(ዘ-ሐበሻ) በአዲስ አበባ ከተማ በተለየ ስሙና ቦታው እንጦጦ የሚገኝው መንበረ ስብሃት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን ንብረት የሆነውን መሬት አዲስ የተመረጠው ሰበካ ጉባኤ ለባለሃብቶች በተጭበረበረ ሰነድ እየሸጠ ነው ሲሉ ምእመናን ብሶታቸውን አሰሙ::
“ለማን አቤት ይባላል? ለፈጣሪ እንጂ” የሚሉት እነዚሁ ተቆርቋሪ ምእመናን “በቅርቡ የተመረጡት የሰበካ ጉባዔ አባላት በቤተክርስትያን ስም ሁለት ማህተም በማሰራት የቤተክርስትያኑ ንብረት የሆነውን ቦታ በማጭበርበር እየሸጡት ነው፡፡” ነው ይላሉ:: ምዕመናኑ አክለውም “የቤተክርስትያኑ ሰንበቴ ቤት የነበረውን ክፍት ቦታ ለቤተክርስትያኑ ገቢ ማስገኛ በማለት ለግለሰብ ቢያከራዩትም ሰነዱን በማጥፋት ካርታ አስወጥተው እንደሸጡት ታውቋል:: አሁን ደግሞ የማቴዎስ ግቢ የሚባለውን የቤተክርስቲያኑን ቦታ አገልጋይ ካህናትን በማስወጣት ለግለሰብ ለ20 ዓመት ሊሸጡት እየተደራደሩ ነው:: ይህንንም ለማሳመን ሁለት ዓይነት የተጭበረበረ ሰነድ አቅርበዋል:: ስለዚህ የሚመለከታችሁ ሁሉ ይህንን የቤተክርስትያን ቦታ በመሸጥ ላይ የተመሰረተ እኩይ ተግባር በህግ አምላክ ብለን እናስቁማቸው::” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርቧል::
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስ አበባ መሬቶች ለሕወሓት ሰዎች እና ለውጭ ባለሃብቶች በልማት ስም ተቸብችበው ያለቁ በመሆኑና የመሬትም እጥረት ስላለ የቤተክርስቲያን መሬቶችን ወድ መቀራመቱ ተደርሷል:: በቅርቡ አዲስ አበባን በማስፋፋት በሚል ሰበብ በወጣው አዲስ ማስተር ፕላን የኦሮሚያ ገበሬዎች መሬት ተቀምቶ ለባለሃብት ሊሰጥ ነው በሚል በተነሳ የሕዝብ ጥያቄ በርካቶች የጥይት ራት መሆናቸው ይታወቃል::
እንጦጦ የሚገኝው መንበረ ስብሃት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን ንብረት የሆነውን መሬት አለአግባብ ለባለሃብት ቸብችበዋል የተባሉትን የሰበካ ጉባኤ አባላት ዘ-ሐበሻ ለማናገር ያደረገችው ጥረት አልተሳካም:: እንደደረሰን መረጃ ከሆነ ግን የቤተክርስቲያናችን ንብረት ሊሸጥ አይገባም የሚሉ ሰዎች ተቃውሟቸውን አደባባይ ይዘው ለመውጣት እየተዘጋጁ ነው::
The post እንጦጦ የሚገኝው መንበረ ስብሃት ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ንብረት የሆነው መሬት በተጭበረበረ ካርታ ለባለሃብቶች መሸጡ ተነገረ appeared first on Zehabesha Amharic.