Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: ስለ እርግዝና መከላከያዎች 10 ነጥቦች

$
0
0

(በዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም ቱፈር)

ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከልና ራስዎን ከአባላዘር በሽታዎች ለመጠበቅ ሲባል የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀሙ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የእነዚህን መከላከያዎች እውነታዎች አውቆና ተረድቶ ጥቅም ላይ ማዋል እጅግ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ ስለማስብ ይህን ጽሑፍ አዘጋጅቼላችኋለሁ፡፡

pregnant test
1) በወር አበባ ጊዜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ቢደረግ እርግዝና ይከሰት ይሆን?

የወር አበባን የምታይ ጊዜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሴት የማርገዝ ዕድሏ የቀነሰ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ግን አይከሰትምለማለት አይቻልም፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት የወር አበባ ከማለቁ በፊት እንቁላል ሊፈጠር ስለሚችልና ወይንም ደግሞ የወንድ ዘር በማኅፀን ውስጥ እስከ 3 ቀን ወይንም ከዚያ በላይ የሚቆይበት አጋጣሚ ስለሚኖር ነው፡፡

2) ጡት ማጥባት እርግዝናን ይከላከላል?

ጡት ማጥባት የእንቁላል መፈጠርን የሚከላከል ቢሆንም የሚቆይበት ጊዜ ግን ለጥቂት ወራት ብቻ ስለሆነ ሰውነት ወደቀድሞ ሁኔታው በሚመለስ ጊዜ የማርገዝ ዕድልም አብሮ ስለሚመለስ ጡት ማጥባት እርግዝናን የሚከላከልብት ጊዜ ውስን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

3) የመጀመሪያ ጊዜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ላልተፈለገ እርግዝና ያጋልጣል?

አዎን! ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ላልተፈለገ እርግዝና ላያጋላጥ ይችላል ብለው የሚያስቡ አንዳንዶች ያሉ ቢሆንም ይህ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በመጀመሪያ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ሕመምና ደም መፍሰስ ሊያጋጥም የሚችል ቢሆንም እርግዝናን ከመከላከል ጋር ግን ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑን ተገንዝቦ ተገቢውን ጥንቀቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

4) የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ምን ያህል እርግዝናን ይከላከላሉ?

የወሊድ መቆጣጠሪያዎች በትክክለኛው መንገድ ከተተገበሩ ከ90% በላይ የሚሆን የመከላከያ አቅም ያላቸው ሲሆን ተአቅቦ ግን ጥርጥር የሌለው አማራጭ ነው፡፡ የወሊድ መቆጣጣሪያ ለመጠቀም በሚታሰብ ጊዜ የትኛውን ዓይነት እንደምንመርጥና አጠቃቀሙን በተመለከተ ሐኪምዎን ማማከር ተገቢ ነው፡፡

5) በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ ሁለት ኮንዶሞች ደርቦ መጠቀም በእርግጥ እርግዝናን የበለጠ ይከላከላል?

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ሁለት ኮንዶምን ደርቦ በመጠቀም የበለጠ ጠቀሜታ እንዳለው ያስባሉ ይህ ግን እጅግ የተሳሳተ እና ከእውነት የራቀ ሲሆን ይባስ ብሎ በሚፈጠረው ፍጭት (Friction) ምክንያት የኮንዶም መቀደድ በማስከተል ላልተፈለገ እርግዝና ለአባላዘር በሽታ የመጋለጥን ዕድል በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ሁለት ኮንዶሞችን ደርቦ መጠቅም አይመከርም፡፡

6) የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን መውሰድ ወዲያውኑ እርግዝናን ይከላከላል?

የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች አጠቃቀም እና የሚወሰዱበትን ጊዜ በሚገባ ማወቅ እርግዝናን ለመከላከል ጠቃሚ ነው፡፡ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን የወር አበባ በመጣ ከመጀመሪያው ቀን እስከ አምስተኛው ቀን ውስጥ መጀመር ወዲውኑ ከአልተፈለገ እርግዝና የሚከላከል ሲሆን፣ ከዚያ ጊዜ ውጭ ከመጀመሩ ግን ወዲያውኑ የመከላከል አቅም ስለማይኖረው ኮንዶምን መጠቀም አስፈላጊ ይሆናል፡፡

7) ሁሉም የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ከአባለዘር በሽታዎች ይከላከሉ ይሆን?

ከወሊድ መቆጣጠሪያዎች ውስጥ ኮንዶምን መጠቀም ብቻ ከአባላዘር በሽታ ራስን መከላከል የሚቻልበት ዋነኛው መንገድ ነው፡፡

8) የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች የሰውነት ክብደት ይጨምራሉ?

አንዳንድ ሴቶች የሰውነት ክብደት መጨመርን እንዳስከተለባቸው የሚናገሩ ሲሆን ምክንያቱም የምግብ ፍላጎትን መጨመርን ማስከተሉና ፈሳሽ በሰውነታችን እንዲቀመጥ ማድረጉ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ስለዚህም የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች መጠነኛ የሚባል የሰውነት ክብደት መጨመርን ያስከትላሉ፡፡

9) የወሊድ መቆጣጠሪያን መጠቀም መሃንነትን ያስከትላል?

አያስከትልም! ሆርሞኖችን በውስጣቸው የያዙ የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ለረጅም ጊዜ ከተወሰዱ መሃንነትን ያስከትላሉ ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም እነዚህን የወሊድ መቆጣጠሪያዎች መካንነትን እንደማያስከትሉ ሊያውቁት የሚገባ እውነታ ነው፡፡

10) ኮንዶምን በሌሎች ቁሳቁሶች መተካት ይቻላል?

በፍፁም አይቻልም! በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ ኮንዶምን በሌሎች እንደ ላስቲክ፣ ፈኛ፣እና የመሳሰሉ ቁሳቁሶች ተክቶ መጠቀም በፍፁም ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እና ከአልተፈለገ እርግዝናም ሆነ ከአባላዘር በሽታም በጭራሽ እንደማይከላከል ሊያውቁት ይገባል፡፡

እባክዎን ለወዳጅዎ ያካፍሉ!

ጤና ይስጥልኝ

The post Health: ስለ እርግዝና መከላከያዎች 10 ነጥቦች appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>