ መሆኑ አውስትራሊያዊውና ኢትዮጵያዊው ያደረጉት ፍልሚያው ከባድ እንደነበረ ለመገመት አያዳግትም።
« የማራቶኑ ሰው » በርሊን 2008
በአትሌቲክስ ስፖርት ዓለም ትልቁና የመጨረሻው በሆነው የማራቶን ውድድር ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በበርሊን ጎዳናዎች ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ክብረ ወሰን ያስመዘገበበት ውድድር ነው፡፡ ይህ ውድድርበራሱ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በ27 ሰከንዶች ከማሻሻሉም በላይ ርቀቱን ከሁለት ሰዓት ከ04 ደቂቃ በታች በመሮጥ የዓለማችን የመጀመሪያው ሰውም የሆነበት ውድድር ነው።
አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ርቀቱን በሁለት ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ59 መሮጡን ተከትሎ « ርቀቱ ከሁለት ሰዓት በታች በሆነ ጊዜ ሊሮጥ ይችላል ? » የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።