የሰሜን ለንደኑ አርሴናል ባለፉት ዓመታት ወደ ክለቡ ያዘዋወራቸውና የተጠበቀውን ያህል መጥቀም ያልቻሉትን ተጫዋቾች የመውጫ በሩን የከፈተላቸው ሲሆን ከእነዚህ በርካታ ተጫዋቾች መካከል የተለያዩ ምንጮች የዘረዘሯቸው አስራ አንድ ተጫዋቾች የሚከተሉት ናቸው።
1
ግብ ጠባቂ
ማኖኒ
ጣሊያናዊው የ25 ዓመት ወጣት ነው። በግብ ጠባቂነቱ የንስ ሌህማንንና ዴቪድ ሲማንን እንደሚተካ ተስፋ ተጥሎበት ከጣሊያኑ ናፖሊ ወደ ሰሜን ለንደን አርሴናል የደረሰው ከሰባት ዓመት በፊት ነበር። ልምድ እንዲያገኝ በማሰብ በውሰት ወደተለያዩ ክለቦች ቢዘዋወርም ከመንከራተት በቀር የታሰበውን ያህል ሆኖ ባለመገኘቱ የ2013/14 የውድድር ዘመን ሳይጀመር ቦታህን ፈልግ ተብሏል። ወደ ምሥራቅ እንግሊዝ በማምራትም ጥቋቁር ድመቶቹ ለሚባሉት ለሰንደርላንድ በሁለት ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳበ ዝውውር አድርጓል።
2
ተከላካዮች
ባካሪ ሳኛ
የቀድሞው የኦግዜር ተጫዋች በሰሜን ለንደኑ ክለብ ከፍተኛ ግልጋሎትን መስጠት ቢችልም በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ያሳየው የወረደ አቋም ቬንገር ፊታቸውን እንዲያጠቁሩበት አድርጓል። በዚህም በቀጣዩ የውድድር ዘመን ለፈረንሳዮቹ ፒ.ኤስ.ጂ ወይም ሞናኮ ሊፈርም እንደሚችል ይገመታል።
3
አንድሬ ሳንቶስ
የአርሴናል ደጋፊዎች የዚህን ብራዚላዊ ስም መስማት አጥብቀው ይጠሉታል። ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ ሜዳ ላይ ከሚሰራቸው ተደጋጋሚ ስህተቶቹ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት ክለቡን ለቆ ለማንቸስተር ዩናይትድ የፈረመውን ሮቢን ቫንፐርሲን ማሊያ እንዲቀይረው መልበሻ ክፍል ድረስ ሂዶ መለመኑ ነበር። ካለበት የአቋም መዋዠቅ ጋር ተደማምሮ በቀጣዩ የውድድር ዓመት የአርሴናልን ማሊያ ከማይለብሱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚችል ሰፊ ግምት ተሰጥቶታል።
4
ሴባስቲያን ስኩላቺ
ፈረንሳዊ ነው። የቀድሞው የሲቪያ ተከላካይ ተጫዋች የነበረ ሲሆን፣ አምስት ሚሊዮን ፓውንድ ተከፍሎበት ነበር በ2010 ኢምሬትስ የደረሰው። ነገር ግን አንጋፋው ተከላካይ ለስህተት በእጅጉ የቀረበ መሆኑ የኢምሬትስ መውጫ በሮች ተከፍተውለት በነጻ ወደ ፈለገው ክለብ እንዲዛወር ፍቃድ ተሰጥቶታል።
5
ዩሃን ዡሩ
ትውልደ ኮትዲቯራዊ የሲዊትዘርላንድ ተከላካይ ነው። ወደ አርሴናል ሲዘዋወር አዲሱ ሶል ካምቤል ይሆናል ተብሎ ነበር። ከጉዳት ጋር ያለው ዝምድና በእጅጉ የቀረበው ይህ ተከላካይ ዓመታት በተፈራረቁ መጠን ብቃቱም ያንኑ ያህል እየቀነሰ መሄዱ ለ2013/14 የውድድር ዘመን ወደ ጀርመን ተጉዞ ለሃምቡርግ እንዲጫወት ቬንገር የአንድ ዓመት የውሰት ውል ፈቅደውለት ወደዚያው አምርቷል።
6
አማካዮች
ጄርቪንሆ
ለአስተያየት ሰጨዎች ግራ ያጋባው ይህ ተጫዋች በቀጣዩ ዓመት የአርሴናል ደጋፊዎች የክለባቸውን ማሊያ እንዲለብሱ ከማይፈልጓቸው መካከል አንዱ ነው። ፈጣን እና ጥሩ የኳስ ችሎታ ቢኖረውም የመጨረሻ ኳሶቹ ማረፊያ ማለትም ዒላማ የሚስት መሆኑ ነበር የክለቡን ደጋፊዎችና የአሠልጣኞች ቡድን ያበሳጫቸው። ወደ ቱርኩ ጋላታሳራይ ወይም ወደ ፈረንሳዮቹ ሊልና ሊዮን ዝውውር ሊያደርግ እንደሚችል ይገመታል።
7
ዴኒልሰን
ብራዚላዊው አማካይ ተጫዋች በ2006 ሃይበሪ ሲደርስ የጂልቤርቶ ሲልቫ ትክክለኛ ተተኪ እንደሚሆን ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት የክለቡ ደጋፊዎች ስሙን እየጠሩ የሚዘምሩለት ኮከብ ቢሆንም ከጉዳት በኋላ ብቃቱ ወርዶ ታይቷል። የቀድሞ ብቃቱን እንዲያገኝ በማሰብ ለብራዚሉ ሳኦፖሎ በውሰት እንዲጫወት ወደ ብራዚል ቢያቀናም እርሱና ብቃቱ ላይገናኙ የተለያዩ መስለው የታያቸው አርሴን ቬንገር በቀጣዩ ዓመት ከክለባቸው ጋር እንደማይቆይ በይፋ ነግረውታል።
8
ኢማኑኤል ፍሪምፖንግ
በትውልድ እንግሊዛዊ የሆነው የጋና ዜግነት ያለው የአማካይ ተከላካይ ተጫዋች ሜዳ ላይ በሚቆይበት እያንዳንዱ ደቂቃ ለውዝግብና ለፀብ የተጋለጠ መሆኑ ክለቡን በተደጋጋሚ ጊዜ አደጋ ላይ ሲጥል ተስተውሏል። በዚህም ተስፋ የቆረጡት አንጋፋው ፈረንሳዊው የክለቡ አሠልጣኝ ወደ ሌላ ክለብ ተዘዋውሮ እንዲጫወት ነግረውታል።
9
አንድሪ አርሻቪን
ታታሪ እንዳልሆነ የሚነገርለት የቀድሞው የሩሲያ ብሔራዊ ቡድን አምበል አርሻቪን፣ አርሴናልን ከተሰናበተ ቀናት ተቆጥረዋል። እስካሁን ለአርሴናል ሪከርድ በሆነ የዝውውር ሂሳብ በ2009 ጥር ላይ ከሩሲያው ዜኒት ሴንት ፒተርስበርግ ነበር የተዘዋወረው። ተቀያሪ ወንበር ላይ መቀመጤ ለአዕምሮ ጭንቀት ዳርጎኝ ነበር ብሎ ለሀገሩ ቴሌቪዥን የተናገረው አርሻቪን በአርሴናል በነበረው ቆይታ የመጨረሻ ዓመታት የተጠበቀውን ያህል መጥቀም አለመቻሉ ነበር በነጻ ዝውውር ኢምሬትስን እንዲሰናበት ያደረገው።
10
አጥቂዎች
ኒኮላስ ቤትነር
ራሱን የዓለም ኮከብ ነኝ እያለ የሚመጻደቅ ዴንማርካዊ ቁመተ መለሎ አጥቂ ነው። ከአርሴናል ጋር ያለው እህል ውሃ የሚያበቃው በዚህ በተከፈተው የዝውውር መስኮት ነው። በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ተለያዩ ክለቦች በውሰት እየተዘዋወረ ራሱን እንዲመለከት ቢደረገም፣ ብቃቱን ማሻሻል አለመቻሉ ሌላው የክለቡ ተሰናባች ሊሆን ችሏል። እርሱም በቀጣዩ ዓመት ወደ ጀርመን ተጉዞ ለሃምቡርግ ወይም ለቱርኩ ግዙፍ ክለብ ጋላታሳራይ ሊፈርም ይችላል።
11
ማሩዋን ሻማክ
መለሎው ሰሜን አፍሪካዊ ማሩዋን ሻማክ ከቦርዶ ወደ አርሴናል በተዘዋወረበት የመጀመሪያ ዓመት ቆይታው አጃኢብ ያስባለ አቋም ነበር ያሳየው። ነገር ግን የሮቢን ቫንፐርሲ ከጉዳት ማገገም ተከትሎ ወደ ተቀያሪ ወንበር መውረዱ የራስ መተማመኑም አብሮ ወርዷል እየተባለ ይታማል። የአካውንቲንግ ምሩቁ ይህ ሞሮኳዊ አጥቂ በቀጣዩ ዓመት ወደ ፈረንሳይ ተመልሶ መጫወት እንደሚፈልግ መናገሩን ተከትሎ ለቀድሞ ክለቡ ቦርዶ ይፈርማል ተብሎ ይጠበቃል።