Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: አርሰን ቬንገር ለአርሰናል የሚፈልጓቸው 10 ከዋክብት

$
0
0

ከይርጋ አበበ
ዴቪድ ቪያ ስፔን ባርሴሎና
የሰሜን ለንደኑን ክለብ እ.ኤ.አ ከኖቬምበር 1996 ጀምሮ በማሰልጠን ላይ የሚገኙት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር በ17 ዓመታት የክለቡ ቆይታቸው እንዳለፈው የውድድር ዓመት ነገሮች ከብደውባቸው አያውቁም። ክለቡን ማሰልጠን ሲጀምሩ «ለእንቅልፍ መጥሪያ የማየው የቶተንሃምን ጨዋታ ነው» ብለው ያጣጣሉት ቬንገር ይኸው የከተማ ተቀናቃኛቸው ክለብ ከለመዱት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ውጪ ሊያደርጋቸው ጫፍ ደርሶ ነበር።
አሠልጣኝ ቬንገር ኮከብ ተጫዋቻቸውን ሮቪን ቫን ፐርሲን ለማንቸስተር ዩናይትድ አሳልፈው በመስጠታቸውና የተጫዋቹን ቦታ በሚገባ መሸፈን ባለመቻላቸው ዘንድሮ የገጠማቸው ፈተና ቀላል አልነበረም። በእዚህ ሳቢያ ቬንገር በ17ዓመት የክለቡ ቆይታቸው ደካማ የተባለ የአማካይ ክፍል ገንብተው ተስተውለዋል።
አጥቂዎቻቸው ኳስ የሚያደርስላቸው አጥተው ሲቸገሩ መታየታቸው፣ ጀርመናዊውን መለሎ ተከላካይ ፔር ሜርቲሳከር በቋሚነት የሚያጣምር ሁነኛ የተከላካይ መስመር ማጣታቸው፣ ከየንስ ሌህማን በኋላ በግቡ ቋሚ መስመር የሚቆም ጠንካራ ግብ ጠባቂ በክለባቸው ውስጥ አለመኖሩና የመሳሰሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተደራርበው አሰልጣኙን ያለፈውን የውድድር ዓመት አስቸጋሪ አድርጎባቸው ነበር ያለፈው።
ለእዚህም ይመስላል ክለቡ ኒውካስልን ሲያሸንፍ እጅግ የተደሰቱት። በፕሪሚየር ሊጉ 38ኛ ጨዋታ በሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም ኒውካስትል ዩናይትድን በተከላካዩ ሎረንት ኮሲዮሊኒ ብቸኛ ግብ አሸንፈው የአራተኛ ደረጃን ሲያስጠብቁ ፊታቸው እንደ ሕፃን ልጅ ፍልቅልቅ ያለ ፈገግታ ተሞልቶ ታይቷል። አራተኛ ደረጃን ይዘው የውድድር ዓመቱን ማጠናቀቃቸው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ስለሚያረጋግጥላቸው የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች ወደ ክለባቸው ለማምጣት በር ይከፍትላቸዋል።
ላለፉት ስምንት ዋንጫ አልባ የውድድር ዓመታት መቋጫ ለማበጀት ቆርጠው እንደተነሱ ለክለባቸው ይፋዊ ድረ ገጽና ቴሌቪዥን የተናገሩት ቬንገር፣ በቀጣዩ ዓመት ብዛት ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ክለባቸው እንደሚያዘዋውሩ ተናግረዋል። እኛም ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያሰባሰብነውን መረጃ ተመርኩዘን አርሰን ቬንገር በጥብቅ ይፈልጓቸዋል የተባሉትን አስር ተጫዋቾች እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

1. ዴቪድ ቪያ
በባርሴሎና ያለውን ቆይታ አልወደደውም፣ ለእዚህም ወደ ውጭ መመልከት ጀምሯል። 31ዓመት ሞልቶታል፤ በቬንገር ዓይን ውስጥ የገባው ይህን ስፔናዊ አጥቂ ወደ አርሴናል ይዘዋወራሉ ከተባሉት መካከል አንዱ ሆኗል። ቬንገር ተጫዋቹን ለማስፈረም ፍላጎት ያሳዩት ባለፈው ጥር የነበረ ቢሆንም 14 ሚሊዮን ፓውንድ መክፈል ከቻሉ የካታሎኑ ክለብ ሊሸጥላቸው እንደሚፈልግ አስቀድሞ ነግሯቸዋል። አርሰን ቬንገር የዕድሜውን መግፋት ባይወዱትም ልጁ ባለው ግብ የማስቆጠር ጥሩ ሪከርድ የተጠየቁትን ገንዘብ ከፍለው መድፈኛ ሊያደርጉት ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል።
2. ክርስቲያን ቤንቴኬ
የ22 ዓመቱ ቤልጄማዊ ክርስቲያን ቤንቴኬ የአርሴናል ደጋፊ መሆኑን ደጋግሞ ሲናገር ይደመጣል። እንዲያውም በአንድ አጋጣሚ ለአስቶንቪላ የፈረመበትን ምክንያት ሲጠየቅ «ወደ አርሴናል ለመዘዋወር ስለሚመቸኝ ነው» ሲል መናገሩ ይታወሳል። ቤንቴኬ ለአስቶን ቪላ 19 ግቦች በማስቆጠር ክለቡን ከፕሪሚየር ሊጉ ከመውረድ የታደገ ተጫዋች ነው። አርሰን ቬንገር ይህን ተጫዋች በ11 ሚሊዮን ፓውንድ ለመውሰድ አስበው ለቪላ ፓርክ ባለ ስልጣናት መናገር ጀምረዋል። ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ቤንቴኬን ማስፈረም ከቻሉ አስፈሪ የአጥቂ መስመር ሊገነቡ እንደሚችሉ የስፖርት ተንታኞች ይናገራሉ።
3. ቪክቶር ቫልዴዝ
በበርካታ የስፖርቱ ተከታታዮች እድለኛው ግብ ጠባቂ እየተባለ የሚጠራውን የባርሴሎና ግብ ጠባቂ አርሰን ቬንገር ይፈልጉታል። ቬንገር ይህንን ግብ ጠባቂ ወደ ክለባቸው በማዘዋወር ዋየቼት ቼዝኒን ማንቃት እንደሚፈልጉ ለክለቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዘሰን ድረ ገፅ ተናግረዋል። 31ዓመት ለሞላው ለቫልዴዝ የአስር ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ መክፈል ከቻሉ ከአማኑኤል አልሙኒያ በኋላ የአርሴናልን ማሊያ የለበሰ ስፔናዊ ግብ ጠባቂ ይሆናል።
4. ቪክቶር ዋንያማ
የ21 ዓመት ወጣት መሆኑና ማቲው ፍላሚኒ ትቶት የሄደውን የአማካይ ተከላካይ ቦታ በአስተማማኝ ብቃት መተካት ያስችላቸዋል። ቬንገር ይህንን ትውልደ ኬንያዊ የሴልቲክ ተጫዋች በጥብቅ ይፈልጉታል። የ12 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ቢጠየቁም፣ አርሰን ቬንገር ግን ከችግራቸው አኳያ የሴልቲኮችን ጥያቄ አሟልተው ልጁን ወደ ክለባቸው ሊወስዱት እንደሚችሉ በስፋት ተገምቶላቸዋል።
5. ፔፔ ሬይና
በሊቨርፑል ደስታ የራቀውን የ30 ዓመት ስፔናዊ ግብ ጠባቂ አርሰን ቬንገር ለረጅም ዓመታት በቅርብ ሲከታተሉት ቆይተዋል። 10ሚሊዮን ፓውንድ ልክፈልና የግብ መስመሬን ይጠብቅልኝ ሲሉ የክለቡን ኃላፊዎች ማነጋገር ጀምረዋል። ግብ ጠባቂው ግን «ያሳደገኝን ክለብ ማገልገል እፈልጋለሁ» ብሎ ወደ ባርሴሎና መመልከት ከጀመረ ቆይቷል። አርሰን ቬንገር ቪክቶር ቫልዴዝን ማስፈረም ከቻሉ ሬይና የተባለውን ግብ ጠባቂ ችላ እንደሚሉት ይጠበቃል።
6.ስቴፈን ኤልሻራዊ
አርሴን ቬንገር የዘር ሐረጉ ከሰሜን አፍሪካዊቷ አልጀሪያ የሚመዘዘው የኤሲ ሚላኑን አጥቂ ስቴፈን እንደሚያደንቁት በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገሩ ይደመጣል። ለውል ማፍረሻው የ25 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሆነ ከ ክለቡ ባለቤቶች ለፈላጊዎቹ ተነግሯቸዋል። ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ግን ከክለቡ ጋር ያላቸውን የቆየ ወዳጅነት ተጠቅመው ኤልሻራዊን ያስፈርማሉ ተብሎ ቢገመትም ካላቸው ገንዘብ ቆጣቢነት አኳያ ግን የስቴፈን ወደ ለንደን መዘዋወር የማይታሰብ ነው ሲሉ አሰልጣኙን የሚያውቋቸው የስፖርቱ ተንታኞች ይናገራሉ።
7.ስቴፈን ዩቮቲች
የ23ዓመቱን የሞንቴኔግሮ ተጫዋች ዩቮቲች በርካታ ታላላቅ ክለቦች በጥብቅ ይፈልጉታል። በፍዮሬንቲና ያለውን የቆይታ ፋይል በእዚህ የዝውውር መስኮት ማቆሚያ ሊያበጅለት ቆርጧል። ይህን አጥቂ ተጫዋች ለማግኘት ሀብታሙ ማንቸስተር ሲቲና የጣሊያንን ስኩዴቶ ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት ማንሳት የቻሉት ጁቬንቱሶች ፍላጎታቸውን ይፋ አድርገዋል። የፍዮሬንቲና ፕሬዚዳንት አጥቂያቸውን ለጣሊያን ክለብ አሳልፈው እንደማይሸጡ መናገራቸው ጁቬንቱሶችን ተስፋ አስቆርጧል። ልጁም ወደ ማንቸስተር ሲቲ የመዘዋወር ፍላጎቱ ዝቅተኛ መሆኑ ለአርሰን ቬንገር ደስ የሚል ወሬ ነው። ለእዚህም 25 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍለው ወይም አንድ ተጫዋች በምትኩ ሰጥተው የሮቪን ቫን ፐርሲን ቦታ መድፈን ይፈልጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
8. ኢትዮን ኮፑ
የፈረንሳዩ ክለብ ቱሉዝ የ24 ዓመቱን አማካይ ተከላካይ የሚገዛ ከመጣ የ12ሚሊዮን ፓውንድ ቼክ ጠረጴዛዬ ላይ ማስቀመጥ አለበት ብሎ መናገሩ የገዥዎችን ጆሮ ያነቃ ዜና ሆኗል። ቬንገርም የሴልቲኩን ዋንያማ ማዘዋወር ካልቻልኩ ብለው በተጠባባቂነት የያዙት ሲሆን፤ የተጠቀሰውን ዋጋም ለመክፈል ካዝናዬ ችግር የለበትም ብለዋል። በፈረንሳይ ሊግ ከሚጫወቱ አማካይ ተከላካይ ተጫዋቾች መካከል ምርጥ እንደሆነ የሚነገርለት ኮፑ ወደ ሰሜን ለንደን መዘዋወር ከቻለ ትክክለኛው የአሌክስ ሶንግ ምትክ ይሆናል ሲሉ በድፍረት የሚናገሩ አሉ።
9. ኒኮላስ ኒኮሉ
አርሰን ቬንገር ቀድሞውንም ቢሆን ለእዚህ ፈረንሳዊ ተጫዋች በራቸውን መዝጋት አይወዱም። የፊታችን ሰኔ ላይ በሚከፈተው የተጫዋቾች ዝውውር መስኮትም ይህን የማርሴይ የተከላካይ ተጫዋች በቀጣዩ የውድድር ዘመን ተጫወትልን ሲሉ ፍላጎታቸውን ገልጸውለታል። ቬንገር ለሀገራቸው ልጅ በክለቡ የተለጠፈበትን የ10 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን በልበ ሙሉነት መናገር ጀምረዋል።
10. ሴባስቲያን ሮድ
በኢንትራ ፍራንክ ፈርት ምርጥ ብቃቱን በማሳየት ላይ የሚገኝ የ22 ዓመት የተከላካይ መስመር ተጫዋች ጀርመናዊ ነው። ሮድ በቶተንሃምና በአርሴናል በጥብቅ የሚፈለግ ነው። የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚያሳትፈውን ደረጃ በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታቸው ከቶተንሃም ሆትስፐር ላይ መንጠቅ የቻሉት አርሴን ቬንገር፣ የከተማ ተቀናቃኛቸውን በልጠው ሮድንም ማስፈረም ከቻሉ ከመለሎው ጀርመናዊ ፔር ሜርቲሳከር ጋር የተዋጣለት ጥምረት መፍጠር ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል።
አርሰን ቬንገር ከእነዚህ ተጫዋቾች መካከል ቢያንስ አራቱን ወይም አምስቱን ማስፈረም ከቻሉ ለዋንጫ መፎካከር የሚችል ቡድን መገንባት ይችላሉ ሲሉ ዘገባዎች ያመለክታሉ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>