ከጥቂት ዓመታት በፊት የፌስቡክ ኩባንያ ባለስልጣናት አንድ ትልቅ ጉዳይ ነበራቸው፡፡ የክርስቲያኖ ሮናልዶን ወኪሎች ማግኘት እና ተጨዋቹ የፌስቡክ ገፅ እንዲኖረው ማሳመን ዋና አላማቸው ነበር፡፡ ፖርቱጋላዊው ኮከብ የራሱን ገፅ አድራሻ ቢኖረው ‹‹10 ሚሊዮን ተከታዮች›› ሊያፈራ እንደሚችል እያስረዱ ወተወቷቸው፡፡
የሮናልዶን የምስል መብት ተያያዥ ጉዳዮች የሚያስተዳድረውን ፓላሪስ ስፖርትስ የተሰኘ ኩባንያ በሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት ሉዊስ ኮሬያ በጊዜው የሆነውን ሁሉ ያስታውሳሉ፡፡ ሮናልዶ ይኖሩታል የተባሉትን የተከታዮች ቁጥር መቀበል ተቸግረው ነበር፡፡ ‹‹አላምናችሁም! የጠቀሳችሁት ቁጥር እና መላ ፖርቹጋልን ያህላል›› ሲሉ የማህበራዊ ድረገፁን ሰዎች ሞገቱ፡፡
የሆነ ሆኖ በ2009 ሮናልዶ ብዙ ሳይወራበት የፌስቡክ ገፅ ኖረው፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ተጨዋቹ ማንነቷ ካልተገለፀ እንስት ወንድ ልጅ ማግኘቱን በዚሁ ገፁ አወጀ፡፡ ባለፈው ወር ሮናልዶ ከየትኛውም ስፖርተና ቀድሞ የተከታዮቹን ቁጥር 100 ሚሊዮን አድርሷል፡፡ በግለሰብ ደረጃ በአጠቃላይ በፌስቡክ ከሮናልዶ የሚልቅ አንድ ሰው ቢኖር ዘፋኟ ሻኪራ ብቻ ነች፡፡
ሶስት ዓመታትን ቆጥረን ወደኋላ ብንመለስ ብዙዎቹ ትልልቅ ክለቦች የፌስቡክም ሆነ የትዊተር ገፅ አልከፈቱም ነበር፡፡ ዛሬ ሁሉም ገብተውበታል፡፡ እንዲያውም በተለያዩ ቋንቋዎች ከአንድ በላይ ገፆች እየከፈቱ በየደቂቃው አዳዲስ ተከታዮችን መቀበል ቀጥለዋል፡፡ የማንቸስተር ዩናይትዱ የማህበራዊ ድረገፅ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሪቻርድ አርኖልድ ክለባቸው ከፌስቡክ ጋር ከየትኛውም ዝነኛ ግለሰብ ወይም በፕላኔታችን ከሚገኙ የስፖርት ክለቦች ሁሉ የላቀ ቁርኝት እንዳለው ይናገራሉ፡፡
ትልልቆቹ ክለቦችም ሆኑ ከዋክብት ተጨዋቾቻቸው ይህንን የሚያደርጉትበከንቱ አይደለም፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድ በዓለም ዙሪያ 659 ሚሊዮን ያህል ደጋፊዎች እንዳሉት ይገለፃል፡፡ ይሁን እንጂ የእግርኳስ ትልቁ ችግር ክለቦች ደጋፊዎቻቸውን እንደሚፈልጉት የሚያገኙበት መንገድ አልነበራቸውም፡፡ አሁን ግን ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ኢንስታግራም፣ ቻይናስ ዌይቦ እና ሌሎችም ደጋፊዎች ለክለቦች እና ለተጨዋቾች እጅግ ቅርብ እንዲሆኑ አብቅቷቸዋል፡፡ ቀጣዩ ሥራ የደጋፊዎችን ፍቅር ወደ ገንዘብ መቀየር ይመስላል፡፡ ይህ የእግርኳስ ኢንዱስትሪ ቀጣይ ፍላጎት ነው፡፡
እግርኳስ ብዙዎች እንደሚያስቡት ትልቅ ቢዝነስ አይደለም፡፡ ባለፈው ዓመት ሪያል ማድሪድ ያገኘው 521 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ በታሪክ ከየትኛውም የስፖርት ክለብ የላቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፊንላንዳዊው የፋይናንስ ተንታኝ ማቲያስ ሞቶላ የክለቡን ገቢ ብቻ እንደመመዘኛ ወስዶ አስገራሚ መረጃ ይሰጣል፡፡ ሪያል ማድሪድ በገቢው ብቻ ከተወዳደረ በፊንላንድ 120ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ኩባንያ ይሆናል፡፡
እግርኳስ ተወዳጅ ስፖርት ነው፡፡ ትልልቅ ክለቦች ደግሞ ስማቸው ይገዝፋል፡፡ እንደ ኢኮኖሚክስ ባለሞያዎች እምነት እግርኳስ የአፍቃሪዎቹን ፍቅር ወደ ገንዘብ ለመቀየር እጅግ ይቸገራል፡፡ ለምሳሌ በኩዋላ ላምፑር የሚኖር እና ስሙ አብዱል የሚባል የማንችስተር ደጋፊን አስቡ፡፡ አብዱል እንኳን በኦልድትራፎርድ ስታዲየም መታደም ቀርቶ አውሮፓን ረግጦ አያውቅም፡፡ ሆኖም በቅጂ የተሰራ የዩናይትድ ማሊያ ይለብሳል፡፡ የክለቡን ዜናዎች ከኢንተርኔት ያገኛል፡፡ ዩናይትድ ሲጫወት በአካባቢው በሚገኝ አንድ ሬስቶራንት በቴሌቪዥን ይከታተላል፡፡ ይሁን እንጂ ክለቡ ከአብዱል የሚያገኘው ሰባራ ሳንቲም የለም፡፡ አብዱል የሚባል ሰው ስለመኖሩም ማንችስተር ዩናይትድ ጨርሶ አያውቅም፡፡
ማህበራዊ ሚዲያ ይህንን ሁሉ ይለውጣል፡፡ በፌስቡክ ገፅ በከፈቱ ከ1.3 ቢሊዮን ሰዎች መካከል 500 ሚሊዮን ያህሉ ለእግርኳስ ጠንካራ ስሜት እንዳላቸው የድረገፁ ሥራ አስፈፃሚ ግሌን ሚለር በቅርቡ በርሊን ውስጥ በተዘጋጀ አንድ ኮንፈረንስ ላይ ተናግረዋል፡፡
በዓለም ዙሪያ የእግርኳስ አፍቃሪዎች ይበልጥ ጨምረዋል፡፡ የአውሮፓ ትልልቅ ክለቦች ዘግየተውም ቢሆን በቻይና፣ ህንድ፣ አሜሪካ እና ኢንዶኔዢያ በርካታ ደጋፊዎችን ማግኘት ችለዋል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ ለዚህ ጥሩ ድልድይ ሆኗቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ማህበራዊ ድረገፅ ለእግርኳስ ክለቦች ዕድል ክፉ ሳይሆን ስጋትም ነው፡፡ በእግርኳስ ትልቁ የግብ ምንጭ የቴሌቪዥን መብት ክፍያ እንደመሆኑ ማህበራዊ ድረገፆች ይህንን እንዳያሳጣቸው ይፈራሉ፡፡ ወደ ስታዲየም የሚመጡ ደጋፊዎች ቁጥር እንዳይቀንስባቸውም ይሰጋሉ፡፡ በሌላ በኩል እንደሌሎቹ ኩባንያዎች ሁሉ የማህበራዊ ድረገፆቻቸው በህገወጥ ግለሰቦች ስወር ጥበብ እንዳይሰበሩ ለማረጋገጥ ይተጋሉ፡፡ በ2010 ፌስቡክን የተቀላቀለው ማንችስተር ዩናይትድ 615 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ሲሆን የገፁን ደህንነት በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ አርኖልድ መስክረዋል፡፡
ማህበራዊ ድረገፆች ከውዝግብ ነፃ አይደሉም፡፡ ተጨዋቾች በገፆቻቸው በሚፅፉት ነገር በተደጋጋሚ ራሳቸውን ለችግር ሲዳርጉ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ የኪውፒአሩ ሪዮ ፈርዲናንድ በቅርቡ በትዊተር ገፁ ባሰፈረው ያልተገባ ፅሑፍ ምክንያት በእግርኳስ ማህበሩ እገዳ ተጥሎበታል፡፡ ከ2011 ወዲህ ብቻ ማህበሩ 60 ሰዎችን ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር በተያያዘ ቀጥቷል፡፡ የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር እነዚህን ድረገጾች በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚያሻ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የትዊተር እና ከክለቡ የሚወጡ ምስጢሮች ያሳስቡናል፡፡ ይህ ጉዳይ ቁጥጥር ይፈልጋል››
ተጨዋቾች በይፋ በሚፅፏቸው ጉዳዮች ጣጣ ውስጥ ሲያስገባቸው የተመሰለከተው ሮናልዶ ጥንቃቄ መርጧል፡፡ የፌስቡክ ገፁ በእንግሊዝኛ ነው፡፡ የእርሱ አፍ መፍቻ ቋንቋ ደግሞ ፖርቹጊዝ ነው፡፡ ስለዚህ መፃፍ የሚፈልገውን መልዕክት የፌስቡኩን ገፅ ለሚያስተዳድሩለት ሰዎች ይልካል፡፡ እነርሱ የተሻሉ አቻ ትርጉም ያላቸውን ቃላት ተጠቅመው ራሳቸው ገፁ ላይ ያስቀምጡለታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ራቱን እየተመገበ ከሚገኝበት ሬስቶራንት ፎቶዎችን የሚልክበት ጊዜ ቢኖርም የምስል መብቱን የሚቆጣጠርለት ኩባንያ በሚፈልገው መጠን ብዙ ፎቶ አይልክም፡፡ ክለቦች ተጨዋቾቻቸው በማህበራዊ ድረገፆች ላይ ስለሚፅፉት እና ስለሚያስቀምጡት ምስል እንዲጠነቀቁ አበክረው ማሳሰባቸው የፌስቡክ ባለስልጣናትን ብዙም አያስደስትም፡፡
ይሁን እንጂ እግርኳስ ማህበራዊ ሚዲያን እንደ ቢዝነስ መልካም አጋጣሚ ወስዶታል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የጀርመኑ በሩሲያዶርትሙንድ የአሰልጣኙን የርገን ክሎፕ ኮንትራት ማራዘም አስመልክቶ የሰውየውን ፎቶግራፍ በትዊተር ገፁ ላይ አስቀምጦ ነበር፡፡ በፎቶግራፉ ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው ግን አሰልጣኙ ፊርማቸውን ያኖሩበት ስታቢሊ የሚል መጠሪያ ያለው ብዕር ነው፡፡ ይህንን በማህበራዊ ሚዲያዎች ያሉ የዶርትሙንድ ደጋፊዎች ሁሉ አስተውለውታል፡፡ በወቅቱ ብዕሩን አምራቹ ሼዋን ስታብሎ የተሰኘ ኩባንያ ባለስልጣናት በሁኔታው እጅግ ተደምመው ነበር፡፡
የማህበራዊ ሚዲያን ጥቅም የተረዳ ክለብ በስፖንሰርሺፕ ክፍያ ብዙ ሊጠቀም ይችላል፡፡ በ2012 ዩናይትድ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ተሳትፎ ማድረግ ከጀመረ በኋላ ከማሊያ ላይ ስፖንሰሩ ቼቭሮሌት ጋር ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበ የ47 ሚሊዮን ፓውንድ ዓመታዊ ስምምነት ላይ መድረሱ የአጋጣሚ አይደለም፡፡
እንደ ማንችስተር ዩናይትድ ላለ ትልቅ ክለብ የማህበራዊ ሚዲያ ጥቅም ከስፖንሰርሺፕም ገቢ ይልቃል፡፡ ዩናይትድ እንደ አብዱል ያሉትን ደጋፊዎቹን ማግኘት ይችላል፡፡ የኦልድትራፎርዱ ክለብ እንዲህ አይነቶቹን አፍቃሪዎቹን መመዝገብ ከቻለ ይበልጥ ይገዝፋል፡፡ የተከታዮቹን ማንነት፣ ፍላጎት እና ምርጫ ማጥናት ቀጣይ ሥራ ይሆናል፡፡
በሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች የሚገኙ ኩባንያዎች ፌስቡክ እና ጎግልን በሚገባ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ የተከታዮቻቸውን ወይም የደንበኞቻቸውን ማንነት ይለዩባቸዋል፡፡ ድረገፆቹ አገልግሎታቸውን ለደንበኞቻቸው በነፃ ያቀርባሉ፡፡ ተጠቃሚው ስለ ማንነቱ በነጻ መረጃ ይሰጣል፡፡ በዚህ ሲስተም ውስጥ የእግርኳስ ክለቦች ከሌሎች ኩባንያዎች በተሻለ የመጠቀም ዕድል እንደሚኖራቸው የብራንዲን ባለሙያው ኦሊቨር ኬይዘር ይመሰክራሉ፡፡
ለምሳሌ ትልልቅ ክለቦች ከሌሎች ኩባንያዎች የበለጠ በማህበራዊ ድረገፅ ተከታይ ይኖራቸዋል፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድ ከናይኪ ወይም ማክዶናልድስ የላቀ ተከታይ አለው፡፡ በሌላ በኩል የእግርኳስ ክለቦች ከሌሎች ኩባንያዎች በተለየ ‹‹ፍቅር እና ታማኝነት›› ይኖረዋል፡፡ ‹‹እንደ ደጋፊ በስሜት የተሞላ አታገኙም፡፡ ማንኛውንም ነገር ያደርጋል›› ይላሉ ኬይዘር፡፡ ደጋፊ በኮምፒዩተር መስኮቱ ጨዋታ በሚያይበት ወቅት ብታገኙት በስሜቱ ጫፍ ላይ ትይዙታላችሁ፡፡ ‹‹ብልጥ የሆነ ክለብ ምናልባት ለወደፊቱ ሌላውን ኩባንያ እንዲህ ሲል ታደምጡ ይሆናል፡፡ ማነህ እኔን 25 ሚሊዮን ደጋፊዎች ፈልገህ ነው? እኛ ራሳችን እንፈልጋቸዋለን›› ይላሉ ኬይዘር፡፡
ክለቦች አሁን የተከታዮቻቸውን እና የደጋፊዎቻቸውን ማንነት የሚለዩላቸውን ሚዲያዎች እንዲሁም ድረገፆች ለመጠቀም በርት ያሉ ባለሙያዎችን እየቀረጠሩ ይገኛሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክለቦች ባለስልጣናት ስለ ደንበኞች ጉዳይ አስተዳደር ደጋግመው ሲናገሩ መስማት ተለምዷል፡፡ የጁቬንቱስ የገቢ ጉዳዮች አስፈፃሚ ፈራንቼስኮ ካልቮ እና አንጋፋው የትምባሆ ኩባንያ ባለሙያ ፊሊፕ ሞሪስ በጋራ ደንበኞቻቸውን ለመጥቀም የተሻለውን ስትራቴጂ እንደሚከተሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ደጋፊዎችን እኛ ወደ አዘጋጀነው መዋቅር እንዲመጡ እንፈልጋለን፡፡ በዚያ መልኩ ይመዘገባሉ፡፡ ደጋፊዎቻችንን ለይቶ ማወቅ እና በእነርሱ ላይ ተፅዕኖ ማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ ለማግኘት እጅግ ወሳኝ ነው›› ይላሉ፡፡
ክለቦች ደጋፊዎቻቸውን ማንነት ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው፡፡ በትዊተር ‹‹አብዱል ከኩሞላ ላምፑር›› ከሚለው አልፎ የ12 ዓመት ታዳጊ ነው? ወይስ የ42 ዓመት ጎልማሳ? ምን ያህል ገቢ ያገኛል? ምን ሊገዛ ይችላል? እነዚህ መረጃዎች አብዱልን ደጋፊ ብቻ ሳይሆን የገንዘብ ምንጭ ያደርጉታል፡፡