Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የወያኔ ምርጫ –ለእርግጫ። (ሥርጉተ ሥላሴ )

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 21.11.2014 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/

ጭል ጭል ስትል የነበረችው የብዕር ጧፍ ተከረቸመች – ለወያኔ የምርጫ እርግጫ ማጫ መመቻ በመሆን ለካቴና – ተሰጠች።

ሥልጠናው እርግጫ፤ መንገዱ ውንብድና፤ መንፈሱ ፍጥጫ የወያኔ ተፈጥሮ ይሄው ነው። ሥርዓትና ወያኔ ተያይተውም አያውቁም። ይልቁንም ሥርዓተ – አልበኝነት የዋኘበትና የናኘበት  መሆኑን ከተፈጠረበት ሀገርን የማክስል ተልዕኮው ቀን ጀምሮ ያሉት ሁኔታዎች አንድ በአንድ ቢፈተሹ ፍሬ ነገሩን ማግኘት ይቻላል።

2007 electionወዬኔ በተፈጥሮው የአውሬነት ሰብዕና የተለበሰ ነው። አውሬነት ደግሞ ጸረ ሰው በመሆኑ በሰበነክ ጉዳዮች ላይ የሚወስዳቸው መጠን ያለፈ የጭካኔ እርምጃዎች እራሳቸው ቆመው ይመሰክሩበታል። እርግጥ ወያኔ በተለዋዋጭ ባህሪው አጥፊ ፍላጎቱን ለማስፈጸም አስችሎታል። በማጭበርበር – በማምታታት ደጉን የኢትዮጵያ ህዝብ አጃቢ በማደረግ ለሥልጣን መብቃቱ ብቻ ሳይሆን፣ የሚገርመው ህዝባዊ የእንቢተኝነት ሞገዳማ ነበልባሉ ዘመን መራዘሙ ምክንያቱ ቅጥፈቱና እራሱን ገልጦ ለማሳዬት ድፍረት የሚያንሰው በመሆኑ ነው። ወያኔ በክንብንብ ኖሮ በክንብንብ ያልፋል። አልማጭ!

ቀባ አድርጎ አብልጭልጮ አንድ ህዝበ ጠቀም ዬሚመሰል ግን ገዳይ ፖሊሲ ያወጣል። ወገን ላይ ላዩን ብቻ አይቶ የተሻለ – የበለጠ – የሚሆን ነገር ተገኘ ብሎ በፍቅር ከአዲሱ የሽፍታ ቅብ ፖሊሲ ጋር ደፋ ቀና ሲል፣ ቀስ እያለ እዬሸረሸረ ወደ አቀደውና ወደ አለመው ላጥ ወደ አለው ገደል ይዞ መሄድ ብቻ ሳይሆን፤ ተስፋን ከነስብዕና ቅጥቅጥ አድርጎ ይቀጣበታል። “ወንዝ ሲወስድ እያሳሳቀ” ይበል የለ – እንደዛ ነው ነገሩ።

ወያኔ በሥልጣን መባቻው ነፃ ፕሬስ አንደ ጉድ ፈቀደ። ማህሌት፤  አዕምሮ፤ ሙዳይ፤ ጦቢያ፤ አፍሪካ ቀንድ፤ ኢትዮጲስ፤ ሳታናው  ወዘተ … መጽሄቱም ጋዜጣውም በገፍ መታተም ጀመሩ። ነፃነት የጠማው ብዕር ስለ ነፃነት፤ ስለመናገር መብት፤ ስለ የህግ የበላይነት፤ ስለ ኢትዮጵያዊነት፤ ስለ አብሮነት፤ ስለ ፍቅር የሚገባውን ያህል ቀን ከሌት – ማሰኑ። … ህዝቡም የራበውን መተንፈሻ ስላገኘ በሽሚያ፤ በቋሚ ደንበኝነት ጸሐፍትን አበረታታ – አደነቀ – ሃቅንና እውነትን ከበከበ … ግን ቀጠለ ….? እእ ….

“የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ” የወያኔ የመቅጫ መንገዱ ማሟሻ ነበር። ነፍሱን ይማረውና በጋዜጠኛ ተፈራ አስማረ ግንባር ቀደምትን ወህኒ ቤቶች በመጽሄትና በጋዜጣ አዘጋጆች ተጨናነቁ። ፍርድ ቤቶችም ሚዛንን ገልብጠው የሚሰቅሉበትን ሁኔታ ወያኔ አመቻችቶ አደራጀላቸው። ከዚህ በኋላ ዒላማውን ጎሰኛው ወያኔ አስተካክሎ እስኪበቃው ድረስ ነጻውን ፕሬስ ወቃው። የመናገር፤ የመጻፍ፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ሆነ የማንበብን የለመለመ ተስፋንም ገንዞ በድፍረት ቀበረው። ጭላጭሏንም ሶሞኑን ዳፍንት አለበሰው። ደፋሩ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቀርቶት ነበር እሱንም ለእግር – ብረት፤ ከህዝብ እውነተኛ ብሶት ተነስታ ጭብጥን – በጭብጥ አዋዳ ለመንፈሳችን ሁነኛ ስንቅ የነበረቸው የተመስገን ትእግስቱ /ደሳለኝ/ ብእር – የካቴና ስንቅ ሆነች። ይህቺ የእርግጫ ምርጫ ስትመጣ ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ የቆዬ ውሻ ያደርገዋል። ደም – ደምም ይሸተዋል – አረሙ።

ይህን ለምሳሌ አነሳሁ እንጂ ወያኔ አቅዶ የሚወጣቸው ማናቸውም ትልሞች ሁሉ የተከደነ ወይንም የተሸፈነ የበቀል ተልዕኮ አሽኮኮ አድርገው ነው የሚወጡት። አንዷ ቃል ወይንም ሐረግ ለምለም ዝግን ትመስላለች። ግን በመርዝ የተቀመመች የመሞቻ እንክብል ናት። አረሙ ወያኔ የተነሳበት ሆነ ያለመው ቂምና በቀልን ሥልጣን ይዞ እንዴት ተግባር ላይ ማወል እንደሚችል ነበር። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከእጁ የገባ ማናቸውም ፍጡር የማናቸውም ዓይነት ሰቆቃ መፈተኛ ነው የሚሆነው። ይህን በግለሰብ ደረጃ አይተን ወደ ሀገራዊ ጉዳይ ስናመጣው ስንት በደልና መከራ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ተሸከመች መገመት ይቻላል።

እኛ ደግሞ ነገረ ሥራችን ግልጥና ቀጥተኛ ስለሆን የምንፈልገውን፤ ያስብነውን፤ ውስጣችን የሚነግረንን፤ ያቀድነውን በነፃው ሚዲያ በሉት በመጸሐፍ እናወጣለታልን። ይህ እሱ ቆልፎ ላስቀመጠው ሸሩ ድውለቱ ነው። በቀጣዩ ጊዜያት ወራት ሆነ አመታት በተገባው ተሰናድቶ አዲስ መሰል ግን በቀልን ያረገዘ ደንብና ህግ ያሰናዳበታል። ወይንም ስስ ነው በተባለው ቦታ እዬሰበረ የሚያኖር አዲስ ህግ ያረቅበታል …. ውድ የፁሁፌ ታዳሚዎች ታስታውሱ ከሆነ የሳውዲው የወገን ሰቆቃ ወያኔ የተጋለጠበት፤ ዬኢትዮጵውያን ቁጣ የነደደበት ወቅት ነበር። ታዲያላችሁ ወያኔ ቀዳዳውን ለብዶ የሸፈነበት መሳሪያው የተከበሩ ዶር/ ካሳ ከበደ ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ በሰጡት የበሰለ በተመክሮ የፀደቀ ትንተና ነበር። ዝሎ የነበረው የወያኔ መንፈስ ተነቃቅቶ ጣዖት አምላኪዎቹ ከበሯቸውን እንዲያንኳኩ ያገዛቸው።

…. ከዛ ግልብ የታይታ ተግባር በኋላ ለወገኖቻችን ምን ተደረገ? ምንም። ሁሉን ነገር ስታዩት የነፈሰበት ጉድ ነው። መጣፍያ ነገር። ለነገሩ ማጣፊያው ለትንፋሽ ስለሚያጥረው ነው። ወያኔ የእኔ የሚለው ብቃት እኮ የለውም። የኢሠፓ ካድሬዎች ናቸው ነፍስ የዘሩበት። …. ስለምን ይህን ወንጀል እንደሚፈጽሙ አይገባኝም። አዎን ወንጀል ነው። የመጀመሪያው በሁለት ቢላዋ መብላት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ እንዲህ ላለ ርኩም – እርጉም ሥርዓት ጧፍ አብርቶ ማሽሞንሞናቸው ነው። ልምድና ተመክሯቸውን በገፍ መለገሳቸው … ታሪክን የማቃጠል ያህል የሀገር በደል ነው። ተደናብሮ እንዲወድቅ ነበር ማደረግ የነበረባቸው። ያውም እኮ እነሱም ቢሆን እንደ አሮጌ አካፋና ዶማ ከተጠቀመ በኋላ …. እህል ውሃቸው እልቅ —-

አሁን ይሄ ምርጫ የሚባለው ነገር ወገኖቻችን በገፍ ወደ እስር ቤት የሚወረወሩበት፤ ሴት ልጆች በግፍ የሚደፈሩበት፤ ደጁ ሜዳው፤ ዱር ገደሉ በፍርሃትና በስጋት የሚዋጥበት፤ መተንፈሻ ባንቧዎች ሁሉ የሚዘጉበት ህዝብን በነቂስ የሚያሳድድበት ዘመቻዊ ትልሙ ነው። እንዲሁም ወያኔ ወዳጅና ጠላቱን የሚለይበትና በጠላቶቹ ወይንም ፊት – ለፊት በወጡት ተቀናቃኞቹ ላይ ቂምን ቋጥሮ አጋጣሚ እዬፈለገ የሚያድንበት መረቡ ነው። ከዚህም በላይ በተነጠላዊ ህይወትም ውስጥ በሚያሰማራቸው ሰላዮቹ አማካኝነት የቤት – ለቤት ውጥረቱን አጠንክሮ ሰላም የለሽ ኑሮ ህዝባችን እንዲኖረው የሚያደርግበት እጅግ የረቀቀ የበደል ጋሜና ቁንጮው ወይንም በደልን የሚያስጌጥበት ወቅቱ ነው። የወያኔ ምርጫ እርግጫን አስልቶ – ወገኖቻችን በጥርስ የሚገበቡት ተለይተው ከላይ እሰከ ታች ዝርዝራቸው ተይዘው በዓይነ ቁራኛ የሚጠበቁበት የመጠራቅቅ ወቅት ነው። …. በአፈና፣ በማሳደድ፣ መርዝ በመስጠት፣ ከሥራ በማስለቀቅ፣ ከእድገት በማገድ፣ ከቦታ በማዛወር ማናቸውም አለ የተበለ የቂም እርምጃውን የሚወስድበት የማጥቂያ፤ አቅዶ የሚፈጽመው አሳቻ * መንገዱ ነው። ለዛውም ከእርግጫ – ከፍጥጫ  – ከአውሬነት ስብእናው ጋር …..

ስለዚህ ይህን አራት አመት እዬቆጠረ በሚያመጣው የማሳደድ ዘመቻ መደገፍ – መሳተፍ – ማሟሟቅ – ተስፋ ማደረግ - አጀንዳ ማድረግ – መንፈስን መስጠት – መስዋዕትን መክፈል – መዋለ ንዋይ ማፍሰስ ያስፈልጋዋልን? ….. ሂደቱ “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማለይ” ሥነ ውበታዊ ፈሊጥ በእውን ተግባራዊ የሚሆንበት ከመሆኑ በተጨማሪ …. በወገኖቻችን ላይ በስተጀርባ የሚፈጸው ድርብ ድርብርብ ሰቆቃ ደግሞ ሚዛን ከቶውም ሊወጣለት አይችልም። ዛቪያው ይሸከረከራል ወገን ይታረስበታል – በግፍ።

ስለዚህ የተገፋ ወገን፣ የከፋው ወገን፣ የተከ ወገን፣ የተራበ ወገን – ባይታዋርነት በሀገሩ ላይ ተፈርዶበታል፤ በሌላ በኩልም ሳይፈልግ ወይንም ሳይመኘው የተሰደደው ወገንም ቢሆን ሃገሩ በዓይኑ እንደ ዞረች – እዬቀረ ነው። ስለሆነም ወገን ምን ማደርግ አለበት? ነው የጹሁፉ መሰረታዊ አናት። የአጭበርባሪን – የእርግጫ ምርጫ ለእሱ የሚፈይደው አንዳችም ነገር አንደሌለ ካለፉት ምርጫዎች በስማ በለው ሳይሆን በህይወት ተኖረበት። አሁን የምርጫው ውጤት በድርጅታዊ ሥራ ድልድል ተደርጎበታል። ለሁሉም ቦታ በውስጥ ታዋቂነት ሰው ተመድቦበታል። ለምስል ነው ዬምርጫ እርግጫ ዳንኪራ የተሰናዳው። ወያኔ የሚመራበት ርዕዮት የሶሻሊዝም አናርኪዝምን ነው። ስለዚህ ሰፊው  ዬኢትዮጵያ ህዝብ የመከራው ገመድ የሚበጥስበትን ዘላቂ ተከታታይ ተግባር መከወን ይኖርበታል።

መበታታኑ ሆነ ተነጠላዊ ትግል ሀገር ቤት ላይ የሚያወጣ መንገድ አይደለም። የወልን ችግር በወል ለመወጣት በጋራ መነሳትን ይጠይቃል። ሰራተኛ፤ ጋዜጠኛ፤ ጸሐፊ፤ የእምነት ማህበር ምእመናን፤ ነጋዴ፤ ተማሪ በዬጊዜው ብሶታቸውን በአንድም በሌላም መንገድ ይገልፃሉ። …. አንድ ነጣላዊ ፍላጎትን ብቻ አንግበው። ነገር ግን ጠቃሚው ነገር ይህን ተናጠላዊ ፍላጎት ወደ አንድ ማዕከል አምጥቶ ህዝባዊ አልገዛም ባይነትን በተከታታይ  አደባባይ ማዋል ብቻ ነው መፍትሄ ሊሆን የሚችለው። የአንድ አካል ብቻ ሩጫ – ትንሽ ነጥብ፤ የሁሉም አካል የጋራ ሩጫ ግን ሙሉ ተስፋን በእጅ ያስገባል። ጥላቻው ሥራዓቱና የሚተዳደርባቸው ህግጋት ብቻ በመሆናቸው ይህን በበሰለ አምሮ አመዛዝኖ ሥርዓቱን እስከነመመሪያው እንዲወገድ የማደረግ ዘመቻ ነው ለነፃነት ትግሉ ስንቅም ትጥቅም ሊሆን የሚገባው። ግለሰብ ቢወርድ ግለሰብ ይተካል። ሄሮድስ መለስ ዜናዊ አለፉ … ግን ሥርዓቱ አለ። … ለዛው ኢትዮጵያዊነትን እዬነቀለ።  የአቶ በረከት ሆነ የአቦይ ህልፈት ወይንም የአቶ ቴወድሮስ አድሃኖም የአውሮፕላን አደጋ ደርሶባቸው ቢያልፉ እንኳን መፍትሄ አይሆንም። መፍትሄው ጠላታችን የሆነው የወያኔ ማንፌስቶ ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ ሥርአት መፍጠር ነው። ለዚህ ደግሞ ፍላጎትን ወደ አንድ አቅጣጫ ማምጣት መሰረታዊ ጉዳይ ነው።

ይህ ደግሞ ይቻላል “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ” መከራውን – ስቃዩን – ፍዳውን – አታካች ኑሮውን ህዝብ አዳምጦ ለምላሹ እያንዳንዱ በነፍስ – ወከፍ የሚሳተፍበት “ሰላማዊ አመጽ” በመንፈስ ማህጸን ሲነግሥ የቅጽበት እንቅስቃሴ  ዬእልፍኝ ባለቤትነትን ያውጃል። ዛሬ እንዲህ ተፈሪ የሆነው የወያኔ የእርግጫ ህግ ህዝባዊ አመጽ ሲፈናዳ ህጉ እራሱ መሸሸጊያ ትንሽ ቁጥቋጦ ብቻ ነው የሚፈልገው። መጓጓት መልካም ቢሆንም ጉጉትን ማናር ግን የተገባ አይደለም። የጉጉት ህያውነትን በእጅ ያለ ብቃት ብቻ ነው የሚወስነው። የበቃ ተግባር – የበቃ ጉጉትን ያሳካል። ቤት ውስጥም ሆኖ እኮ ጸጥ ብሎ ማመጽ ይቻላል።

ምርጫውን ወያኔ የሚካሂደው ሳይወድ የተቀበላቸውን አሻንጉሊቱን ጠ/ሚር አውርዶ የራሱን ደም የሆኑትን አቶ ቴወድሮስ አዳህኖምን ለማጸደቅ ነው። ያው ከላይ የጠቃቀስኩላችሁ የቂም ማወራረጃው ሁነቶች እንደተጠበቁ ሆነው። ስለሆነም የነጻነት ትግሉ የእሱን የጢባጢቦ ግርድፍ ተውኔቱን ለራሱ አሸክሞ፤ ቀጣይ ሥራን መስራት ያስፈልጋዋል። “የእርግጫን ምርጫ” አይደለም ለ2007 ተሳክቶለት በቀጣዩም 2011 ክፍለ ጊዜ ቢያመጣው ከህሊና መሰረዝ ያስፈጋል። “የእርግጫ ምርጫ” ለእኛ በዕድ ራዕይ ነውና። እስከ እርግጫ ምርጫው መባቻ ሆነ እስከ ምርጫው ድንፋታ ስክነት ከዚያም ባለፈ ወደ ነፃነታችን ሊያሸጋግረን የሚችለው ድልድዩ ተጎሳቅሎ ሊቆይ ይችላል። ይህን ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባናል። … ድሉ ዛሬ ወይንም ነገ ላይሆን መቻሉ የነፃነት ትግል ባህሪ ነው። ትግል ረጅሙን የጨለማ ጉዞ ተጋፍጦ ነው ብርሃን ማግኘት የሚቻለው … ተፈጥሮው ይሄው ነው። አታካች – አቅምን ፈታሽ ነው – የነፃነት ትግል። ትንፋሹ ግን ጠንካራና የማይሞት ነው።

አሁን ባለፈው አመት ሰፊ የማደራጀት የተቃውሞ ተግባራት ሀገር ቤት ተከውነዋል። እነዛ መልካም ናቸው። ያደጉና የሰለጠኑም ነበሩ። አሁን ደግሞ ትግሉን ከፍ በማደረግ “ወያኔ በቃህን! ከሥልጣን ውረድ” የሚል መንፈስን መፍጠር – ማደራጀትና መምራት ያስፈልጋል። ምርጫው የእኛ አይደለም። ወደፊትም ወያኔ እስከ አለ ድረስ የእኛ ሊሆን ከቶውንም አይችልም። የእኛ ምርጫን የምንጠብቀው እራሳችን አምጠን በምንወልደው ነፃነት ብቻ ነው። ነፃነቱን በመንፈሱ የጸነሰ የነፃነት አርበኛ የጊዜው መርዘም ወይንም የሂደቱ አድካሚነት ወይንም የመንገዱ ኩረታማናት ወይንም የተስፋው ሩቅነት ምኑም አይደለም። እንዲውም ለነፃነት ትግል የጊዜ መስፈርት ግጥሙ አይደለም።

ስለሆነም ለዘላቂ ፍላጎት ዘላቂ ጽናት በእጅጉ ያስፈልጋል። ጽናቱን ወያኔ በሰላዮቹ አማካኝነት ብል አስብልቶ ተስፋ ቆራጭነት እንዲነግሥ ሊያደርግ ይችላል። ቀሪዎቹ ጽናት ያላቸው ሃይላቸውን ለወያኔ ግብር ሳያውሉ በሥልጡን ስልታማ አመራር ትግላቸውን ቆርጠው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ወገኖቼ አንድ ሰው ብዙ ነው። ይህን አንዲት ጠንካራ ሴት እጅግ ዝቅ ካለ ማህበረሰብ ተፈጥራ ለተነሳችበት ዓላማ አይደለም ሀገሯን አህጉሩን እንዴት እንደ ፈወሰች ጹሑፉን ስጨርስ አስነብባችኋለሁ። እንኳንስ ከአንድ በላይ ሆነን ….። የነፃነት ትግሉ ቤተስብ ሲሰበሰብ አዳራሹ ሞላ አልሞላ ጭንቀታችን ሊሆን አይገባም። ከተሰብሳቢዎቹ በአንዱ መንፈስ ውስጥ ያለው ቅዱስ ሃይል አቅሙ ብሩክ ሊሆን ይችላል። አድህኖት ሊሆን ይችላል። ብርሃን ሊሆን ይችላል። ስናሸንፍ ደግሞ አጃቢያችን እልፍ ነው የሚሆነው …

ትግላችን የመምረጥ መብት ሀገር ቤት ብቻ ሳይሆን፤ ውጪ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵውያን በዬሚኖሩበት ሀገር ድምጻችን የመስጠት መብታችን አስኪረጋገጥ ድረስ መድከም ይኖርብናል። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን የጎሳ አስተዳደር ከነማኒፌስቶው ግብዕተ – መሬቱ በህዝብ ህብረ አመጽ ሲደረመስ ብቻ ይሆናል። እንችላለን! ከቆረጥን! አሁንም እንደ ገና ሃይላችን አቅማችን ገንብተን ከብረት ቁርጥራጭ በተሰራ ዬመንፈሰ ጥንካሬ ትግላችን ከመራነው ነገን እናበራለን …. እኛም እንበራለን – በመሬታችን ላይ።

የማከብራችሁ ደሞቼ የሀገሬ ልጆች የነፃነት ትግሉን ፍላጎት እናሳድገው። ወያኔን ተወዳድሮ በምርጫ ማሸነፍ እንደማይሆን እናውቀዋለን። ከጎሳ ሥርዓት ተፈጥሮ ስንነሳ የምናገኘው አምክንዮ ይሄው ነውና። ነገር ግን ወያኔን ከሥሩ ለመንቀል የምንሰራቸው የመንፈስ ሥራዎች በራሳቸው ለድል ያበቁናል። የወያኔ ሥርዓት እሾኃማ ብቻ ሳይሆን ለትውልዱ መርዛማ ነው። ስለሆነም መወገድ አለበት። ሰሞኑን  ዛሬም ባዬሁት ሪፖርት በትንታጎቹ በነአቶ ሃብታሙ አያሌው ክስና በውዴ በአብርሽ የክስ ጭብጥን በሚመለከት እንዴት አድርጎ እንደ በለተው አይታችኋል። ውዴን አብርሽን ወደ ማነው ጠጋ ያደረገው ወደ ደምሂት አያችሁት ይህን ፍልስፍና … እባካችሁ የኔዎቹ ጊዜ ወስዳችሁ መርምሩት። … በኛ መንፈስ እንዴት ቢላዋውን አስልቶ ሽንሸና ለመፈጸም እንደ ተሰናዳ። እንዲህ ነው ሃሳባችነን ህሊናችንን ወላዊ ጥንካሪያችን ስንጥቅጥቅ የሚያደርገው። ስለዚህ ወያኔ ለኢትዮጵያዊነት ህልውና አጥፊ ዘር ነውና መወገድ አለበት። ወያኔ አረማሞ ዘር * ነው።

እርገት ይሁን – አንድን ነገር ማብሰል ያለብን ይመስለኛል። ይሄ “ወያኔ አልቆላታል፤ ባዶ ቀርቷል” በማለት የምናቃልለው ነገር መቆም ያለበት ይመስለኛል። ጠላትን ማቃለል የተገባ አይደለም። ባቃለልነው ቁጥር ሃይላችን ይሰንፋል። ጉልበታችን ይዝላል። ለነፃነት ትግሉ ልንሰጥ ያሰብነው ጉልበትም በተቀናሽ እሳቤ ይሆናል። ወገኖቼ – የኔዎቹ ወያኔ ሥልጣን ላይ ያለ፣ በተሟላ ሎጅክስቲክ የተደገፈ፤ በውጭ ሃይሎች ሙሉ ድጋፍ የሚደረግለት መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ከዚህም በላይ የጎጥ ድርጅት መሆኑ ደግሞ ሌላው ስብጥር ዕዳ ነው። …. ጎጡ በጋብቻ – በዝምድና – የተሳሰረ ነው። ስለዚህ ይሄን ጥሶ ለመውጣት የነፃነት ትግሉ የበለጠ ሃይልና ጥንካሬ ይጠይቀዋል። ጊዜም።  የፍላጎታችን መዳረሻ መዝግዬትም ምክንያቱ ይሄው ነው። ስለሆነም ሳያጋኑ ወይንም ሳያንኳስሱ …. ሚዛኑን በጠበቀ …. ግንዛቤ መጓዙ ጠቃሚ ይመስለኛል። ኑሩልኝ የኔዎቹ። የትናንት 20.11.2014 Tsegaye Radio የወግ ገበታ ካሰኛችሁ አርኬቡ ላይ አለ። ገባ ብላችሁ ኮምኩሙ … መሸቢያ – ሸበላ ሰንበት።

  • አረማሞ … ዘሩ ያፈራል። የሚያፈራው ግን ተፈጥሮ የማያውቀው የጥቁር ቀለም አመድ ነው። እርግጥ ሲያድግ ልክ እንደማናኛውም ባህር ማሽላ፤ ወይንም ስንዴ ቡቃያ ተስተካክሎ ነው። እሸቱን ከተሸፈነበት ስተግልጡት ግን የላመ ጥቁር የተቃጠለ አመድ ነው። ወያኔም እንደ እኛው ሰው ሆኖ የተፈጠረ ግን በተፈጥሮ የተበደለ የተቃጠለ አፈር ነው
  • አሳቻ – በግልጽ የማይታይ አሳሳች ስውር መንገድ፤
  • ማሳሰቢያ በትህትና … ለተስፋ መተያያ የአቶ ዮፍታሄ ክፍል አንድ – ሁለት – ሶስት እና ተከታይ ጹሑፎችን ደግመን ደጋግምን እናንበብው። እጅግ ጠቃሚ ጹሑፍ ነው ከምለው ጭብጡን “የኢትዮጵያዊነት ማኒፌስቶ” ብለው ይቀለኛል። “ሰንደቃችን” ነው። በድምጽም እኔ በተከታታይ እሰራዋለሁ።

 

ፅናትን የሰነቀ የነፃነት አርበኛ ድሉን ያያል!

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles