ምርጫ ቦርድም ነገሩን በቅንነት በማየት ጥቃቅን ግድፈቶችን ቸል በማለት ወደ ምርጫው እንዲገቡ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል ብለን እናምናለን:: …. እናምናለን።ይህ ካልሆነ ግን ለሚገነባው የመድብለ ፓርቲ( multi-party) ሲስተምና ለሃገሪቷም ትልቅ ውድቀት ይሆናል።”
“ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰት በባለስልጣኖች ይፈጸማል። ሳይውል ሳያድር በዜጎች ላይ በደል የሚያደርሱት ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት።የሰብአዊ መብት ጥሰት ከባድ ወንጀልና ሃጢያትም ነውና።”
ዳንኤል ጣሰው በአለም ዙሪያ ወንጌልን የሚሰብኩ አለምቀፍ ወንጌላዊ ነው። ሰላምን መግባባት በአገራችን ኢትዮጵያ ይሰፍን ዘንድ፣ የፊታችን የ2007 ምርጫ ሁሉንም ባሳተፈና ፍትህዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ፣ እንደ ፍርድ ቤት ምርጫ ቦርድ ያሉ ተቋማት ሁሉን በእክሉነት እንዲያስተናግዱና መንግስት የሚያደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ቢደገፉም ሰብዓዊ መብት መርገጡን እንዲያቆም ጠይቋል። ወንጌላዊ ዳነልል ጥሰው በፌስ ቡክ የለቀቅትን ጽሁፍ ለማንበብ እንሆ
ፍትህና ሰላም በምርጫ 2007 – ወንጌላዊ ዳንኤል ጣሰው
ክርስቲያኖች ለሀገር መሪዎችና ለሰላም እንድንጸልይ ታዘናል።እርቅን፥መግባባትን ማወጅ ሃላፊነታችን ነው፤የሚያስተራርቁ ብጹአን ናቸው ተብሎ ተጽፏልና::
በቅርቡ በሀገራችን ምርጫ ይካሄዳል።ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፉክክር፥ክርክር፥ውድድር ይኖራሉ።አንዳንዴም በሌላውም ዓለም እንደሚታየው መረር ያሉና መስመር ሊያስለቅቁ የሚችሉ ሽኩቻ ስድብና በጥላቻ ላይ የተመሰረታ ዘመቻ ይታያል።ከዚህም በፊት በሀገራችን ብዙ ሰዎች የሞቱበት አሳዛኝ ሁኔታ ተከስቶ ነበር።ያ እንዲደገም አንፈልግም።ለሰላምና ለመግባባት እንጸልያለን።
ገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ውድድር ማድረግ እንዲችሉ ሜዳውን ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ማመቻቸት ይጠበቅበታል። ምርጫ ቦርድ፥ፍርድ ቤትና ሚዲያው ሁሉንም እኩል የሚያስተናግዱ ሊሆን ይገባል።ኢትዮጵያ የምታድገው የተለያዩ ሃሳቦች ተፋጭተው ከውድድር በሚገኝ የነጠረ አስተሳሰብ ነው።ተቃዋሚ ሲኖር ለገዢው ፓርቲ መስተዋት ይሆናሉ፤ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋሉ፤ሙስናን ሌሎች ህገወጥነትን ያጋልጣሉ።ተወዳድረው ከተመረጡ ደግሞ ሀገር የመምራት እድል ያገኛሉ።
የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች እንግልትና እስራት በተለያዩ ባለስልጣኖች ይደርስባቸዋል።እነዚህ በአግባቡ ታይተው መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል።ወንጀል የሰሩና ያልሰሩ መለየት አለባቸው።ባልተጣራ ሁኔታና በግል ቂም በቀል ንጹህ ሰው በፍጹም መንገላታት የለበትም።
መንግስት ምንም አላደረገም ማለት አይቻልም።ሀገሪቷ ከቀደሙት መንግስታት የተሻለ የዲሞክራሲ ብልጭታ ታይቶባታል።ሆኖም ግን ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰት በባለስልጣኖች ይፈጸማል። ሳይውል ሳያድር በዜጎች ላይ በደል የሚያደርሱት ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት።የሰብአዊ መብት ጥሰት ከባድ ወንጀልና ሃጢያትም ነውና።
ሰሞኑን በአንዳንድ ፓርቲዎችና በምርጫ ቦርድ መካከል ያለው መቃቃር በሰላምና በመግባባት እንዲያልቅ እንጸልያለን።
እነዚህ ፓርቲዎች ክፍተኛ ዝግጅት አድርገው ለመወዳደር ተነስተዋል፤አንዳንድ ግድፈቶች አሉ ከተባለ በማለፍ በተቻለ መጠን ምርጫውን እንዲካፈሉ መንግስት መጣር አለበት።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመካከላቸው የሚነሱትን ልዩነቶች ብስለት በተሞላበት መንገድ በውይይት መፍታትና አንድነት መፍጠር ሀገራዊ ግዴታቸው መሆኑን በውሉ ሊያጤኑት ይገባል። በአንዳንዶች የምናየው ስር የሰደደ ጥላቻ፥ስድብ፥የሰውን ስብእና ማዋረድና ዘረኝነት መግባባትንና እርቅን ይጎዳልና በአስቸኳይ መቆም አለበት።
በሀገራችን የዲሞክራሲ ግንባታ ትልቅ ሚና የሚጫወቱና ባሁን ሰአት ካሉት ፓርቲዎች ሁሉ በተሻለ ደረጃ ላይ ካሉት ከአንድነትና መኢአድ ጋር ያለው ችግር ተወግዶ ወደ ምርጫው እንዲገቡ ያስፈልጋል። ምርጫ ቦርድም ነገሩን በቅንነት በማየት ጥቃቅን ግድፈቶችን ቸል በማለት ወደ ምርጫው እንዲገቡ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል ብለን እናምናለን።ይህ ካልሆነ ግን ለሚገነባው የመድብለ ፓርቲ( multi-party) ሲስተምና ለሃገሪቷም ትልቅ ውድቀት ይሆናል።እነዚህም ፓርቲዎች በሰላማዊ ትግል ላይ ተስፋ ይቆርጣሉ።እነርሱ ወደ ህዝባዊ እምቢተኝነት(Civil Disobedience) እንገባለን እያሉ ነው፤በዚህም ሀገሪቷ ወደ አላስፈላጊ ውጥረት ውስጥ የምትገባ ሲሆን ይህ ደግሞ የሚካሄዱትን የልማት ስራዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊያዳክም ይችላል።
ዛሬ በኢትዮጵያ አንዱ የጎደለው ነገር ቅንነት ነው።ቅንነት ከሌለ መጨቃጨቅ፥መካሰስ፥ፍርድ ቤት መንከራተት ብቻ ይሆናል።አንዱ አንዱን ለማጥቃት ሰበብና ምክንያት ብቻ ነው የሚፈልገው፤አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱትም አይነሳምና። ስለሆነም ችግሮች ሁሉ የሚፈቱት በመነጋገርና በመከባበር ነው።ያለፈውን በደል ይቅርታ በመጠያየቅ ህዝባችን ከድህነት የሚወጣበትን መንገድ ማፋጠን እንጂ እኛ ለስማችንና ለክብራችን ስንከራከር ህዝብ ማለቅ የለበትም።
እግዚአብሔርም ይሄን አይወድም፤ይቅር ተባባሉ፥ተከባበሩ፥ክፉን በመልካም አሸንፉ እንጂ በክፉ አትሸነፉ ነው ያለው።ሌላ አማራጭ የለም።
“እርስ በርስ መግባባት፥ሀገርን መገንባት” መርሃችን ይሁን።
አብያተ ክርስቲያናትና የሃይማኖት ተቋማት እውነትን በፍቅር የመናገር ሃላፊነትና ግዴታ አለባቸው። ቅንነት ለኢትዮጵያ!
ፍቅርና ፍትህ ለኢትዮጵያ!
ዳንኤል ጣሰው
ከኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ