Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እንዴት? (ሥርጉተ ሥላሴ )

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 03.10.2014 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/

ዛሬ የተመለደውን የዘበኝነት ተግባሬን ልከውን – እነሆ መጣሁኝ።

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

እንዲህ ሆነ „በሳምንቱ እንግዳ“ የኢሳት ዝግጅት ክፍል ሁለት ላይ … አቶ ኤርምያስ ለገሰ „ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት“ በሚመለከት የሰጡት አሰተያዬት የግል ዕይታ ቢሆንም በህዝብ መገናኛ በመሆኑ ሰፊ አድማጭ እንደሚኖረው ስለተገነዘብኩኝ የትርጉም ማቃናት ያሰፈልገዋል በማለት ሃሳቤን ወይንም ግንዛቤዬን ላጋራ ወደድኩ። ቢቻል አቶ ኤርምያስ ከመርሁ ጋር እንዲታረቁልኝ፣ ባይቻል ደግሞ ሚዛኑን የጠበቀ ግንዛቤ በአድማጮች ዘንድ መኖር እንዳለበት በእጅጉ ፈለግሁኝ። በቅድሚያ ግን ማዶ – ለማዶ የነበረ ወገን እንዲህ በጠራ መስመር ተገናኝቶ ሃሳብን  – በሃሳብ ለማታገል የተቻለበት መሰረታዊ ምክንያት አቶ ኤርምያስ ለገሰ በመሆናቸው፣ የጎጥ አስተዳደርን አሻም ብለው የነፃነት ትግሉን በመቀላቀላቸው ነውና ለወሰዱት ሥር ነቀል እርምጃ ከልብ በአክብሮት ላመስግን እወዳለሁ። እንዲሁም ውይይቱን ልብ ብሎ ላዳመጠው በወያኔ ሥር የወደቀችው እናት ሀገራችን ኢትዮጵያና ልጆቿ የሚከፍሉትን አሳር እጅግ መራራነት በዬአጋጣሚው በመግለጸዎት ደስ ብሎኛል። እንኳን ወደ እኛ መጡ – አብረን ለመዝለቅም ያብቃን አምላካችን። አሜን!  http://ethsat.com/video/esat-bezih-saminte-with-tamagne-beyene-ermias-legesse-wendimagegne-gashu-august-10-2014-part-2/ የእኔን መንፈስ ያነሳሳው ሊንክ ይኸው ሲሆን፤ ከገለጻው ውስጥ ሥንኞቹ ከ45 አስከ 48 ደቂቃ ባለው ጊዜ ይገኛሉ። እርግጥ ነጥብ በነጥብ አልጻፍኩትም – አልሄድበትም  – እንዳላሰለች በማሰብ። በጥቅሉ ግን የጓጎለ መንፈሱን ትንሽ ለማለዘብ እንዲህም እላለሁ … እንሆ።

የዕለቱ ቃለ ምልልስ ከመከወኑ በፊት ከተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር ተያይዘው የታሰሩ  ወጣቶችን ምክንያት በማድረግ ማጠቃለያ እንዲሰጡ ጋዜጠኛና ጸሐፊ /fact/* ሲሳይ አጌና ሲጠይቃቸው ከሰጡት መልስ ነው የምነሳው።  በጥቅሉ የመልሱ ጭብጥ መንፈስ እንዲህ ነው። ለተጠዬቁት ጥያቄ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ሲመልሱ እንዲህ ይሉናል። „ እኔ አልጠራጠርም እነዚህ ሰዎች በዶክመንተሪው /documentary/* ይሁን በክሱ ሂደት ላይ ከአቶ አንዳርጋቸው ክስ ጋር ተስታኮ እንደሚነሳ ለሰከንድ አልጠራጠርም። እነዚህን ሰዎች በተለይም ወጣቶች ለምን ታሰሩ? ለምንስ አሰሯዋቸው እነ አብርሃም ደስታን፤ እነ ሃብታሙን ለምንስ አሳደው ያዟዋቸው? የሚለውን ነገር የግሌን ግምት መስጠት እፈልጋለሁ። ኢህአድግ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚባል መርህ አለ እና ያ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ በነገራችን ላይ አቶ አንዳርጋቸው ኢህአድግን ጥሎ ወጣሁበት ያለው አንዱ መጸሐፉ ውስጥ አይተኸው ከሆነ ይኼው ነበር። ባጭሩ ምን ማለት ነው። ዴሞክራሲያ ማዕከላዊነት ማለት ማዕከላዊ እስር ቤት ማለት ነው።“ ጋዜጠኛና ጸሐፊ /fact/ ሲሳይ አጌና ከማህል ገብቶ እንዲህ ሲል ጠዬቀ „በራስህ አስተሳሰብ ማለት ነው?“  አቶ ኤርሚያስ ቀጠሉ …

„አንድ ሰው ከላይ ይናገራል፤ አቶ መለስ ሊሆን ይቻላል። ከላይ አቶ መለስ የተናገረውን አርማጭሆ ያለው የገጠር አባላችን ሳይጨምር ሳይቀንስ ይናገራታል። ከአንድ ቦታ የሚፈስልህን ነገር መቀበል ማለት ነው። አንዱ ባህሪው ይኸው ነው። ታስታውስ ከሆነ በ1997 ዓ.ም የምርጫ ውደቀታችን ጋር ተያይዛ የተነሳች ቃል ነበረች እንግሊዘኛ ነበረች ….የተቃውሞ ድምጽ /protecting vote / “ አቶ መለስ ይህችን ተናገራት፤ ያቺውኑ ቃል አቶ በረከተ ደገማት፤ የቀበሌ አባላችን አርማጭሆ ደንበጫ ያለው ኦሮምያ ያለውም የገጠር አባላችን እንዲሁ።“

„ ዴሚክራሲያዊ ማዕከላዊነት በባህሪው ከአንድ ቦታ የሚፈስልህን መቀበል ማለት ነው። ኢህአድግ እስካለ ድረስ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አለ። ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እስካለ ድረሰ ደግሞ አድርባይነት አለ። አድርባይነት እስካለ ድረሰ ደግሞ የሚማር ድርጅት አይኖርም ማለት ነው። የኢህአድግ ዋነኛ መግለጫው አድርባይነት ነው። የአንድ ፓርቲ አመራር ብቻ እስካለ ድረስ የሚማር ድርጅት የለም። ኢህድግ የሚማር ድርጅት አይደለም ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ የሚማር ወጣት መፍጠር አይችለም። ይህ ድርጅት 20፣ 23፣ 22 አመት በሥልጣን የምታያቸው የሚማር ድርጅት ስለልሆነ ወጣቶችን መፈጠር አልቻለም ማለት ነው። ስለሆነም ኢህድግ የወጣት መሃን ሆኗል። አድርባይነት በሚመለከት እነሱ ራሳቸው አድርባይ ሆነናል ብለዋል?“ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ስለ አድርባይነት የሚሰማቸውን ስሜትና ህሊናዊ ፍርድ ከሰጡ በኋላ ንጽጽሩን ቀጥለው … „በተቃራኒው ዬተቃዋሚው ፓርቲዎች ማብራራት፣ ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ የሚችሉ ወጣቶች እዬፈለቁ ነው። እነዚህ ወጣቶች  ለኢህአድግ ከሚቀጥለው ምርጫ አኳያ እነ ሃብታሙ ያልካቸው ሰዎች“ /አቶ ሃብታሙ፣ ወጣት አብርሃም፣ አቶ ዳንኤል፣ አቶ የሺዋስ / ማለታቸው ነው „ሥጋት ናቸው። ዬምርጫ ክርክ ቢነሳ ከበረከት ጋር ሃብታሙ ይከራከራል ማለት ነው። የሁለት ትውልድ ሰዎች … “ በተጨማሪም አቶ ኤርምያስ የጋዜጠኛ አብርሃም ደስታንም የለውጥ ሃዋርያነት ለማነፃፀሪያ በማመሳከሪያነት አቅርበዋል።

እንግዲህ በነበራቸው የሦስትዮሽ ሁለተኛ ዙር „የሳምንቱ እንግዳ“ የኢሳት ቆይታ የወያኔ ሥርዓተ ሂደት በዴሞክራሲ ማዕከላዊነት የታሰረ ነው፤ አዳዲስ ዬወጣት ፖለቲከኞች መፈጠር ማህነነትም በአጽህኖት ከመርሆ የመነጨ ስለመሆኑ ገልጸዋል። ይህ አገላለጽ የትርጓሜ ማቃናት ሊደረግለት ይገባል ባይ ነኝ። ምክንያቱም ዴሚክራሲያዊ ማዕከላዊነት ዛሬ ብቻም ሳይሆን ነገ የብዙኃኑ ድምጽ እንዲሁም ብቃት እንዲመራት በምንመኝላት ልዕልት ኢትዮጵያ ተግባራዊ መሆኑ አይቀሬ ነው ባይ ነኝ። ዛሬም ቢሆን እያንዳንዱ ዬተቃዋሚ ፓርቲ መርሁን አጉብጦ ሳይሆን በትክክለኛ ትርጉሙ የአመራር ጥበብነቱን ህግጋት ጠብቆ ተግባር ላይ እስካዋለው ድረስ በውስጡ እዬኖረበት ነው ብዬ አስባለሁ። በጣም በሰከነ ሁኔታ መርሁና አድማጩ ከጽነሰ ሃሳቡ ትርጓሜና የአፈጻጸም ሂደት ፍትሃዊነት ጋር ተጣልቶ ከመቃብሩ አያቁመኝ እንዳይል ከወዲሁ በጥንቃቄ ሊያዙ የሚገባቸውን ጉዳዮች ማብራሪያ መስጠቱ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ነገ ሲታሰብ በዝልቦ ጉዞ ሳይሆን፤ ከድክመቶች ትምህርትን – ከጥንካሬዎች ደግሞ ፍሬን መዋራረስ ግድ ስለሚል።

ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት /Democratic centralism/  ምንድን ነው? ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የአንድ ድርጅት የአደረጃጀት መርህ ነው። የትኛውም ድርጅት እንደ ድርጀት በዚህ መርህ ዙሪያ ማለፉ ወይንም መኖሩ ወይንም ህልውናውን መገንባቱ ግድ ይሆናል። ፖሊሲዎችም እንዲሁ በዚህ መንፈስ ሊቀረጹ ይችላሉ። በተለይ ግራ ዘመም ከሆነ። አግባብነቱ ስለምን? ማዕከላዊነት ከልክ በላይ ከጠበቀ አንባገነንነት፤ ዲሞክራሲ ከመጠን ካለፈ ደግሞ ሥርዓተ አልበኝነት ድርጀቱን ይወረውና ህልፈቱን ያውጃል ከሚል ግንዘቤ ተነስቶ በሌኒንስቱ ዘመን ተግባር ላይ የዋለ ነው። መንፈሱ የፓርቲዎች ነፃ መፈጠር፤ ነፃ ውይይትና ፉክክር እንዲሁም የድምጽ ብልጫን የመምራት አቅምን ይግልጻል። ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አራት ሁልአቀፍ መርሆች አሉት፤ በዬርከኑ ፓርቲውን የሚመሩ አካላት ሁሉም አካላት በምርጫ ከታች ወደ ላይ የመመረጥ፤ ጥቂቶች ለብዙሃን ውሳኔ ዬመገዛት፤ ከታች ወደ ላይ በቀጥታና በውክልና የሚመረጡ አካላት በህዝብ ምርጫ ከላይ ደረሰው የሚወስኑት ውሳኔ ተፈጻሚ የመሆን ግዴታ … የፓርቲ ከፍተኛ መሪ አካላት የምርጫ ዘመን ውስኑነትና ተለዋጭነትን ያመለክታል ….

ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተፈጥሮው ከአመራር የጥበብ ስልት ጋር የተዋዋጠ ነው – ህሊና ላላው ድርጅት። በቀላል አገለላጽ የመብትና ግዴታ ጋብቻ ማለት ነው። ሁለቱም ልክ እንደ አፍንጫ ቀዳዳ፤ ወይንም እንደ ሁለት ዓይን ተመሳሳይ ወርድና ቁመት፤ ስፋትን ጥበት ያላቸው ዬአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ለአንድ ድርጅት የሁለቱ ተስማምቶ መኖር የነፍሱ ማደሪያ- የሩኹ ማሳዳሪያ እንደመሆኑ ሁሉ መዛባታቸው ደግሞ ህልፈቱ ይሆናል። ለህዝብም ርትኃዊ ትንፋሽ ወሳኙ ክፍል ነው። በግልጽና በይፋ ይህን መርህ ተግባር ላይ በማዋል ደረጃ የሶሻሊስቱ ንድፈ ሃሳብ በማንፌስቶው ሆነ በደንቡ ቁልጭ አድርጎ የሚያስቀምጠው ሲሆን በካፒታሊስቱም ዓለምም በተግባርና በሂደት በአብዛኞቹ ጥቅም ላይ ሲውል የሚታይ መርህ ነው። መብትና ግዴታን አጣጥሞ አንባገነንትን አርቆ ሥርአት አልበኝነትን ማሰር የሚቻለው መርሁን በትክክል ተግባር ላይ ሳያጣሉ ማዋል ሲቻል ብቻ ነው። ሳያበላልጡ የተደላደለ መስመር በመዘርጋት።

መብት … የነፃነት ትልቁ መገለጫ ነው። አንድ ሰው መብት ሲኖረው መተንፈስ ይችላል። አንድ ሰው መብት ሲኖረው መኖርን ይጀምራል። መኖር ደግሞ ሥርዓትና ወግ አለው። ዬሥርአትና ወጉ መተላለፊያ የድርጊት በሩ ደግሞ የፍጥረት አውራ የሆነው ልዑቁ የሰው ልጅ ነው። አንድ ሰው መብት አለው የሚባለው በሀገሩ በነፃነት ለመኖር የሚያስችለውን የህጎች ዕንብርት በፈቃዱ ይሆነኛል ብሎ ማጽደቅ ሲችል፤ ለሚፈልገው መሪ ካለምንም ተጽዕኖ ድምጽ የመስጠት ወይንም የመንፈግ መብቱ የተረጋገጠለት ሲሆን፤ በዜግነቱ ብልጫ ወይንም ግት ወይንም መደፍጠጥ ሳይኖርበት እመጥናለሁ ብሎ ባሰበው የኃላፊነት እርከን በእጩነት እራሱን አቅርቦ በድምጽ ብልጫ የመሸነፍ ወይንም የማሸነፍ አቅሙ በአራዊት ግፍያ የማይጠወልግበት ሲሆን። ይመራኛል ብሎ የመረጠው አካል ቢያጠፋ የመገሰጽ፤ ሲበዛ በቃህኝ ብሎ በሰላማዊ መንገድ ከሥልጣን የማገድ እንዲሁም የማውረድ ህጋዊ ድጋፍ፤ የህግ ዕውቅና እንዲሁም ጥበቃ ሲኖረው፤ በዬትኛውም የሀገሪቱ ክልል የመኖር  – የመሥራት – የመዘዋወር – የማይገሰስ መብት ሲኖረው፤ ሀገሩ በምታስገኘው ጥቅም እኩል ተሳታፊ ሲሆን፤ በውጪ ሀገርም ቢኖርም ሀገሩን በፈለጋት ወቅትና ጊዜ ካለምንም ተዕቅቦ ተመልሶ ካለ ሥጋት መኖር ሲችል፤ አይቶ ለመመለሰም ቢሆን ያልታሰረ ፈቃድ ሲኖረው የመኖር – የመማር – የመሥራት – ሃብት የማፍራት ወዘተ … ያ ሰው ነፃነት ባለው ሀገር ነፃነቱ ተጥብቆለት ይኖራል ማለት ይቻላል።

ይህ ሙሉዑ መብት የተረጋገጠለት ሰው ግዴታው ደግሞ በሌላ ኃይል የተጫነበት ሳይሆን እራሱ ፈቅዶና ወዶ የተቀበለው የማድረግ ወይንም የመፈጸም ሂደቱ ነው። ከዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ላንሳ … ይህ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የታዬው በዘመነ ቅንጅት ነበር። አሁን የተከበሩ ዶር/ ብርሃኑ ነጋ በህዝብ ሙሉ ፈቃድና ይሁንታ – ውዴታም ለአዲስ አበባ ከንቲባነት በ1997 የተመረጡ ህዝባዊ መሪ ነበሩ። ዕድሉን አግኝተው ቢሆን ኖሩ መሪና ተመሪ የፈቃድ ውርርስ ስለተከናወነ ሰምና ወርቅ የሆነ የአገልግሎት ጊዜ ይኖራቸው ነበር ማለት ነው። የሰላ የሰመረ መስመር …ô ከታች ወደ ላይ ተፈቅዶ ለተሰጠ መብት ከላይ ወደ ታች ህግ ሆኖ ሲመጣ ያለምንም እንከን ወይንም ማንገራገር ይፈፀም በነበረ …. ህልም …. ሆኖ የቀረ መራራ ስንብት ….

ሌላ ምሳሌ ትንሽ ዘርዘር አድርጌ ስለ እውነተኛው የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መንፈስ ላንሳ ….  የአንድ ሀገር ህዝብ የህጎች ሁሉ እናት ህግ የሆነውን ህገ መንግሥቱ ከረቂቁ ጀምሮ በስፋት እንዲወያይበት ይደረጋል። በራዲዮ፤ በጋዜጣ፤ በግልና በጋራ አስተያዬት ህዝብ ሃሳቡን እንዲሰጥበት ይደረጋል። ረቂቁ በህዝብ አስተያዬት ዳብሮ ወይንም ተሻሽሎ ተጠቃሎ ከታች ጀምሮ በበሰለ ሁኔታ እያንዳንዱ አንቀጽ ከነማብራሪያው – ከነማሻሻያ ሃሰቦቹ ቀርበው ከታች በመሰረታዊ ቀበሌው ምላዕተ ጉባኤ ካለምንም ተጽዕኖ ረቂቁ ይጽድቅና ለቀጣዩ አካል ሰነዱን ይላካል። በዚህ ሂደት ክንውኑ መብት ጎልቶ ይታያል ….

ከቀበሌ ቀጥሎ ያለው አካል የወረዳው ጉባኤ ነው። የወረዳው ጉባኤ እንደ ቀበሌው የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ሳይሆን ከዬቀበሌው ይወክሉናል የተባሉ ውክል አካላት ብቻ የሚገኙበት ይሆናል። ማለት መሰረታዊው አካል ድምጹን የሰጣቸው በድምጽ ብልጫ ለቀጣዩ አካል ውክልና ያገኙ ማለት ነው። እነሱም በተመሳሳይ ሁኔታ አብስለው ለቀጣዩ አካል ያስተላልፉታል። በዚህ መልክ በአውራጃ፤ በክ/ሀገር በተመሳሳይ መልኩ ይከውንና …. ሀገራዊ የህዝብ ተወካዮች ጉባኤ ላይ የህዝብን ፍላጎት ያማከለው ከታች ጀምሮ እዬታሸ የዳበረው ረቂቅ፤ በውይይት እንዲጸድቅ ይደረጋል። ከመሠረታዊ ጉባኤ እስከ ሀገራዊ ሸንጎ ውሳኔ ድረስ ዬህዝቡ መብት በስፋት ጎልቶ ይታያል። ጉባኤው ውይይት ላይ እያለም የተሻለ አዲስ ሃሳብ ከዬትኛውም ወገን ከማናቸውም ዜጋ ከቀረበ ጉባኤው መርምሮ ሊጠቀምበት ይቻላል አዲሱን ሃሳብ። አሁን ከዚህ ላይ ሰባት ነገሮችን እናያለን።

  1. የነፃነት መንፈስን ንጡርነት፣
  2. አክብሮተ – የህዝብ ድምጽ ተደማጫንትን፣
  3. የበታች አካልና የበላይ አካል የመብት አፈፃፀም ዬእኩልነት ሂደትን፣
  4. የፍላጎት ሁለንትናዊነት – ሰላማዊ ቅብብሎሽን፣
  5. የአቅም ተደማጭነትና ተቀባይነትን፣
  6. የነፃነት ነፍስ ህልውና ድርጊት ላይ መገኘትን፤
  7. ፈቅዶ የሰጠው አካል ፈቃዱን የማንሳት መብትን / የመሻር/ የማሰናበት/የማግለል/ የመገሰጽ/

ዬሀገራዊው ጉባኤ ውክል አካላቱ በህዝብ ድምጽ ብልጫ የሚመጡ ናቸው። በተጨማሪም ህገ መንግሥቱን ፈጻሚው አካል ካስፈጻሚው አካል ጋር በፈቃድ የሚያገባ ሂደቶች በተገባው ሁኔታ ተከናውነዋል። ከዚህ በኋላ ብሄራዊው ጉባኤ በረቂቁ ላይ ተወያይቶ በድምጽ ብልጫ ያጸድቀዋል። እያንዳንዱ አንቀጽ በድምጽ ብልጫ ይጸድቃል። አሁን የመፈጸም ሂደቱ ምን ይሆናል ማለት ነው ግዴታ ይሆናል ማለት ነው። ግዴታው ግን ተወዶና ተፈቅዶ የሚቀበሉት ከመሆኑም በላይ ለአፈጻጸሙ ሠራዊቱ -ጠባቂው ህዝቡ ይሆናል ማለት ነው። ከዚህ ነጥብ ጋር በዬደረጃው በተካሄደው ውይይት ሆነ ጉባኤው ላይ ድምጽ የመስጠት፤ ድምጽ የመንፈግ። የመደገፍና የመቃወም መብቶች ክፍት ናቸው። ነገር ግን በአብዛኛው ድምጽ ከጸደቀ በኋላ ጥቂቶች ማለትም ያልደገፉት ለብዙኃኑ ድምጽ የመገዛት ግዴታ ይኖርባቸዋል። ይህ ማለት የተቃወሙት፤ የደገፉትና ድምጽ ያልሰጡት ለህገ መንግሥቱ ተፈጻሚነት እኩል ግዴታና ተጠያቂነት አላቸው ማለት ነው። በሌላ በኩል በብዙኃን ድምጽ የሚጸድቁ ጉዳዮች አሸናፊነታቸው ለሁሉ እንጂ ለደጋፊዎች ብቻ ባለመሆኑ አሸናፊዎች በተሸናፊዎች ላይ ቅንጣት ታክል ተፅዕኖ የማሳደር ኃይል የላቸውም። ይህ እንግዲህ ቁልጭ ያለው የዲሞክራሲያዊ ማዕካለዊነት የመብትና የግዴታ ማዕከላዊ መርህ ነው።

ይህ ማለት በብዙሃን ድምጽ ለምትመራ ለነገ የነጋላት ሀገር ለኢትዮጵያ ዬዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ በአግባቡ ተግባር ላይ እንዲውል ነው ምኞቱና ህልሙ። የበላይ አካላት ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው ከታች በህዝብ ሙሉ ተሳትፎ ስለሚመረጡ፣ ከታች በስሎ ለውሳኔ የበቃውን ወደ ታች ሲልኩት ህዝቡ ላይ የሚጫን አይሆንም ô። ህዝቡ መብቱና ግዴታው ተስማምተው ዴሞክራሲን በህይወቱ ውስጥ ያለውን ድርሻ ይተገብረዋል – ፈቅዶ። ስለዚህ አስፈሪም – አሰፈራሪምገዢም ጨቋኝም  – ቀጥቃጭም አ -ንገራጋሪም በዚህ መስመር ድራሻቸው ይጠፋል። አንድ ሰው ነፃነቱ ከተከበረለት አድርባይ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለውም። የተከደነበት ወይንም የተዘጋበት መድረክ አይኖርምና። የፈለገውን ነውና ድምጽ የሰጠበት። በትክክል በተፈጸም ሂደት – ሂደቱን ህዝቡ እንደ ሃይማኖታዊ ዶግማ ነው ወዶ ከደሙ ጋር የሚያዋህደው። ለተግባራዊነቱም ግንባር ቀደም ተዋናዩ ህዝቡ እራሱ ይሆናል። የህዝብ ጥበቃ ይደረግለታል። ስምምነት – መደማመጥ – ኑሮን መውደድ – ዘለግ ያለ ዕድሜን መመኘትም የሚመጡት በዚህ መልክ በተከወነ የመርሁ ጤናማ ….. ጉዞ እንጂ የሰው ልጅ እንደ በግ አረስቶ ሆኖ በቤንዝን አራሱን አቃጥሎ የሚሞትበት … ሁኔታ አይፈጠረም – በፍጹም።

ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በአውሬያዊነት ተመክሮ ትርጓሜ ጽልመታዊ መልከና ገጽ ተስጥቶት እንደማስፈራሪያ፤ እንደ በቀል መወጣጫ ተቆጥሮ ለነገ አያስፈልግም እንዳይባል ጥንቃቄ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። የተነሳውን ሃሳብ እንደ ወረደ ወይንም እንደ ተለቀቀ ዝም ብሎ ማለፍ አስፈላጊ ባለመሆኑም ማብራሪያ ሰጥቶ በትርጉም ማቃናት ሊታለፍ የማይገባው የሃቅ እንክብል ነው። ማብሰል የግድ አስፈላጊ ስለሆነ እንደ ተንጠለጠለ እንዳይቀር መሬት የያዘ፤ ቀለል ባለ የትርጓሜ ይዘት ማስተዳደር ለይደር ሊቀጠር ስለማይገባ እነሆ ልጽፍ የተገደድኩት በዚህው ምክንያት ነው።

አሁን በኢትዮጵያ ለዛውም ከአንድ ጎሳ ድርጅት የፈለቀ ነገር ሁሉ ኮሽ ሳይል የመፈጸም ድርብ ግዴታ አለ – ጫና አለ። በስለላና በስጋት በተወጠረ ሁኔታ ህዘብ አምጦ እንዲቀበል ተገዷል። ስለምን? ቀድሞውንም በወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ላይ መወያዬት የሚችሉት አባላቱ – ዝርያው ያላቸው ብቻ ናቸው። በአፈጻጸሙ ደረጃ ግን በውስጡ የሌለ አባል ለመሆን የማይፈቀድለት፤  በአካበቢ ዝር እንዳይል የተዘጋበት – ወይንም የተቆለፈበት ወገን ተገዶና ታስሮ በፍርሃት ተቀፍዶ እንዲቀበል ይገደዳል። ዘነፍ ያለች ጉዳይ ቢነሳ አሸባሪ ነው። ይታሰራል፤ ይገደላል። ይሰደዳል። ቢኖርም በስጋት ተንዘፍዝፎ ጥላውን እዬሸሸ እንዲኖር ይገደዳል። ቀድሞ ነገር መርሁና ትርጓሜው እኮ ለጎሳ አስተዳደር ተብሎ የተቀመረ አልነበረም። ለምልዕት ህዝብ ለሰለጠነ ህዝባዊ አስተዳደር እንጂ። አብሶ ንድፈ ሃሳባቸው የሶሻሊስት ርዕዮት የሆኑ ሀገሮች ህብረ ብሄራዊ የፓርቲ ሥርአትን ሳይሆን የአንዳዊነት ፓርቲ ሥርአትን ስለሚከተሉ ተወዳዳሪዎችም መራጮችም እነሱ በመሆናቸው ማዕከላዊነቱ እጅግ ጥብቅ፤ ያመራሩ ዝንባሌውም አንባገነናዊ ሊሆን ይችላል። ለዛውም ከአልባንያ ንድፈ – ሃሳብን የወረሰው ወያኔም ከዚህ ሊያመልጥ ከቶውንም አይችልም። እንዲያወም በከፋ ሁኔታ ጎሳዊነትን በሶሻሊስት ንድፍ፤ ነፃ የኢኮኖሚ ንድፍን ከዞጋዊ ጋር ቀላቅሎ የወዘተረፈ ስንክሳር መጨፈሪያ ነው ያደረገው መርሁን …. LMNO ይህ ነው የወያኔ ዴሞክራሲያዊ መግለጫው  – የጎበጠ – ጎብዳዳ ጉድ።

ወያኔ ሲያስፈልገው ሶሻሊስት፣ ሲያሰኘው – አረቢስት፣ ሲለው – ካፒታሊስት ለታላቋ ትግራይ ቅዠት እንደሚያመቸው ይጨፍርበታል። ሲጠቀለል ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሁ እራሱ ለጫካ ተመክሮው አቅሙ አይደለም። መርሁ ለጎጥ አስተዳደርም ልኩ አይደለም። መርሁ ለኢሰባዊነት ድፍረታዊ አገዛዝ ግጥሙ አይደለም። ቀድሞ ነገር የወያኔ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እኮ ቁመናው ሲታይ ሥር የሌለው ዕጽ ነው። ሥር የሌለው ዕፅ እራሱንም መሸከም አይችልም እንኳንስ ሌላውን ….

ለወያኔ ቀልቡ ረገጣ – ርግጫ – ፍጥጫ – ውንብድና – መቅጠፍ – ቃልን ቅርጭም አድርጎ መብላት –  መዝረፍ – ማስፈራራት አምሳያዎቹ ናቸው። ከዚህ ባለፈ ወያኔ እሾኽ ዘርቶ እሾኽ ያመረተ የዘመናችን ጃርታዊ አስተዳደር በመሆኑ ዘመኑ ፈቅዶለት ዓለምአቀፋዊ ዕውቅና ካገኘው የነፃነት ትንሳኤ ጋር አይተዋወቅም። „አንድ ሜትር በአንድ ሜትር“ የሰው ልጅ ታስሮ ውሎ አድሮ ህልፈቱን የሚጠብቅበት የድቅድቅ የጨለማ ዘመን። ቀና የዴሞክራሲ አስተሳሰቦች ባዕዱ ነው – ለአረሙ ወያኔ።  እንደ አንድ ልጅ እግር ኮበሌ እኮ አቅም የለውም። የማሰብ ህሊናው የተሰለበ ነው። አቅዶ ይዋሻል። አቅዶ ይበቀላል። አቅዶ ያጠፋል። አቅዶ ስህተት ይፈብርክና ያሰራል – ይገድላል – ያሳድዳል። ወጣት እያለሁ ያነበብኩት አንድ መጸሐፍ ነበር “ሞገድ“ ይባላል። ዬሞገድ መጽሐፍ ጭብጡ ዜና ዬሚሰራው በ500000 ከፍሎ ወንጀል ያሰራል። ሌሊቱን እራሱ ከፍሎ ያሰራውን ወንጀል እንደ ተጠናቀቀ በዚያው ቅጽበት ዜናው የተሰራበት ጋዜጣ ህትም ያወጣል። 10000000 ከዚህ በላይ ጋዜጣው ይሸጣል። የወያኔ ድራማ ብናውቀው ይሄው ነው። ሚዲያን በማዕከል የሚመራው ድርጅት በፖለቲካ ነክ ተግባሮች ላይ አይሳተፍም። ተግባሩን የሚሠራው ተዳብሎ -ተብድሮ ነው። ለእያንዳንዷ ስንኝ የነፃነት ነፍስ በጎጥ የተደራጀ የወሮበላ ቡድን አለው። ወያኔ አይደለም ወጣት አዲስ መንፈስ ያለውን ኃይል ማብቀል ቀርቶ እራሱንም ማዳን የሚችል ድርጀት አይደለም። ዘመኑ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው የመንፈስ ዕሴቶች በእጀጉ ርቆ ሚገኝ የአራዊት ማፍያ ነው።

ወያኔ እኮ እንባ ጠበቂ ብሎ በሚ/ር ማዕረግ ጽ/ቤት አለው። ወይ ማላገጥ። ዕንባ ሲቃጠል ሲነድ ቤንዚን አብሮ አርከፍክፎ በአንባ የሚዘመን – ቢሮ። ወያኔ የሰብዕዊ መብት በሚመለከት ዓለም ዓቀፍ በዓላትን አክብራለሁ ይላል። ግን በ2014 እኤ.አ. በዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን ምን እንዳደረገ የዓለም ህዝብ አይቶለታል። የሰብዕዊ መብት ጉባኤም ተለጣፊ አለው። ዜጎች በቤንዚን ተቃጥለው ሲሞቱ፣ ሴቶች እስር ቤት አርግዘው ሲወልዱ – እስር ቤት ሲደፈሩ፤ እስረኞች በካቴና ታስረው ቃለ – ምልለስ ሲደርግላቸው፤ ከነካቴናቸው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፤ በወንበዴ ሰራዊቱ የማገጠ ተግባር ሲፈጸምባቸው፤ ለሴቶች አስፈሪ የሆነው በሽታ የጡት ነገር ሆኖ ጆሮ አልባ ሲሆን፤ የሰሞናቱ እራሱ ከሁለተኛው ከተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ቃለ ምልልስ ጋር የሰማነው የጣር የድረሱልኝ ሰቀቀን …. ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል …. የሰብዕዊ መብት አለ፤ በላቀ የዴሞክራሲ ምጣኔ እያለ ያላግጣል። ስለሆነም የዴሞክራሲ ማዕከላዊነት ሥሙ መጠራቱ ሳይሆን ቁም ነገሩ መርሁና ህግጋቱ ከአራዊት ተፈጥሮ ጋር አይተዋወቁም። እንዲያውም በመርሁ ውስጥ „ነባርና ወጣት“ መሪዎችን የማወራረስ፣ የማተካካት የተመክሮ ቅብብሎሽ መኖሩን አሳምሮ ይፈልጋል …. መርሁ። ይህ ማለት ባልተቋረጠ ሁኔታ ዬወጣት መሪዎችን ችግኝ ያፈላል ማለት ነው። ስለሆነም ማናቸውም የሰብዕዊ መብት መርህ በወርደ ጠባቡ ወያኔ ልኬታ መታዬት አይገባውም ባይ ነኝ። ይልቁንም ጠቃሚዎችን ከማይጠቅሙት ጋር በሚገባ እዬለዩ ጥናታዊ ተግባራትን በተከታታይ መከወን የነፃነት ትግሉ አውራ ተግባር ይመስለኛል። እያወላገደ የሚተረጉማቸውን የበቀል ጉርስና ስንቅ ያደረጋቸውን አሳሪ ህግጋቶቹን ሁሉ እያፍታቱ ለአደባባይ ማብቃትም ይጠበቃል።

እርገት ይሁን የኔዎቹ። ወያኔ በባህሬው የአንድ ሀገር ትውልድን የሚያጠፋ ድርጀት ነው። ስለሆነም ትውልዱ ከሚያጠፋው ጋር መተባበርን አይፈቅድም። ወጣቱ እንደ ዘመኑ መሄድ ይሻል። ወያኔ ደግሞ ከቤተሰብ ቀጥሎ ካለው የጎሳ ሥርዓት ላይ ነው ያለው። ወያኔ ከወጣቱ ራዕይና ከራሱ ከዘመኑ እድገት ወደ ኋላ የተመለሰ ነው ዙሮ የሚሄድ ነው። ወጣት ደግሞ ሲሆን ቀድሞ በስተቀር ከዘመኑ ጋር ተፈጥሮው የተዋህደ ነው። ስለሆነም „ለምን ወያኔ የወጣት መሃን ሆነ?“ ለሚለው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ዓለማቀፋዊ መርህ ተጠያቂ ሊሆን አይገባም። በሌላ በኩል ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የጥቂቶች መርህ ነው የሚለውም ቢሆን መርሁ ጥቂቶች ለብዙኃን ውሳኔ መገዛትን ነው የሚቀበለው። በተጨማሪም አድርባይነት መብቀያው ነፃነት አጥቶ ከመታፈን፣ ከፍርሃት እንዲሁም ከውጥረት የሚመጣ እንጂ ከዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አይደለም። ተግባራዊ ተሳትፎ ከቀጥተኛ ትርጉሙ እንኳን የሚፈልቅ ስላልሆነ።

ወገኖቼ በፖለቲካ ድርጅቶች ሆነ በሙያና ህዝባዊ ድርጀቶችም የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አፈጻጸም ሥርዓቱ ተመሳሳይ ነው። ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የፖለቲካ አመራር ሥልጣኔ ጥበብ ነው። የነፃነት ሂደት ተመክሯዊ መሰላል ነው። የፍትህ ድል ልዩ እርካብ ነው። ሃሳቤን በዚህ ከውኜ ብዕሬን ለሌላ ጉዳይ እንድተሰናዳ አሳስቤ እናንተንም ውዶቼ በመታደማችሁ አክብሬና አምስግኜ ልሰናበት እኔ ሎሊያችሁ ሥርጉተ።  መሸቢያ – ሰንበት።

  • ጋዜጠኛና ጸሐፊ ብዬ በቅንፍ /fact/ ብያለሁ። በኢትዮጵያዊው የሥነ ፁሑፍ ህግጋት አንድ መጸሐፍ ተራኪ፤ ገላጭ፤ ስዕላዊ ሊሆን ይችላል። መጸሐፍት ከሦስቱ አንዱን ወይንም ሁሉንም ሊሆኑ ይችላሉ። የጋዜጠኛና የጸሐፊ ሲሳይ አጌና መጸሐፍ ሶስቱንም አሟልቶ፤ ተተርጓሚነቱንም አክሎ፤ መረጃዊ – ሪፖርታዊ – ዘገባዊ ተንተኝነትንም አበልጽጎ እንዲሁም ታሪካዊ ቅኝቶችን ደምሮ መደቡ ህግና ህገ ነክ ጉዳዮችን ከሚካተቱበት መምሪያ  ውስጥ ስለሚመደብ ነው በቅንፍ ውስጥ ዬጸሐፊነቱን ደረጃ /fact/ ብዬዋለሁ።
  • Documentary ቀጥታ ትርጉሙ እውነትን ማንጸባረቅ፤ በማስረጃ የተደገፈ ዬፊልም – ዬቲቪ – ዬራዲዮ ዝግጅት፤ ማስረጃነት ያለው የጹሁፍ ቅኝት፤ ከመረጃ ጋር የተያያዘ፤ መረጃዎቹ እውነትን የሚያረጋግጡ ማለት ስለሆነ ወያኔ ግን በበቀል የበቀለ፤ በማሸበር – የሰከነ፤ በማስፈራራት – የተከዘነ ቁልጭ ያለ የመንፈስ ስርቆት ተግባር በራዲዮ ሆነ በቴሌቪዢን እንዲሁም በጹሑፍ ዝግጅት አዝለብልቦ ቢያዘጋጅ ለትርጉሙ Documentary አይመጥነውም እላለሁ።
  • ለእኔ ኢህአድግ የሚባል ድርጅት የለም። ቢኖርም ቅርፊት – የባህር ማሽላ አዘርዛሪ ዓይነት ነው አሮ ረግፎ የቀረ፤ ምንም ጥቅም የማይሰጥ። ስለዚህ በሌለ ነገር ላይ ሳይሆን ባለ ነገር ላይ ስለሆነ ሙግቴን ያቀረብኩት „ኢህአድግ“ እያሉ አቶ ኤርምያስ ለገሰ የተጠቀሙበትን ቅርቅር አድርጌ የዘጋሁት በመሆኑ በጭንብሉ ሳይሆን ገዢውን – ዘረኛውን በግልጽ ሥሙ በሚመካበትና በማያፍርበት ሥሙ ወያኔ እያልኩኝ ነው የፃፍኩት። ለእውነት ይቅርታ ቢጠዬቅበት ሰማይ ይፈርሳል …. እና ….

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።

   እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles