Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ቁርሾ – (እውነተኛ የወንጀል ታሪክ)

$
0
0

crime
ይህ ታሪክ ለብዙዎች ድራማ እስኪመስላቸው ድረስ ሲያስገርማቸው የኖረ ታሪክ ነው፡፡ በሀገራችን በአብዛኛው ብሔሮች ዘንድ ሰፍኖ የኖረው ቂም በቀልና የጥቁር ደም ባህል ምን ያህል የሰው ልጅን አርቆ አሳቢነት እንደሚፈትንና ከሰብአዊ አስተሳሰብ እንደሚያወጣ ጭምር የሚመሰክር የወንጀል ታሪክ ነው ይሉታል ብዙዎች፡፡ ከአስር ዓመት በፊት የተፈፀመ ቢሆንም ወንጀሉን መዝግቦ የተቀመጠው ሰነድ ግን አሁን ድረስ ለሁሉም መማሪያ የሚሆነውን ቁም ነገር አስቀርቷል፡፡

1980 ዓ.ም
ደራ
ሰሜን ሸዋ

ፍቼን ተሻግሮ ጀሊሳን አልፎ ወደ ጎሐፅዮን በሚወስደው መንገድ ላይ የሚመጣው ደራ ከተማ ለስሙ ከተማ ይባል እንጂ የመሰረተ ልማትም ሆነ ለከተማ ብቁ የሚያስብለው መዋቅር የተሟላለት ስፍራ አይደለም፡፡ ደራ የሚኖሩትን ሰዎ የታችኞቹን ህዝቦች ‹ደሮዬ› ብለው ይጠሯቸዋል በተለምዶ፡፡ ደሮዬዎች በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች ሲሆኑ ‹ቆፍጣናና እንቢ ባይነት ባህሪያቸው የሆነ ነው› ይሏቸዋል ሲገልጿቸው፡፡ ከደገምና ከጀሊሳ አካባቢ ያሉ ሰዎች ሲመራቸውና ከሰው ተጣልተው ደም ሲቃቡ የሚሸሹት ወደዚህ ደራ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ደራ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ የነበረው ስፍራ በመሆኑ ለመሸፈት የሚመች አካባቢ ስለሆነ ነው፡፡ ደራ በአካባቢው ባሉ የኦሮሞ ተወላጆች ዘንድ እንደ ጀግና ምሽ የሚታይ ጫካ ነበር፡፡ (የዛሬን አያድርገውና)፡፡ ብዙዎች የጀግኖች ጀግና ነው እያሉ የሚያሞካሹትና በአፄ ኃ/ሥላሴ ጊዜ የነበረውን ግፍ ተቃውመው ከሸፈቱት የአካባቢው የኦሮሞ ተወላጆች አንዱ የነበረው ሀገሬ ቱሉ መደበቂያ ቦታ ነበር ይላሉ፡፡ ሀገሬ ቱሉ በአብዛኛው የደገምና አካባቢው ነዋሪ ዘንድ ‹የድሃ ጠበቃ› ሲባል በሌሎች ዘንድ ደግሞ ዘራፊ ሽፍታ ነው ይሉታል፡፡ እዚያ ደራ ጫካ ውስጥ መሽጎ የአካባቢውን ጭቃ ሹሞችና ባለቤቶች ድንገት አደጋ ጥሎ እየገደለና እየዘረፈ ለሌሎች ያከፋፍል ነበር ይባላል- ሀብትና ከብት፡፡
በዚህ አካባቢ ልማድ ጥቃት ክፉ በትር ነው፡፡ ባለነፍጥ የሆነው ህዝብ በደም ከተፈላለገ ያንን የጥቁር ደም ሰንሰለት የሚበጥስ አንዳች ነገር የለም፡፡ የለገሰ በዳ ታሪክም የሚመዘዘው ከዚሁ የመጠላለፍና የመጠባበቅ ማህበራዊ ተራክቦ ውስጥ ነው፡፡ ለገሰ በዳኔ በ1980 ዓ.ም የ26 ዓመት ወጣት ሆኗል፡፡ ነገር ግን እሱ የ2 ዓመት ልጅ ሳለ በ1956 ዓ.ም አካባቢ አባቱ በዳኔ ቱፋ እንዴት ህይወታቸው እንዳለፈ በአክስቱ ሲነገረው የኖውን ዕውነት ነው ይዞ ያደገው፡፡ እነሆ ያ ታሪክ፡፡

1956 ዓ.ም
መስከረም ወር

ደገም አካባቢ ባሉ የኦሮሞ ተወላጆች ዘንድ በታላቅ ጉጉት ይጠበቅ የነበረው የመስቀል በዓል እየተቃረበ ነው፡፡ ገና ነሐሴ አጋማሽ ላይ ክረምቱ ግም ብሎ እንደገባ ግም ብሎ እየወጣ ሳለ ነው አካባቢው በአደይ አበባና በለምለም ሜዳው ፍንትው ብሎ የሚታየው፡፡ ይህ የአዲስ ዘመን መምጫ ብስራት ለመቀበልና ለማቀባበል ወጣቶቹ ዱላቸውን ይዘው ጅራፋቸውን እያጮሁ ‹‹መስቀላ ሞቲን አያና›› ይላሉ፡፡ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ይህን የመስቀል በዓል ለማክበር ቀድመው የሚዘጋጁትና እየጨፈሩ የሚዘልቁት ቢያንስ ከ16 ቀን በላይ ለሆነ ጊዜ ነው፡፡ የመጨረሻው የመስቀል በዓል እስኪከበር ድረስ፡፡ ከዘመን መለዋጫ በዓለም በላይ የሆነ ክብር ያለውን ይህንን ቀን ለማክበር ወዲህ ወዲያ ሲሉ ከነበሩት ወጣቶች አንዱ ደግሞ በዳኔ ቱፋ ነው፡፡

በዳኔ የተዳረው ገና የ18 ዓመት ወጣት ሳለ ነው አባቱ ቱፋ ጎዳና በአካባቢያቸው የታወቁ ገበሬ ናቸውና በሰው ዘንድ ያላቸው ክብር የላቀ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ዘራቸው ከባላበትና ከፍ ካለው የኦሮሞ ብሔር ወገን ባይሆንም አቶ ቱፋ በኃይለኝነታቸው የሚነካቸውና የሚደርስባቸው የሌላቸው የተከበሩ ሰው ናቸው፡፡ እኚህ ሰው ከወለዷቸው አራት ልጆች መካከል አንደኛው ልጅ ብቻ ወንድ ሲሆን ሶስቱ ሴቶች ናቸው፡፡ በኦሮሞ ባህል ወንድ ልጅ ሲወለድ በከፍተኛ ስነ ስርዓትና በጥይት ተኩስ ነው ደስታ የሚገለፀው፡፡ ወንድ የወለደ አባት ‹‹የወንድ አባት›› ተብሎ ይከበራል፡፡ ይህ ኩራትም አቶ ቱፋ ቤት ገባ፡፡
ልጃቸውን በዳኔ አሉት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሙሉ መሆን የቻሉት የመሰላቸው፡፡ ለዚህ ነው በዳኔን በቶሎ የዳሩት፡፡ በዳኔ ወንድ ልጅ ወልዶ ለማየት የነበራቸው ህልም እንደተመኙት ከሁለት ዓመት በኋላ ተሳካላቸው፡፡ የ20 ዓት ልጅ ሳለ ካገባት ኮረዳ የመጀመሪያውን ልጅ አገኘ፡፡ በቤተሰቡ ዘንድ ደስታና ፌሽታ ሆነ፡፡ ለገሰ አሉት ይህን ልጅ፡፡ አቶ ቱፋ በዓይናቸው ሁለት ወንድ ልጆቻቸውን አይተው ደግሞ ሌላ እንዲመጣላቸው በመመኘት ላይ ሳሉ ነው ያልታሰበ ነገር የተፈጠረው፡፡ ልጃቸው በዳኔ አደጋ ውስጥ ወደቀ፡፡

በዚያን የፀደይ ወር መስከረም ጠብቶ መስቀል ሞቲን አያና ተከብሮ ሲያልቅ አንድ ሰው በበዳኔ ላይ ዓይኑን ጣለ፡፡ በዳኔ ገና የ22 ዓመት ወጣት ሳለ ሚስቱም ሁለተኛ ልጇን በፀነሰችበት ወቅት ቱሉ ሲጠብቀው የነበረው ቀን መጣለት፡፡ በዳኔን አብዝቶ ይጠላው ነበርና አንድ ቀን ከዚህች ዓለም ጋር ያለውን የኮንትራት ሕይወት ሊያቆራርጥበት አጥብቆ ይመኝ ነበር፡፡
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የበዳኔ ሚስት ናት፡፡ ጊፍቲ በአካባቢው ጎልማሶች ዘንድ ዓይን ውስጥ የገባችና ያም ይሄም የኔ በሆነች ብሎ የሚሳሳላትና የሚመኛት ሴት ነበረች፡፡ ይህች ወጣት ገና በ16 ዓመቷ ሊያገቧት የሚራኮቱባትን ጎረምሶች በመፍራት ከቤቷ ሳትወጣ ያደገች ናት፡፡ ይህ የመጣው ደግሞ አባቷ የተላከባቸውን ‹ልጅዎን ለልጄ› የሚል ጥያቄ ሁሉ አይሆንም ብለው በመመለሳቸው ሳቢያ ነው፡፡ ከጎረምሶቹ ሁሉ አብልጦ ይወዳት የነበረው ቱቦ በአባቱ በተመረጡለት ሽማግሌዎች አማካኝነት ልጅቷን አስጠይቆ የግሉ ለማድረግ ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም፡፡ ምንም አማራጭ አልነበረውም፡፡ በቁጭትና በንዴት መሀል ሆኖ አንድ ቀን ውጪ ቢያገኛት እንደሚጠልፋት እያሰበ ሳለ አስደንጋጭ ወሬ ሰማ፡፡ በዳኔ ሊያገባት ነው ተባለ፡፡ በዳኔ በእኒያ ባለግርማ ሞገስ አባቱ የተነሳ የተመኘው ተሳክቶለት የጊፍቲን አባት ስምምነት አግኝቷል፡፡ የጊፍቲ አባት ለአቶ ቱፋ ‹ልጅን ለልጄ› የሚል ጥያቄ አሉታዊ ምላሽ የሚሰጡበት ጊዜ አልነበራቸውም፡፡

ለስንቱ ከልክዬ እችላለሁ ብለው ለሚያከብሯቸው ወዳጃቸው ልጅ ፈቀዱ፡፡ በአካባቢው ይህ ጉዳይ ወሬ ሆኖ ተሰማ፡፡ ቱሉ አንጀቱ አረረ፡፡ በበዳኔ ሰርግ ጊዜ የአጨዳ ስራ አለብኝ ብሎ በማሳበብ በሰርጉ ላይ ሳይገኝ ቀረ፡፡ ወደ ሌላ ከተማ ዘልቆ ነበር የጠፋው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እሱም ሳያገባ በዳኔም የወንድ ልጅ አባት ሆኖ ሁለተኛ ልጁን ሊደግም ሲጠባበቅ ሳለ ነው ቱሉ ንዴት የገነፈለበትና ራሱን መቆጣጣር ያቃተው፡፡ የመስቀል በዓል ተከብሮ እንዳለቀ መስከረም 22 ቀን የሆነው ሆነ፡፡
ቱሉ አደፈጠ፡፡ በዳኔ ደግሞ ጀሊሳ ወደተባለ መንደር የሚወርድበት ጉዳይ እንዳለው መረጃ ደርሶታል፡፡ ከ6 ሰዓት ያላነሰ የሚያስኬደው የእግር መንገድ ተከትሎ ብቻውን እያንጎራጎረ ወደ መንገዱ የገባው በዳኔ ከ30 ደቂቃ በላይ ሳይጓዝ ነው ድንገት ጭው ባለው አፋፍ ላይ ቱሉ ከች ያለበት፡፡ ቱሉ በዳኔ ፊት ለፊት ቺኮዝ ጠመንጃውን ወድፎ ሲቆም በዳኔ ዓይኑን ተጠራጠረ፡፡ ቱሉ ሊገድለው እስኪፈልግ ድረስ ቂም ይይዝብኛል ብሎ አልገመተም፡፡ ይህን ቢያውቅ አባቱ ለገሰን ሲወልድ የሰጡትን ጠመንጃ ይዞ በወጣ- ለዚያውም ውውል ጠመንጃ፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ተቀደመ፡፡

በአንድ ጥይት ደረቱን የበሳው ተኩስ የኋልዮሽ ቁልቁለቱ ላይ ዘረረው፡፡ የአካባቢው ወፎች በርግገው እስኪጠፉ ድረስ በድምጿ እየሰነጠቀችው ጥይት በበዳኔ ልብ ላይ ከተሳበች በኋላ ፀጥ አለች፡፡ ቱሉ ከአካባቢው ጫካ ጫካውን አቆራርጦ ተሰወረ፡፡ ከዚያ በኋላ አንድም ሰው አላወቀም፡፡ ቱሉ አረቄ ቤት ገብቶ ቀኑን ሙሉ ሲዘፍን ነበር የዋለው፡፡ የበዳኔ አስከሬን በነጋዴዎች ተገኝቶ ጉዳዩ ሲሰማ ጊዜ ግን አካባቢው ተተራመሰ፡፡

አቶ ቱፋ ጠመንጃቸውን ይዘው ወጥተው አገር ይያዝልኝ አሉ፡፡ ቱሉ ማንም ባይጠረጥረውም ሁኔታው ሲያስፈራው አመሻሹ ላይ ጠፋ፡፡ በማግስቱ የቱሉ ቀብር ላይ አለመኖር ሲታወቅ ነው ገዳዩ እሱ መሆኑ የተረጋገጠው፡፡ በዳኔ በታላቅ ስርዓት ታጅቦ በተኩስ ተጋግሎ በዋለ ቀብር ግብአተ መሬቱ ሲፈፀም የቱሉ ቤተሰቦችም በቁጣው ለመሸሽ ሀገር ለቀው ጠፉ፡፡ የበዳኔ ቤተሰቦች የቱሉን ወለጆች ቤትና ንብረት በእሳት አቃጥለው ከብቶቻቸውም ገድለው ጠፉ፡፡ አገሩ ተረባበሸ፡፡ ደራ ጫካ ቱሉ ተደብቆበታል ተብሎ ስለታሰበ ታመሰ፡፡ ልጁ ግን አልተገኘም፡፡

ከጊዜ በኋላ በቱሉ ጥፋት ወላጆች መቀጣት የለባቸውም ተብሎ ትልቅ ሽምግልና ተካሄደና የቱሉ ቤተሰቦች ወደቅያቸው እንዲመለሱ ተፈቀደ፡፡ ያም ሆኖ ስጋት ቤተሰቡን መጫኑ አልቀረም፡፡ ጥቁር ደም አንድ ዕለት ድንገት ለዚያ የፈሰሰ ደም በቀል ይህን ቤት ማንኳኳቱ እንደማይቀር ይታወቅ ነበር፡፡

ጊዜ የሁሉም ችግር መፍትሄ ነውና አቶ ቱፋ በልጃቸው ሞት የደረሰባቸውን ሀዘን መቋም ባለመቻላቸው ሳቢያ ህይወታቸው አለፈ፡፡ አሁን የቀሩት የሟቹ እህቶች ብቻ ናቸው፡፡ ዘመን እያለፈ በሄደ ቁጥር ወሬው የደበዘዘና የተረሳ መሰለ፡፡ ነገር ግን የሟችን ልጅ ለገሰ በዳኔን ባሳደገችው የሟች እህት ዘንድ ይህ ቂም አልረገበም፡፡

የቱሉን ቤተሰቦች ባየች ቁጥር ሁሌም ሟች ወንድሟ እየታሰባት እንደተሳቀቀች ኖራለች፡፡ ይህን ደግሞ ለህፃኑ ለገሰ እየነገረች አሳድጋዋለች፡፡ ‹‹የአባትህ ገዳዮች ቤት ያውልህ- የአባትህን ገዳይ አባት ይኸውል- ወደነርሱ አጠገብ እንዳትደርስ›› ወዘተ… እያለች ነበር ያሳደገችው፡፡ ለገሰ በዚህ የበቀል መርዝ ተመርዞ ነው ዕድሜውን የቆጠረው፡፡ አክስቲቱ አርፋ አልተቀመጠችም፡፡ አንዳንዴ ቱሉ እቤት መጥቶ ቤተሰቦቹ ጋር አድሮ ሌሊት ሄደ ሲባል እየሰማች- አንዳንዴ ታይቶበታል የሚባልበትን ቦታ እያጠናች ኖረች፡፡ አንድ ወቅት ግን ቱሉ ጫንጮ ውስጥ እንደሚኖር ደረሰችበት፡፡ ሚስት አግብቶ ቤት መስርቶ ይኖራል፡፡ ይህን የነገራት ደግሞ አንድ የደገም ተወላጅ የሆነ ወዳጇ ነው፡፡ አሁን የበቀል ጉማ የሚረከብበትን ወቅት አሰበች፡፡

1980 ዓ.ም

ለገሰ የ24 ዓመት ወጣት ሆኗል፡፡ አባቱን በዳኔን የመሰለ ጉብል፡፡ ፀጉሩና መልኩ ከእናቱ የተወረሰ ቁመናው ግን እንደ አባቱ የተዘነከተ ሰው፡፡ ይህን ጉልበትና በአባቱ በቀል ቂም የነደደ ልቡን ይዞ ተነሳ፡፡ አክስቱ መክራ ላከችው፡፡ በደንብ ያጠናችው የጫንጮን ከተማ አካባቢውን ሁሉ አስረግጣ ነግራ በመኪና ተሳፍራ ቦታውን አሳይታው ተመለሰች፡፡ የዘመናት ምኞቷ ሊሰምር መሆኑን አስባ በውስጧ ፈንድቃለች፡፡

1980 ሐምሌ ወር
ጫንጮ

አንድ ወጣት ኮስመን ያለ ገፅታውን ይዞ የነቱሉን ቤት አንኳኳ፡፡ የ48 ዓመት ጎልማሳው ቱሉ ነበር በር የከፈተው፡፡ በሩ ላይ የቆመው አሳዛኝ ገፅታ ያለው ወጣት በኦሮምኛ ‹‹እባካችሁ ከብት እረኛ ትፈልጉ ከሆነ ማደሪያ ስጡኝና አብሬያችሁ እየኖርኩ እረኛ ልሁን›› ብሎ ጠየቀ፡፡ ቱሉ በሩ ድረስ የመጣለትን ሲሳይ በዋዛ ሊያልፈው አልፈለገም፡፡ ልጁን አስገባው፡፡ ለእግሩ ውሃ ለሚባለው ደግሞ ትኩስ እንጀራ እንዲያመጡለት አዘዘ፡፡
ከዚያም ስለ አመጣጡ ሁኔታ ጠየቀው፡፡ ወጣቱ ከገብረጉራቻ መምጣቱንና ሥራ ፍለጋ ሲንከራተት መኖሩን ተናግሮ መጠጊያ ብቻ እንደሚፈልግ በመግለፅ የሰውየውን ቀልብ ሳበ፡፡ ከዚያ በኋላ የእረኝነት ስራውን በሚገባው መጠን መፈፀም ጀመረ፡፡ የቤተሰቡ አባላት ወደውት ልጆቹ እንደ ወንድማቸው አይተውት ቱሉም አቅርቦት እረኝነቱ 2 ወር አለፈው፡፡ ይህ ወጣት ለገሰ ነው፡፡

ከአክስቱ ጋር የነጋገረው ቀን ደረሰ፡፡ መስከረም 22 ቀን፡፡ ልክ አባቱ የሞተበት ቀን፡፡ ቱሉ በዳኔን የገደለበት ቀን፡፡ በዚያን ዕለት ደግሞ ቱሉ ጫንጮ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሚሄድበት ጉዳይ ነበረው፡፡ ከዋናው መንገድ ራቅ ብሎ በማሳ ውስጥ ባለ ቀጭን መንገድ የሚያመራው የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ቱሉ ከሚኖርበት ስፍራ ራቅ ይላል፡፡ ለገሰ የዛሬው እረኝነቱ ነገር አለበት፡፡ ከብቶቹን ከቤት ያወጣቸው ገና በማለዳ ነው፡፡ 12፡00 ሰዓት በረት ከፍቶ ሲወጣ እነ ቱሉ ‹ጎበዝ› ብለውታል በልባቸው፡፡ ይህን ጉብዝናውን መስክረውለታል፡፡ እሱ ግን ዕቅድ አለው፡፡ ከብቶቹን በፍጥነት እያካለበ ሜዳ አደረሳቸው፡፡ ከዚያም ቶሎ ብሎ ተመለሰ፡፡ ወገቡ ውስጥ የሻጣት ጥልቆ መኖሯን አረጋግጧል፡፡ በጋቢው ሸፍኗታል፡፡ ቀኑ ጭጋግ ውጦታል፡፡ ይህ ደግሞ ለርሱ ተመችቶታል፡፡ በነቱሉ ቤት እና በቤተክርስቲያኑ መሀል የተዘረጋው መንገድ ላይ ዘወር ያለ ቁጥቋጦ የወረሰው ቦታ አለ፡፡ እዚያ ስፍራ ላይ ጥጉን ይዞ አደፈጠ፡፡ ለ1 ሰዓት ሩብ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ቱሉ ፈጠን ፈጠን እያለ በቆቅ ዓይኑ አካባቢውን ገርመም እያደረገ ዱላውን በትከሻው አንግቶ መጣ፡፡ ከሩቅ ይታየዋል፡፡ ጎፈሬ ፀጉሩ አሁንም አስፈሪ አድርጎታል፡፡ ለገሰ ተዘጋጀ፡፡ ቱሉ እዚያ ቁጥቋጦ ዘንድ ደረሰ፡፡ በውስጥ እየቆራረጠ ሲያልፍ ድንገት ከተደበቀበት እመር ብሎ ወጣ ለገሰ፡፡

ያቺን ጥልቆ በእጅ ይዟል፡፡ በፍጥነት ላዩ ላይ ተከመረበት፡፡ ቱሉ ሳይዘጋጅበት ስለነበር ወደ ኋላ ወደቀ፡፡ ለገሰ አልራራም ቱሉ ዓይኑ እያየው የአባቴ በዳኔ ገዳይ አገኘሁህ ብሎ በጥልቆው ጭንቅላቱን መታው፡፡ ግንባሩ ለሁለት የተከፈለው ቱሉ ወዲያው ነበር የሞታው፡፡ ለገሰ የቱሉን ጎፈሬ በእጁ ጎትቶ ነጩና ኪሱ ከትቶ እየበረረ ወደ ጫንጮ ከተማ አመራ፡፡ እዚያ በቀጠሯቸው መሰረት የምትጠብቀውን አክስቱን አገኘ፡፡
‹‹የወንድሜን ገዳይ ገደልከው?››
‹‹አዎ አዳዶ ገድዬልሻለሁ››
‹‹በምን ልመንህ?››
‹‹ይኸው ፀጉሩ››
ከኪሱ አውጥቶ አሳያት፡፡ አቅፋ ሳመችው ተያይዘው ወደ ሀገራቸው ሄዱ፡፡

ከ15 ቀናት በኋላ

ለገሰን ለመፈለግ ወደ ቤቱ የሄዱት የአካባቢው ታጣቂዎችና ፖሊሶች ገና የነለገሰ በር ሳይከፈት ነው የደረሱት፡፡ ዓለም ዘጠኝ ያሉትን እነለገሰንና አክስቱን በቤት እንዳሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል ነበር እቅዱ፡፡ ውሻው ሲጮህ ግን የለገሰ አክስት በር ከፈተች፡፡ ተሰብስበው ስታያቸው ዘላ ገባችና በሩን ዘጋች፡፡ በዚህ መሀል የፀጥታ ኃይሎቹ በር ከፍተው ለመግባት ሲዘጋጁ ድንገት ከውስጥ የተኩስ ድምፅ ተሰማ፡፡ ያኔ ሁሉም መሳሪያቸውን አወጠና ጥግ ጥግ ያዙ፡፡ ለገሰ በጓሮ መስኮት ዘሎ ወጥቶ ጥሻው ውስጥ ሲመሽግ በጥይት አካባቢውን አመሱት፡፡ እሱም ተኮሰ፡፡ ብዙ አልቆየም ወዲያው ሲያቃስት ተሰማ፡፡ ተመታ፡፡ እዚያው የቤቱ ቢሮ ጓሮ ውስጥ ወደቀ፡፡ አልሞተም ነበርና ወደፍቼ ይዘውት መጡ፡፡ ይህን ሁሉ ቃል የተናገረው ሆስፒታል ሳለ ነው፡፡ ለ10 ቀናት ነበር በህይወት የቆየው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በጉዳቱ ሳቢያ አሸለበ፡፡ ፖሊሶች እዚህ ወጣት ላይ ያደረሱበት የቱሉ አባት የልጄ ገዳይ ለገሰ እንጂ ሌላ ማንም አይሆንም ብለው በማመልከታቸውና ለገሰ ለ3 ወር ከሰፈሩ ጠፍቶ መመለሱ በመታወቁ ነበር፡፡ አክስትየው ግን ለ3 ዓመታት ታስራ ተለቃለች፡፡ የበቀል ጦስ ሶስት ሰው ከዚህች ዓለም አሰናብቶ ተጠቃለለ፡፡ የሚቀጥል ይኖር ይሆን? ከ16 ዓመት በኋላም ቢሆን አሁንም የእነዚያ ሰዎች ቤተሰብ በስጋት መተያየቱን አላቆመም::

The post ቁርሾ – (እውነተኛ የወንጀል ታሪክ) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>