ሰሞኑን 35 ስደተኞች የያዘ ጀልባ የመን ሳይደርስ ሰጥሟል
በዓመት 200 ገደማ ኢትዮጵያውያን በበረሃ እና በባህር ጉዞ ላይ ሞተዋል
“በህጋዊ ምዝገባ የስራ ጉዞ መታገዱ ህገወጥ ስደትን አባብሷል”
በህጋዊ ምዝገባ ወደ አረብ አገራት የሚደረግ ጉዞ ከታገደ ወዲህ፣ በየመን በኩል እየተሰደዱ ለአደጋ የሚጋለጡ ኢትዮጵያዊያን መበራከታቸውንና ባለፉት ስድስት ወራት 47ሺ ያህል ስደተኞች የመን እንደገቡ RMMS ሰሞኑን ገለፁ፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን እና ሌሎች አለማቀፍ ድርጅቶች በጋራ ያቋቋሙት ይሄው ተቋም እንደሚለው፣ ዘንድሮ የስደተኞቹ ቁጥር ከአምናው በእጥፍ ይበልጣል፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ውስጥ 250 ስደተኞች የመን ለመግባት ሲሞክሩ፣ በባህርና በበረሃ ጉዞ ላይ መሞታቸውን ተቋሙ ጠቅሶ ከስደተኞቹ መካከል ሰማኒያ በመቶ ያህሉ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ሰሞኑን በባህር ጉዞ ላይ በተፈጠረ አደጋ አንድ ጀልባ መስመጡን የዘገበው ኤኤፍፒ፤ ጀልባዋ 35 ስደተኞችን አሳፍራ ነበር ብሏል፡፡ ከጉዞ አደጋ በተጨማሪ ስደተኞቹ የመን ከገቡ በኋላም ግማሽ ያህሉ በወሮበላ ቡድኖች እንደሚታገዱ የገለፀው RMMS፤ ከእገታ ለመለቀቅ ከቤተሰብ ገንዘብ እንዲያስልኩ ይገደዳሉ ብሏል፡፡ ለስደት የሚገፋፉ ዋና ዋና ምክንያቶችን ለማወቅ በሺ በሚቆጠሩ ስደተኞችና በትውልድ አካባቢዎቻቸው ላይ ጥናት ያካሄደው ይሄው ተቋም፤ በኢትዮጵያ ዋናዎቹ መንስኤዎች የኑሮ ችግር እንዲሁም ህይወትን የሚያሻሽል ነገር ፍለጋ ናቸው ብሏል፡፡ የፖለቲካ ችግርም የተወሰነ ጫና እንደሚፈጥር ተቋሙ ጠቅሶ፣ የደላሎች ድርሻ ግን ብዙዎች እንደሚያስቡት አይደለም፤ ከመቶ ስደተኞች መካከል በደላላ ግፊት ለስደት የሚነሳሱት ከሁለት ወይም ከሦስት አይበልጡም ብሏል፡፡
ብዙ ወጣቶች ወደ ስደት የሚያቀኑት አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ባለማወቃቸው ነው ለማለት እንደሚያስቸግር ተቋሙ ሲያስረዳ፤ በአመት ውስጥ ወደ የመን ከገቡት ኢትዮጵያዊያን መካከል ሩብ ያህሉ ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አገራቸው የተባረሩና ካሁን በፊት ስደትን የሞከሩ ናቸው ብሏል፡፡ ከቅርብ ወራት ወዲህ የስደተኞቹ ቁጥር የተባባሰበት ሌላው ምክንያት፣ በህጋዊ ምዝገባ ወደ ሳዑዲ አረቢያና ወደ ኩዌት ሲደረግ የነበረው የስራ ጉዞ በመንግስት መታገዱ ነው ብሏል – የተቋሙ ጥናት፡፡ በሌላ በኩል ሶማሊያ ውስጥ ከድህነት በተጨማሪ የሰላም እጦት ወጣቶችን ለስደት እንደሚገፋፋ ተቋሙ ገልፆ፤ በኤርትራ ደግሞ ከኑሮ ችግር ሌላ ዋነኛው ግፊት የመንግስት ከፍተኛ የፖለቲካ አፈና ነው ብሏል፡፡ በሊቢያና በግብጽ በኩል ወደ አውሮፓ ለመግባት ከሚሞክሩ ስደተኞች መካከል ከሶሪያዊያን በመቀጠል በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ኤርትራዊያን መሆናቸውን የጠቀሰው ይሄው ተቋም፤ ባለፉት አራት ወራት 15ሺ ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጵያ እንደተሰደዱ ገልጿል፡፡ ስደት የተባባሰው በድህነትና በአፈና ምክንያት አይደለም በማለት የኤርትራ መንግስት ሲያስተባብል፤ ወጣቶች እንዲሰደዱ በማድረግ አገሪቱን ኦና ለማድረግ አለማቀፍ ሴራ እየተካሄደብኝ ነው ብሏል፡፡
ምንጭ: አዲስ አድማስ ጋዜጣ
The post በግማሽ ዓመት 47 ሺ ኢትዮጵያዊያን ወደ የመን ተሰደዋል * በዓመት 200 ገደማ ኢትዮጵያውያን በበረሃ እና በባህር ጉዞ ላይ ሞተዋል appeared first on Zehabesha Amharic.