Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በረከት ስሞዖን “መርጋ አድማሱ”በሚል የብዕር ስም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ስለ ግንቦት 7ና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጻፉ

$
0
0

ኤርትራዊው አቶ በረከት ስምዖን መርጋ አድማሱ በሚል የብዕር ሥም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “«ግንቦት ሰባት» ያመነው ተላላኪነቱና አንድምታው” በሚል ርዕስ ጽሁፍ ማስፈራቸው ተጋለጠ። ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅርብ የሆኑ ሰዎች እንዳጋለጡት ከዚህ ቀደምም አቶ መለስ ዜናዊ እንዲሁ በብእር ስም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከመፃፍ በተጨማሪ “አዲስ ራዕይ” የተባለው የኢሕ አዴግ ጋዜጣ አዘጋጅ እንደነበሩ ከሞቱ በኋላ መገለጹን ጠቅሰዋል። አቶ መለስም ሆነ አቶ በረከት ስምዖን በብዕር ስም ስለአንድ ድርጅት በአዲስ ዘመን ከፃፉ የዛ ድርጅት እንቅስቃሴ አስፈርቷቸዋል ማለት ነው የሚሉት ይህን ያጋለጡት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ምንጮች ግንቦት 7 አሁንም የኢሕ አዴግ ራስ ምታት እንደሆነ ቀጥሏል ብለዋል።፡ኤርትራዊው አቶ በረከት ግንቦት ሰባትን እና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን በኤርትራ ተላላኪነት የከሰሱበት ጽሁፍ መርጋ አድማሱ በሚል በአዲስ ዘመን ጋዜጣ “አጀንዳ” በሚል አምድ ስር የጻፉት ጽሁፍ ደርሶናል ለግንዛቤዎ አቅርበነዋል።
ከመርጋ አድማሱ (በረከት ስምዖን)

አቶ በረከት

አቶ በረከት

«…100 ሺ ዶላሩን ሀገር ውስጥ ለሚካሄደው ሰላማዊ ትግልና ለዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ፣ 200 ሺ ዶላሩን ለኢሳት እንዲሁም 200 ሺ ዶላሩን ደግሞ ለወታደራዊና ለደህንነት ስራዎች አውሉት ተብለናል…» ይላል- ሰሞኑን ራሱን «ግንቦት ሰባት» እያለ የሚጠራውን የሽብር ቡድን የሚመሩት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር ያካሄዱት ምስጢራዊ የቴሌኮንፍረንስ ውይይት።«የዶክተር ኢኮኖሚስቱ» በራስ አንደበት የተነገረው የተላላኪነት ምስክርነት በዚህ ብቻ አያበቃም። ቀጥሎም ያለ አንዳች ሃፍረት «…እናመሰግናለን እግዚአብሔር ይስጥልን ስንላቸው፣ ‘ለምን ታመሰግኑናላችሁ? እኛ ለራሳችን ብለን እኮ ነው የምንሰጣችሁ አሉን!’…»ይላል።
ይህን የዶክተር ተብዬውን ‘ተላላኪዎች ነን’ የሚል አሳፋሪ አባባል በቦታው ተገኝቼ የሰማሁት እኔ የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ አይደለሁም። ሰሞኑን አይጋ ፎረም የተሰኘው ድረ-ገፅ ምንጮቹን በመጥቀስ ካሰማን ትክክለኛው የዶክተሩ ድምፅ ያዳመጥኩት እንጂ። እርግጥ አሸባሪው ቡድን በየስድስት ወሩ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ከሻዕቢያ እንደሚሰጠው ያመነበት ይህ አባባል፤ የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስትና ታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ የሽብር ቡድኑን አስመልክተው «…ግንቦት ሰባት በሻዕቢያ ነጭ ለባሽነት የሚንቀሳቀስ የሽብር ቡድን ነው…» በማለት ደጋግመው የተናገሩትን ዕውነታ የሚያረጋግጥ ነው- «ጉድና ጅራት ከበስተኋላ ነው» እንዲል የሀገራችን አርሶ አደር።
ታዲያ በእኔ እምነት በራስ ማንነታዊ ተግባር ላይ የተሰጠው ይህ የተላላኪነት ምስክርነት የአሸባሪው «የዶክተር ኢኮኖሚስቱ » ቡድን ሀገሩን የካደ እንዲሁም ለገንዘብና ለባዕዳን ጥቅም ሲል በፖስተኝነት ተቀጥሮ የሚሰራ ባንዳ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ የሚያስረዳ ብቻ አይደለም። ከዚህ ባለፈም ምንም እንኳን ከላይ ላዩ አዛዡና ፋይናንስ አድራጊው የአስመራው ቡድን ይሁን እንጂ፣ በኤርትራ መንግስት ትከሻ ላይ ዶላሩን በመያዝ ያለ ከልካይ እግሩን አንፈራጥጦ በመቀመጥ (የሽማግሌው የአቶ ኢሳያስ ትከሻ ምን ያህል እንደሚችለው ባላውቅም)፣ ሀገራችን ታላቁን የህዳሴ ግድብ እንዳትገነባ ለማደናቀፍ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችን መደገፍ ጨምሮ «…ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው»ያሉትና በአሮጌው ዘመን አስተሳሰብ የሚዳክሩት የግብፅ ገዥ መደቦች እጅም ከበስተጀርባው ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም ይህ እሳቤ በቀጥታ በካይሮ መንግስት ሚዲያዎች ሲስተጋባ የነበረ በመሆኑ ነው።
እርግጥ የተላላኪው ዶክተርም ይሁን የሽብር ቡድናቸው የትናንት ዳራ ሲፈተሽ ስብዕናቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ሃቆች ይገኛሉ፡፡ በትረ ስልጣን የሚያስገኝልኝ ከሆነ ከዲያቢሎስ ጋርም በሽርክና የመስራት ችግር የለብኝም ብለው ነበር አሜሪካ ቁጭ ብለው ስልጣን እንደ እህል ውሃ የሚርባቸውና የሚጠማቸው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ። ይሁንና ሰውዬውም ሆነ ድርጅታቸው ከትናንት እስከ ዛሬ ድረስ የኤርትራ መንግስት ተላላኪና ተወርዋሪ ድንጋይ በመሆን ተንቀሳቅሰውና ለመንቀሳቀስ ሞክረው አንዳችም ፋይዳ አላስገኙም። ወትሮም ቢሆን «ሊቁ ዶክተር» ሀገርን አጫርቶ ለባዕዳን የመሸጥ እንጂ የዲፕሎማሲ ዕውቀት ስለሌላቸው ሃሞታቸው ሁሌም እንደፈሰሰ ነው።
ያለ አንዳች ሰራዊት «ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው» የሚል አሮጌ ብሂልን ይዘው ኢሳትን በኤርትራ ዳረጎት ሰጪነት ያቋቋሙት የአሸባሪው ቡድን መሪ፤ ልክ እንደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ይካሄድ እንደነበረው ግብረ-መልስ በሌለው ባለ አንድ መንገድ የተግባቦት ስራ ታጥሮ በአሉባልታ የሚመራ ህዝብ ያለ የሚመስላቸው የሞኝ አዝማች ናቸው። በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ሳንባ የሚተነፍሱት አሸባሪው ዶክተር ከተራ ጉራ እና አሉባልታ በስተቀር ስለ ዴሞክራሲ የሚያውቁት አንዳችም ነገር የለም፡፡ ዴሞክራሲን እንደ ተላጠ የኤሌክትሪክ ሽቦ በመፍራት ራሳቸውን ለሽብርተኝነትና ለአመጽ ያዘጋጁና ኢትዮጵያን መበታተን ከሚሹ ወገኖች ጋር «ጎሮ ወሸባዬ»የሚሉ ግለሰብ ናቸው፡፡
አስመራ ውስጥ አቶ ኢሳያስ ሲያሰነጥሳቸው፤ መሃረብ አስይዘው እንዲያብሱ ወደዚያች ትንሽዬ ሀገር ምክትል አሸባሪያቸውን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን የመደቡት እኚህ ፀረ – ሠላም፣ ፀረ-ልማትና ፀረ – ዴሞክራሲ ግለሰብ፤ ምን ያህል የሀገራችን ደመኛ ጠላት መሆናቸውን የእዚህ ጽሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምንም እንኳን ሰውዬው በአሜሪካ ፔልሲቪኒያ ግዛት ውስጥ ፀንሰውት አስመራ በሚገኘው የሽብር ማህፀን ውስጥ የተገላገሉትን ባንዳ ቡድን ቢመሰርቱም፤ ይህን የሁከት ስብስብ በአግባቡ መምራት ያልቻሉ ናቸው አሸባሪ ቡድናቸው ሁለትና ሶስት ቦታዎች ላይ ተሰነጣጥቋልና።
ታዲያ ከሽብር ቡድኑ ያፈነገጡት ቡድኖች እንደሚገልጹት፤ አቶ አንዳርጋቸው በአቶ ኢሳያስ ትዕዛዝ ለ«ጓል አስመራ» (ለአስመራ ሴት) ተድረዋል ምናልባትም በዓላማም ይሁን በግብር ከማይገናኟቸው«እሳትና ውሃ» ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ተስማምተው ለመስራት ካላቸው ፍላጎት አኳያ ተመዝነው ሊሆን ይችላል። እንዲያውም የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ የአስመራው የሽብር አዝማች ዋና ምስጢረኛ ሆነው የአቶ ኢሳያስ አማካሪ የሆኑትን የአቶ የማነ ገብረአብን (መንኪ) ስልጣንን ሳይጋሩ የቀሩ እንደማይመስልም እኚሁ ተሰንጣቂዎች ይናገራሉ። እርግጥም አንድ ሀገሩን ለገንዘብ ሲል የሸጠ ግለሰብና ቡድን ከዚህ መሰሉ የመላላክ ተግባር የተለየ ምንም ዓይነት ቁም ነገር ሊሰራ አይችልም፡፡
ለነገሩ የእነ «ሊቁ ዶክተር» ፍላጎት ስልጣንን አቶ ኢሳያስ ጫንቃ ላይ ቁጭ ብሎ ለማግኘት የራስን ትከሻ ለአቶ ኢሳያስና ከጀርባቸው ላሉት የግብፅ ገዥ መደቦች ማከራየት ነው። ይሁንና ስልጣን በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ፉክክር እንጂ፤ የራሱ ስልጣን በቫይረስ ተጠቅቶ አንድ ሐሙስ የቀረውን የአስመራው የሁከት ቡድን አጋፋሪን «የጡት አባት» በማድረግ ሊገኝ አይችልም- የኢትዮጵያ ህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት ሆኖ ላለፉት አራት ተከታታይ ምርጫዎች የሚበጀውን ኃይል እየመረጠ መጥቷልና- እነ «ዶክተራችንን» እና መሰል ፀረ-ህገ-መንግስት ኃይሎችን እያንጓለለ በመጣል። እናም ሚዛናዊውና ሁሌም እውነትን ፈራጅ የሆነው የሀገራችን ህዝብ ሰውዬውንና ጀሌዎቻቸውን አንቅሮ ከተፋቸው ስምንተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ የተተፋ ነገር ደግሞ ተመልሶ ስለማይላስ በሀገራችን ህዝብ ስም ባይነግዱ በጄ ነው። ስለሆነም ተላላኪው ዶክተርና ባንዳው ቡድናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ህዝብ ይሁንታ ስልጣን ማግኘት «እንቁልልጭ» መሆኑን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
ውድ አንባቢዎቼ ስለ «ሊቁ ዶክተር» እና ስለ ሽብር ቡድናቸው ባንዳዊ ማንነት በመጠኑም ቢሆን ይህን ያህል ከተገነዘባችሁ ዘንዳ፤ አሁን ደግሞ «በአዲስ መልክ የሽብር ስራ ጀምረናል» በማለት በቀቢፀ-ተስፋ ሀገራችንን ለማተራመስ ከሻዕቢያ በዳረጎት መልክ የተቀበሉትን የ500 ሺ ዶላር ክፍፍል እና ቡድኑ እንዲያውለው ስለታዘዘው ስራ ብሎም ከበስተጀርባው ሊኖር ስለሚችለው የግብፅ ቡድን ጥቂት እናውጋ።…እስቲ በቅድሚያ ስብዕናቸውን መሬት ላይ አፈር ድሜ እስኪበላ ድረስ ፈጥፍጠው ተላላኪ የሆኑት «ዶክተር ኢኮኖሚስት» አንድ መቶ ሺህ ዶላሩን «ሀገር ውስጥ ለሚካሄደው ሰላማዊ ትግልና ለዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች» እንዲያውሉ ከታዘዙበት ጉዳይ እንነሳ። ማንም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚያውቀው የአሸባሪው ሰውዬ ቡድን ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በወሬም ቢሆን በኃይል ለመናድ የተነሳ ተላላኪ እንጂ፣ ሀገራችን ውስጥ ሰላማዊ ትግልን የሚያካሂድ አይደለም። በሻዕቢያ የአሸባሪነት ባህር መዝገብ ውስጥ እንጂ፣ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ በምርጫ ቦርድ ሰነድ ላይ ተመዝግቦም አይገኝም። ስለሆነም ‘እናስ ለየትኛው ሰላማዊ ትግሉ ነው በሀገር ቤት አማካይ ስሌት የሁለት ሚሊዮን ብር በጀት የመደበው?’ የሚል ጥያቄን ማንሳት በእጅጉ ያስፈልጋል።
የጽንፈኛው ፖለቲካ መንገድ በሀገር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችንም ይበክል ይሆን እንድል የሚያደርገኝ አንድሪው ሚለር የተባሉ ግለሰብ ‘ትራንፔት ዶት ኮም’ በተሰኘው ድረ-ገፅ ላይ እ.ኤ.አ. ጁላይ 13 ቀን 2013 ዓ.ም የሰማያዊ ፓርቲን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክተው እንደፃፉት፤ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ፀረ-መንግስት ሰልፎች በግብፅ የሚደገፉ ናቸው ማለታቸው ነው። ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚጠቅሱት የካይሮውን መንግስት የሚመራው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ (ዛሬ ችግር ላይ ነው ያለው) ዴሞክራሲያዊ አብዮቶችን ወደ እስልምና ጉዳዮች የመቀልበስ ልምድ ስላለው ነው ባይ ናቸው። ፀሐፊው አክለውም ‘የኢትዮጵያ ህዝብ ቀጣዩ የዚህ አጀንዳ ሊሆን ይችላልን?’ ሲሉም ይጠይቃሉ።
እርግጥም በእኔ እምነት በሰላማዊ ፓርቲነት ስም ተመዝግቦና ከመንግስት ፈቃድ ወስዶ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣው ሰማያዊ ፓርቲ በቅድመ-ሰልፍ ሂደቱ የሀገራችንን ገፅታ ጥላሸት ለመቀባት በማሰብ ማቅ ለብሼና ማቅ መስዬ የአፍሪካ መሪዎች ካላዮኝ ማለቱ እንዲሁም ፓርቲው ያዘጋጀው ሰልፍ በአብዛኛው በሃይማኖት ስም የሚነግዱ ፅንፈኛ ግለሰቦች አሊያም የዶክተር ብርሃኑ ዓይነት አቋም ያላቸው እንደ ዶክተር ያዕቆብ ኃ/ማርያም የመሳሰሉ የከሰሩ ፖለቲከኞች ተፅዕኖ ስር መውደቁ የሚስተር ሚለርን ምክንያታዊ አመክንዩ ጥያቄን ሚዛን እንዲደፉ ያደርገዋል። አዎ! የግብፅ መንግስት ዶላሩን ለሻዕቢያ፣ ሻዕቢያ ደግሞ የራሱን የድለላ «ኮሚሽን» በመውሰድ ትራፊውን ለ«ግንቦት ሰባት» ይሰጠውና ከዚያም የዶክተሩ ቡድን ደግሞ እንዲሁ የራሱን ኪራይ መሰብሰቢያ ኮሮጆ ከሞላ በኋላ ሽርፍራፊውን ለሀገር ውስጥ «ጉዳይ ፈፃሚዎቹ» ይልካል ማለት ነው። እናም ይህ ትስስር ቀደም ሲል የተጠቀሰው የ100 ሺህ ዶላር የሁከት ማስፈፀሚያና ገፅታን የማጠልሺያ በጀት እንዴት እንደሚውል የሚያሳይ ይመስለኛል።
ተጨማሪ አስረጅ እንካችሁ ልበል-በአንድ ወቅት የመድረክ አመራር አባል የሆኑት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሳት ብሏቸው ያሉትን አባባል። ፕሮፌሰሩ እንዲህ ብለው ነበር-«በውጭ የሚገኙ ዲያስፖራዎች 50 ዶላር እየሰጡ መንግስት እንድንገለብጥ ይፈልጋሉ።» …ታዲያ ይህ የመድረክ አባባል ሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አክብረን እንንቀሳቀሳለን እያለ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ህገ-መንግሰቱን በሚፃረር አግባብ መንግስት እንዲገለበጥ ከሚሹ ሃይሎች ጋር በመሞዳሞድና 50 ዶላር በነፍስ ወከፍ ከአክራሪ ዲያስፖራዎች በመቀበል ሲሰሩ እንደነበር የሚያረጋግጥ ነው። ምክንያቱም ራሳቸው እማኝነት የሰጡበት ጉዳይ ነውና።
ያም ሆነ ይህ ግን ከአሸባሪው ዶክተር ምፅዋት በመቀበል በአንድ በኩል ህጋዊነትን እየተከተሉ በሌላ በኩል ደግሞ ህገ-ወጥነትን የሚያጣቅሱና በሰላማዊ መንገድ እንንቀሳቀሳለን የሚሉ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ካሉ፤ ይህ ድርጊት ሽብርን መደገፍ ብቻ ሳይሆን በኤርትራ ነጭ ለባሽነትና በግብፅ ገንዘብ ሰጪነት በሀገራችን ላይ ለማካሄድ እየታሰበ ያለውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ የማደናቀፍ የማይሳካ ሴራ አካል መሆናቸውን የሚዘነጉት አይመስለኝም። ይህ ደግሞ ሀገር ውስጥ ቁጭ ብሎ (ለዚያውም በሰላማዊ መንገድ በመታገል ስልጣን እይዛለሁ የሚል ፓርቲ) የባዕዳንን ጥቅምና አጀንዳን ማስጠበቅ በመሆኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ይቅር የማይባል ነውር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። እናም ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ እንደማይወጣው ሁሉ፤ የሀገራችን ተቃዋሚዎች እንዲህ ያለውን ጅልኛ አካሄድን ለገንዘብ ብለው የሚመርጡ ከሆነ አደጋው ከአንዴም ሁለቴ መሰባበር ሊሆን እንደሚችል መገመት ያለባቸው ይመስለኛል። ለምን ቢሉ፤ የሀገራችን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ህጋዊና ህገ-ወጥ አካሄዶችን እያጣቀሱ በህዝብ ሀብትና ንብረት ላይ እንዲቀለድ የሚፈቅድ አንዳችም ዓይነት ቀዳዳ የሌለው በመሆኑ ነው።
የዚህን ፅሑፍ አቅራቢ በጣም ያስግረመኝ ሌላኛው ነገር «ግንቦት ሰባት» ከ100 ሺህ ዶላሩ ቀንሼ ለዲፕሎማሲያዊ ተግባሬ አውለዋለሁ ያለው አስገራሚ ልቦለድ ነው። ኧረ ለመሆኑ አሸባሪው ቡድን ምን ዓይነት ዲፕሎማሲ ነው የሚያካሂደው?- መቼም የዶክተሩ ቡድን ይህን ያህል ታዋቂ ባለመሆኑ የዲፕሎማሲያዊ ስራ ልሰራ እችላለሁ ማለቱ የቀልዶች ሁሉ ቀልድ ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም።
እርግጥ የሽብር ቡድኑ ዲፕሎማሲ ያካሂዳል ብለን ብናስብ እንኳን፤ ምናልባትም ተግባሩን ሊከውን የሚችለው አስመራ ውስጥ ቁጭ ብለው የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂን ትዕዛዝ ከሚጠባበቁ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር ብቻ ነው-እንዴት አድርገው ኢትዮጵያን ሊያሸብሩ እንደሚችሉ በወሬ ደረጃ ብቻ ለመመካከር። ግና እርሱም ቢሆን ጠብ ያለ ነገር ለሁሉም አላስገኘላቸውም፤ ከአሜሪካ በግብፅ በኩል አድርገው አስመራ እንደ ውሃ ቀጂ በየጊዜው እየተመላለሱ ቢማስኑም። ለነገሩ አሸባሪው ዶክተር ባይቀናቸውም ሀገርን እያስማሙ ለመሸጥ ላይ ታች ከማለት በስተቀር የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል የዲፕሎማሲ ዕውቀት የላቸውም። እናም ‘ዲፕሎማሲ ምንትስ’ የሚሉት ነገር ወግ ወጉ መያዙ መሆኑ ነው። መቼም ‘ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ’ የሚለውን ብሂል እዚህ ላይ ሳልጠቅሰው ባልፍ ራሳቸው ጋሼ ብርሃኑ የሚታዘቡኝ ይመስለኛል። ምክንያቱም ሰውዬው ለገንዘብ ሲሉ የማያስማመሙት ነገር ስለማይኖር ሊቀየሙኝ ስለሚችሉ ነው-ህሊናውን ለጥቅም ሲል የሸጠ ግለሰብ በትንሹ ሆድ ይብሰዋልና።
ዶክተር ብርሃኑ ከሻዕቢያ«አየር ተይዞባቸው» ከተቀበሉት 500 ሺህ ዶላር ውስጥ 200 ሺ ዶላሩን ‘ኢሳት’ ለተሰኘው የሽብር ማቀጣጠያ ጣቢያቸው እንዲያውሉት ታዘዋል። አንዳንድ ሰዎች ይህ የውሸት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ 22 ዓመት ሙሉ በእንቶ ፈንቶ ወሬ መኖር ባልሰለቻቸው በእነ ታማኝ በየነ አማካኝነት ከዲያስፖራው በሚሰበሰብ መዋጮ የሚንቀሳቀስ ይመስላቸዋል። አሁን ግን አሸባሪው ሰውዬ እውነቱን ግልጥልጥ አድርገው ነግረውናል-በራሳቸው አንደበት። አዎ! ዘር ከዘር እየከፋፈለ ህዝቦችን ለማባላት ቆርጦ የተነሳው እሳትና ኢሳት ባለቤትነቱ ‘የግንቦት ሰባት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት’ ነው። ‘ኢሳት’ የሻዕቢያዊያን ነው-በግብፆች የእጅ አዙር ዶላር የሚንቀሳቀስ ተላላኪ የሬድዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ። እናም ‘ኢሳት’ አንድም ሶስትም ነው ማለት ይቻላል። በቅርብ ርቀት ተላላኪው ዶክተር የሚቆጣጠሩት፣ ራቅ ብሎ ደግሞ አጀንዳው እንዲተላለፍለት የሚሻው የኤርትራ መንግስት ከአስመራ የሚመራው እንዲሁም ግብፅ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ በውጭ ያለው የሀገራችን ዲያስፖራ ቦንድ እንዳይገዛ ቅስቀሳ እንዲካሄድለት ገንዘብ እየከፈለው የሚያንቀሳቅሰው ባንዳ ጣቢያ።
ለዚህ አባባሌ ዶክተር ብርሃኑ ከሰጡን ተጨባጭ ማስረጃ ባሻገር ሌሎች አብነቶችንም መጥቀስ እችላለሁ። በቅርቡ የኤርትራ መንግስት በራሱ ወታደሮች የመፈንቅለ መንግስት ዓይነት ሙከራ ሲካሄድበትና ዓለም አቀፍ ታላላቅ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ሲዘግቡት ‘ኢሳት’ የተሰኘው በኤርትራ ዶላር መዳቢነት የሚሰራው የሽብር ጣቢያ ግን ዓለም ላይ የሌለ ይመስል አሊያም ነገሩን እንዳልሰማ በመቁጠር እርሱም በፊናው ልክ እንደ ሻዕቢያ መገናኛ ብዙሃን ትንፍሽ አለማለቱ የመጀመሪያው ተጠቃሽ አስረጅ ነው። ይኸውም ኢሳትም ይሁን የአስመራ በሬ ወለደ ሚዲያዎች በኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አጀንዳ እየተሰጣቸው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ነው። እርግጥም አንድ ገንዘቡን የከፈለ አካል ተላላኪውን እንዳሻው መቆጣጠሩ አግባበነት አለው። ተላላኪውም የተባለውን መፈፀም እንጂ ‘ለምን?’ ብሎ ሊጠይቅ አይችልም። አዎ! ዓለም የሰማውንና በአቶ ኢሳያስ ላይ የተካሄደውን መፈንቅለ-መንግስት ዓይነት ነገር፣ ሽብር መቀመሪያ ፋብሪካው ‘ኢሳት’ አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ የሆነው ለዚሁ ነው።
እጅግ በሚያስገርም ሁኔታ ግንቦት ሰባትና የሁከት ልሳኑ ታላቁን የህዳሴ ግድብ እንደሚቃወሙት መግለፃቸው እንዲሁም ሰሚ ባያገኙም ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ የሚውል የቦንድ ግዥን እንዳይፈፅሙ መወትወታቸው፤ እነዚህ ተላላኪዎች በተዘዋዋሪ መንገድ በግብፅ ለተከፈላቸው ዳራጎት ውለታ እየከፈሉ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው። ይህ ሃቅም አሸባሪው ሰውዬና የሽብር ጣቢያቸው ህሊና የሚባለውን ነገርዬአቸውን አሽቀንጥረው በመጣል ለከፈላቸው ባዕድ ሁሉ የሚሰሩ ግዑዞች እንደሆኑ የሚያስረዳ ነው።
ግና ታላቁ ህዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሐብት ነው። አዎ! የዘመን ቁጭታችንን ያረገበው ይህ ታላቅ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን መላው ኢትዮጵያዊ በአንድ ድምፅ የተቀበለው እንዲሁ ዝም ብሎ አይደለም-ከልብ ከመነጨ ስሜት እንጂ፡፡ የምንናገረው ነጭና ጥቁር ሃቅ መሆኑን ለማመልከት የግድ ዋስ መጥራት አሊያም ቃላት መደረት የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ሁሉም እንደየ አቅሙ፣ በጉልበቱ፣ በዕውቀቱ፣ በገንዘቡ የሚጠበቅበትንና ከሚጠበቅበትም በላይ የዜግነቱን ለማበርከት ቃል ገብቶ፤ ቃሉንም በተግባር መለወጥ መቻሉን ማስታወስ ብቻ በቂ ነው- ከምግባር የቀደመ ታማኝ እማኝ የለምና። ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለግድቡ ግንባታ የሰጠው ምላሽ እርግጥም በታሪክ ድርሳን ተከትቦ መቀመጥ ያለበት ይመስለኛል፡፡ የግድቡ ግንባታ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠሩም ክስተቱ የታሪካችን ልዮ ሁኔታ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው- ኢትዮጵያዊ እንደ አንድም እንደ ሰማንያ ሚሊዮንም ሆነው ዘብ የቆሙለት በመሆኑ። እናም የተላላኪዎቹ የአሸባሪው ዶክተርና የሽብር ልሳናቸው የቁራ ጩኸት እዚህ ግባ የማይባል መሆኑን ላኪውም ይሁን የላኪ ላኪው መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል። ከግድቡም ይሁን ከሌሎች ጉዳዮች አኳያ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተፈጠረው የብሔራዊ መግባባት ቋጠሮ እንኳንስ በአሉባልታ ቀርቶ በሌላም ፈታኝ ድርጊት ቢሆን የሚፈታ አይደለምና።
እስቲ አሁን ደግሞ ተላላኪው ዶክተር 200 ሺ ዶላሩን ለወታደራዊና ለደህንነት ስራዎች እንዲያውሉት መታዘዛቸውን ወደ ጠቀሱት አባባላቸው እንሸጋገር። እርግጥ ሰውዬው በሌለ ማንነታቸው በጀት የሚመድቡት ለማን እንደሆነ ባይታወቅም፤ አባባሉ ግን በአስቂኝነቱ ከ«ኮሜዲ ድራማ» ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ምክንያቱም የሽብር ቡድኑ አንድም ወታደር ስለሌለው የሚመድበው በጀት ለሌለ ነገር ስለሆነ ነው። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አንድ «ድርጅት» ገንዘብ የሚመድበው በገሃዱ ዓለም ላለ፣ ለሚጨበጥና ለሚዳሰስ አካል ነው። ለምናባዊ ኃይል የሚመደብ በጀት ሊኖር አይችልም። እናም የኤርትራ መንግስት ገንዘቡን በቀጥታ እየሰጠ ያለው ለዶክተር ብርሃኑ ተላላኪነት ወረታ መሆኑ ነው። ለምን ቢባል፤ ለእርሱም ይሁን የገንዘቡ ባለቤት ለሆነው የግብፅ መንግስት «ሰራዊት» ማለት ሀገራቸውን የካዱት እነ «ጋሼ ሽብሩ» እና እፍኝ የማይሞሉት ግብረ-አበሮቻቸው ናቸውና።
ያም ሆነ ይህ ግን ስለ ተላላኪው ዶክተር በሻዕቢያውያን ስለደረሰባቸው አሳፋሪ ውርደት ጥቂት ልበልና ፅሑፌን ልቋጭ። ሰውዬው ገንዘብ ስላገኙ ብቻ እየቀላመዱ የአስመራውን ቡድን አመራሮች ‘እናመሰግናለን፣ እግዚሐብሔር ይስጥልን’ ሲሏቸው፤ ሻዕቢያውያኑ ‘አንተ አታመስግነን፣ ተላላኪያችን እኮ ነህ፣ ዋናው ጥቅም የእኛ ስለሆነ ምስጋና ምን ይሰራል?’ በማለት አዋርደዋቸዋል። እንግዲህ ይታያችሁ!-አንድ የተማረ፣ ለዚያውም አሜሪካ ሀገር ውስጥ የሚያስተምር «ዶክተር ኢኮኖሚስት» እዚህ ግቡ በማይባሉ የሻዕቢያ አሽቃባጮች ‘ሀገርህን በመሸጥ ራስህን ያዋረድክ፣ ሞራልህንም ጫማህ ስር የከተትክ በመሆንህ ያንተ ምስጋና ከቁብ አይቆጠርም’ ሲባል!…አዬ ቅሌት! መቼም «የቅሌት ቀን አይመሽም» የሚባለው በእንዲህ ዓይነቱ ወቅት ሳይሆን አይቀርም።
እርግጥም አሸባሪውን ዶክተር ከዚህ በላይ የሐፍረት ካባን የሚያከናንባቸው ነገር ያለ አይመስለኝም-አንተ ከመላላክ ውጪ ስለ ምስጋና የማውራት መብት የለህም መባል። ለነገሩ ሰውዬው ለገንዘብ ሲሉ ራሳቸውን ዛሬም ይሁን ነገ እያዋረዱ በባዶ ሜዳ ላይ መንጎዳቸው አይቀርም-«ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም» እንዲሉ አበው። ግና እርሳቸውና ቡድናቸው «መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል» እንደሚባለው የባዕዳን ተላላኪ ሆነው ያለ አንዳች ውጤት በውርደት ላይ ውርደትን እየደራረቡ ቢቀጥሉም፤ ሀገራችንን እና ህዝቦቿ ግን የተያያዙትን የዕድገት ትልም አጠናክረው ይቀጥላሉ-የወሬ ሽብርተኞችና ላኪዎቻቸው ለሰኮንድም ያህል የልማት ዕቅዶቻቸውን የማደናቀፍ አቅሙም ይሁን ብቃቱ የሌላቸው መሆናቸውን አሳምረው ያውቃሉና።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>