Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ከጠባቡ እስር ቤት ሰፊውን መርጠናል –ጋዜጠኛ መልካም ሰላም ሞላ

$
0
0

ጋዜጠኛ መልካም ሰላም ሞላ

ጋዜጠኛ መልካም ሰላም ሞላ

ጋዜጠኛ መልካም ሰላም ሞላ

..እነሆ በስደት ስሜት ውስጥ ሆነን፣ ከሃገር መውጣት ከሞት የመረረ ጽዋ እንደሆነ እያወቅነው፤ ህሊናችንን ሽጠን ለሆዳችን ማደር ቢያቅተን ፣ ከህዝብ በተሰበሰበ ብር ተንደላቀን የህዝብን እውነት ቀብረን ህዝብ ለእኛ ባደራ ያስረከበንን እምነት ረግጠን እያጭበረበርን እየዋሸን እየቀጠፍን እንድንኖር የቀረበውን ጥያቄ ንቀን፣ እንደአለቆቻቸው እንደገደል ማሚቶ በሉ የተባሉትን እያስተጋቡ ከህሊናቸው ተጣልተው እንደሚያድሩት “የቁጩ በጎች”፤ በጋዜጠኛ ስም ተሸፍነን በአንድ ወቅት አብረናቸው ከበላን እና ከጠጣን በማህበራዊ ህይወታችን ብዙ መልካም ነገሮችን አብረን ከተቋደስናቸው ሰዎች /ኧረ ባጋጣሚም ቢሆን አንድ ቤት ውስጥ ከ20 በላይ ሰዎች ሆነን ካደርን/ ከወያኔ መዶሻ ተርፈው ጥቂት መራመድ ከቻሉ እና የነገ የሃገር ተስፋ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁትን ሰዎች ጀርባ እንድንሰልል፣ስማቸውን እንድናጠፋ እና ለነደፉት የመበታተን እቅድ ተባባሪ እንድሆን ስንጠይቅ በፍጹም! ብለን የቀረበልንን የጉቦ ማታለያ ቤት እና ገንዘብ ረግጠን፣ እኛ የጀግኖች ኢትዮጰያዊያን ልጆች እንጂ የባንዳ ውላጆች አለመሆናችን አስረድተን፤ በተጨማለቀ ስርአት ውስጥ ህዝብን ለማታለል ከሚገነቡ ጥቂት ህንጻዎች ይልቅ በየጉራንጉሩ የሚጠፋው የሰው ህይወት የሚረገጠው የዜጎች መብት የሚካሄደው ኢ-ሰብአዊ ጥሰት አይተን እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን ከማለፍ የሚመጣብን መቀበል ይሻላል ብለን እሾህና አሜኬላ በበዛበት የኢትዮጵያ የፕሬስ ስርአት አመታት አስቆጥርን፡፡

በጥቂት የገዥው መደብ ባለስልጣናት የሚካሄደውን ምዝበራ እና ዝርፊያ እያወቁ ጸጥ ማለት ከአእምሯችን በላይ ቢሆንብን፤ ገንዘብ የኢትዮጵያን ህግ ሲገዛ፤ ጥቂት የገዥው መደብ አቀንቃኞች ተመችቷቸው አብዛኛውን ሲጨቁኑ በዲሞክራሲ ስም አምባገነንነት አስፍነው እንደፈለጋቸው ታሪክ እያበላሹ፤ በፌዴራሊዝም ስም በጎሳ እና በዘር ኢትዮጵያን ለመበታተን ቆርጠው መነሳታቸውን እኛ እወቅን እነርሱ እየዋሹ እድሚያቸውን ለማረዘም የሚያደርጉትን ሂደት ለማክሸፍ ህይወታችን አደጋ ላይ ጥለን፤ እንደአህያ በዱላ የሚያምነው ጭንቅታቸው ሌት ከቀን አንዴ ከቤታችን አንዴ ከቢሯችን አንዴ በስልካችን አንዴ በቤተሰባችንን …. እየመጡ ችለን ብዙ መንገድ ለመጓዝ ጥረናል፡፡

የኢትዮጵያን ህዝብ ብሶት ማሰማት ለሙያ መታመን ነው ብለን፤ በሙያችን በቆየንባቸው ጊዜያት ዛሬም ከጫካ አስተሳሰብ ያልተላቀቀው የደህንነቶች የጉልበት ማስፈራሪያና መደለያ ሳያሸንፈን ለሙያችን ተገዝተን የኢትዮጵያ ህዝብ የናፈቀውን እውነትን ፍለጋ፣ ሰላምን ፍለጋ፣ ፍትህን ፍለጋ፣ ከሞቀው ቤታችን፣ ከደመቀው መንደራችን፣ በስስት ከሚያዩን ቤተሰቦቻችን፣ ሌት ከቀን ስለኛ ከሚያስቡ እና ከሚጨነቁ ጓደኞቻችን ርቀን፤ የነበረንን ሜዳ ላይ በትነን የምንወዳትን ሃገራችንን ትተን ከሃገር ተሰደንም ቢሆን ፤በዓሉ ቢያልፍም አልዘገየንም እና እንኳን ለዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ አልን፤ ከዚሁ ከስደት መንደራችን ከሌባ እና ፖሊስ ሩጫ ባስተረፍናት ጊዜ ተጠቅመን፡፡ ኮካዎች ሲንጫጩ (በልቶ ዝም የለምና) እኛም እዚህ ሆነን ከመከራችን ባስተረፍነው ፈገግታችን ሂሂሂ አልንባቸው፡፡ የራሳቸውን ማንነት ክደው የሙት መንፈስ ቅዠት የማስጠበቅና የማስቀጠል ቋሚ ስራቸው ስለሆነ ከእነርሱ የሚጠበቅ ነውና “የመለስ ራእይ” እየተሳካ ስለሆነ ደስታቸውን እንዲያከብሩ ፈቀድንላቸው፤ ባንፈቅድም ፈቅደዋልና ሳቅንባቸው፡፡ እድሜ ለወያኔ በዚህ 23 አመት የተወለድን ልጆች ራሳችንን እንድንችል የሚያደርግ ስርአት ባይፈጠርልንም ቤተሰቦቻችን ከእኛ አልፎ ለሌላው የሚርፍ ስራ እንደሚሰሩ እና መሰደዳችን እንዳመማቸው ግልጽ ነው፡፡

በተለይ ልክ እንደማንኛውም ሰው ከሃገር ተሰደዱ የሚለውን ዜና አይሉት ሰቆቃ በአዲስ አመት መግቢያ በአውዳመት መዳረሻ ሲሰሙ በጳጉሜ ያሳለፍነው ጥቁር ሳምንት ለእነርሱ አዲስ አመት አዲስ ሰቆቃ ይዞ በአደይ አበባ ሳይፈካ እንደጨለመ 2007 እያሉ ቀን መቁጠር ጀመሩ፤ ጥቁራቸውን እንደለበሱ፤ በርቀት የብርሃን ፍንጣቂ ጮራ እየናፈቁ እንደልባቸው ሰላም ተመለሱ ብለው መልካም ምኞታቸውን ለመናገር እንኳን ሲቃ አንቋቸው ሳይተነፈሱ ሰማይ ሰማዩን እያዩ ከፈጣሪያቸው ጋር እያወሩ ቤተሰቦቻችን አስቧቸው፡፡ አብዛኞች ስደተኛ ጋዜጠኞች የወያኔ ትውልድ ስላልሆኑ አብዛኛውን የእድሜ ዘመናቸውን የኖሩለት ሙያ የከፈላቸውን “ዉለታ”፣ ንብረታቸውን ሜዳ ላይ በትነው ግማሹን በማይረባ ዋጋ በነጻ መስጠት ከማይተናነስ አውጥተው ጥለው፤ አይደለም በዓል ደርሶ እንዲሁም በአዘቦት መምጣታቸውን በጉጉት ከሚጠብቁት ልጆቻቸው በስስት ከሚያዩዋቸው ቤተሰባቸው ከሚያስተዳድሩዋቸው ቤተዘመዶቻቸው ተነጥለው ቢሰደዱም፤ ቅሉ አንድ ሁለቱ እዚህ ያለውን ሁኔታ እንዲሰልሉ በወያኔ ተልከው የመጡም አልጠፉም፡፡ ለነገሩ ይሄ አይገርምም፡፡ እንኳን ተሰደን፤ ሀገር ቤት በጋዜጠኛ ሽፋን፤ በጓደኛ ሽፋን፤ በጉርብትና ሽፋን ተደብቀው አብረውን እየበሉ አብረውን እየጠጡ ክፉ ደጉን እያሳለፉ አብረውን እየሰሩ የገዥው መንግስት ተላላኪ ሆነው እያንዳንዷን እንቅስቃሴያችንን የሚያቃጥሩ “ጓደኞቻችን” እያወቅን እንዳለወቅን ሆነን ብዙ ኮካዎችን ስቀን አልፈናቸዋል፡፡ ጥያቄው የነጻነት እንጂ የዳቦ ቢሆን ኖሮማ ከተሰደደው አብዛኛው ጋዜጠኛ ተንደላቆ ለመንግስት አሸርግዶ በኖረ ነበር፡፡

ጥያቄው ኢኮኖሚ ቢሆን ኖሮማ ገና ድሮ እባካችሁ አትጻፉብን ምን እንዳርግላችሁ የየት ሃገር ቪዛ እንምታላችሁ ስንባል ዘንጠን በመረጥነው ሃገር በሄድን ነበር፡፡ ምን እስክንከሰስ አስቆየን? ጥያቄው የህሊና ሆነ እንጂ የሆድ ቢሆን ኖሮማ ባመጡልን መደለያ ተጠቅመን ለኛም ለቤተሰቦቻችን ህይወት የሚቀይር ብር በተቀበልንና የኢትዮጵያን ህዝብ ሮሮ እንዳልሰማን ባለፍን፡፡ መንገዳችን ሃገር ለመልቀቅ ቢሆን ኖሮ አብዛኛው ጋዜጠኛ ፓስፖርት በእጁ ያስምጣል እንጂ በተከሰሰ ማግስት ስለፓስፖርት ማውጣት ባልተጨነቀ ነበር፡፡ ጥያቄው የፍትህ እና የነጻነት ሆነ እንጂ ቪዛ ማግኛ ቢሆን ኖሮማ የተደራጀ ኑሮ እና ቤተሰብ ሃገር ቤት ውስጥ ባልመሰረተ ነበር፤ ባሳለፍነው ጥቁር ሳምንት አንዳንዱን ሰው ታዘብነው ብዙውን አከበርነው፡፡ ኮካዎችን…. አይ እነርሱማ ኮካ ናቸው፡፡ እኔን የገረመኝ ግን የባለቀለሞች ነው ፤ የባለ ቀለም ምልክቶች አስተሳሰብ፡፡ ወያኔ ለራሱ እንኳን በቅጡ የማይገባውን ፖሊሲውን በሰዎች ላይ ለመጫን እንዴ በስብሰባ አንዴ በስልጠና አንዴ በአበል ብዙ ጊዜ በግድ ለማስረጽ ሌት ተቀን ሲለፋ አካኪ ዘራፍ ያልነው፤ “የመለስን ራእይ በማጣጣል” ተብለን ስንወነጀል የመለስ ራእይ የዮሃንስ ራእይ አይደለም ያለመቀበል መብት አለን ብለን ስንከራከር እኮ አቋማችንን እየገለጽን እንጂ የመቃወም ሱስ ኖሮብን አይደለም፡፡ ዛሬም እናንተ አንዳንድ የባለቀለም አባላቶች ለምን ተሰደዱ ብላችሁ የራሳችሁን አስተሳሰብ እኛ ጋር ለመጫን ማሰባችሁ ያስቃል፡፡ ሰው የሚኖረው በገባው ልክ ነው፡፡ እኛ አስበን እንጂ አስበውልን አንኖርም፡፡ (በተለይ አንቺ የ10 ቀን መታሰር “ጀግና” ያደረገሽ ባለቀለም ሳሞራ የኑስ ከ11ኛ ክፍል አቋርጦ የኢትዮጵያን መከላከያ ልምራ ብሎ “ታሪክ” አበላሸ፤ ታሪክ እንዳይደገም እስኪ እልፍ ….እልፍ በይ… ) ለነገሩ እናንተ ባለቀለሞች ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ጋዜጠኛ ውጭ ያለ አይመስላችሁም ፤ እርሱ እናንተ ያላችሁ ባይመስለውም፡፡

ቢሆንም በጥቂቶች ብዙሃንን አንፈርጅም “ለምጣዱ ስንል አይጧን ትተናል” እና አፉ ብለን አሁንም ተስፋ ጥለናል፡፡ ቅር ብሎንም መልካም ምኞታችን አንነፍግም እና እንኳን አደረሳችሁ ብለናል፡፡ እናም ከዚህ ሁሉ ሃተታ በኋላ ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ በመሰደዳችን ከማንም እና ከምንም በላይ ላዘናችሁ ፈጣሪ እንዲከተለን ለጸለያችሁ ቤተሰቦቻችን፣ ጓደኞቻችን፣ ሳትነግሩን ብላችሁ የተቀየማችሁን ወያኔ ራሳችንን እንዳናምን አድርጎን በስልክ ማውራት ባንደፍርም፣ ከሃገርም ውስጥም ሆነ ውጭ ሰምታችሁ ደንግጣችሁ መልእክት የላካችሁ፣ ተናዳችሁ እላፊ ስድብ ላወረዳችሁብን ባለቀለሞችና ኮካዎች ፣ ካላችሁበት እኛን ለመርዳት እየተንቀሳቀሳችሁ ላላችሁት በሙሉ ለሁላችሁም መጭው ዘመን የሰላም እና የእርቅ እንዲሆን ተመኘን፡፡ ከጠባቡ እስር ቤት ሰፊው ይሻላል ብለን መርጠናል እና ሃገራችንን ኢትዮጵያ እግዚአብሄር ሰላሙን ያምጣላት፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>