ነቢዩ ሲራክ
እህት ሃና በሰው አራዊቶች ለአምስት ተከታታይ ቀናት ተደፍራ ወድቃ ያገኟት አባት ልጃቸው ህክምና ታገኝ ዘንድ ከሆስፒታል ሆስፒታል ስለተንከራተቱበት ፣ የህክምና እርዳታ ስለተነፈጉበት አሳዛኝ ሂደት ሀገር ቤት በሚተላለፈው ኤፍ ኤም ራዲዮ ተናግረዋል ። አባት ሲናገሩ ለሃና ህክምና ማድረግ ያልቻሉት የመንግስት ህክምና ተቋማት ሳያንስ ፖሊስ ጉዳዩን እንዲመረምር በልመና ካሳኩ በኋላ ህክምና ማግኘት ባለመቻላቸው የሚረዳቸው አጥተው ተጎጅ ልጃቸውን ይዘው ወደ ቤታቸው ወስደው ስላሳደሩበት እንግልት ሰምተናል ፣ ይህም ያማል: (
እንደ አባት አቶ ላላንጎ ገለጻ ልጃቸው እህት ሃና ከጋንዲ ጥቁር አንበሳ ከጥቁር አንበሳ ዘውዲቱ ግልጋሎት ተነፍገው ተንከራተዋል ። ወደ መጨረሻም በዘውዲቱ ሆስፒታል አልጋ ተሰጥቷን መታከም መጀመሯንና በህክምና እያለች የምስክርነት ቃሏን በደል አድራሽ ያለቻቸውን ሶስቱ በፖሊስ ተይዘው ቀርበው ለይታ ማሳየቷን አባት ተናግረዋል ። ሃና በመጨረሻ ሰአቷ ከምስክርነት አልፎ በኑዛዜዋ በጉዳዩ የሉበትም ያለቻቸው እንዲለቀቁ መናገሯንና ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት አላት ያለቻትን ጓደኛዋን ፖሊስ ” በቂ መረጃ የለም!” በሚል እንደለቀቃት ሲናገሩ ይህም ከሃዘን በላይ ሃዘን እንደጨመረባቸው ቅሬታቸውን ተናግረዋል !
ምስኪኗ እናት ወሮ ትርፊ …
የሃና እናት ወሮ ትርፊ የልጃቸው የሃናን ስቃይ መመልከታቸውን ፣ በማደንዘዣ መቃጠል መንገብገቡ በረድ ሲልላት ነፍስ እየገዛች የሆነው ሁሉ መናገሯን እያነቡ እያነቡ ከአድማስ ራዲዮ ጋር የተናገሩት እናት የሃናን በደል መደበቁ ትድናለዕ የሚል ተስፋ ስለነበራቸው እንደነበር እያነቡ ልብን በሃዘን በሚሰብር ስሜት ተናግረዋል … በመጨረሻም ባስተላለፉት መልዕክት ” በሃና ግፉ ይብቃ ሲሉ ባስተላለፉት መልዕክት እንዲህ ” … እኔ ያለኝ ነገር በሃና ሁሉም ነገር እንዲቀር ፣ ለምን አሁንም ትውልዱ አየተበላ ነው ፣ ህጻን እየተበላ ነው ፣ የህጻናት መብት እንዲከበር ፣ ትክክለኛ ፍርድ እንዲሰጥ ነው የምፈልገው ፣ ልጀ አትመጣልኝም በቃ ምን አደርጋለሁ? አሁንም እንደቀጠለ ነው … ለእኔ እንደሁ አትመጣልኝም ….ትክክለኛ ፍርድ እንዲሰጥ ነው የማስተላልፈው! ” የዚህች እናት ህመም ህመማችን ነው ! መልዕክታቸው መልዕክታችን ነው ! ያም ሆኖ ይህም ያማል ፣ ያማል ፣ ያማል !
አዎ በርካታ ሃናዎች በአረብ ሃገራት መካከል የሁለትዮሽ ውል ባልተደረገበት ሁኔታ ለኮንትራት ስራ ወዳለሁበት ጃገር ተልከው ግፍ ተፈጽሞባቸው አይቻለሁ ፣ ሰምቻለሁ! ምንዱባኑ ታዳጊዎች እድሜያቸውን ቆልለው በመጡ በርካታ እህቶች ባልጠነከረ ለጋ ገላቸው ተጎድቷል። ግፍን አስተናግደውየተረፉት ተርፈው በመንግስት ወኪሎች አማካኝነት ሱሸኙ በቂ ህክምናና ፍትህ አግኝተው አላየንም። ይህ ሆነና እውነቱ ግፉአኑ ተገፍተው ወደ ድሃ ጎጇቸው ለመሸኘታቸው እማኝ ነኝ ። የእኒያ እናቶች ድምጽ እንደ ሃና እናት ባንሰማውም የሰቆቃ ህይወታቸውን ፣ በድህነት ቤት የተረከቧቸውን ልጆቻቸውን ህይወት እናስበው !
በእህቶቻችን ደልላ የበለጸጉት ክፉዎችን ዛሬ ወደ ፍርድ የሚያቀርባቸው ቀርቶ ዝንባቸውን ” እሽ ” ማለት የሚቻለው የለም ! ይባስ ብለው ዛሬ ዳግም ወደ አረብ ሃገራት የተዘጋው የኮንትራት ስራ ይጀመር ዘንድ እያጎበጎቡ ነው! ይባስ ብለው የኮንትራት ስራው የመጀመሩን ለእነሱ የሃሴት ለእኛ መርዶ የሚሆነውን ቀን መቅረብ ባለጊዜዎች ናቸውና በድፍረት እየነገሩን ነው! ይህም ያማል ፣ ያማል ፣ ያማል :(
ባደገች በተመነደገች ሃገራችን እየሆነ ያለውን ላሰበው ያማል …ያኔ ታዋቂው ድምጻዊ ዶር ጥላሁን ገሰሰ በቂ ህልምና የሚያገኝበት ሆስፒታል ጠፍቶ መንከራተቱን አስታውሰን ፣ የሃናን የህክምና ተቋማት ግፍ የተፈጸመባትን እህት መታደግ አለመቻላቸውን ስናስበው ልባችን በሃዘን ይሰበራል :( ይህም ያማል ፣ ያማል ፣ ያማል ይህም ያማል ! ዛሬ ህመማችን ጸንቷል ፣ የጸናው ህመም የሚታከመው ደግሚ ትክክለኛ ፍትህ ስናገኝ ብቻ ነውና ፍትህን ተጠምተናል ፣ ፍትህን እንሻለን !
ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 13 ቀን 2007 ዓም