የአስር ሺ ሜትር ጀግኖቹ ቀነኒሳ በቀለና እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ በዩጂን ዳይመንድ ሊግ በአስር ሺ ሜትር እንደሚወዳደሩ ታውቋል፡፡ የሁለቱ አትሌቶች ፍጥጫ የአትሌቲክስ አፍቃሪዎችን ትኩረት ከማግኘቱም በላይ የውድድሩ ድምቀት ሆኗል፡፡
የፊታችን ዓርብ ምሽት በሚካሄደው በእዚህ ውድድር የቀነኒሳ ታናሽ ወንድም ታሪኩ በቀለ ተሳታፊ መሆኑም ውድድሩን ከምን ጊዜውም በላይ ደማቅና አጓጊ አድርጎታል፡፡ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ወንድማማቾች ቀነኒሳና ታሪኩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሞ ፋራህ የተወሰደባቸውን የበላይነት ለመቀልበስ እንደሚሮጡም ይጠበቃል፡፡
የአስር ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነው ቀነኒሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ውድድሮች በሞ ፋራህ የበላይነት እንደተወሰደበት ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ቀነኒሳ ከለንደን ኦሊምፒክ ወዲህ ወደ ቀድሞ አቋሙ ለመመለስ እያደረገ ያለው ጥረት በዩጂን ዳይመንድ ሊግ ለተቀናቃኙ የሚያሰጋ ሆኗል፡፡
የኦሊምፒክ የሦስት ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ቀነኒሳ ባለፈው ለንደን ኦሊምፒክ አራተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በኦሊምፒክ መድረክ የሚያስመዘግብበትን ዕድል በሞ ፋራህ ተነጥቋል፡፡ ይሁን እንጂ ቀነኒሳ በእዚህ ውድድር የኦሊምፒክ ቁጭቱን ለመወጣት ጠንክሮ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡
ቀነኒሳ የአስር ሺ ሜትር ክብረወሰንን በ 26፡17፡53 ጨብጧል፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 ደግሞ እስካሁን ድረስ በአሜሪካ ምድር በአስር ሺ ሜትር ከተመዘገቡ ምርጥ ሰዓቶች ዋነኛውን በስሙ አስመዝግቧል፡፡ ይህም ሰዓት 26፡25፡17 ነው፡፡
ቀነኒሳና ሞፋራህ በአትሌቲክሱ ዓለም የረጅም ጊዜ ተቀናቃኝ ከሆኑ አትሌቶች መካከል ግንባር ቀደሞቹ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ አትሌቶች በአሁኑ ወቅት ዕድሜያቸው ሰላሳ ቢሆንም በታላላቅ ውድድሮች ላይ መፎካከር የጀመሩት ገና የአስራ ሰባት ዓመት ወጣት እያሉ ነው፡፡
የቀነኒሳና ሞ ፋራህ ፉክክር የጀመረው እ.አ.አ በ 1999 ፖላንድ ባይዳጎዝ ላይ በተካሄደው የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በሦስት ሺ ሜትር ነው፡፡ በእዚያ ውድድር ቀነኒሳ ሁለተኛ በመሆን ሲያጠናቅቅ ሞ ፋራህ ስድስተኛ ሆኖ ነበር የጨረሰው፡፡ ሁለቱ አትሌቶች በአስር ሺ ሜትር ውድድር ሁለት ጊዜ የመፎካከር ዕድል ገጥሟ ቸዋል፡፡ ሞፋራህ ሁለቱንም ጊዜ በማሸነፍም በርቀቱ ከቀነኒሳ የተሻለ ታሪክ አለው፡፡
ሞፋራህ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ በአምስት ሺ ሜትር ውድድር ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ሲያሸንፍ የአውሮፓን ክብረወሰንም ማሻሻል ችሎ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በፊትም በአስር ሺ ሜትር ሃያ አምስት ዙሮችን በ 26፡46፡57 በማጠናቀቅ በርቀቱ ፈጣን ከሚባሉት አትሌቶች መካከል ተካትቷል፡፡
በእዚህ ውድድር ያልተጠበቀ ክስተት ሊያሳይ የሚችለው አትሌት ታሪኩ ነው፡፡ ታሪኩ አስር ሺ ሜትር መሮጥ ከጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆንም እያስመዘገበ ያለው ውጤት ወደ ፊት በርቀቱ ትልቅ ታሪክ መስራት እንደሚችል የሚያመላክት ነው፡፡
ታሪኩ በለንደን ኦሊምፒክ አስር ሺ ሜትር ላይ ትልቅ ጥረት አድርጎ የነሐስ ሜዳሊያ ማስመዝገቡ ይታወሳል፡፡ ታሪኩ በእዚህ ኦሊምፒክ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ውድድሩን በመምራት ድንቅ ብቃት ቢያሳይም የሚያግዘው አትሌት በማጣቱ በሞ ፋራህና በአሜሪካዊው ጋለን ሩፕ ተቀድሟል፡፡
ታሪኩ ከቀነኒሳም በላይ የለንደን ኦሊምፒክ ቁጭት አለበት፡፡ ይህንንም ለመወጣት የፊታችን ዓርብ ምሽት ጠንካራ ዝግጅት አድርጎ እንደሚቀርብ ተገምቷል፡፡ ታሪኩ በአምስት ሺ ሜትር ከሦስት ዓመት በፊት 12፡58፡93 የሆነ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበ ጠንካራ አትሌት ነው፡፡ ይህን ፈጣን ሰዓት ሞ ፋራህ ባለፈው ዓመት እንዳሻሻለው ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል ኢማና መርጋ የእነ ቀነኒሳና ሞ ፋራህ ዋነኛ ተቀናቃኝ እንደሚሆን ታውቋል፡፡ የተለያዩ አገር አቋራጭ ውድድሮችን በማሸነፍ በዓለም ካሉ ታዋቂ አትሌቶች መካከል መካተት የቻለው ኢማና፣ በዩጂኒ ዳይመንድ ሊግ ለድል ከሚጠበቁ አትሌቶች አንዱ መሆን ችሏል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ድንቅ ብቃት በማሳየት የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለው ኢማና፣ ባለፈው ለንደን ኦሊምፒክ ሜዳሊያ እንደሚያስመዘግብ ግምት ቢሰጠውም በጉዳት ምክንያት አገሩን ወክሎ መወዳደር ሳይችል ቀርቷል፡፡
↧
Sport: ቀነኒሳ በቀለ እና ሞ ፋራህ በዩጂኒ ዳይመንድ ሊግ ይፈታተናሉ
↧