Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: ዋሊያዎቹ ኡጋንዳን ቢያሸንፉም ለቻን ዋንጫ ትኩረት ይስጡት

$
0
0

ከቦጋለ አበበ
Ethiopia national team
ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች የማይሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ (የቻን ) ጨዋታ ላይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ድልድል ከሩዋንዳ አቻው ጋር ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጀመሪያውን ጨዋታ አካሂዷል፡፡
ዋልያዎቹ ጨዋታውን በአስራት መገርሳ ብቸኛ ግብ አንድ ለባዶ ማሸነፍ ቢችሉም ለጨዋታው ብዙ ትኩረት እንዳልሰጡ መመልከት ተችሏል፡፡ በጨዋታው የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም በርካታ ግቦችን አስቆጥረው ወደ ሻምፒዮናው የሚያልፉበትን ሰፊ እድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡
በጨዋታው ዋልያዎቹ ከደቡብ አፍሪካው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በተሻለ ማራኪ እንቅስቃሴ ማሳየት ችለዋል፡፡ ኳስን መሠረት ያደረገ አጨዋወት መከተላቸውም ውበት ያለው ጨዋታ እንዲያሳዩ አስችሏቸዋል፡፡
ዋልያዎቹ በጨዋታው የመጀመሪያ አርባ አምስት ደቂቃ በተሻለ የኳስ ፍሰት በተቃራኒያቸው ላይ ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል፡፡ ለግብ የቀረቡ በርካታ ሙከራዎችን በማድረግም ከተቃራኒያቸው የተሻሉ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ያገኟቸውን መልካም አጋጣሚዎች ወደ ግብ መቀየር ባለመቻላቸው ካለምንም ግብዕረፍት ለመውጣት ተገደዋል፡፡
በመጀመሪያው አርባ አምስት ደቂቃ የጨዋታ ጊዜ በተለይም ተከላካዩ ዓይናለም ኃይሉና ሽመልስ በቀለ ያደረጉት ለግብ የቀረበ ሙከራ የሚያስቆጭ ነበር፡፡ በዚሁ የጨዋታ ጊዜ በግራ ክንፍ በኩል ምንያህል ተሾመ፣ በቀኝ ክንፍ ደግሞ ስዩም ተስፋዬ ያሻገሯቸው ጥሩ ኳሶችን ወደ ግብ የሚቀይር አጥቂ አለመኖሩ የሚያስቆጭ ሆኗል፡፡
በተከላካዮች በኩል የመዘናጋትና የጥንቃቄ ጉድለት ቢስተዋልም በአማካይ ስፍራ አስራት መገርሳና ሽመልስ በቀለ ማራኪ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ አጥቂው ዳዊት ፍቃዱም ጥሩ ተንቀሳቅሶ ኳስን ከመረብ ማገናኘት ሳይችል ቀርቷል፡፡
በሁለተኛው አርባ አምስት የጨዋታ ጊዜ ዋልያዎቹ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ቢሆኑም በኃይሉ አሰፋ ሃምሳ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ያሻገራትን ኳስ አስራት መገርሳ በግንባሩ ገጭቶ በግሩም ሁኔታ ካስቆጠራት ግብ ውጪ ተጨማሪ ግብ ከመረብ ማሳረፍ አልቻሉም፡፡
ዋልያዎቹ በጨዋታው እንደነበራቸው የበላይነት በርካታ ግቦችን አስቆጥረው የመልስ ጨዋታው ላይ የሚኖርባቸውን ጫና ማስወገድ ይችሉ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ያገኟቸውን መልካም አጋጣሚዎች ባለመጠቀማቸው በመልሱ ጨዋታ ጫና ውስጥ ገብተዋል፡፡
ዋልያዎቹ ከዝግጅት ጀምሮ ለሻምፒዮናው ብዙ ትኩረት እንዳልሰጡ በጨዋታው መመልከት ይቻላል፡፡ በርካታ ግቦች አስቆጥረው በቀጣዩ ጨዋታ ቢያንስ በጠባብ ግብ ተሸንፈው በቀጥታ የሻምፒዮናው ተሳታፊ ከመሆን ይልቅ በአንድ ግብ ብቻ በራስ መተማመን ታይቶባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በቀጣዩ ጨዋታ አደጋ ውስጥ እንዲገቡ ከማድረጉ በተጨማሪ ከሻምፒዮናው ከወዲሁ የሚሰናበቱበትን አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል፡፡
ሻምፒዮናው በፊፋ እውቅና ያለው እንደመሆኑ መጠን የአገራችንን የእግር ኳስ ደረጃ የት እንደደረሰ የምናሳይበት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በአህጉር ደረጃ የተዘጋጀውን ዋንጫ ማንሳት ባይቻል ጥሩ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ እግር ኳሳችንን በማነቃቃት ረገድ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
የመልሱ ጨዋታ ከሜዳችን ውጪ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሩዋንዳ አማሃሮ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡ ዋልያዎቹ በሻምፒዮናው ለመሳተፍ በዚያ ጨዋታ የአቻ ውጤት በቂያቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሙቫቢ ወይንም ተርቦቹ በመባል የሚታወቁት ሩዋንዳዎች ቀላል ይሆናሉ ብሎ መገመት ከባድ ስለሆነ ከወዲሁ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል፡፡
የቻን ሻምፒዮና በመጪው ዓመት በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት ይካሄዳል፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ ሦስት አገሮች የተሳትፎ ኮታ አላቸው፡፡ ከዋልያዎቹና ከተርቦቹ አሸናፊ በተጨማሪ ከቡሩንዲና ከሱዳን እንዲሁም ከታንዛኒያና ኡጋንዳ አሸናፊ የሚሆኑ አገራት የሻምፒዮናው ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
በቅድመ ማጣሪያው ጨዋታ ዋልያዎቹ ከኤርትራ ጋር ተደልድለው ኤርትራ ከሻምፒዮናው ራሷን በማግለሏ በፎርፌ በቀጥታ ወደ መጨረሻው ማጣሪያ ማለፋቸው ይታወሳል፡፡
በአሰልጣኝ ኤሪክ ኒሺሚያማ የሚሰለጥኑት ተርቦቹ በዚህ ሻምፒዮና ከሁለት ዓመት በፊት በመሳተፍ ከዋልያዎቹ የተሻለ ታሪክ አላቸው፡፡
ሻምፒዮናው ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ2009 በኮትዲቯር አዘጋጅነት ተካሂዶ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋናን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ዋንጫ አንስታለች፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደውን ሻምፒዮና ደግሞ ሱዳን አዘጋጅታ ቱኒዚያ አንጎላን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ሻምፒዮን እንደነበረች ይታወሳል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>