ሊሊ ሞገስ
ቆዳችን ያለንበትን የጤና ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ መግለፅ የሚችል የአካላችን ክፍል ነው፡፡ ጤናማ ቆዳ አስተውላችሁ ከሆነ በተፈጥሮ በጣም ለስላሳ፣ የሚያበራ(Glow)፣ ከሁሉም ቦታ እኩል የውጥረት(Tone) ደረጃ ያለው፣ ከምንም አይነት ሽፍታና የቆዳ እክሎች የጠራ ሆኖ እናያለን፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የተቆጣ ቆዳ በተለይ ለሌላው በሚታየው ክፍላችን ላይ ማለትም እንደ ፊትና እጅ የመሳሰሉት ላይ ሲታይ በጣም ያስጨንቃል፤ ይረብሻልም፡፡
ግን ለምንድን ነው ቆዳ የሚታመመው? ባሉት መረጃዎች መሰረት ይህ ነው የሚባል አንድ መልስ የለም፡፡ ነገር ግን ለቆዳ መቆጣትና ለተለያየ የቆዳ ችግሮች እንደ መንስኤ ከሚጠቀሱት ውስጥ በዋነኛነት ዘመናዊ የአኗኗር ዘዴ የሚፈጥረው ጫና እና አካላዊ ውጥረት(Physical stress) ተፅዕኖዎች ቅድሚያ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል የአካባቢ ብክለት በስራችንና በኑሮአችን ምክንያት የሚፈጠር ውጥረት፣ በየምግቦቻችን፣ የመዋቢያና የመፀዳጃ ዕቃዎች ውስጥ የሚገቡ ከጤና አኳያ አላስፈላጊ የሆኑ ኬሚካሎች ወዘተ… ሲሆኑ ይህ ሁሉ ግብዓት እንደ ኮክቴል ሆኖ በአካላችን ስርዓት ላይ እንደ ውርጅብኝ ይወርዳል፤ የአካላችንን በሽታ የመከላከል አቅሙን ያዳክሙታል፡፡ በተለይ ደግሞ ስር የሰደዱ የጤና ችግሮች ካሉ ተደራርቦ የዚህ ሁሉ ጫና ውጤት በቆዳችን ላይ ይንፀባረቃል፡፡
ይህንን የቆዳ ችግር ለመፍታት ግን ይሄ ነው የሚባል አንድ የምግብ አይነት ብቻ እንዳለ ብነግራችሁ ምን ያህል ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ጉዳዩ ግን ሌላ ነው፡፡ እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ ግን አመጋገብና የአኗኗር ዘዴአችን በቆዳችን ጤንነት ማለትም እንደአንዱ የአካላችን ትልቁ ክፍል ስራውን በትክክል መስራት እንዲችል፣ የማርጀት ፍጥነቱ ላይ የቆዳ ችግሮችን መበርታትና የመዳን ፍጥነት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንዳለው ነው፡፡
ስለዚህ ልክ እንደወትሮ ስለምግብ አይነቶችና ስለ አመጋገብ ከመግለፄ በፊት የቆዳችን ስራ ምን እንደሆነና እንዴት እንደሚሰራ በቅድሚያ መገንዘቡ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡
የቆዳችን አገልግሎት
ቆዳችን በሰውነታችን ውስጥ ከሚገኙ ክፍሎች ውስጥ እጅግ በጣም ትልቁ ሲሆን በአማካይ ወደ 2.7 ኪ.ግ ይመዝናል፡፡ ቆዳችን ከሚያከናውናቸው ስራዎች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. የመከላከል ሥራ (Protection)
የመጀመሪያው የቆዳችን ሥራ የተለያዩ የአካላችንን ክፍሎች ከውጫዊው ዓለም ጥቃት መከላከል ነው፡፡ ቆዳችን ሙሉ ለሙሉ የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ስርዓት (immune sysetem) ዋና ክፍል ነው፡፡
በሚደንቅ ሁኔታ ቆዳችን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዓይን በማይታዩ ባክቴሪያዎች የተሸፈነ ነው፡፡ እነዚህ ባክቴሪያዎች ምንም አይነት ጉዳት በቆዳችን ላይ ሳያስከትሉ በሰላምና በተድላ በቆዳችን ላይ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ባክቴሪያዎች ታዲያ ምንድን ነው የሚሰሩት አትሉም? ስራቸውማ በሚገርም ሁኔታ ጎጂ ባክቴሪያዎችን መዋጋትና ጥቃት መከላከል ነው፡፡
ሌላው የመከላከል ስራ አካል የሆኑት ደግሞ በቆዳ ህዋሶች መካከል ተቀብረው አካላችንን የሚጎዱ ጎጂ ህዋሳቶች ሲመጡ ለበሽታ መከላከል ስርዓት መረጃ የሚያቀብሉ ላንገር ሐንስ (Langerhans) የሚባሉ የህዋስ አይነቶች አሉ፡፡ በእነዚህ ህዋሶች በመታገዝ የሰውነታችን በሽታ መከላከል ስርዓት አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል፡፡
2. የሰውነትን ሙቀት መቆጣጠር
ሌላው የቆዳችን ስራ እና ችሎታ ደግሞ የሰውነትን ሙቀት መቆጣጠር ሲሆን የአካባቢያችን ሙቀት በጣም በትንሹ ቢቀየር እንኳን በቀላሉ መለየት ይችላል፡፡ ታዲያ የአካባቢያችንን የሙቀት መጠን መረጃ ለአዕምሮአችን በመላክ የሰውነት የሙቀት ደረጃ እንዲስተካከል ይረዳል፡፡
በቅዝቃዜ ወቅት አዕምሮአችን ለቆዳችን ትዕዛዝ በማስተላለፍ በቆዳችን ስር ያሉትን የደም ስሮች እንዲጠቡ በማድረግና ከቆዳ የላይኛው ክፍል ርቀው ወደታች ዝቅ በማለት ሙቀት ከሰውነታችን እንዳይባክን ከማድረግ በተጨማሪ ቅዝቃዜው ቢበረታ ደግሞ ጡንቻዎቻችን እንዲቀጠቀጡ በማድረግ ሰውነታችን ራሱ ሙቀት እንዲያመነጭ ያደርጋል፡፡
በሙቀት ጊዜ ደግሞ በተቃራኒው ለቆዳችን መልዕክት በመላክ ቀጫጭን የደም ስሮቻችን እንዲሰፉ በማድረግ ከልክ ያለፈ ሙቀት በቆዳችን አማካኝነት እንዲወገድ ከማድረግ በተጨማሪ የላብ አመንጭ ዕጢዎች ላብ እንዲያመነጩ በማድረግ ሰውነት እንዲቀዘቅዝ ያደርጋል፡፡
3. እንደ የስሜት ህዋስ ክፍል ያገለግላል
በቆዳችን ላይ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ነርቮች ሲኖሩ በዋናነት አራት ነገሮችን እንድንለይ ያደርጋሉ፡፡ ሙቀት፣ ቅዝቃዜን፣ ንክኪን እና ህመምን፡፡ በንክኪ ላይ ብቻ ሻካራን፣ ለስላሳን፣ ግፊትን የመሳሰሉ የተለያዩ ንክኪዎችን የሚለዩ የነርቭ ህዋሶች አሉ፡፡
4. ቫይታሚን ዲ ማምረት
ሌላው የሚደንቀው የቆዳችን ስራ ደግሞ ፀሐይ ስንሞቅ ሙቀቱን ተጠቅሞ ቫይታሚን ዲ ማምረቱ ነው፡፡ ይህንን የሚሰራው ጠቃሚ ኮሌስትሮልን ወደ ቫይታሚን ዲ 3 በመቀየር ከዚያም በጉበትና ኩላሊት እገዛ አማካኝነት ዲ 3 ወደ አክቲቭ ወደሆነው ስሬቱ እንዲቀየር ያደርጋል፡፡
የቆዳችን አወቃቀር ምን ይመስላል?
ጤናማ ቆዳ እንዲኖረን ከፈለግን የቆዳችንን አፈጣጠር እና ስራ ማወቅ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ቆዳችን በሶስት ንብርብር ክፍሎች የተዋቀረ ነው፡፡ እነርሱም የላይኛው ክፍል(ኤፒደርሚስ)፣ የመካከለኛው ክፍል(ደርሚስ) እና የታችኛው ክፍል(ሐይፓደርሚስ ወይም ሰብኩታንዬስ) በመባል ይታወቃል፡፡
1. የላይኛው የቆዳ ክፍል(ኤፒደርሚስ)
ይህኛው የቆዳችን ክፍል ከላይ የምናየው ክፍል ሲሆን ውፍረቱ በቆዳችን ላይ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ያህል የተረከዝና የመዳፍ ቆዳ ላይ ይህ ክፍል ከ1-5 ሚ.ሜ ውፍረት ሲኖረው በዓይናችን ቆብ ላይ ደግሞ 0.5 ሚ.ሜ ያህል ውፍረት ይኖረዋል፡፡
ይህ ክፍል ብቻውን እስት ንብርብር ክፍሎች ሲኖሩት በዚህ ንብርብር ውስጥ አንደኛ የሚባለው በውጭ የሚታየው ነው፡፡ አምስተኛው ደግ የንብርብሩ የታችኛው ክፍል ነው፡፡ በአንደኛው ክፍል ውስጥ የሚገኙት ህዋሶች ጠፍጣፋና ከሞቱ ህዋሶች የተሰሩ ሲሆን በየጊዜው እየተሸረሸሩ የሚራገፉ ናቸው፡፡ ይኸውም በአማካይ በየሁለት ሳምንቱ በመርገፍ በአዲስ ይተካል፡፡ የመጨረሻውና አምስተኛው ደግሞ አዳዲስ ህዋሶች የሚወለዱበት ክፍል ሲሆን አዳዲስ ህዋሶች ተወልደው እስኪያድጉ ድረስ በንብርብሩ ውስጥ ከአምስተኛው ወደ አንደኛው ክፍል ሽቅብ ይጓዛሉ፡፡ በመጨረሻም አርጅተው አንደኛ ክፍል ላይ ይወገዳሉ፡፡
የቆዳችንን ቀለም የሚያመርቱ ሜላኖሳይት፣ ጎጂ ህዋሳትን ለይተው የሚጠቀሙ ላንጋርሐንስ የተባሉት ህዋሶችና ሌሎች ምንነታቸው የማይታወቁ ህዋሶችም የዚሁ የኤፒዲርሚስ የተባለው ቆዳ ክፍል አካሎች ናቸው፡፡
2. የመካከለኛው የቆዳ ክፍል(ደርሚስ)
ይኸኛው የቆዳ ክፍል ከላይኛው (ኤፒደርሚስ) ከ10-40 ጊዜ እጥፍ ውፍረት ያለው ነው፡፡ ይህ የቆዳ ክፍል ሲታይ ወጣ ገባ የበዛበት ሲሆን በውስጡም የተለያዩ የደም ስሮች፣ ነርቮች ኮላዲንና ኢላስቲንን የሚያመነጭ ፋይብሮ ብላስት የሚባሉ ህዋሶች፣ የወዝ ማመንጫ ዕጢዎች፣ ፀጉርና የፀጉር ስሮች፣ የላብ ማመንጫ ዕጢዎችና ቱቦዎቻቸውን ይዞ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የምናገኛቸውን ኮላጅንና አላስቲን በዋነኛነት የቆዳችንን ውጥረት፣ የመለጠጥ አቅም ወዘተ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
3. የታችኛው የቆዳ ክፍል(ሐይፓደርሚስ)
ይህ ክፍል ደግሞ ከሁሉም ክፍሎች ወፍራሙና ትልቅ የሆነ ሲሆን የተሰራውም በዋነኛነት ከኮላጅን ስሮችና ስብን ከሚያጠራቅሙ ህዋሶች ነው፡፡ በዚህ ክፍል የሚጠራቀመው ላብ በተወሰነ ደረጃ ስንቀመጥ ስንጋደም ምቾት ከመፍጠር በተጨማሪ የኃይልና የሙቀት ምንጭም ሆኖ ያገለግላል፡፡ የሰውነታችን ክብደት ሲጨምር በእነዚህ ህዋሶች ውስጥ የሚጠራቀመው የስብ መጠን ይጨምራል፡፡ ስለዚህ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ በማድረግና አመጋገብን በማስተካከል የላቡን መጠን መቀነስ ይቻላል፡፡
የቆዳ እርጅና ሒደት
የቆዳን እርጅና ማስቆም ባይቻልም የእርጅናውን ፍጥነት(Aging Speed) ግን ማዘግየት ይቻላል፡፡
ቆዳ እንዴት እንደሚያረጅ ለማወቅ ከላይ የተብራሩትን የቆዳ አፈጣጠርና ዋና ዋና ክፍሎቹን ማወቅ ግድ ይላል፡፡ በዚህ መሰረት እያንዳንዱ የቆዳ ንብርብር ክፍሎች የሚያረጁበት አካሄድም ይለያያል፡፡
የላይኛው የቆዳ ክፍል(Epidermis) እርጅና
የቆዳ የላይኛው ክፍል ሲያረጅ የቆዳን ቀለም የሚፈጥሩ ህዋሶች ቁጥር መቀነስን ያስከትላል፡፡ እነዚህ ህዋሶች ሜላኒን የተሰኘውን የቆዳ ቀለም የሚያመነጩ ሲሆን የእነርሱ ቁጥር አነሰ ማለት የሜላኒን መጠን ቀነሰ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቆዳችን የፀሐይ ጨረርን(Ultraviolet ray) መቋቋም እንዲያዳግተው ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቆዳችን ላይ በሚገኙ ፍሪራዲካሎች መጠቃትና በቆዳ ካንሰር እስከ መያዝ ያደርሳል፡፡
ሌላው በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ላንገርሐንስ የተባሉ የተህዋሲያን መምጣትን የሚያሳውቁ ህዋሶች ቁጥር መቀነስ ሲሆን ይህም ተህዋሲያን በቆዳ ላይ ሲያርፉ በፍጥነት በሽታን የመከላከል ስርዓትን(Immune sysetem) የማሳወቅ ሁኔታ ይቀንሳል፡፡
በተጨማሪ ይህ የላይኛው የቆዳ ክፍል ወዙን እና ውጥረቱን(tone) ያጣል፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት የላይኛው የቆዳ ክፍል ከመካከለኛው(Dermis) ከሚባለው የቆዳ ክፍል ተነስተው ጫፋቸው በላይኛው የቆዳ ክፍል(Epidermis) ብቅ ብቅ ከሚሉት የደም ስሮች ውጭ የራሱ የሆነ በውስጡ የተዘረጉ የደም ስሮች የሉትም፡፡ በመሆኑም ቆዳ ሲያረጅ በዚህ ክፍል እና በመካከለኛው ክፍል መካከል መለያየት(መራራቅ) ይፈጠራል፡፡ በዚህም ምክንያት በቂ አየርና ንጥረ ነገሮች ስለማይደርሱት ህይወት አልባ ቆዳ ይሆናል፡፡
የመካከለኛው የቆዳ ክፍል (Dermis) እርጅና
በዚህኛው የቆዳ ጤና ላይ እርጅና የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ስንመለከት በዋነኛነት የቆዳን የመጠንና ባህሪ (የልጅ ቆዳ) የምንለውን ባህሪ የሚያሳጡት የኮላጅን እና ኢላስቲን መጠን መቀነስ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ኮላጅንን የሚያመርቱ ፋይብሮ ብላስት የተባሉ የህዋስ አይነቶች መኮማተር መጀመር ነው፡፡ ሌላው ኮላጅን ራሱ መቅጠን ይጀምራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሜታሎ ፕሮቲኔዝ የተባለ ኢንዛይም መጠን በቆዳ እርጅና ጊዜ መጠኑ ስለሚጨምር ኮላጅንን በመሰባበር የቆዳን የመለጠጥ ችሎታውን ይቀንሰዋል፡፡
ሌላው በዚህ ክፍል እርጅና ጊዜ የሚታየው ለውጥ ደግሞ የደም ዝውውር ስለሚቀንስ የአየርና የጠቃሚ ንጥረ ነገሮች ማግኘትም ተያይዞ ይቀንሳል፡፡ ለዚህም ነው በእርጅና ጊዜ ቆዳ የመገርጣትና የመቀዝቀዝ ባህሪ የሚያሳየው፡፡
የታችኛው የቆዳ ክፍል እርጅና
ይህኛው የቆዳ ክፍል ደግሞ ላብ የሚከማችበት ክፍል ሲሆን በእርጅና ጊዜ የላብ ክምችቱ ይቀንሳል፡፡ ይህም የቆዳውን ሞላ የማለት ባህሪ ያዳጣዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቅዝቃዜን የመቋቋም አቅሙ ይቀንሳል፡፡
የቆዳን እርጅና የሚያፋጥኑ ነገሮች ምንድን ናቸው?
የቆዳን እርጅና ከሚያፋጥኑ ነገሮች ውስጥ በዋነኛነት የሚጠቀሰው የቆዳ ህዋሶች በፍሪ ራዲካሎች መጠቃት ነው፡፡ ስለ ፍሪ ራዲካሎች ባለፈው ወር እትም ላይ በዝርዝር ያየን ስለሆነ ጠለቅ ብለን አንገባበትም፡፡ ለማስታወስ ያህል ግን ፍሪ ራዲካሎች ያልተረጋጉ፣ የኤክትሮን ጥማት ያለባቸው ባዕድ ኬሚካሎች ሲሆኑ የሚፈልጉትን ኤሌክትሮን ለመስረቅ ሲሉ ከህዋሶቻችን ጋር ይጋጫሉ፡፡ በዚህ ሂደትም ህዋሶቻችን ይጎዳሉ፡፡ ይህም ጉዳት ህዋሶች ዳግመኛ በትክክል ስራቸውን መስራት እስኪያቅታቸውና ይህም የህዋሶች የመራባት ሂደትን አውኮ ወደ የካንሰር በሽታ እስከማምጣት የሚያደርሱ ናቸው፡፡
ፍሪ ራዲካሎች በተወሰነ ደረጃ በተፈጥሮ ሰውነታችን ውስጥ የሚመረቱ ሲሆን በብዛትና በአደገኛ ሁኔታ ደግሞ የሚመረቱት ሰውነት ጎጂና መርዛማ የሆኑ ነገሮችን በምግብ፣ በመጠጥ፣ በሲጋራና ሌሎች ሱስ አስያዥ ነገሮች፣ በመድሃኒት፣ በተለያዩ ኬሚካሎች አጠቃቀም ምክንያት ወደ አካላችን ሲገቡ እነርሱን ለመሰባበር በሚያደርገው ጥረት ፍሪ ራዲካሎች በብዛት ይመረታሉ፡፡ ይህንን የፍሪ ራዲካሎች ምርት ለመቀነስ ግን በዋነኛነት ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ስርዓትና የአኗኗር ዘዴ መከተሉ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡
ሌላው የቆዳን እርጅና የሚያፋጥኑ ነገር ግን ብዙም የማይወራለት ነገር ደግሞ ጣፋጭ ምግቦችና መጠጦችን በተለይ የታሸጉ ምርቶችን መጠቀም ሲሆን እነዚህ የምግብ አይነቶች የሚይዙት የተጣራ የካርቦሃይድሬት ምግቦችን ጨምሮ አዘውትሮ መመገብ የቆዳን እርጅና ያፋጥናል፡፡
የተጣራ የካርቦሐይድሬት ምግቦች የምንላቸው ስንል ደግሞ ገለባቸው የወጣላቸው እንደ የነጭ ዱቄት ምርቶች ማለትም ነጭ ዳቦ፣ ነጭ ፓስታ፣ በፈጣን ሁኔታ የሚዘጋጁ ምግቦችን ያካትታል፡፡
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የምግብ አይነቶች በውስጣቸው ከልክ በላይ የሆነ ስኳር የያዙ ሲሆን በኢንሱሊን አማካኝነት ስኳር በፍጥነት በሰውነታችን እንዲመጠጥ ያደርጋል፡፡ ይህ ሁኔታ ከጊዜ በኋላ ሰውነታችን ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንዲጋለጥ ከማድረግ በተጨማሪ በቆዳችን ውስጥ ያሉትን የኮላጅንና ኢላስቲንን ስሮች በማስተሳሰርና በማጣበቅ የመለጠጥ ባህሪያቸውን ያሳጣል ብሎም የመሰባበር ባህሪ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ የቆዳ መሸብሸብን ያስከትላል፡፡ ስለዚህ ከተጣራ የካርቦሐይድሬቶችን ከመጠቀም ይልቅ እህሉን እንዳለ ፈጭቶ መጠቀም እንደዚሁ ጣፋጭ ምግብና መጠጦችን ቀንሶ በልክ ብቻ ማድረጉ ይመከራል፡፡