በመጪው ግንቦት በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ካለፈው ምርጫ የተለየ ውጤት ቨመጣል ብለው እንደማይጠብቁ የተናገሩት የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው፤ በምርጫውም እንደማይወዳደሩ አስታወቁ፡፡ በ “ቴአትረ ቦፖለቲካ ፣ አሉባልታና የአገራችን ፖለቲካ ገመና” በሚል ርዕስ የፃፉት አዲስ መፅሀፍ በቅርቡ በገበያ ላይ እንደሚውልም ተናግረዋል፡፡
“የኢህአዴግን አካሄድና የተቃዋሚው ጎራ ያለበትን ሁኔታ ሳየው በግንቦቱ ምርጫ ካለፈው የተለየ ነገር ይመጣል ብዬ አላስብም” ያሉት አቶ ልደቱ፤ ኢህአዴግ ምርጫውን ሙሉ በሙሉ በራሱ ቁጥጥር ስር አድርጎ እንደቀጠለ ነው፣ ተቃዋሚው ጎራም ካለፉት ስህተቶቹና ድክመቶቹ ተምሮ ራሱን ለማሻሻል ያደረገው ብዙ ነገር የለም ሲሉ ምክንያታቸውን ገልፀዋል፡፡ “ድፍረት አይሁንብኝ እንጂ ተቃዋሚው ጎራ በፓርላማ ያለችውን አንድ መቀመጫ አስጠብቆ ይቀጥላል ወይ የሚለው በራሱ ለኔ ጥያቄ ነው” ሲሉም ጥርጣሬያቸውን አስቀምጠዋል፡፡
በተቃዋሚ ፓርቲ ዙሪያ የተደረጉ የትብብር ሙከራዎች ትግሉን የጎዱ እንጂ የጠቀሙ አይደሉም ሲሉ የሚሞግቱት አቶ ልደቱ፤ ፓርቲዎች በእንተባበር ጥያቄዎች ባይዳከሙ ኖሮ በአሁኑ ወቅት ሁለት ወይም ሶስት ጠንካራ ፓርቲዎች ይኖሩን ነበር ብለዋል፡፡
“ቴአትረ ቦለቲካ፡ አሉባልታና የአገራችን ፖለቲካ ገመና” የተሰኘ ሶስተኛ መፅሃፋቸው በቅርቡ እንደሚወጣ የጠቆሙት አቶ ልደቱ፤ መፅሃፉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አሉባልታዎች ዙሪያ እንደሚያጠነጥን ተናግረዋል፡፡ አሉባልታ የተቃውሞ ጎራውን ትግል ክፉኛ እንደጎዳውም ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል፡፡
The post ልደቱ አያሌው በቀጣዩ “ምርጫ” አልወዳደርም አሉ – “ካለፉት ምርጫዎች የተለየ ምንም ነገር አይመጣም” ሲሉ ምርጫውን አጣጣሉት appeared first on Zehabesha Amharic.