(ዘ-ሐበሻ) “ወይ ጉድ!” ሊያስብል የሚችል ዜና እንደሆነ ይሰማናል። ይህን ዜና ከነምስሉ የበተነው በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሥር የሚታተመው ‘ፖሊስና እርምጃው” የተሰኘው ጋዜጣ ነው።
“ይህ የምትመለከቱት ፎቶ ሰሞኑን በምሥራቅ ሸዋ ዞን ቱግጃ ወረዳ መቂ ከተማ ውስጥ የተከሰተ ሲሆን በምስሉ ላይ የሚታየው ተከሳሽ ጅቡን አጥምዶ ከነሕይወቱ በመያዝ በአህያ ጋር ጭኖ መቂ ከተማ ውስጥ ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይ በመዘዋወር ላይ ሳለ በህብረተሰቡ ጥቆማ መሠረት በቁጥጥር ስር ውሏል። ተከሳሹ በምን ምክንያት እና ለምን ጅቡን እንደያዘው ለፖሊስ ያልገለጸ ሲሆን እንስሳትን በማንገላታት ክስ ተመስርቶበት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛል” ይላል ሰሞኑን ታትሞ የወጣው የፖሊስ እና እርምጃው ጋዜጣ ዘገባ።
“ሰው የሚያስብ እንስሳ” ነው ሲሉ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። የ እንስሳት መብት አይከበር እያልን ሳይሆን፤ የሚያስበውን ሰው በአሸባሪነት በመክሰስ፣ እንደፈለገው እንዳይንቀሳቀስ በማገድ የሚታወቀው መንግስት ደርሶ ለእንስሳት ተቆርቋሪ መስሎ በሚዲያ መቅረቡ የሚያስገርም ነው። ጅቡን አንገላታ የተባለው “እንስሳትን የማንገላታት አንቀጽ” ተጠቅሶበት ታሰረ፤ እነ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ነፃ አሳቢ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎችን እስር ቤት እያንገላቱ ያሉትስ? ነው ወይስ “መንግስታችን” የቆመው ለማያስቡ እንስሶች ብቻ ነው?
ዘ-ሐበሻ አስተያየትዎን ጨምሩበት ስትል ትጋብዛለች።