ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ከቦትስዋና ጋር ሎባትሴ ላይ ባደረገችው የመልስ ጨዋታ ላይ ሁለት ቢጫ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተውን ምንያህል ተሾመን አለአግባብ ማሰለፏን ተከትሎ በርካታ የደቡብ አፍሪካ የመገናኛ ብዙኃን « ተጫዋቹ አንድ ጨዋታ መቀጣት ሲገባው ሳይቀጣ ከደቡብ አፍሪካ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ ተሰልፏልና በጨዋታው የተመዘገበው ውጤት ተሰርዞ ደቡብ አፍሪካ ፎርፌ ማግኘት አለባት » የሚሉ ዘገባዎችን በስፋት አሰራጭተዋል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ በሰጡት አስተያየት « ኢትዮጵያ ተገቢ ያልሆነ ተጫዋች በማሰለፏ የምትቀጣው ተገቢ ያልሆነው ተጫዋች የተሰለፈበት ጨዋታ ውጤትን ብቻ ነው። በመሆኑም ተጨማሪ ሦስት ነጥብ ፈጽሞ አይቀነስባትም » ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ጋር በስልክ መነጋገራቸውንና ፊፋም በአንድ ጥፋት ሁለት ጊዜ ቅጣት እንደማይጣል እንዳረጋገጠላቸው አብራርተዋል።
የተለያዩ የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ረስተንበርግ፣ ኢትዮጵያና ቦትስዋና አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት ጨዋታዎች ላይ ሁለት የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርዶችን የተመለከተውና የሚቀጥለውን ጨዋታ ማረፍ ሲገባው ሎባትሴ ላይ ከቦትስዋና ጋር በተደረገው ጨዋታ የተሰለፈው ምንያህል ተሾመ ዋሊያዎቹ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ባለፈው እሁድ ባደረገችው ጨዋታ ላይ ተሰልፎ መጫወቱ ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ በስፋት ጽፈዋል።
መገናኛ ብዙኃኑ የአገሪቱ እግር ኳስ ማህበር ጉዳዩን ወደ አወዳዳሪው አካል ፊፋ እንዲወስደውና በጨዋታው የተመዘገበው ውጤት ተሰርዞ ለአገራቸው እንዲሰጥ አቤት እንዲልም ጠይቀዋል። ይህንን ሐሳባቸውን የሚደግፉ «ባለሙያዎችንም» ቃለ መጠይቅ በማድረግ ሃሳቡን ለማጉላት ሞክረዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ግን ይህ ሃሳብ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና የሕግ ድጋፍ የማይገኝለት መሆኑን ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ አክለውም ፊፋ የምንያህል ተሾመን ጉዳይ እንደሚያጣራ በላከው ደብዳቤ ላይ ተጨማሪ ቅጣት እንደሌለ ማረጋገጡንም አስታውቀዋል።
የፊፋ የዲስፕሊን መመሪያ አንቀጽ 19 ንጹስ አንቀጽ 5 መሠረት አንድ ጊዜ ፎርፌ የተሠጠበት ጨዋታ ለዳግም ቅጣት አይዳርግም እንደሚልም ተናግረዋል። ይህ ማለት ምንያህል ተሾመ በቦትስዋናው የመልስ ጨዋታ ላይ ማረፍ ሲገባው በመጫወቱ ቦትስዋና በፎርፌ ኢትዮጵያን ሦስት ለባዶ እንዳሸነፈች ተደርጎ ስለሚቆጠር ተጫዋቹ በደቡብ አፍሪካ ጨዋታ ላይ በመሰለፉ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ቅጣት አይጣልባትም።
ኢትዮጵያ ሁለት ቢጫ ያለው ተጫዋች በማሰለፏ ከሚቀነስባት ነጥብ በተጨማሪ ስድስት ሺ የስዊዝ ፍራንክ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልባትም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ቦትስዋናን በማሸነፍ ያገኘው ሦስት ነጥብና ሦስት ግብ ቢቀነስበትም ምድብ አንድን በአስር ነጥብና በአንድ ንጹሕ ግብ የሚመራ ይሆናል። ጷጉሜ ሁለት ቀን 2005ዓ.ም ከሜዳው ውጪ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር የሚያደርገውን የመጨረሻውን የዓለም ዋንጫ ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ ለቀጣዩ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ማለፉን ያረጋግጣል።
የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ቡድናቸው ጠንካራ ዝግጅት አድርጎ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ማጣሪያ እንደሚያልፉና ሕዝቡን እንደሚክሱ ከትናንት በስቲያ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በተያያዘ ዜና እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ያልተገባ ተጫዋች በማሰለፏ ምርመራ እየተደረገባት የምትገኘው ቶጎ ሎሜ ላይ ከካሜሩን ጋር ባደረገችውና ሁለት ለባዶ ባሸነፈችው ጨዋታ ላይ ያልተገባ ተጫዋች ማሰለፏን አምናለች።
የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ቱሳ ኮሚ ጋብርኤል ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት አሌክሲስ ሮማኦ የተባለው ተጫዋች ከካሜሩን ጋር በተደረገው ጨዋታ መሰለፍ እንዳልነበረበት አምነው ጉዳዩን በተመለከተ ለፊፋ ምንም ዓይነት ማስተባበያ እንደማያቀርቡ አሳውቀዋል።
↧
ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ተጨማሪ 3 ነጥብ አይቀነስባትም ሲሉ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ተናገሩ
↧