Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የአቶ ከተማ ዋቅጅራ ፍርሃትና በኢትዮጵያውያን ሙስሊም ማህበረሰብ ላይ የተቃጣ እሳት የሚተፉ ብእራቸው ምላሽ –በመሃመድ ሙፍቲህ

$
0
0

በ መሃመድ ሙፍቲህ፣ ነጻ አስተያየት

የእስልምናን ካባ ለብሰው ህዝብን እርስ በርስ ማጋጨትም ሆነ መግደል ሀይማኖቱ አጥብቆ ይከለክላል ያወግዛል፣ ሰሞኑን ከወደ ኢራቅ የሚሰማው ዘግናኝ ዜና እንዲሁም ለማየት እንኳ የሚሰቀጥጠው ድርጊት በሙስሊሞች ስም የሚደረግ መሆኑ እጅግ ሀይማኖቱን ለማዋረድና ለማንቋሸሽ ብሎም በአለም ህዝቦች ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻና ስጋት እንዲኖር ሆን ተብሎ የታቀደበት እንደሆነ ታስቦና ታቅዶ የተሰራ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፣ይህን የምልበት የራሴን ተጨባጭ ምክንያት ከተለያዩ ሚድያዎች ካነበብኩትና ከሰማሁት ተነስቼ ምክንያቴን ማቅረብ እችላለሁ::
ISIS
ISIS ጠሀፊው እንዳሉት ግጭቶችን ምክንያት በማድረግ እራሱን እንዳስፋፉ ምክንያት ቢሆንም፣የተፈጠረበት ምክንያት ግን ጻሃፊው አቶ ከተማ ሆን ብለው ሳይነግሩን አልፈዋል፣መልሱን እራሳቸው ብቻ ነው ሊነግሩን የሚችሉት፣ ISIS ከመነሻው በእስራኤል የተፈጠረ የማፊያ ድርጅት ሲሆን፣ አመሰራረቱም በኢራን ና በኢራቅ ላይ ያለመረጋጋትና ውጥረት እንዲኖር ታስቦ በተለይ ኢራቅ በሳዳም ሁሴን ዘመን ከአሜሪካ ጋር በነበራት እልህ አስጨራሽ ግጭት ፊትዋን ወደ አሜሪካ ባዞረችበት ማግስት እዛው የተፈጠረ ስለመሆኑ አንድ የሚድል ኢስት የፓለቲካ ተንታኝ በቅርቡ አልጀዚራ ላይ ቀርበው አስተያየት ሲሰጡ አስታውሳለሁ::

እስራዔሎች በዚህ አያበቁም በሰላማዊ ትግል እና ዲፕሎማሲ ይታወቅ የነበረውን በያሲን አረፋት ይመራ የነበረውን ፋታህን ብዙ ዋጋ የተከፈለበት የፍልስጤም ነፃነት ከጫፍ ሊደርስ ሲል በተቃረበበት ወቅት፣ የፍልስጤም ነጻነት፣በሰላማዊ ትግል ሳይሆን በመሳርያ መሆን አለበት ብሎ የሚያምነውን፣ ሃማስን ፈጥረዋል፣ እንደ ሂዝቦላህ ሁሉ፣ እስራዔሎች ሃማስን ሲፈጥሩት ከፍተኛ የሆነ መሳሪያ አስታጥቀውት ስለነበር የፋታህ ደጋፊዎች ልባቸው ለሁለት ተከፍሎ በመጨረሻም ለስልጣን መብቃቱን እኝሁ የፓለቲካ ተንታኝ አስረድተዋል::

ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል እንደሚሉት ሃማስ ስልጣን ሲይዝ መጀመሪያ ስትጮህ የነበረችው እስራኤል ነበረች የሰራቸውን ታውቃለችና፣ ያስታጠቀችው ጦር መልሶ እራሷን እንደሚወጋት ያሳሰባታለና፣እስራዔሎች በፍልስጤማውያን ላይ የሚያደርሱት ተመጣጣኝ ያልሆነ የግፍ ግፍ እንዳለ ሆኖ ዛሬ ወደ እስራዔል በሀማስ የሚወነጨፉት ሮኬቶች የእስራኤል የራሷ እንደሆነ ታምናለች፣ ነገር ግን ይህን እውነት መዋጥ ይከብዳታል፣
አሁንም ቢሆን ለቀጠናው አለመረጋጋት ወሳኝ ሚና የሚጫወተውን ISIS ፈጥራ ኢራንን ለመበታተን ያልተሳካላት እስራዔል ሮኬቶቹ የ ኢራን እንደሆኑ ከመግለጽ አልተገደበችም፣ በቅርቡ ኒዎረከ ታይምስ ይፋ በተደረገ የድህረ ገጽ የቪዲዬ መረጃ፣ ISIS ክርስቲያኖችን ብቻ ሳይሆን ሙስሊሞችንም ታርጌት እንደሚያደርግ በተሰራጨው ቪድዬ ያሳያል፣በምስሉ እንደሚታየው አንድ ISIS አባል በጭነት መኪና ሙሉ ተቀጣጣይ ነገር ይዞ ሙስሊሞች በብዛት የሚገበያዪበት መንደር ገብቶ እራሱን እንዴት አጥፍቶ እንደሚያጠፋ ሲያሳይ የማይታመን ፈረንጀቹ live show የሚሉትን አይነት ድፍረት የተሞላበት ድርጊት አሳይቶ እራሱንም አጥፍቶ አለምን ጉድ አሰኝቶአል፣ለዚህም ይመስላል ባራክ ኦባማ ሳይቃጠል በቅጠል አይነት እርምጃ በ ISIS እርምጃ መውሰድ የጀመሩት::

ዛሬ በሙስሊም ሽፋን የሚፈጠሩት አሸባሪ ድርጅቶች በምእራባዊያን ጥቅም ላይ ከዋሉ ቦሃላ ማብቂያቸው ሲደርስ፣ አሊያም ሲያኮርፏቸው መለስው ሰላማዊው ህዝብ ላይ አሊያም ፈጣሪያቸው ላይ ጦር የሚመዙት፣ለምሳሌ አልቃኢዳ አሜሪካኖች ሩቅ ምስራቅ ላይ ሩሲያ ያላትን የበላይነት ለማኮላሸት በ ሲ አይ ኤየተፈጠረ ድርጅት እንደሆነ ይነገራል፣ ሱማሊያ ከዚያድ ባሬ ቦሃላ ብትንትኗ ወጥቶ በሰፈር አንጃ በምትመራበት ወቅት ብዙ መንደሮችን ተቆጣጥሮ የነበረውን አንዱን ቡድን ለመበታተን አልሸባብ በ ሲ አይ ኤ ተፈጥሮአል፣ ሲ አይ ኤ በዚህ አያበቃም በነዳጅ ሀብቷ እና በህዝብ ብዛቷ የምትታወቀው የብዙ ብሄር ብሄረሰብ ባለቤት የሆነችውን ትልቌን ናይጄሪያ ከፉፍሎ እና አድቅቀወ ለመግዛት እና ለመገነጣጠል ቦኮ ሃራምን ፈጥረውት ሲደግፉት ኖረዋል፣ ይህንን አንድ የናይጄሪያ የፓለቲካ ሙሁር ከአንድ መንደር በ ቦኮ ሃራም ታግተው የተወሰዱ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ልጃገረዶችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ጠቅሰዋል::

በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቅሰው የማላልፈው ነገር አሜሪካኖች ሻእቢያንና ወያኔን ጥፍጥፍ አድርገው ሰርተዋል፣እነሆ መከራቸውም ለኛ ከ ኢስ ኢስ በላይ ሆኖ ተርፏአል፣ በአጠቃላይ ወደ ድምዳሜው ስንደርስ ይህ ፖለቲካና የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል የሚደረግን ነገር ኪሳራው ሲበዛ ከእስልምና ሃይማኖት ጋር መያያዙ እጅግ አስከፊ ወደ ሆነ ግጭት ሊያመራ ይችላል፣በዚህ ጉዳይ ላይ አንዱ የ አንዱን ሃይማኖት ከመኰነን ይልቅ በቂ እውቀት ግንዛቤ ጨብጦ መውቀስም ካለበት ወቅሶ መተራረምም ካለበት ተራርሞ ከወዲሁ ሊባንን ይገባል፣ በተለይ በሃገራችን ለብዙ ዘመናት ተቻችለን ከመኖራችን አንጻር እንዲህ አይነቱ አስቀያሚና ሰብአዊነት የጐደለው ወሬ ማራገቡ ተገቢና የማይመጥን ነው ብዬ አምናለሁ፣ኢስላም ሰላም ነውና::

ኢስላም የእዝነትና የሰላም ሃይማኖት ነው፣ጌታችንም የእዝነት ጌታ ነው፣የሰራንው ወንጀል ቢከብደን የብናኝን ያህል እንኳ ቢሆን በሱ ተስፉ እንዳንቆርጥ ያደረገንን ጌታ ስም ጠርቶ፣ ሰዎችን መግደል አይደለም መበደል እንኳ ቢሆን ትልቅ ሀጢአት ነው፣ የሰዎችን ወንጀል ማላከክ ትልቁን ሃይማኖታችንን እንደሚያከስመው ጠሃፊው ጠንቅቀው ሳይረዱ የሚቀር አይመስለኝም፣ ሌሎች በእኛ ሃይማኖት በእውቀታቸው ጥግ ሲሳለቁብን ፣ እንዲሁም እንደፈለጉ ሲፈነጩ፣ ያሻቸውን ሲጥፉ አይቶ እንዳላየ መሆንም፣ በእኔ እምነት ችግሩ ይበልጥ እንዲበረታ መፍቀድ ማለት ነው፣አላህ የማይገዙትን ባሪያዎችንም ሆነ ሰዎችን ቅጡልኝ ብሎ የትኛውም የቁርአን አስተምህሮት ላይ አልታዘዘምም፣ አልተገለጸም፣ የሰዎችን ህይወት እንደዚህ ማጥፋት ይቅርና፣ የራስንም ነብስያ ቢሆን ማጥፉት አይቻልም፣እውቀታችን ከሰዎች ስሜትና ፍላጐት ጋር ሳይሆን በቍርአንና በሃዲስ ላይ ሲሆን አንድን ሰው ሙሉ ሙስሊም ያስብለዋል::

እኔ ሙሉ ሙእሚን ባልሆንም፣ ፍርድ ግን ከአላህ መሆኑን ከልጅነቴ ጀምሮ ዘር ማንዘራቸው ሙስሊም የሆኑት ቤተሰቦቼ አስተምረውኛል፣በእስልምና ስም በተለይ የነብያችንና የአላህን ትልቅነት ተናግሮ የሰው ልብ አውልቆ የሚበላ ሙጃሂዲን ማየት ለእኔ ከአውሬነት አይተናነስም፣ የነብያችንና የአላህን ትልቅነት ተናግሮ ሰዎችን በጅምላ የሚጫረስ አጥፍቶ ጠፊ አላህ እራሱ የሚቀጣው ይመስለኛል፣ እውነት ነው ከፓለቲካው ጀርባ የተቃጣው እስልምናን የማራከስ ተግባር የሚከናወነው፣ በእንደዚህ አይነት ሙጀሂድኖች ነው::

የ ኢስኢስ ም የማፊያ ተግባር፣ ከእስልምና ያፈነገጠ ተግባር ባይሆን ኖሮ፣ በአለም ላይ ያሉ መሪዎች ተሰባስበው፣ሀይማኖቱን ተከታይ እንዳይኖረው ማድረግ በቻሉ ነበር፣ ነገር ግን ፓለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት ብለው የከፈቱት ቀዳዳ አሁን መድፈን የተቻላቸው አይመስልም::

አለምን፣ ኢስኢስ የሚመራት ይመስል፣ ሁሉም ድምጻቸውን ማጥፉታቸው የሚገርም ነው፣ እስቲ እራሳችንን አንድ ጥያቄ እንጠይቅ፣ የት አለ እስቲ የፈረንሳይ ጦር የጋዳፊን መንግስት፣ ከዙፋኑ ያስለቀቀ፣ የት አለ የታላቌ ብርቴን ጦር፣ የት አለ እስቲ የአሜሪካ ጦር ታላቍን ሳዳም ሁሴን ለስቅላት ያበቃ፣ የት አለ እስቲ የእስራኤል ሳይንሳዊ የጦር ሃይል ሚሊየን ጊዜ የሰው ድንበር እየጣሰ ህጻናትን የሚገለው፣ ምነው ኢስ ኢስ ሲሆን ለምን እጃቸው ዛለ፣ ይህንን ከጀርባው አንድ ግልጽ ያልሆነ ነገር እንዳለ፣ ለመረዳት አያስቸግርም፣በተለይ እስራኤል ከማንም በላይ ለሃገሯ አደጋ እንዳለው እያወቀች ለምን ኢስኢስን አይቶ እንዳላየ ሆና ዝምታን መረጠች፣ ብዙ ብዙ ማለት ይቻላላል::

ሆኖም ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለስ፣ አቶ ከተማ ዋቅ ጅራ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፣ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ግራና ቀኝ ሳያጤኑ፣ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ በጥቅል ፈርደዋል፣ ከላይ የጠቀስኴቸውን ቅድመ ጥቆማ ከግምት ውስጥ ያስገቡም አይመስለኝም፣
የ ISIS ሁኔታ አቅሎ ከ ማየት እና መደባበስ ሳይሆን ትክክለኛውን ነገር በመናገር በአገር ላይ የተቃጣውን ጥፋት ማስቆም ያስፈልጋል ቢሉም ቅሉ፣ ለሳቸው ገንቢ በሚመስል አስተያየት ያቀረቡት ሃሳብ፣ የኢትዬጵያውያን ሙስሊሞች ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፣እንደውም በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የተቃጣ እሳት የሚተፉ ብእራቸውን ለቀዋል ማለት ይቻላል::

 
በዚህ ጥሁፍ የገባኝ ነገር ቢኖር፣ሰውየው ምንም አይነት በእውቀትና በጥንቃቄ የቀረበ ማስረጃ ሳያቀርቡ፣ ሀገራችን ውስጥ ኢስ ኢስ ስለመኖሩ በርግጠኝነት መናገራቸው ነው፣ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ለተነሱ የሃይማኖት ግጭቶች፣ በተለይ በገጠሪቱ የሃገሪቱ ክፍሎች መንግስት አንድንም ሰው ጠርቶ ተጠያቂ አላደረገም፣ሁሉም ክስተቶች ከፕሮፓጋንዳ ውጭ በጉዳዩ ላይ በተጨባጭ የተሰራ አንድም ነገር የለም፣ እርሶ ኢትዬጵያን በምታህል የብዙ ሃይማኖቶች እንዲሁም ብሄረሰቦች ተከባብረውና ተፈቃቅደው በሚኖርባት ሰፊ ሃገር ውስጥ ባልተጨበጠ መረጃ አንድ ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ መልእክት ማስተላለፎ ተገቢ አይደለም፣ ዋጋ ስለ ሚያስከፍል::

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች፣ ሀይማኖታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣እርሶ ከሚያስቧቸው በላይ ለሃገር የሚቆረቆሩ ናቸው፣ ችግራቸውን ዋጥ
አድርገው፣መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ ከጀመሩ ቅርብ ጊዜ ከመሰላቹህ ተሳስታቹሃል፣ ድሮ ከአጤዎቹ ዘመን ይጀምራል፣አጤ ዬሀንስ ኢትዬጵያውያን ሙስሊሞችን በአደባባይ ቢያርዱም፣ ጃንሆይ ሀገራቸው ውስጥ ሙስሊም ኢትዮጵያዊ የሚባል እንደሌለ በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ አቶ መለስም የ አልቃይዳ ሴል አገኘሁ ቢለንም፣ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በሁሉም መንግስታት የቀረበባቸውን ክስና በደላቸውን ረስተው በሃገራቸው ጉዳይ ላይ የራሳቸውን አስተዋፅ አበርክተዋል፣ ሃገራቸውን እንደማንኛውም ዜጋ ይወዳሉ፣እነሱን በሃገራቸው ጉዳይ የተለየ አመለካከት እንዳላቸው ማሳየት ከቅን ልቦና የማይመነጭ ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል፣ ሌላው ሳላነሳው የማላልፈው ነገር አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች የሙስሊም ድምጽ የሆኑትን መፍተሄ አፈላላጊዎችን ከኢስ ኢስ እኩይ ተግባር ጋር በማገናኘት ከንቱ የሆነ ተቀባይነት የሌለው ማስረጃ ማስተላለፍም ሆነ ማሰራጨት፣ ከአንድ ወገን የማይጠበቅ አሳፋሪ ድርጊት ነው፣ ባልተጨበጠና ውሽት ላይ የተመረኮዘን ማስረጃ በማቅረብ፣ ዜጐች እርስ በርስ የጐሪጥ እንዲተያዪና ጥላቻንና ግጭትን ከማትረፍ ዉጭ የሚገኝ አንድም ጥቅም አይኖርም፣ በመጨረሻም ጠሃፊው፣ አሁን የምትጽፈው ጹሁፍ፣ ነገ ልጆችህ ሲያነቡት እንዳይቸገሩ አድርገህ ብትጽፍ መልካም ነው፣ ሃገራችንን ሰላም ያድርግልን፣፣
የካቲት 16/2007

The post የአቶ ከተማ ዋቅጅራ ፍርሃትና በኢትዮጵያውያን ሙስሊም ማህበረሰብ ላይ የተቃጣ እሳት የሚተፉ ብእራቸው ምላሽ – በመሃመድ ሙፍቲህ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>