ባለፉት ወራት ኢምሬትስ ስታዲየም አስደሳች ድባብ አልነበረውም፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ያልተጠበቁ ሽንፈቶች አስተናግዶ አሰልጣኙ አርሰን ቬንገርን የበዛ ጫና ውስጥ ያስገባቸው ቡድን ከመልካም ነገሮቹ ይልቅ እንከኖቹ ይበዛሉ፡፡ የተከላካይ ክፍሉ የጥራት ብቻ ሳይሆን የአማራጮችም እጥረት አለበት፡፡ አማካይ ክፍሉ በተጨዋቾች ጉዳት መታመሱን ቀጥሏል፡፡ በሜዳ ላይ በንፅፅር የተሻለው ነገር የአጥቂዎቹ ጥሩ የሚባል ብቃት ላይ መገኘት ይመስላል፡፡
ከጉዳት ገና ከመመለሱ ጎሎች ማስቆጠር የጀመረው ኢሊቪዬ ዢሩ ከመልካም ብቃት ላይ ይገኛል፡፡ ዳኒ ዌልቤክ ኳስ ከመረብ ያለማገናኘት ድክመቱ እንዳለ ሆኖ ከተቀሩት የቡድን ጓደኞቹ ጋር የፈጠረው ድንቅ ጥምረት ሁልጊዜም ለተጋጣሚ ቡድን አደጋ ፈጣሪ አድርጎታል፡፡ አሌክሲስ ሳንቼስ ባልዋዠቀ ብቃት መጫወት ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ጎሎችን ማግኘት ቀጥሏል፡፡ ሌላው ቀርቶ ብዙም ተስፋ ያልተጣለበት ያሳኖጎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደጋፊዎችን ልብ ማግኘት ጀምሯል፡፡ በዚህ ላይ የአሌክስ ኦክስሌድ ቼምበርሌይን እየተሻሻለ መመጣት የመድፈኞቹን የማጥቃት ኃይል የማይናቅ አድርጎታል፡፡ እነዚህ ለውጦች በኢምሬትስ ቲዮ ዋልኮት እንዲዘነጋ እያደረጉት ይመስላሉ፡፡
በእርግጥ የአርሰናል ደጋፊዎች ዋልኮትን ጨርሰው ሊረሱት አይችሉም፡፡ ባለፈው ወር በርንሊን ሲገጥሙ ለ10 ደቂቃዎችም ቢሆን ወደ ሜዳ ተመልሶ አይተውታል፡፡ ወዲያው በኢንተርናሽናል ጨዋታ ወቅት ያስተናገደው የብሽሽት ጉዳት አሰልጣኙ እንዳሰቡት እንዳይጠቀሙበት ሰበብ ሆኗል፡፡
የዋልኮት ዳግመኛ ጉዳት የፈጠረው ችግር አስተዳደራዊ ፈተናም አለው፡፡ እንግሊዛዊውን በኤምሬትስ የሚያቆየው ኮንትራት ሊጠናቀቅ የሚቀሩት 18 ወራት ብቻ ናቸው፡፡ ቬንገር ቲዮን ለማቆየት ጥረት መጀመራቸውን ቢናገሩም ድርድሩ የት እንደደረሰ ወሬ የለም፡፡ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የክለቡ ደጋፊዎች ግን ሁኔታዎች እየሄዱበት ያለው መንገድ ስጋትፈ ጥሮባቸዋል፡፡ የዋልኮት ወቅታዊ የኮንትራት ሁኔታ በ2012 በካሪ ሳኛ ከነበረበት ጋር እጅጉን ይመሳሰላል፡፡ በጊዜው የአርሰናል ባለስልጣናት ዕድሜው 30 ሊሞላ ከተቃረበው ፈረንሳዊ ተከላካይ ጋር ውል ለማራዘም ብዙ እንደሚያስቸኩል አላመነበትም ነበር፡፡ በወቅቱ ሳኛ ልክ እንደ ዋልኮት ከከባድ ጉዳት መመለሱ ነበር፡፡ ስለዚህ የአርሰናል ሰዎች በሁለት እግሮቹ ላይ ከደረሰበት ስብራት ያገገመው ተጨዋች ወደ ብቃቱ መመለስ ስለመቻሉ ጊዜ ወስደው ማረጋገጥ ፈለጉ፡፡ ኮንትራቱን ለማራዘም መቸኮል እንደሌለባቸውም አመኑ፡፡ በዚህ ሰበብ ውሉን አዘገዩት፡፡ መድፈኞቹ አሁን የዋልኮትን ድርድር ቢቀጥሉ የተጨዋቹ አማካሪዎች ከበድ ያሉ ጥያቄዎች እንደሚያቀርቡላቸው አውቀዋል፡፡ ስለዚህም ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት የዋልኮት የጉልበት ጉዳት በቀጣይ ውጤታማነቱ ላይ ችግር እንደሚያመጣ ማረጋገጥ ይሻሉ፡፡
በሳኛ ጉዳይ የክለቡ ሰዎች ዘግይተውም ቢሆን ፉልባኩ ወደ ብቃቱ መመለስ እንደሚችል አረጋግጠው ነበር፡፡ ኮንትራቱ 18 ወራት እየቀረውም አዲስ ውል አቅርበውለታል፡፡ ዋልኮት ግን ከወዲሁ እዚያ ቀሪ ጊዜ ላይ ደርሷል፡፡ ስለዚህም ተጨዋቹ ኮንትራትጉዳት አርሰናል ፈጣን እርምጃ መውሰድ ያለበት ይመስላል፡፡ ተጫዋቹ በመጪው ጃንዋሪ አርሰናልን የመልቀቅ እድል ባይኖረውም እስከ ክረምቱ በኮንትራቱ ዙሪያ የሚኖሩት ለውጦች የክለቡ ቆይታውን ይወስናሉ፡፡
በእርግጥ የጉልበት ጉዳት አደገኛ ነው፡፡ የተጨዋቾችን ቀጣይ የእግርኳስ ህይወት የሚወሰንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ነገር ግን የዋልኮት ዕድሜ አደጋውን ለመቋቋም የተመቸ ነው፡፡ ቬንገር ቲዮን ለማቆየት የሚደረገው ድርድር ፈታኝ እንደሚሆን የተረዱ ይመስላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ብዙ የተጓተተው የተጨዋቹ ኮንትራት ፊርማ በስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኙ የብዕሩ ቀለም መድረቁን የገቡለትን ቃል ወደ ጎን ማለታቸውን የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ በጊዜው ዋልኮት ውሉን ለማራዘም ያስቀመጣቸው ጠንካራ ቅድመ ሁኔታዎች በወቅቱ ቡድኑ ከነበረበት ችግር አንጻር አርሰናልን አቅመ ቢስ አስመስለውት ነበር፡፡
በ2012/13 ሮበን ቫን ፔርሲን አጥቶ የተቸገረው አርሰናል ሉካስ ፖዶልስኪን እና ኦሊቪዮ ዢሩን አምጥቶ ዠርቪንሆን ደግሞ በሀሰተኛ 9 ቁጥር ሚና እየሞከረ ይገኝ ነበር፡፡ ስለዚህም ዋልኮት የአጥቂነት ሚና ለማግኘት የበዛ ጫና መፍጠር ችሏል፡፡ ሆላንዳዊውን አምበላቸውን ሸኝተው ብዙ የተወቀሱት ቪንገርም በቀጣይ ዋልኮትን አጥተው ራሳቸውን ለተቺዎች ማመቻቸት አልፈለጉም፡፡ ስለዚህም የፊት መስመር ዕድል ለሰጡት ተስማምተው እንግሊዛዊው ፊርማውን አኑሯል፡፡
አሁን ግን ዋልኮት የቀደመ ጠንካራ ተፅዕኖው አዝኖት የለውም፡፡ ዌልቤክ እና ሳንቼዝን በአጥቂው ክፍል የጨመረው አርሰናል በቁጥር ብቻ ሳይሆን በጥራትም ተሻሽሏል፡፡ እንደቀደመው ጊዜ በዋልኮት ፍጥነት እና ሰብሮ የመግባት ብቃት ላይ ጥገኛ አይደለም፡፡ ቬንገር እነዚህ የዋልኮት ብቃቶች በፊት መስመር ከአንድም በሁለት ተጨዋቾቻቸው ላይ አግኝተዋቸዋል፡፡
ዘንድሮ በውድድር ዘመኑ ጅማሬ ይህ ሁሉ አልነበረም፡፡ በሴፕቴምበር ቬንገር ከቲዮ ጋር የሚደረገው ድርድር ቀላል አለመሆኑን ሲናገሩ ምክንያታቸው የገንዘብ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ዋልኮት ደጋግሞ በይፋ እንደተናገረው የፊት አጥቂ መሆን ይፈልጋል፡፡ ባለፈው ጊዜ በንፅፅር የአጭር ጊዜ ኮንትራት ማራዘሚያ መፈረሙም ዋልኮት የተገባለትን ቃል ተፈፃሚነት ለማየት ጥንቃቄ ማድረግ መምረጡን ያሳያል፡፡
በእርግጥ ቬንገር እድሉን በጥቂቱም ቢሆን ሰጥተውት ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ግን ተጨዋቹን ወደ ቀድሞው ቦታው የመስመር አማካይነት መለሱት፡፡ በእርግጥ በእንቅስቃሴ መሀል አርሰናል ሲያጠቃ ወደፊት እየተጠጋ ዢሩን እንዲያጣምር ነፃነት ሰጥተውታል፡፡ አሁን የቲዮ እንቅፋት ዌልቤክ ይመስላል፡፡ የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ልጅ ዋልኮት ሊሰራ የሚችለውን ባልተናነሰ መልኩ ይሰራል፡፡ ሳንቼዝ ስዋንሲ ላይ ጎል ሲያስቆጥር ያቀበለው ኳስ እና ሌሎችም ውጤታማ ሙከራዎቹ ይህንን ይመሰክራሉ፡፡
ዌልቤክ ከዋልኮት የሚሻልባቸው ነጥቦችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዳኒ የተሻለ ጉልበተኛ እና በመከላከል አጨዋወቱም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ በዌስትብሮም ጨዋታ የትኛውም የአርሰናል ተጨዋች ዌልቤክን ያህል ሸርተቴ አልወረደም፡፡ በተለይ ዢሩ ወደ ሜዳ ከተመለሰ በኋላ ራሱ ዢሩ፣ ዌልቤክ፣ አሌክሳስ እና አሮን ራምሴይ ፍጥነት የቀላቀለ የአንድ ኳስ ቅብብል ሲፈፅሙ ተስተውለዋል፡፡ ዋልኮት ለቡድኑ ይህንን ያደርጋል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡
አርሰናል ሳንቼዝን ከጨመረ በኋላ የሚታወቅበትን በቡድን ቅብብል ላይ የተመሰረተ ጨዋታ በቺሊያዊው የአጨዋወት ባህርይ ምክንያት በጥቂቱም ቢሆን ተመሳሳይ ችግር የሚጨምርባቸውን ዋልኮት በተመሳሳይ ጊዜ በበላይኛው የቡድኑ መስመር እንዲገኛ ለመፍቀድ ሊያቅማሙ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ በአሌክሲስ፣ ዢሩ እና ዌልቤክ የሚቀናጀው የአርሰናል የፊት መስመር የሜዳውን ስፋት ያለመጠቀም ችግር ይስተዋልበታል፡፡ ዋልኮት ለዚህ ጥሩ መፍትሄ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ኦክስሌድ ቻምበርሌይንም ይህንን ማድረግ ይችላል፡፡
ይህ ሁሉ ግን ዋልኮትን በአርሰናል አላስፈላጊ ወይም ትርፍ ተጨዋች አያደርገውም፡፡ የቬንገር ቡድን እንደማንኛውም ለክብር የሚፎካከር ቡድን አማራጮች ያስፈልጉታል፡፡ በተለይ የውድድር ዘመኑ እየገፋ ሲመጣ ከተጠባባቂ ወንበርም ቢሆን እየተነሱ ውጤት የሚለውጡ ከዋክብት ይሻል፡፡ አርሰናል ሳውዛምፕተንን ለመርታት ብዙ ሲቸገር ዢሩ እና ፖዶልስኪ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስተው ውጤት ሲለውጡ ታይተዋል፡፡
አጓጊው ነገር ክለቡ እና ተጨዋቹ የተሻለ ስምምነት ላይ መድረስ ይችሉ ይሆን? የሚለው ነው፡፡ ዋልኮት ከክለቡ ከፍተኛ ተከፋዮች ጎን የሚያስቀምጠውን ደመወዝ መጤቁ አይቀሬ ይመስላል፡፡ አርሰናል ስምምነት ላይ ለመድረስ ከተጨዋቹ የሜዳ ላይ አስተዋፅኦ ሌላ የምስል መብቱ ለክለቡ ገቢ የሚኖረውን ተፅዕኖ ከግምት ማስገባቱ እንደማይቀር መገመት ይቻላል፡፡ ዋልኮት በአውሮፓ ምስላቸው ለገበያ የተመቹ ከሚሰኙ ተመራጭ ተጨዋቾች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ይህንን የተጨዋቹ ወኪሎችም አይነጉም፡፡ ስለዚህ እነዚህ እውነታዎች የአርሰናልን ተደራዳሪዎች ይበልጥ ይፈትናሉ፡፡
ምናልባት አንድ መረሳት የሌለበት ጉዳይ አርሰናል ዘንድሮ የጎል ዕድሎችን ፍሬያማ ለማድረግ እየተቸገረ ይገኛል፡፡ ቲዮ ደግሞ በዚህ በኩል የተመሰከረለት ምርጥ ጎል ጨራሽ ነው፡፡ ነገር ግን ጎል ጨራሽነት ለአርሰናል ቤት የተለየ ቦታ እንደሚያስገኝ በፖዶልስኪ ማየት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ የአርሰናል ደጋፊዎች አሁንም በወረቀት ላይ ያጓጓቸውን የሜሱት ኦዚል እና ዋልኮት አስፈሪ ጥምረት በሜዳ ላይ ማየት ይሻሉ፡፡ ምናልባት ቲዮ ራሱ ይህንን መጠቀም ከፈለገ እና በ2012/13 የፈጠረውን ተሰሚነት መልሶ ለማግኘት ከጓጓ የኮንትራት ድርድሩን ቀለል ያደርገው ይሆናል፡፡ በአርሰናል አጣሁት የሚለውን የፊት መስመር ሚና ከመድፈኞቹ ከፍ ባለ ደረጃ ላይ በሚገኝ ሌላ ክለብ በፍፁም እንደማያገኘው ክለቡም በኢምሬትስ መቆየትን ይመርጥ ይሆናል፡፡