ኢትዮጵያውያን በታሪክ በተለያዩ ዘመኖች ከውጭ ወራሪዎች ጋር ተፋልመዋል። ሁሉም የውጭ ወራሪዎች ዘለቄታዊ ግባቸው ተመሣሣይ ነበር፦ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛታቸው አድርገው ሕዝቧን በባርነት ቀንበር ሥር መግዛት። በዚህ ረገድ አረቦች ከ፰ኛው (ስምንተኛው) መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ በእስልምና ኃይማኖት ማስፋፋት ሽፋን ተደጋጋሚ ወረራ ፈፅመዋል። ቱርኮችም በአረቦች እግር ተተክተው ከ፲፮ኛው (አሥራ ስድስተኛው) መቶ ክፍለ-ዘመን መግቢያ ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ ከሰሜን-ምዕራብ እና ከሰሜን አቅጣጫ በሱዳን፣ ከሰሜን-ምሥራቅ አቅጣጫ በቀይባሕር፣ እንዲሁም ከምሥራቅ እና ደቡብምሥራቅ አቅጣጫ ግራኝ አሕመድን በጦር ኃይል ድጋፍ እየሰጡ በግማሽ ቀለበት ኢትዮጵያን የከበበ ወረራ አካሂደው ነበር። የቱርኮች ወረራ ያከተመው አዳዲሶቹ ቅኝ ገዢዎች እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ እና ጣሊያን በ፲፱ኛው (አሥራ ዘጠነኛው) መቶ ክፍለዘመን አጋማሽ ጀምሮ ሲተኩ ነበር። ሆኖም ቱርኮች በኢትዮጵያውያን ላይ ትተውት የሄዱት የጥፋት ጠባሣ እስካሁን ድረስ አልጠፋም። በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን በ፲፰፻፷ (1860) ዓ.ም. እንግሊዞች «የታሠሩብንን እስረኞች እናስፈታለን» በሚል ሠበብ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አወጁ። በወቅቱ ከኢትዮጵያ መሣፍንት መካከል ለእንግሊዞች ወረራ ቀጥተኛ ድጋፍ ያደረጉት ጥሶ ጎበዜ (በኋላ አፄ ተክለጊዮርጊስ) እና ካሣ ምርጫ (በኋላ አፄ ዮሐንስ ፬ኛ) ነበሩ። የእንግሊዞች ወረራ ዓላማ እሥረኛ ማስፈታት ስላልነበረ፣ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በብዙ ድካም ያሰባሰቡትን ልዩ ልዩ ቅርስ የዘረፉትን ዘርፈው፣ አብዛኛውን አቃጥለው እና አውድመው ተመለሱ። እንግሊዞች ቆዬት ብለውም በአፄ ዮሐንስ ፬ኛ ዘመን ጣሊያኖች በቀይ ባሕር ዳርቻ ግዛት እንዲያገኙ እና ምፅዋን እንዲቆጣጠሩ አደረጉ፤ በኢትዮጵያም ላይ መሠሪ ጠላት ተከሉባት። እስከዛሬም ድረስ እንግሊዞች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን የጠላትነት ፖሊሲ አልሰረዙም።
ኢትዮጵያውያን ከጣሊያኖች ጋር ሁለት ጊዜ ተዋግተዋል፦ በመጀመሪያ በ፲፰፻፹፰ (1888) ዓ.ም. በአድዋ ሲሆን ከዚያም ከ፵(አርባ) ዓመታት በኋላ ለ፭(አምሥት) ዓመታት ከ፲፱፻፳፰ – ፲፱፻፴፫ (1928 – 1933) ዓ.ም.። ጣሊያኖችን በአድዋ ድል የነሣቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተመራው የኢትዮጵያ ጀግኖች ሠራዊት ነበር። ጣሊያኖች፣ እና በአጠቃላይም ቅኝ ገዢዎች፣ የአድዋን ድል ጠባሣ ለመፋቅ ለ፵(አርባ) ዓመታት ቂም ቋጥረው፣ አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ አድርገው ሲያበቁ በቤኔቶ ሙሶሎኒ በሚመራው የፋሽስት ጦር ኢትዮጵያን ፲፱፻፳፰ (1928) ዓ.ም. ዳግም ወረሩ። በ፭(አምስቱ) ዓመት ወረራ ፋሽስቶች ከአንድ ሚሊዮን የማያንሱ ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፈዋል። በተለይም በየካቲት ፲፪/፲፱፻፳፱ (12/1929) ዓ.ም. በአዲስ አበባ እና በአካባቢዋ ያደረሱት የግፍ ግድያ በታሪካችን ካጋጠሙን ዘግናኝ የጭፍጨፋ ድርጊቶች የሚስተካከሉት በግራኝ ዘመን እና አሁን በትግሬ-ወያኔ የአገዛዝ ዘመኖች የተፈጸሙት እና የሚፈጸሙት ናቸው።
የውጪ ወራሪ ኃይሎች በጣሊያኖች ፊታውራሪነት ሁለት ጊዜ ሲወርሩን ከመጀመሪያው በሁለተኛው የበለጠ ጉዳት እንዳደረሱብን ግልፅ ነው። ሆኖም የውጭ ኃይሎች በቀጥታ ወረራ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ቅኝ ለማድረግ እንዳልቻሉ ተገንዝበዋል። ስለዚህ በፋሽስት ዘመን በመለመሏቸው ባንዳ ሎሌዎቻቸው አማካይነት ኢትዮጵያን ለዘለቄታው ለማፈራረስ የሚስችላቸውን ተተኪ ዕቅድ ነድፈው ተግባራዊ ማድረግ ቀጠሉ። ለ፶(ሃምሣ) ዓመታት በአገር-በቀል ባንዶች በእነ ሻቢያ፣ ትግሬ-ወያኔ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ሲዳማ አርነት ንቅናቄ፣ ወዘተርፈ አማካይነት በመጠቀም በአዲስ ዘይቤ ኢትዮጵያን ገዝግዘው፣ በ፲፱፻፹፫ (1983) ዓ.ም. አገራችንን ለመቆጣጠር በቅተዋል። ስለሆነም ላለፉት ፳፬(ሃያ አራት) ዓመታት ኢትዮጵያን ለሁለት ከፍለው የሚገዟት ሻቢያ እና የትግሬ-ወያኔ የሚያከናውኗቸው ተግባሮች ሁሉ ጌቶቻቸው የውጭ ኃይሎች የሠጧቸውን መመሪያ ተከትለው እንደሆነ ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም።
ልክ የዛሬ ዓመት በዚህ ዕለት ሞረሽ ወገኔ አንድ ወቅታዊ መግለጫ አውጥቶ ነበር፦ «የየካቲት ፲፪ ሠማዕታትን ስናስብ» የሚል። ከአንድ ዓመት በኋላ ሁኔታው ሲታይ፣ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለእንደዚህ ዓይነቱ ጥሪ ተግባራዊ ምላሽ ሊሠጡ ቀርቶ፣ በተቃራኒው የትግሬ-ወያኔዎች የጥፋት ድርጊት ይበልጥ ተስፋፍቶ ይታያል። የእኛ የኢትዮጵያውያኑ ዝምታ እና ምንቸገረኝነት እንኳን ሕያዋንን ሙታንን ያስደነግጣል። ለመሆኑ በዚህ ዓይነት ቸልተኝነት ለተተኪው ትውልድ ምን እያወረስነው ነው? በዚህ ከቀጠልንስ ከተተኪው ትውልድ መካከል የየካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ሠማዕታትን የሚዘክር ይኖረን ይሆን? ብሎ መጠየቅ አግባብነት ይኖረዋል። ስለሆነም ቸልተኝነቱ ይብቃ! ሠማዕቶቻችንን እናስብ፣ ለእነርሱም ተገቢውን ክብር እንስጥ!
– See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/4771#sthash.3PaVn2ym.dpuf
The post ለመሆኑ ለወደፊቱ የየካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ሠማዕታትን የሚዘክር ተተኪትውልድ ይኖረን ይሆን? appeared first on Zehabesha Amharic.