ፍኖተ ነፃነት ጋ
የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ዛሬ መስከረም 23 ቀን 2007 ዓ.ም ለምሳ ከቢሮ እንደወጡ መታሸጉን ዋና አዘጋጁ አቶ ጌታቸው ወርቁ ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ገለጹ፡፡ እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ ህትመት ካቋረጥንበት ነሐሴ 14 ቀን ጀምሮ ወደ ተለያዩ ማተሚያ ቤቶች ሄደን ለማተም ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ነገር ግን ከ2 ሳምንት በፊት ማተሚያ ቤት አግኝተን ዝግጅታችንን ካጠናቀቅን በኋላ ወደ ህትመት ልንገባ ስንል ፊውዝ ተቃጠለ በሚል ሰበብ ልትታተም አልቻለችም፡፡ አሁንም ወደ ሌላ ማተሚያ ቤት በመሄድ ለማተም ተስማምተው ዝግጅት በምናደርግበት ሰዓት ከማዕከላዊ ተደውሎ ትፈለጋላችሁ እንድትመጡ የሚል የስልክ መልዕክት እንደደረሳቸው አቶ ጌታቸው ገልጸው፣ ለምን እንደተፈለጉ ቢጠይቁም በስልክ አልነግርክም ማዕከላዊ ቢሮ ቁጥር 75 አቶ አለበል ብለህ እንድትመጣ እንደተባሉ እሳቸውም ሰኞ እንደሚመጡ ለደዋዩ እንደገለጹላቸው ነገር ግን በዛሬው ዕለት ለምሳ እንደወጡ ቢሮዋቸው እንደታሸገ ለፍኖተ ነፃነት ገልጸዋል፡፡