Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“አሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን (አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን)”

$
0
0

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

Amsalu

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

በተለያየ ጊዜ በተለያየ የክህደት አስተምህሮ በመሰናከል በመውደቅ ከዚህች ሐዋርያዊት አንዲት ቤተክርስቲያ እየተለዩ በኑፋቄያዊ አስተምህሮ ጸንተው በመቀጠል ለዚህች አንዲት ሃይማኖት አንዲት ቤተክርስቲያን ጠላቶች የሆኑ ዲያብሎስን የሚያገለግሉ ከ40 ሽህ በላይ ይቆጠራሉ፡፡ ሃይማኖት ነንም ይላሉ፡፡ ክርስቶስ በወንጌሉ ሐዋርያትም በመልእክቶቻቸው እንደተናገሩት ግን ከአንዲቷ በስተቀር ይሄ ሁሉ ሃይማኖት ነኝ ባይ ዝግንትል ሐሰተኛና ዲያብሎሳዊ የክህደትና የጥፋት መንገዶች ናቸው፡፡ የዘመኑ ፍጻሜ ሲቃረብ ብዙዎች ሐሰተኞች መምህራን በየ እልፍኙ የሚሰብኩላቸው ሐሰተኞች ኢየሱሶች ሐሰተኞች ክርስቶሶች ይመጡ ዘንድ እንዳላቸውና ከእነሱም እንድንጠበቅ አስጠንቅቆናል፡፡ ማቴ. 24፤1-28  “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት” ኤፌ. 4፤5 “መንፈስ ግን በግልጥ በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንት ትምህርት እያዳመጡ ሃይማኖትን ይክዳሉ”  ብሏል 1ኛ ጢሞ. 4፤1-2 “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም የቀደመችውንም መንገድ ወዴት እንደሆነች ዕወቁ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች ዕወቁ በእርሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳቹህም ዕረፍትን ታገኛላቹህ እነሱ ግን አንሄድባትም አሉ” ኤር. 6፤16 “የመጀመሪያዋን እምነት እስከመጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና” ዕብ. 3፤14 “ነገር ግን ወንድሞች ሆይ እናንተ የተማራቹህትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና መሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንዳትመለከቱ እለምናቹሀለሁ፡፡ ከእነሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ እንደነዚህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ያታልላሉ” ሮሜ 16፤15-23 “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯቹህን ዋኖቻቹህን አስቡ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታቹህ በእምነት ምሰሏቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘለዓለምም ያው ነው ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፡፡ ልባቹህ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና ” ዕብ. 13፤7-9  “በጠበበው ደጅ ግቡ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጁ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና ወደ እሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ወደ ሕይዎት የሚወስደው ደጁ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ ነውና የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” ማቴ. 7፤13-14

ቤተክርስቲያን ካቶሊካዊያኑ በክህደት ውስጥ እንዳሉና ሰሐትያን እንደሆኑ አረጋግጣ አውግዛ የለየቻቸው ገና ከመለየታቸው 451ዓ.ም. ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ካቶሊካዊያኑ ለኢትዮጵያዊው ካቶሊካዊ መነኩሴ ብርሃነ ኢየሱስ በቅርቡ በየካቲት 7 2007ዓ.ም. የካርዲናልነት ማዕረግ ሰጥተዋል፡፡ ይንን ሹመት ተከትሎ አቦይ ማትያስ (የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ነኝ ባይ) የእንኳን ደስ አለዎት የደስታ መግለጫ መልእክትን በቅድስት ቤተክርስቲያን ስም  “…..አሁን የተሰጥዎት ከፍተኛ ሐዋርያዊ ሥልጣን በቤተክርስቲያን ለፈጸሙት የረጅም ዘመን አገልግሎት ሁነኛ ማረጋገጫ ነው” በማለት አስተላልፈዋል፡፡

እንግዲህ ይታያቹህ! አቦይ ማትያስ ይሄንን የሚሉት በካቶሊካዊያኑ ክፉኛ የተደቆሰችን የተሰበረችን መራራና አረማዊ ግፍ የተፈጸመባትን ቤተክርስቲያን እመራለሁ እኔም የዚህች ቤተክርስቲያን ዶግማና ቀኖና አማኝ ተከታይ ነኝ እያሉና በካቶሊካዊያኑ ላይ ያስተላለፈችውን ግዝት በመተላለፍ ነው ይሄንን እያሉ ያሉት፡፡ ካቶሊካዊያኑ በዚህች ሀገርና ሕዝብ ቁሳዊ መንፈሳዊ ጥበባዊ ሥልጣኔና ሰብአዊ ሀብቶቿ ላይ እስከዛሬ ያልተጠገነ ወደፊትም የማይጠገን ከባድ ስብራትና ኪሳራ ያደረሱ ከንቀታቸው የተነሣም ለዚህ አረመኔያዊ ድርጊታቸውም እስከዛሬ ድረስ ተገቢውን ይቅርታ እንኳን ለመጠየቅ ያልቻሉና ያልፈለጉ መሆናቸውን እያወቁ ነው እንግዲህ አቦይ ማትያስ ይሄንን ያደረጉት፡፡ እንደቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አስተምህሮ ቀኖናና ሥርዓት አቦይ ማትያስ በግልም ይሁን በቤተክርስቲያን ስም እንዲህ ዓይነት ቃል ከቤተክርስቲያን ለተለዩ ወገኖች ማስተላለፍ አይችሉም የተከለከለና የተወገዘ ነው፡፡ አድርጎት ለተገኘም በግዝት የታሰረና የኑፋቄ የክህደት ተባባሪ በመሆኑ ተወግዞ እስከመለየት የሚያደርስ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡

እዚህ ላይ አቦይ ማትያስን ልጠይቃቸው የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር፡- አቦይ ማትያስ ሆይ! የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምእመናን ከዚህ ንግግርዎ ምን እንዲረዳ ምን እንዲማር ነው ምን እንዲወስድ ነው የሚፈልጉት? እርስዎ እንዳሉት ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሐዋርያ መሆናቸውንና ካቶሊካዊያኑም ሐዋርያዊ መሆናቸውን ነው?  እናም እነሱን ተከተሉ ነው እያሉን ያሉት? ምእመናን በረታችንን ጥለን እንድንወጣና ወደ ተኩላት በረት ጥርግ ብለን እንድንገባ ነው? አየ አቦይ ማትያስ! ለካም ወያኔ ብቻ አይደሉም ካቶሊካዊ ተኩላም ነዎትና! ባለ ሁለት አፍ የጥፋት ሰይፍ ሆነው ነዋ የቤተክርስቲያንን አንገት ለመቁረጥ ተስለው የገቡት?

ቅድስት ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ካላት ሕግና ሥርዓቷን ከማስጠበቅ መንጋዋን ከመጠበቅ አንጻር በዚህ በተፈጸመባት ክህደት የሚጠበቅበትን እርምጃ እንደሚወስድ እንጠብቃለን፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

 

The post “አሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን (አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን)” appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>