ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዩን አካባቢ አንቀጸ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡ በልጅነቱ ከገጠር በእንግድነት ወደ ቤታቸው የሚመጡ ሰዎችን ያነጋገር ዘይቤ ለማስመሰል በመጣር ለቤተሰብና ለት/ቤት ጓደኞቹ ሲያሳይ ጎበዝ በርታ የሚል አስተያየት በማግኘቱ ወደ ኪነ ጥበቡ እንዲሳብ ምክንያት እንደሆነው ይገልፃል፡፡ የዚህ እትም የመሿለኪያ አምድ እንግዳችን ሁለገብ አርቲስት የሆነው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ አዘጋጅ እና ተዋናይ ንብረት ገላው ነው፡፡
በፈረንሳይ ኪነት ውስጥ የገጠሩን የሀገራችንን የቋንቋ ዘዬ ሲሰራ ያየው አንድ ሰው ከአብረሃም አስመላሽ ጋር እንዲገናኝ ያደርገውና ኢትዩጲያ ሬዲዩ ገብቶ ለመስራት እድሉን ይከፍትለታል፡፡ ከዚህ በኋላ በበርካታ በቴሌቭዥንና ሬድዮና የማስታወቂያ ስራዎች ላይ በድርሰት፣ አዘጋጅነትና በትወና ሰርቷል፡፡ ለአብነትም ሬድዮ ፋና ላይ በራሱ የቴአትር ፕሮሞሽን ስር በሚያቀርበው ‹ብሩህ ተስፋ› በተሰኘ አካል ጉዳተኞች ላይ በሚያተኩር ፕሮግራም ላይ ‹ጅረት› የተሰኘ ሃምሳ ሁለት ተከታታይ ክፍል ያለው ድራማ ደራሲ፣አዘጋጅ፣ተዋናይ በመሆን ፣ፖፕሌሽን ሚዲያ ሲያስተላልፈው በነበርው ‹መንታ መንገድ› የሬድዮ ድራማ ላይ በትወና፣ ኢትዮጲያ ሬድዎ የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ ከአብረሀም አስመላሽ ጋር ለረጅም ዓመት ጭውውት በማቅረብና በለያዩ የሲኒማ ፊልሞችና የመድረክ ቲያትሮች ላይ ሰርቷል፡፡
ንብረት ገላው በተለይም በህዝብ ዘንድ በደንብ ያስተዋወቀውና ተወዳጅ ያደረገው በአሁኑ ወቅት ማክሰኞ ማታ በኢትዮጲያ ቴሌቨዥን በሚቀርበው ‹ቤቶች› የቤተሰብ ኮሜዲ ድራማ ላይ በሚጫወተው ‹እከ› የተሰኘ ገፀ ባህሪ ነው፡፡ መጽሔታቸንም ‹ከእከ ደከ ማን ችሎት በብልጠቱም ሆነ በጉልበቱ ከወንድ በላይ አበጀ› ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡
ቁም ነገር፡- አንድ ሰው ምች መታኝ ቢልህ ምን ትመክረዋለህ?
ንብረት፡- ምስክር ነበር? ብዬ እጠይቀዋለሁ፡፡ ለመክሰስ! /…ሳቅ/፤ ወይም ከቻልከው ሂድና ግጠመው ነው የምለው ፤እና እኔ ሄጄ ልጣላለት ኖሯል!
ቁም ነገር፡- በሀገራችን የቤት ሰራተኞችና የጥበቃ ሠራተኞች የሚገባቸውን ያህል ቦታ ተሰጥቷቸዋል ብለህ ታምናለህ ?
ንብረት፡- በፍጹም! እኔ እንደውም አንዳንድ ጊዜ አረብ ሀገር ከፎቅ ላይ ተጣሉ ምናምን እያልን ስናማርር አንድ ቀን ግን ለምን ራሳችንን ዞር ብለን አናይም እላለሁ፡፡ እዚህም አገር ላይ እንኳ በገዛ ወገኖቻቸው ሰራተኛቸው ላይ ምግብ ቆልፈው የሚሄዱ፣የሚደበድቡና እንደውም ሰራተኛ ሊቀጥሩ ሲሉ ትማራለች ከተባሉ የማይፈልጉ ሞልተዋል፡፡ በጣም የሞላና የተረፋቸው ውሻቸውን በቂቤ እያሻሹ በጣም በሚያሳፍር ሁኔታ ለዘበኛቸው ከውሻ ያነሰ ምግብ የሚሰጡ አሉ፡ ፡ በዛው ልክ ደግሞ እጅግ በጣም ጥሩ ሰዎች እንደውም ለቤተሰባቸው እስከ መዳር የደረሱ ጥሩ ሰዎችም ገጥመውኛል፡፡ አሁን እኔ የምናገረው እንደ ሙያዊ አስተያየት አይወሰድብኝና ቤቶች ላይ የምናየው ግንኙነት ትንሽ ለቀቅ ይላል፡፡ ይህ ደግሞ የሆነው የሚሰራው የኮሜዲ ስራ ስለሆነ በታሪኩ ውስጥ የሰራተኞቹ ከቤተሰቡ ጋር ያላቸው ግኑኙነት እንደዚህመሆኑ ወሳኝ ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡ እንጂ እንደዛ መሆን አለበት ማለት አይደለም፡፡
ቁም ነገር፡- ገበጣ ፣ዳማ ፣ካርታ ልዩነታቸው ምንድ ነው ?
ንብረት፡- ምን አይነት የሚገርም ጥያቄ ነው የምጠይቂኝ? ገበጣና ዳማ የኢትዩጵያ ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡ በቅርቡ እንደውም አንድ ጥናት ላይ ተሳትፌ ነበር ፤‹የባህል ስፖርቶቻችን ለምን ቀሩ?› የሚባል እና ዳማም ኢትዮጵያ ውስጥ ጥንት ነገሥታቶች ይጫወቱት ነበር የሚልነገር አለ፤ ስለ ካርታ ግን አላውቅም፤ የሚመስለኝ የፈረንጆቹ ጨዋታ ነው ፡፡ እኔ እንደውም ካርታ ሲነሣ ቁማር ቀመስነቱ ነው ትዝ የሚለኝ (ይቅርታ ይደረግልኝና) /…..ሳቅ/፤ልዩነታቸው ካርታ በወረቀት ነው፡፡ ገበጣ በድንጋይ ነው በጠጠር፤ዳማም ጠጠር አለው፡፡
ቁም ነገር፡- ከቤቶች ድራማ ጋር በተያያዘ የገጠመህ ነገር አለ?
ንብረት፡- ምን የማይገጥመኝ ነገር አለ ?ብዙ ነው፡፡ ድንገት ስጠየቅ አይመጣልኝም እንጂ፤አሁን እኔ ቤቶች ድራማ ላይ ልክ በቀረፃ ወቅት ልብሱን አንዴ ከለበስኩ በኋላ እራሱን እከን የዘሩ ሞላ ዘበኛ ነኝ፤ ማንም ይምጣ ማንም
ትዕግስት ታደለ
በዚያ ገፀ ባህሪ ውስጥ ሁኜ ነው የማዋራው፡፡ እና አንዳንዴ በቀረፃ ወቅት ሐያት አካባቢ ነው የምንቀረጽበት ቤት፤እየሰራን እንዳለ ቁራሌው የሚሉ ይመጣሉ፣ ልዋጭ የሚል ይመጣሉ፤ የዛኔ ድምጹ ይረብሸናል፤ እኔ እረፉ ልል እወጣለሁ፤‹እባካችሁ ሥራ ይዘን ነው ዝም በሉ› ስላቸው ‹ባክህ አንተም ዘበኛ ነህ እኛም ቁራሌው› ይሉኛል፡፡ እንዲሁም እከን ሲያዩ በጣም የሚገረሙ ሰዎች አሉ፤በቅርቡ መኪናዬን አስነስቼ ስሄድ አንዲት ልጅ የእውነት በመገረም ዘበኛው እኮ ነው፡፡ በሚል ስትገረም አየኋት፤ ልክ ዘበኛ ሁኜ የባለቤቱን መኪና ሰርቄ እንደምነዳ አድርጋ ነው የቀወጠችው፤ እንደዚህ አይነት ነገሮች በተደጋጋሚ ይገጥሙኛል፡፡
ቁም ነገር፡- ሰዎች ወሽመጤን በጠሰው፤ ወሽመጤ ተበጠሰ ሲሉ እንሰማቸዋለን ፤ለመሆኑ ወሽመጥ የትኛው የአካላችን ክፍል ነው?
ንብረት፡- ብዙ ቦታ ወሽመጥ እንዳለ ላስብና፤ አንደኛው ብብት ላይ አለ ወሽመጥ /….ሳቅ/፤ ሁለተኛው ደግሞ እግርና እግር መካከል ውስጥ ወሽመጥ አለ፡፡
ቁም ነገር፡- በምድር ላይ ስትመለከተው እጅግ የሚያስደንቅህ ነገር ምንድ ነው?
ንብረት፡- ሰው ነው የሚያስደንቀኝ ነገር፡፡ እግዚአብሔር ሰውን እንዴት አድርጎ ፈጠረው የሚለው ነገር ያስደንቀኛል፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ይሄ ሰው ከዝንጀሮ ነው የመጣው የሚል ሳይንስ አይመቸኝም ፡፡ እንደዚህ አይነት ሳይንስን ሲያንስ ነው የምለው፤እግዚአብሔር ሰውን ምን ያህል ቢወደው ነው እንዲህ አድርጎ የፈጠረው እላለሁ፡፡ ከፈጠረው በኋላ ጥበብን ጥግ ድረስ ሰጠውና፤ አሁን አውሮፕላን ላይ ሆነን ስናይ አቤት የሰው ልጅ ስራ እንላለን፡፡ ግን ሰው መፍጠርና አንዲት ጣታችን እንኳን ተቆርጣ መልሶ መፍጠር አልቻልንም፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው መፍጠር ያስደንቀኛል፡፡
ቁም ነገር፡- እከን ብዙ ህፃናት ይወዱታል፤ ይህ የሆነው ለምን ይመስልሀል?
ንብረት፡- አዎ እኔ ብዙ ጊዜ ሕፃናት ፕሮግራም ላይ ተገኝቼ አውቃለሁ፤ ልክ ስገባ ይጮኻሉ፤ ይህንን እንግዲህ እኔ ክብር ለእግዚያአብሔር ብዬ ማለፍ ነው የምችለው፡፡ ምክንያቱም የእከን ገፀ ባህሪ አይተሽው እንደሆን የሚጮህ ነገር ነው፣ ጀው ጃዋ ዓይነት ነገር ነው፡፡ ሕፃናት ደግሞ እንደዚህ አይነት ሰውን የመፍራት ነገር ነው ብዙ ጊዜ የሚታይባቸው፤ የግርቢጥ ብዬ ልገልጸው እችላለሁ በአማርኛ እከን ወደውታል፡፡ እውነቱን ለመናገር ልጆች ላይ በትወና ግብት ማለት ይከብዳል፤እንደ አዋቂዎቹ አይደለም ነገሩ፤ማለት የምችለው ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ፕሮዳክሽኑን የጀመረው ጥላሁን ጉግሳ ወዳጄ በጣም ጀግና ሰው ነው ለኔ፤ወቅታዊ ኮሜዲ ተከታታይ ድራማን በድፍረት የጀመረ ሰው ነው፡፡ ከዛ ውጭ አዘጋጁ ይታገሱ ገስጥ ተጫኔና ሌሎችም ከፕሮዳክሽን ጀርባ ያሉት በሙሉ የነሱ አስተዋጽኦ እከን እንዲወደድ አድርጎታል፡፡
ቁም ነገር፡- ህይወትህን የምትመራው በዕቅድ ነው? ወይስ እንደ አመጣጡ?
ንብረት፡- እኔ ምን አስዋሸኝ? እንዳመጣጡ ነው የምኖረው /….ሳቅ/፤ የምን ዕቅድ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ከሞት በኋላ ቀጣዩ ምዕራፍ ምን ይመስልሀል?
ንብረት፡- እኔ ሰማያዊቷን እየሩሳሌምን እወርሳለሁ፡ ፡ ምክንያቱም እየሱስ ሞቶልኛል፡፡
ቁም ነገር፡- ከሰማኸው ውሸት ውስጥ በጣም ያስገረመህ ውሸት አለ ?
ንብረት፡- እንዴ ብዙ ውሸት፤እኔም እራሴ ስኖር ውሸታም ነኝ፤ዓለም እንዳለች በውሸት የተሞላች ነች፤ ስለዚህ የትኛውን ውሸት ለይቼ ልንገርሽ?
ቁም ነገር፡- አይዶል ላይ ተወዳደር ብትባል በምን ብትወዳደር ይሳካልኛል ትላለህ ?
ንብረት፡- በድብድብ! /….ሳቅ/ የሚችለኝ ካለ ይምጣ ፡፡
ቁም ነገር፡- የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እናድርግ ሲባል ምንድን ነው ወደ አዕምሮህ የሚመጣው?
ንብረት፡- ማድረግ ይቻላል፤ በጣም ቀላል ነው፡፡ እኔ ክርስቲያን ስለሆንኩ እግዚያአብሔር ሟችን በገነት አኑርልኝ እላለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ምን ይመጣብኛል መሰለሽ? ሰው አይደለሁ! ተንኮልም ወደ አዕምሮዬ ይመጣብኛል፡፡ በአካባቢሽ ያሉ ሰዎች ሀሳብሽን ሊሰርቁት ይችላሉ፤አንዳንዱ የሆነ ተመስጦ በራሱ ሙድ ውስጥ የሚገባ ሰው አለ፣ሀሜት የሚጀምርም ሰው አለ፤እነዚህ እነዚህ ነገሮች ሳይ ሐሳቤ ሊሰረቅ ይችላል፤ከራሴ ህሊና ጋር ስሆን ግን የሞቱትን ነፍስ ይማር እላለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- የዝና ጥቅሙ ይታወቃል፤ ጉዳቱስ ምንድን ነው?
ንብረት፡- እንደፈለጉ አለመሆን ፤ሰው በመሆን የምትፈጽሚያቸው ስህተቶች አሉ፤ አንዳንድ ጊዜ፤ያን ማድረግ አይቻልም፡፡ እኔ ግልፍተኛ ነበርኩኝ፤ያንን አሁን እህ….. ብዬ እተወዋለሁ፤ እንደምንም ችዬ እና ተወጣጥሬ፤ ይቺ በጣም ከባድ ነች፡፡ አንድ ጊዜ ከመገናኛ ጀምሮ አንድ መኪና መንገድ እየዘጋብኝ እየዘጋብኝ ይመጣል፤እኔም ችዬ ዝም አልኩት፡፡ መጨረሻ ላይ አልፌው ወደ ባልደራስ ጋር ልዞር ስል መልሶ ከፊቴ መጣና ተናገረኝ፤ተናድጄ የሆነ ኃይል ቃል ስናገረው በአካባቢው ከነበሩት ጎረምሶች መካከል አንዱ ‹ኧረ እከዬ አንተም ስድብ› ሲለኝ ‹ሂድ እኔ ሚካኤል ነኝ› አልኩት /..ሳቅ/ ይቺ ይቺ ናት ጉዳቷ፡፡
ቁም ነገር፡- ህይወት ምን አስተማረችህ ?
ንብረት፡- ብዙ ነገር፡፡ እኔ ነገን አላውቃትም ፤በእግዚያአብሔር ቸርነት እዚህ እንደደረስኩ አውቃለሁ፤ ተንገላትቼ ነው ያደኩት፤የረሐብ ጥጉን አውቀዋለሁ፤ከዛ ደግሞ አግኝቼ በግል ሄሊኮፕተር አልሄድኩም እንጂ የመዝናናት ጥጉንም አይቻለሁ፤ ስለዚህ ህይወት ከዚህ በላይ ምንም ልታስተምረኝ አትችልም፡፡ ከዚህ በኋላ ከኔ ምን ይጠበቃል የሚለውን ለማድረግ ነው የምጥረው፤ እንደሰው ስህተት ብሰራም አሁን ለህይወት ዋጋ እሰጣለሁ፤ታላላቆቼን አከብራለሁ፣ማህበራዊ ጉዳይ ላይ በደንብ እሳተፋለሁ፣እንደ አንድ አርቲስት በአካል ጉዳተኞች ላይ የኢትዮጵያ የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማህበር አምባሳደር ነኝ፤እንደውም በዚህ አጋጣሚ መጽሔታችሁን የሚያነቡ ሁሉ ብሔራዊ ማህበሩን እንዲጎበኙ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው የአዕምሮ እድገት ውስንነት የሌለበት ልጅ ላለመውለድ ዋስትና የለውም፤ማንም ሰው ደግሞ ባጋጣሚ
ድንገተኛ አደጋ ይህ እንደማይከሰትበትም ዋስትና የለውም፤ ስለዚህ ብሔራዊ ማህበራችን ከዘሪሁን ህንፃ ጀርባ ይገኛል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ መስራት የሚፈልጉ ሰዎች መጥተው እንዲያናግሩኝና አብረን እንድንሰራ እላለሁ፡ ፡ እና ህይወት እነዚህን እነዚህን ኃላፊነቶቼን እንድወጣ አስተምራኛለች፡፡
ቁም ነገር፡- የመጀመሪያ ፍቅር ከሁለተኛው በምን ይለያል?
ንብረት፡- አዎ! ብዙ ሰው እንደዚህ ይላል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ የሚሉትን ጠይቂያቸው እኔ አላውቅም /..ሳቅ/ ስለሁለቱም ፡፡
ቁም ነገር፡- በልጅነትህ በባህሪህ ምን አይነት ልጅ ነበርክ ?
ንብረት፡- በልጅነቴ ቀይ ልጅ ነበርኩ /…ሳቅ/፤በባህል ታንፆ የማደግ ነገር ነበር ቤተሰባችን ውስጥ፤ይህ ማለት ስማር እራሱ የመጀመሪያ ትምህርቴ ሀ. ሁ ነው ፤ፊደል ተማርኩት ለጥቆ አቦጊዳ ከዚያ መልዕክተ ከዚያ ደግሞ ዳዊት ደገምኩኝ፤ እንደዚህ እያልኩ መደበኛ ትምህርት ቤት ስገባ እንደ አሁኑ ዕውቀት ተኮር መመዘኛ ሳይሆን እጄን ጭንቅላቴ ላይ አድርጌ በእጄ ተቃራኒ በኩል ያለውን ጆሮዬን ንካ ተብዬ በቃ ደርሷል ተብሎ ነው የገባሁት፡፡ በባህሪዬ የተረጋጋሁ ልጅ አይደለሁም ፤ቶሎ አኩራፊ ነኝ፣ትንሽ ደግሞ ተደባዳቢ ቢጤም ነበርኩኝ፤ቶሎ ውጤት ፈላጊ ልጅ፣ ብዙ የምጠይቅ ነበርኩ በአጭሩ /..ሳቅ/፡፡
ቁም ነገር፡- ከዘሩ ሞላና አዛሉ ለቤተሰቡ ይበልጥ የሚያስበው ማነው?
ንብረት፡- ለኔ ሁለቱም እኩል ናቸው ፡፡ ዘሩ ሞላ ስናየው ዝም ብሎ ቋጣሪ ስግብግብ ይመስላል፤የሚንገበገበው ግን ለልጆቹ ነው ፡ ፡ ዘሩ በአሳማኝ ወጪ ብቻ የሚያምን ሰው ነው ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን አሳማኝ ወጪዎችን ጭምር መሸወድ የሚፈልግ ሰው ነው /..ሳቅ/ ፤ለመኖር ደግሞ ይሄ አስፈላጊ ነገር ነው ፡ ፡ አሳማኝ ያልናቸውን ነገሮች ትተን ወደፊት ደግሞ በርከት ብሎ ከዛ ይበልጥ አሳማኝ ነገሮች ሲመጡ ለነዛ ልናውላቸው እንችላለን፤እና ዘሩ ሞላ እንደዚያ አይነት ሰው ነው ፡፡ ደግም ነው፡፡ እከን ያህል እንቅልፋም ሰውዬ፣ትርፌን ያህል ሆዳም ሴትዮ፣ሻሼን ያህል ምላሳም ይዞ መኖር እንደቤተሰብ አባል፤ የዘሩን ደግነት ነው የሚያሳየው፡፡ አዛሉንም ካየናት ቀለል ያለች እናት ነች፡፡
ቁም ነገር፡- ሀገራችን በቀላሉ ከድህነት መውጣት ያልቻለችው ለምን ይመስልሀል ?
ንብረት፡- ለምዳው ነዋ! /…ሳቅ/ ፤ ለምዳው ነው የሚለው ቃል ከማሳቅ አንፃር ይታይልኝና፤እኔ ትልቁ ምክንያት ብዬ የማስቀምጠው ሰው ላይ አልተሰራም ፡፡ ከድህነት ለመውጣት ሰው አለማም ፡፡ የመስራት ባህላችን የደከመ ነው፡፡ ድሮ ይህችን ሐገር ቅኝ ግዛት ሊያደርጓት የፈለጉ ፈረንጆች ስለቱን የሚሰራውን ቀጥቅጦ ጎራዴውን የሚያበጀው፣መቆፈሪያውን ፣ማልሚያውን የእርሻ መሳሪያውን የሚሰራውን ቀጥቃጭ እያሉት፣ ሸማ የሚሰራውን ቡዳ ነው እያሉ፣ሸክላ የሚሰሩትንም እንደዛው እያሉ ማንነታችንን ወሰዱት፤ እኛም እስካሁን ቁጭ ብለናል ስንሰዳደብና ስንጣላ እንዲሁ አለን፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ በዘመናዊ እውቀት ሄደዋል ለመረጃም ቅርብ ናቸው፤ግን የማንነት ችግር በጣም አለ፡፡ ኢትዩጵያዊ የሚባለው ነገር በጣም ያሰጋል፤ በኪ ነጥበብ ስራዎቻችን ላይም የራሳችን የሆኑ ብዙ የሚሰሩ ታሪኮች እያሉን የውጭ አድናቂ ሆነናል፡፡ ሙዚቃችን ፣ፊልሞቻችን ፣የመድረክ ቴአትሮቻችን በውርስ ትርጉም እየተጨናነቁ ነው ያሉት፡፡ እና እነዚህ ነገሮች ተንከባለው ተንከባለው የሆነ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ እፈራለሁ፡፡ ክፉ ትንቢትም እየተናገርኩ አይደለም ስለዚህ ሰው መልማት አለበት እላለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- በመጨረሻ የጠቅላላ ዕውቀት ጥያቄ ነው የቀረን፤ የመጀመሪያው የአጭር ልብ ወለድ መጽሐፍ ደራሲ ማናቸው?
ንብረት፡- አላቃቸውም፡፡
ቁም ነገር፡- አመሠግናለሁ፡
The post “እከ ደከ ማን ችሎት በብልጠቱም ሆነ በጉልበቱ ከወንድ በላይ አበጀ” ይናገራል appeared first on Zehabesha Amharic.